ከ1ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዛሬ ከጣሊያን ፖሊስ ጋር ተጋጩ

ኢሳት ዜና–ነሐሴ 18/2009)ከመኖሪያ ህንጻቸው በሌሊት የተፈናቀሉት ከ1ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዛሬ ከጣሊያን ፖሊስ ጋር ተጋጩ።

ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት በድንገት ህንጻቸውን በመውረር ከመኖሪያቸው ያስወጣቸው ፖሊስ ዛሬ በጊዜያዊነት ካረፉበት ጎዳና ላይ እንዲነሱ ለማድረግ በወሰደው እርምጃ ግጭት ተከስቶ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ጉዳት እንደደርሰባቸው ለማወቅ ተችሏል።

የጣሊያን ፖሊስ እየወሰደ ያለው እርምጃ ዓለም ዓቀፍ ህግን የጣሰ ነው በሚል ከተለያዩ አካላት ተቃውሞ እየተሰማ ነው።
በጣሊያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዜጎች ላይ ለደረሰው አደጋ ምንም ምላሽ አለመስጠቱ ኢትዮጵያውያኑን አስቆጥቷል።

ቅዳሜ ሌሊት ነው። ፒያሳ ኢንዲፔንዴንዛ በተባለ የሮም ጎዳና ላይ በሚገኘው ሮማ ተርሚ ህንጻ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ያን ቀን ሌሊት የሚደርስባቸውን አላወቁትም።
ቀድሞ የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያም ሆነ ማስታወቂያ አልነበረም። ድንገት በሌሊት እስከ አፍንጫው የታጠቀ ቁጥሩ ወደ 50 የሚጠጋ የጣሊያን ፖሊስ ከህንጻቸው ይመጣል። ሁሉም በእንቅልፍ ላይ ነበሩ።

ፖሊስ ድንገተኛ ወረራ አድርጎ ከተኙበት ላፈናቀላቸው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ያዘጋጀው መጠለያ የለም። ለአራት ዓመታት ከኖሩበት ህንጻ በድንገት በሃይል ሲፈናቅሉ የገጠማቸው ጎዳና ላይ ማረፍ ነበር። ላለፉት አምስት ቀናት በመሃል ሮማ ጎዳና ላይ ውሎና አዳራቸውን አደረጉ።

ኢሳት ያነጋገረው አንድ ወጣት እንደሚለው ከሞቀ ቤታቸው ያለማስጠንቀቂያ ድንገት የመፈናቀላቸውን ምክንያት በግልጽ አያውቁትም። ህንጻው የግለሰብ ነው የሚል አጭር መልስ ብቻ ነው ያገኙት። አሁን ከማንም በላይ ህጻናት እየተጎዱ ነው።
ከአፍሪካ በሊቢያ በኩል አውሮፖ ለመድረስ አደገኛውን የባህር ላይ ጉዞ የሚያደርጉ ስደተኞች በቅድሚያ የሚያገኟት ጣሊያንን ነው።

ካለፉት 3እና 4 ዓመት ወዲህ የባህር ላይ ጉዞ የብዙ ሺዎችን ስደተኞች ህይወት በአጭሩ ማስቀረት መጀመሩ አሳዛኝ ክስተት ሆኖ እየተሰማ ነው። ጣሊያንም ይህንን የስደተኞች ፍልሰት ለማስቆም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥብቅ የሆነ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች።

ይሁንና ባለፈው ቅዳሜ ለዓመታት ከኖሩበት በድንገት የተፈናቀሉት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ጉዳይ የተለየ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ በሃይል ከሚኖሩበት የተፈናቀሉት ወገኖች የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው፣ቤተሰብ መስርተው የሚኖሩ፣ በጣሊያንም ከ10እና ከዚያ በላይ ዓመታት የቆዩ እንደሆኑ ይገልጻሉ።

ራሳቸውን ችለው ስራ ሰርተው በህጋዊ መንገድ የሚኖሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ወገኖች እንዲህ ዓይነት ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት መፈጸሙ አስቆጥቶአቸዋል።
በተለይ ዛሬ ለአምስት ቀናት ከተጠለሉበት ጎዳና ላይ ለማስነሳት በፖሊስ የተወሰደው ርምጃ ጉዳዩን የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት አግኝቷል።

በተፈናቃዮቹና በፖሊስ መሃል ዛሬ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን መጎዳታቸውንና ሆስፒታል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል። በጣሊያን ፖሊስ የተወሰደው እርምጃ ‘’አፍሪካ ያለሁ ነው የመሰለኝ’’ ሲል የኮነንው ኢትዮጵያዊው ወጣት የዛሬን ግጭት እንዲህ ይገልጸዋል።

ሌሎችም ስጋት ላይ ናቸው። በተመሳሳይ ህንጻዎችን ተከራይተው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሌሎችም አፍሪካውያን ከህንጻቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ በስጋት ይገልጻሉ።
ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ በሮም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰጠው መግለጪያ የለም። ተጎጂ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት ኤምባሲው ዞር ብሎም አላያቸውም።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሀገራት በሚገኙ የጣሊያን ኤምባሲዎች ላይ ተቃውሞ እንዲያሰሙና እየደረሰባቸው ያለው ጥቃት እንዲቆም ያደርጉላቸው ዘንድ ኢትዮጵያውያኑ ወገናዊ ጥሪ አቅርበዋል። ጉዳዩን በተመለከተ የጣሊያንን ፖሊስ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.