የታጐሉት የአ/አበባ አድባራት የዕቅበተ እምነት ጉባኤያት እየተነቃቁ ነው፤ የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ፥ በአውራነት የተሳካ ጉባኤ አካሔደ!

ሐራ ዘተዋሕዶ

 • በዝግጅቱና በስኬቱ የተደሰቱ ምእመናን፣ የጉባኤውን መዝጊያ በርችት ተኩስ አደመቁት
 • የአለቃው፣ የስብከተ ወንጌል ክፍሉና የሰንበት ት/ቤቱ ውጤታማ ቅንጅት የታየበት ነው
 • የኑፋቄ ማሳያ ኅትመቶች ተሰብስበው ተቃጥለዋል፤የሞባይል መጥሪያዎችም ተሰርዘዋል
 • የኑፋቄው ቅጥረኞች፥ ተሳታፊ መምህራንን በስልክ ዛቻ አስፈራሩ፤ ለስኬቱ ምስክር ነው!
 • በትዕይንተ አ/አበባ የተተከለው ደብር ስኬት፣ ለሀ/ስብከቱ አጥቢያዎች ማትጊያ ይኾናል
 • “ከዚህ ተራራ የነፈሰው ነፋስ፣ ሜዳውን ያጠራል!”/መ/ር በላይ ወርቁ፥ “የጸናች ከተማ”/

†††

 • መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና፣ ኮተቤ ኪዳነ ምሕረትና ጃቲ ኪዳነ ምሕረትም አካሔዱ
 • አንዳንድ የሀገረ ስብከቱና ከአድባራቱ ሓላፊዎች ጥቂቶቹም፣ ለማደናቀፍ እየሞከሩ ነው
 • ለአሰግድ ተቆርቁሮ መወገዙን የተቸው የክ/ከተማው ሓላፊ፣ ሰሎሞን ንጉሤም ተጠቀሰ
 • የአጥቢያዎች የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ መዳከሙን፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አምኗል
 • አጠቃላይ ገቢያቸው ብር 1 ቢል. ተመዝግቧል፤ የሀ/ስብከቱ ድርሻም ብ. 202 ሚ.ኾኗል
 • የአጥቢያዎች ገቢና የ20% ፈሰሱ የተሰበሰበበት ትጋት፣ በስብከተ ወንጌሉም ይደገም!!!

የታጐሉት የአ/አበባ አድባራት የዕቅበተ እምነት ጉባኤያት እየተነቃቁ ነው፤ የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ፥ በአውራነት የተሳካ ጉባኤ አካሔደ! 1ፀራውያንና መናፍቃን፥ አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ከኹሉ በላይ በኾነችው ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ከዘመቱባቸው ስልቶች አንዱ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰርጎ ገብ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስልቱ፣ “ውስጥ ውስጡን የሚጎዳ የመናፍቃን ስውር ተልእኮ” እንደኾነ፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ መግለጫዎችና የተላለፉ ውሳኔዎች በጉልሕ አስገንዝበዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ፣ የኑፋቄውን ስውር ተልእኮ፣ ከአገልግሎትና የአስተዳደር መዋቅራችን ለማፍለስና ለመደምሰስ፦ በንቃት መከታተል፣ በማስረጃ ማጋለጥ፣ በትምህርተ ወንጌል ምእመናንን መጠበቅና መከላከል እንደሚገባ ተደጋጋሚ አቅጣጫዎችና መመሪያዎች ለየአህጉረ ስብከቱ ወርደዋል፡፡

ትግበራውም፥ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ፥ በ120 ቤተሰብ፣ በ72ቱ አርድዕት እና በ12ቱ ሐዋርያት ስያሜ የተዋቀረውን “የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ የሥራ አመራር ጉባኤ” እና “የፀረ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ”በማቋቋም ሲኾን፤ የእንቅስቃሴ ዕቅድ እየነደፉና በገንዘብ አስተዋፅኦ እየተደገፉ እንዲሠሩና ስለመጠናከራቸውም በየጊዜው መምከር እንደሚያስፈልግ፣ የጋራ አቋም የተያዘበትና በምልአተ ጉባኤ የጸደቀ ሲኖዶሳዊ ትእዛዝ ነው፡፡

