ባለፉት 25ዓመታት የዳኝነት ነጻነት የለም ሲሉ የአማራ ክልል ዳኞች ገለጹ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 10/2009) ባለፉት 25ዓመታት የዳኝነት ነጻነት የለም ሲሉ የአማራ ክልል ዳኞች ገለጹ።

በክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና በፍትህ ቢሮ ሃላፊው በአቶ ፍርዴ በተመራውና አቃቢያን ህግ፡ ፖሊስ፡ ዳኞችና ሌሎች የፍትህ አካላት በተገኙበት ስብሰባ ላይ ዳኞች በአንድ ድምጽ እንደገለጹት በአማራ ክልል የዳኝነት ነጻነት የሚባል ነገር የለም።

የፖለቲካ ጫና የበዛበት፡ በህግ አግባብ ያስረነው በቀጭን ትዕዛዝ የሚፈታበት፡ ነጻ ተብሎ በፍርድ ቤት የተለቀቀ ወዲያው በፖሊስ ተይዞ የሚታሰርበት፡ ዳኝነት መጫወቺያ የሆነበት የተበላሸ የፍትህ ስርዓት ሰፍኗል ሲሉ መግለጻቸው ታውቋል።
የመንግስት ሃላፊዎች በዳኞቹ አቋም ተደናግጠው የሚሰጡት መልስ ማጣታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ስብሰባውን የተከታተሉ የኢሳት ምንጮች ከላኩት መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው በዳኞች በኩል የቀረበው ቅሬታ ለክልሉ ባለስልጣናት ያልተጠበቀ ነበር
ፖሊስ፣ አቃቢ ህግና ዳኞች በአንድነት ተባብረው መስራት በሚችሉበትን አሰራር ላይ ለመወያየት የተጠራው ይሔው ስብሰባ የተጠናቀቀው ከታቀደው አላማ ውጪ በሆነ መልኩ ነው ተብሏል።

ከተቀመጠለት አጀንዳ በመውጣት በትኩረት ውይይት የተደረገበት የዳኞች ነጻነት ሲሆን በስብሰባው ላይ የተገኙት የክልሉ ዳኞች በአንድ አቋም ላለፉት 25 አመታት የዳኝነት ነጻነት የለም ሲሉ መግለጻቸው ነው የተሰማው።
ከተነሱት ሃሳቦች መሃል በዳኞች ውሳኔ ላይ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የተለመደ ሆኗል፣በፍርድ ውሳኔ የተለቀቀን በትእዛዝ ድጋሚ እንዲታሰር አድርጉ እንባላለን።

ወንጀለኝነቱ ተረጋግጦ ፍርድ የተበየነበትን ልቀቁት የሚል መመሪያ ከፖለቲካ ሹመኞች ይመጣልናል።ለአብነትም በባህርዳር በማስረጃ በተረጋገጠ የሀገር ውስጥ ገቢ መስሪያ ቤት ላይ የተፈጸመውን የ22 ሚሊየን ብር ዘረፋ የፈጸመው ግለሰብ ዘጠኝ አመት ፍርድ ከተሰጠው በኋላ በአስቸኳይ ልቀቁት ተብለን ሶስት ሳምንት ቆይቶ ነጻ የተባለበትን አጋጣሚ ጠቅሰዋል።

ፍትህ ሳይኖር ስለዳኞች ነጻነት ማውራት እንዴት ይቻላል ሲሉ የጠየቁት ዳኞች ከአቃቢ ህግና ከፖሊስ ጋር ተባብራችሁ ስሩ ማለት መሰረታዊ የህግ ክፍተት ያለው እንደሆነ በመግለጽ ተቃውመዋል።
መንግስት ይህን አሰራር ለመዘርጋት ያቀደው የፍትህ ስርአቱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር መውደቁን ለማረጋገጥ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።

በነጻነት እንስራ ብለን ከተነሳን ከስራችን እንባረራለን፣የጥብቅና ፈቃዳችን ይነጠቃል በማለት በምሬት የገለጹት ዳኞች ተሸማቀን ተሳቀን የምንሰራው ስራ ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል።
በሚዲያና በማህበራዊ መድረኮች በየጊዜው የሚገለጸው የፍትህ ስርአት የህግ የበላይነት ውሸት ነው።ህዝብን በዚህ እያሞኙ መቀጠል አይቻልም በማለት በድፍረት ተናግረዋል።

የዳኞቹ ጠንካራ አቋምና ተቃውሞ ያስደነገጣቸው የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት መልስ ለመስጠት ተቸግረው ይስተካከል በሚል ብቻ ስብሰባው እንዲጠናቀቅ እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል።
በቅርቡ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው በእስር ላይ የሚገኙት ኮለኔል ደመቀ ዘውዱን ጉዳይ የሚከታተሉት ዳኛ በችሎት ላይ እያሉ በደህንነት ሃይሎች ታስረው መወሰዳቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ በፍትህ ስርአቱ ላይ እምነት እንደሌለው በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ ታሪክም ከቀድሞ መንግስት በከፋ ሁኔታ የፍትህ ስርአቱን ሙሉ ለሙሉ የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ የሚጠቀሰው የአሁኑ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መንግስት እንደሆነም ይናገራሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.