መመሪያውን ለማስፈጸም ጥረት በተደረገባቸው አህጉረ ስብከት፥ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ቀኖናውንና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ያልተፈቀደላቸውና መነሻቸው የማይታወቅ ሕገ ወጦችን ለመከላከል አቅም ፈጥሯል፡፡ የኑፋቄውን ስውር ተልእኮና ወኪሎቹን የሚያጋልጡ ወቅታዊ ማስረጃዎችና ማብራሪያዎች በዐውደ ምሕረት በማቅረብ፣ እልፍ አገልጋዮችንና ምእመናንን በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥና አቋም ለማስያዝ ተችሏል፡፡ ሰለባዎችና በተጽዕኖ ውስጥ ያሉትም፣ ሤራውን እንዲነቁበትና የተቀሩትም እንዲያስቡበት አገብሯቸዋል፡፡

በሒደት እየታየ እንዳለውም፣ አንዱ ሀገረ ስብከት የሌላውን ተሞክሮ እየቀሰመና በስኬቱም እየተነሣሣ በሚዘጋጁ የፀረ ተሐድሶ ጉባኤያት፣ የዕቅበተ እምነት ተጋድሎው፣ የኑፋቄውን መረብ ለመበጣጠስ በሚያበቃ ግለት፣ በእያንዳንዱ የከተማና የገጠር ሰበካ እየተቀጣጠለና እየተፋፋመ ነው፡፡ በሰንበታትና በክብረ በዓላት ተወስነው የነበሩ ጉባኤያትም፣ በተመረጡ የሳምንቱ ቀናት “ልዩ ጉባኤያት” ጭምር የሚካሔዱበት ትጋት እየታየ ነው፡፡ ይህ ጥንቅር በሚሰናዳበት ዛሬ ዓርብ፣ ነሐሴ 19 ቀን ጀምሮ እስከ እሑድ፣ ነሐሴ 21 ቀን ባሉት ዕለታት ብቻ፥ በድሬዳዋ፣ በይርጋለም፣ በቦንጋ፣ በሻሸመኔ፣ በደብረ ዘይት፣ በአዳሚ ቱሉ፣ በሃላባ፣ በሀገረ ማርያም እና በሻኪሶ(መጋዶ)፣ ከውጭዎቹም አህጉረ ስብከት በዱባይ እና በአሜሪካ አትላንታ፥ የኑፋቄው ሤራ በማስረጃ የሚጋለጥባቸው፣ ኦርቶዶክሳዊውን አስተምህሮም ምእመኑ በንጽጽር የሚረዳባቸውና እምነቱን የሚያጸናባቸው የፀረ ተሐድሶ ጉባኤያት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

21078517_1554643234592357_3177276056829840727_n

እኒህ ጉባኤያት፣ ቤተ ክርስቲያናችን፥ “ሑሩ ወመሐሩ ውስተ ኵሉ አጽናፈ ዓለም” ብላ ከላከቻቸው የቤተ ጉባኤያቱ እና የመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃን መምህራን ጀምሮ፣ በኹለገብ የዕቀበተ እምነት አቀራረባቸው የተመሰከረላቸው በርካታ የትሩፋት ሰባክያንና ዘማርያን በጥምረት የተሰማሩባቸው ናቸው፡፡ ሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት እና መ/ር ኅሊና በለጠ(በድሬዳዋ ቅዱስ ገብርኤል)፤ መጋቤ ሃይማኖት ተስፋዬ ሞሲሳ እና መጋቤ ሐዲስ ቀለም ወርቅ ታደሰ(በይርጋለም ዐማኑኤል)፤ መ/ር ምትኩ አበራ እና ዲ/ን ታደሰ ወርቁ(በቦንጋ ኪዳነ ምሕረት)፤ መ/ር በላይ ወርቁ እና መ/ር ተመስገን ዘገየ(በደብረ ዘይት ቅዱስ ሚካኤል እና በአዳሚ ቱሉ ቅድስት ማርያም)፤ መ/ር ዐብይ መኰንን እና መ/ር ኢዮብ ይመኑ(በሻሸመኔ ቅድስት ልደታ)፤ ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ እና መ/ር ዐብይ መኰንን(በሃላባ ቅድስት ማርያም)፤ መ/ር በኃይሉ በቀለ እና መጋቤ ጥበባት ሲያምር ተክለ ማርያም(በሻኪሶ – መጋዶ)፤ መጋቤ ሐዲስ ድጋፌነህ ኃይለ ሚካኤል(በሀገረ ማርያም)፤ መ/ር ምሕረተ አብ አሰፋ እና ዲ/ን ብሌን ጌታቸው(በዱባይ)፤ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እና ቀሲስ መስፍን(በአትላንታ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም) ይጠቀሳሉ፡፡

ለብፁዓን አባቶችና በየደረጃው ለሚገኙ ሓላፊዎች ጥሪ፣ በወትሮ ዝግጁነት እየታዘዙ የኑፋቄውን ሤራ በማጋለጥና በመከላከል ለእልፍ ምእመናን አለኝታ የኾኑት እኒህና ሌሎችም ቀናዕያን መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል፣ ተልእኳቸውን የሚፈጽሙት ከአዲስ አበባ እየተነሡ ነው፡፡ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉት አህጉረ ስብከት በከፍተኛ ጉጉትና ስሜት እየተቀበሉ የአገልግሎታቸው ተጠቃሚ እየኾኑ ባሉበት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጥቢያዎች ግን፣ ከፊሎቹ እንዳያገለግሉ ተከልክለው ነው ያሉት፡፡ የሚበዙት የአጥቢያ አስተዳደር ሓላፊዎችና የስብከተ ወንጌል ክፍሎች ለመጋበዝ እንደሚሹ ቢታወቅም፣ “ከምድብ ሰባክያን በስተቀር መድረኩን እንዳትሰጡ” በሚል ከቀድሞው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ በተላለፈ ክፋትና ተንኰል በተጠናወተው ሸውራራ መመሪያ ተሸብበው ይገኛሉ፡፡

ይህ ማለት፣ የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ ሊካሔድ የሚችለው ከላይ የተዘረዘሩት መምህራንና ሰባክያን ሲጋበዙ ብቻ ነው፤ ማለት እንዳልኾነ ግልጽ ነው፡፡ ክፋቱ ግን፣ በምድብ ሰባክያኑ እንኳ፣ የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ ለማዘጋጀት በስብከተ ወንጌል ኮሚቴዎች ሲታቀድ የሚታየው መሣቀቅና ውጣ ውረድ ነው፡፡ “ምእመኑን ይከፋፍልብናል” በሚል ሽፋን ጥረቱን ማሰናከል፣ በአማሳኝና ሰርጎ ገብ የአጥቢያና የክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ሓላፊዎች ዘንድ ይሰማል፡፡ በሲኖዶሳዊ ውሳኔ የታወጀን የኑፋቄ ስውር ተልእኮ ማጋለጥ፣ ምእመኑን ያነቃል፤ ያጸናል እንጅ እንዴት ነው የሚከፋፍለው? እንዲያውም፣ ምእመኑ የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ እንዲዘጋጅለት በአንድነት መጠየቁ ብርታት ኹኗቸው፣ ግልምጫውንና ዛቻውን ተቋቁመው እንዲካሔድ ያደረጉ አለቆችና የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች፣ የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፤ ቦታቸው በጉቦ ተሽጦ ወደ ሌሎች አድባራት የተዛወሩም አሉ፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት፣ በክፍለ ከተማው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አስተባባሪነት፣ ባለፈው መጋቢት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. አዘጋጅቶት የነበረው የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ፣ ብዙ ሺሕ የሰንበት ት/ቤቶች አባላትንና ምእመናን በሚያሳትፍ አኳኋን በተመረጠው አመች ቦታ በድምቀት እንዳይካሔድ፣ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የታጐለበትና ለዝግጅቱ አስተዳደራዊ ድጋፍ የሰጡ የክፍለ ከተማ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ በሰበቡ ከሓላፊነታቸው ዝቅ ተደርገው መዛወራቸውን እንደ ምሳሌ ማንሣቱ ይበቃል፡፡

ይህም ባልከፋ፡፡ “የፀረ ተሐድሶ ቋሚ ጉባኤ” እንዲዋቀር የተላለፈውን ሲኖዶሳዊ መመሪያ ሀገረ ስብከቱ እስከ አኹን ተግባራዊ አለማድረጉ አስገራሚም አሳዛኝም ነው፡፡ ይብሱኑ ውሳኔው፣ ለሀገረ ስብከቱ እንዳልደረሰው ነው የተነገረው፡፡ የኑፋቄው ስጋትና አደጋ፥ ከጽ/ቤቱና ዋና ክፍሎቹ ጀምሮ በክፍላተ ከተማ ጽ/ቤቶችና በየአጥቢያዎቹ ከተሰገሰጉት ወኪሎቹና አቀንቃኞቹ አሻጥር የተነሣ፣ ግልጽና ድርስ ኾኖ በሚታይበት ኹኔታ፣ የሀገረ ስብከቱ ዳተኝነት፣ የቸልተኝነትና የአቅም ማነስ ብቻ አይመስልም፡፡

ኑፋቄውን የምንከላከለውና ምእመናንን የምንጠብቀው፣ በትምህርተ ወንጌል እንደኾነ ቀደም ሲል ተገልጿል፡፡ የሐዋርያዊ ተልእኮው ስጋትና ተግዳሮቶች ዳሰሳዊ ጥናትም፣ “ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆዩ የሚያስችል የሐዋርያዊ አገልግሎት ስትራቴጂ ካልቀረፀች በስተቀር፣ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ስጋት እያየለ እንደሚገኝና ምእመናኗ ለአደጋው እንደሚጋለጡ፤” አስጠንቅቋል፡፡ በልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌው፣ አዲስ አበባን በበላይነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም፦ ስለ ሀብት ድልብ ሳይኾን ስለ ምእመናን ድልብ ዘወትር መጨነቅ እንደሚገባ፤ ስብከተ ወንጌሉን በማስቀደም፣ ከዐውደ ምሕረትም አልፎ በቤተሰብ ደረጃ የግብረ ኖሎት ክትትሉና ጥበቃው እንዲጠናከር መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ ምእመናን፥ በተደራጀና በተሟላ ኹኔታ የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ስለ ሃይማኖታቸው በሚገባ እንዲያውቁ፣ በባዕድ እምነት አስፋፊዎች እንዳይሰረቁ በትኩረት መሥራትና ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግም፣ ሀገረ ስብከቱ በሕገ ቤተ ክርስቲያንና በቃለ ዐዋዲ ደንቡ የተጣለበት ሓላፊነትና ግዴታው ነው፡፡

ኾኖም በአዲስ አበባ፣ በየአጥቢያው፣ ከ7 እስከ 11 ሰባክያነ ወንጌል ተከማችተው ቢገኙም፣ በተለይ የሠርክ ጉባኤያቱ በምእመናን ድርቅ እየተመቱ ናቸው፡፡ ከሰባክያኑ ጥቂት የማይባሉት፣ ጸጋው ወይም ሥልጠናው የሌላቸውና ምደባውንም የሚፈልጉት፣ “ከመቅደሱ አገልግሎት ድካም ለማረፍ” መኾኑን፣ የ7ቱ ክፍላተ ከተሞች የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸም፣ ባለፈው ሐምሌ ወር በተገመገመበት ወቅት ተገልጿል፤ ኦርቶዶክሳዊ ላህይና ጠባይ፣ የትሕትና አቋም፣ አባታዊ አገላለጥና አርኣያ ክህነት የሚጎድላቸውም በብዛት እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ፣ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴው መዳከሙን ሀገረ ስብከቱ አምኗል፡፡ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍሉም፣ በበጀት ዓመቱ ከ200 ለማያንሱ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክርና ሥልጠና መርሐ ግብር ዐቅዶ የነበረ ቢኾንም ለማስፈጸም ተስኖታል፡፡

በግምገማው ወቅት፣ “ከምድብ ሰባክያን በቀር መድረኩን እንዳትሰጡ” የሚለው የሀገረ ስብከቱ መመሪያ፣ ጸጋው፣ ዝግጅቱና አቅሙ ያላቸውን ልሙድና በካር ኦርቶዶክሳውያን መምህራንንና ሰባክያነ ወንጌልን እንዳራቀና ለማሳተፍም ዕንቅፋት እንደፈጠረ በመጥቀስ እንዲጤን ተጠይቋል፡፡ “መመሪያው ከላይ ከቅዱስ ሲኖዶስ የመጣ ነው፤” ያለው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ግን፣ “ውሳኔውን የሰጠው አካል እንደገና ካላየው በቀር ማሻሻልና መሻር አንችልም፤” በማለት የችግሩን ስዕበት ያላገናዘበና ለመፍትሔም የማይበቃ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

እውነታው ግን፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ፣ “በቅጥር/ምድብ ሰባክያን ብቻ” የማይል መኾኑ ነው፡፡ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ እየተላለፉ የመጡት መመሪያዎች በተቀራራቢ አገላለጽ፡- “በትምህርተ ወንጌል የበሰሉ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታወቁና የተፈቀደላቸው” ጭምር ነው የሚሉት፡፡ የስብከተ ወንጌል ፈቃዱም የሚሰጠው፣ ከአህጉረ ስብከት የመምህራን ይላክልን ጥያቄ ሲቀርብና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አልያም ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሲፈቀድ እንደኾነ ነው በግልጽ የሚያስቀምጡት፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት እንዳይሰብኩ የተከለከሉት ቀደም ሲል የተዘረዘሩት መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል፣ በሌሎች አህጉረ ስብከት በሰፊው እያገለገሉ ያሉት በዚሁ መመሪያ አግባብ እንደኾነ እሙን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መዳከምና ለሲኖዶሳዊው የፀረ ተሐድሶ ጉባኤያት ዝግጅት መስተጓጐል፣ ብቸኛው ባይኾንም ከዋነኞቹ ምክንያቶች አንዱ፣ ስሑትና ተንኰል የተመላበት የቀድሞውና የወቅቱ ሥራ አስኪያጆች የመመሪያው አተገባበር እንደኾነ በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል፡፡

“ከብቃትና ታዛዥነት ማነስ የተነሣ፣ ስብከተ ወንጌሉንና ሐዋርያዊ ተልእኮውን በመደበኛ/ቅጥር አገልጋዮች ብቻ በተፈለገው መጠን ለማዳረስ እንደማይቻል” የታወቀ ነው፡፡ በመኾኑም በግምገማው ላይ፣ ሓላፊዎች በቀናነት ያቀረቡት ጥያቄ፣ የችግሩን ክብደት ባገናዘበ መልኩ ዳግም የሚታይበትና መመሪያውም፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ትክክለኛ መንፈስ ተከትሎ የሚተገበርበት ኹኔታ ቢመቻች የተሻለ ይኾናል፡፡


እንግዲህ፣ በዚህ መሰሉ የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ይዞታ ውስጥ ነው፣ የአድባራቱ የዕቅበተ እምነት ጉባኤያት እየተነቃቁ መኾናቸው የተገለጸው፡፡ የፀረ ተሐድሶ የዕቅበተ እምነት ጉባኤያቱ ዝግጅት ከተስተጓጎለበት ከቀድሞው ሥራ አስኪያጅ የሥራ ዘመን ወዲህ፥ የኮተቤ መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና፣ የኮተቤ ኪዳነ ምሕረት እና የጃቲ መካነ ሕይወት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል በቅርቡ ያከናወኗቸው የሚጠቀሱ ሲኾኑ፣ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስም፣ ነሐሴ 20 እና 21 ቀን ለማካሔድ ታቅዷል፡፡

የሦስቱ አድባራት ክንውን፥ ዲ/ን ታደሰ ወርቁ፣ መ/ር ተመስገን ዘገየና መጋቤ ምስጢር ቡሩክ አሣመረ የተሳተፉባቸውና የተሳካ ፍጻሜ የነበራቸው ናቸው፡፡ ከዕንቅፋት ግን ነጻ አልነበሩም፤ ጫናውና ስጋቱም አልተወገደላቸውም፡፡ ጉባኤው በመካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ደብር ከተካሔደ በኋላ፣ ሀገረ ስብከቱ የደብሩን ሓላፊዎች ወቅሷል፤ አስጠንቅቋል፡፡ በጃቲ መካነ ሕይወት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል፣ የኑፋቄው ማስረጃና ማብራሪያ በፕሮጀክተር እንዲቀርብ ጽ/ቤቱ ቢፈቅድም፣ “የኑፋቄው አቀንቃኞች በገንዘብ ገዝተውታል” የተባለው የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊው በመከላከሉ፣ ትምህርቱ ብቻ ተሰጥቷል፡፡ ይህም ኾኖ ኹለቱም አድባራት፣ ከምእመናኑ ባገኙት አጥጋቢ ግብአትና መጋቤ ምላሽ ላይ ተመሥርተው ጉባኤያቱን ማዘጋጀታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ወስነዋል፡፡

debrasina egab2

በሰሜናዊ አዲስ አበባ የእንጦጦ ጋራ ተረተር፣ የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ግን፥ የአስተዳዳሪው መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ፣ የስብከተ ወንጌል ክፍሉ አባል መ/ር አስቻለው ከበደና የሰንበት ት/ቤቱ የሠመረ ቅንጅት የታየበትና ምእመኑንም በእጅጉ ያረካ ደማቅ የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ ማካሔዳቸው ተገልጿል፡፡

ከነሐሴ 12 እስከ 16 የተካሔደው ይኸው የዕቅበተ እምነት ጉባኤ፣ ከሰኔ ወር ጀምሮ ረዘም ያለ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግበት እንደቆየ ተጠቅሷል፡፡ የዕቅዱ መነሻም፣ መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ የተወገዘበት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ፣ በሀገረ ስብከቱ ሰርኩላር ደብዳቤ ለአድባራት መተላለፉና ለምእመናን ማሳወቅን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አስተዳዳሪው፣ የስብከተ ወንጌል ክፍሉ ሓላፊና የሰንበት ት/ቤቱ አመራር፣ በአፈጻጸሙ ላይ በመወያየትና አስፈላጊውን በጀት በሰበካ ጉባኤው በማጸደቅ ለቅድመ ዝግጅቱ የሥራ ድርሻ ተከፋፍለዋል፡፡

አስተዳዳሪው፥ ለሚመለከተው የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና የሀገረ ስብከቱ አካል፣ ስለ ጉባኤው ዝግጅት ማብራሪያ ሲሰጡ፤ የስብከተ ወንጌል ክፍሉም ከሰንበት ት/ቤቱ ጋራ በመምከር፣ ተሳታፊ መምህራኑንና ዘማርያኑን በመለየት፣ የቅሰቀሳውና የጉባኤው አጠቃላይ ይዘትና ሒደት ምን መምሰል እንዳለበት ነድፈዋል፡፡ ከጉባኤው በፊት በነበሩት የሱባኤው ቀናት፣ አስተዳዳሪው ሳይቀሩ በቅስቀሳው በንቃት ተሳትፈዋል፤ የማስታወቂያ ባነሮች በአጎራባች አድባራትም እንዲለጠፉና በማኅበራዊ ሚዲያም እንዲሠራጩ ተደርገዋል፡፡

መርሐ ግብሩ ነሐሴ 12 ቀን የተጀመረው፣ “እርሱን ስሙት” በሚል ርእስ፣ “የምንሰማውን መለየትና መጠንቀቅ እንዳለብን በሚያዘክር የመዘጋጃ ጉባኤ ነበር፤” ብሏል ከአዘጋጆቹ አንዱ፡፡ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐ ጥበብ እና ቀሲስ መፍቀሬ ሰብእ አነቃቂ ትምህርት የሰጡ ሲኾን፣ ከዚሁ ጋራ የተያያዘው የደብረ ታቦር በዓል ትምህርትም፣ በዕለቱ ነሐሴ 13 ቀን፣ በመጋቤ ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ በጥሩ ኹኔታ ተተንትኖ ቀርቧል፡፡

የመናፍቃኑ ወቅታዊ አሰላለፍና ማስረጃዎች ከቤተ ክርስቲያን አቋም ጋራ የተካተተበት መግለጫና ማብራሪያ በፕሮጀክተር ተደግፎ ነሐሴ 14 ቀን ቀርቧል፡፡ “መንፈሳዊ ዕድገት” እና “የጸናች ከተማ” በሚል ርእስ በመጋቤ ሃይማኖት ብርሃኑ ቦጋለ እና በመ/ር በላይ ወርቁ፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ የተሰጡ ትምህርታዊ ስብከቶችም፣ የፀረ ተሐድሶ ገለጻውን የሚያጠናክሩና ለመንፈሳዊ ሕይወት መጽናትም የሚያግዙ መልእክቶች እንደተላለፉባቸው ከምእመናኑ ስሜት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በተከታዩ ነሐሴ 15 ቀን፣ ከምእመናኑ ሲሰበሰቡ ለቆዩና በኑፋቄው ሤራ ላይ ላተኮሩ በርካታ ጥያቄዎች፣ በመጋቤ ምሥጢር ፍሬው ዋለ፣ ትምህርት አዘል የኾኑ ምላሾች ከአባታዊ ምክር ጋራ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ መደምደሚያ በነበረው ነሐሴ 16 ቀንም፣ “ታዖማጎሲስ – የእግዚአብሔር ጠላቶች” በሚል ርእስ፣ በሦስት ተከታታይ ክፍል ከተዘጋጀው ቪሲዲ፥ ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ፣ ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ እና መ/ር ኢዮብ ይመኑ ንጽጽራዊ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡበት የአንድ ሰዓት ቪሲዲ ቀርቦ፣ ምእመኑ በከፍተኛ ጥሞናና ጉጉት ተከታትሎታል፡፡ የተቀመጠበትን ወንበር ጥላ አድርጎ፣ ለግማሽ ሰዓት ሳያቋርጥ በጣለው ዶፍ ዝናምና ብርቱ ነፋስ ሳይሠቀቅ በመጽናት፣ ቁጭቱንና ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡ በመጨረሻም፣ የጉባኤው ውጤታማነት፣ አካል ገዝቶና መልክ አውጥቶ የተገለጸባቸው ክሥተቶች ታይተዋል፡፡

burning of tehedesso publications

ማስረጃውና ማብራሪያው ከቀረበበት ምሽት አንሥቶ፣ የኑፋቄው ማሳያ የኾኑ ልዩ ልዩ ኅትመቶችን ምእመኑ ከየቤቱ እያመጣ ሲሰበሰቡ ቆይተው ነበርና እዚያው እንዲጋዩ ተደርገዋል፡፡ የሞባይል መጥሪያ የተደረጉ ‘መዝሙር’ ተብዬዎችም ተደምስሰዋል፡፡ ኑፋቄያቸው ከነትውስታው፣ ከምእመናኑ ሞባይል ብቻ ያይደለ ከልቡናቸውና ከአእምሯቸውም ለመሰረዙ ትእምርታዊ ኾኖ ተወስዷል፡፡ ይህም፣ “ከዐውደ ምሕረት ቢወርዱም በሕዝብ ልብ አሉ፤” እያሉ በእነአሰግድ ሣህሉና መሰሎቹ መወገዝና መታገድ፣ በመዋቅር ውስጥ ወሳኝ የሓላፊነት ቦታ ይዘው የሚያላዝኑ የኑፋቄውን ቀሪ ወኪሎች ዐይን ያወጣ ሙግት ያስተባብላል፤ ሰልፋቸውን በፍጥነት እንዲያስተካክሉም የማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡

ሰሎሞን ንጉሤ የተባለ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል ሓላፊ፣ ከኑፋቄው ኅቡእ ሠልጣኞችና ሰርጎ ገብ ጥቅመኞች አንዱ ነው፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በመራው የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ግምገማ ላይ፣ የአሰግድ ሣህሉ ተወግዞ መለየት እንደከነከነው ግልጽ አድርጓል፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትንም፥ “አውጋዦቹ” በማለት ተችቷል፡፡ አሰግድና መሰሎቹ፣ ከሕዝብ ልብ እንዳልጠፉ በጥራዝ ነጠቅ አንደበቱ ተንተባትቧል- “እየተወገዙና እየታገዱ ከዐውደ ምሕረት ቢወርዱም፣ ከሕዝብ ልብ አላወረድናቸው፤” ብሏል፡፡ የሌሎቹ ይቅርና፣ ሳይገባው፣ በስብከተ ወንጌል ሓላፊነት ተመድቦ የሚመራቸው፣ የመካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና እና የኮተቤ ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን እንኳ፣ ለፀረ ተሐድሶው ጉባኤ ያሳዩትን ምላሽ ማስተዋል ቢችል፣ ልቱት አነጋገሩ መልሶ ያንቀው ነበር፡፡

በደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ፣ የኑፋቄው ማሳያ ኅትመቶች ከየመኖርያ ቤቱ ተሰብስበው በተቃጠሉበት የፀረ ተሐድሶ ጉባኤው ማጠቃለያ፣ ምእመናኑ፣ “ዲያብሎስ ተመታ በመስቀል” እያሉ ዘምረዋል፤ በትዕይንተ አዲስ አበባ በእንጦጦ ተረተር የሚገኘውን ደብር ሰማይ በርችት ተኩስ አድምቀውታል፤ ጉባኤውም በተጠናከረ ዝግጅት እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ አስተዳዳሪው መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽም፣ ለሳምንታዊው የእሑድ ልዩ ጉባኤ፣ ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ በአካል የተገኙትንና በቪሲዲውም የታዩትን መምህራንም በመጋበዝ፣ የዕቅበተ እምነት ትምህርቱ ሳይቋረጥ በበለጠ ይዞታ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

debrasina faithfuls firework glittering the sky

ደብሩ፣ አውራ በመውጣት ያከናወነው የፀረ ተሐድሶ ጉባኤው ስኬት፣ በምእመናኑ ተግባራዊ ምላሽ ብቻ ሳይኾን፣ ከኑፋቄ ወኪሎች በታየው ብስጭትም ነው የተረጋገጠው፡፡ ከመርሐ ግብሩ መጠናቀቅ ማግሥት፣ በጉባኤው ወደ ተሳተፉት መምህራን ስልክ በመደወል፣ “ደማችሁን እናፈሰዋለን፤ ጠብቁ” በማለት እየዛቱ ለማስፈራራት ሞክረዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከተደወለባቸው የሞባይል ቁጥሮች ውስጥ፥ በ0920-190425፣ እስጢፋኖስ በሚል ስም የተመዘገበው እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቀቢፀ ተስፋቸውን ከማጋለጥ ውጭ፣ የእነርሱ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚያስደነግጠው የፀረ ተሐድሶ መስተጋድል ከቶም እንደሌለ ሊያውቁት ይገባል፡፡

aba hailgariel negash and mmr aschalew kebede

ከግራ ወደ ቀኝ፤ የአራዳ ጉለሌ /ከተማ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል ሓላፊ መጋቤ ሐዲስ ሶፎንያስ ጎመ፤ አስተዳዳሪው መልአከ ሕይወት አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ እና የስብከተ ወንጌል ክፍል አባል መ/ር አስቻለው ከበደ ከደብሩ ካህናት ጋራ

ቀደም ሲል ደብሩ፣ በኑፋቄው ወኪሎችና አቀንቃኞች ተጠቅቶ የነበረ ቢኾንም፣ ፈጥኖ ራሱን ማጽዳቱን ያወሱት መ/ር በላይ ወርቁ፣ አኹንም በሀገረ ስብከቱ አድባራት ተስተጓጉሎ የቆየውን የፀረ ተሐድሶ የዕቅበተ እምነት ጉባኤ፣ በአውራነት በማዘጋጀት አርኣያ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ “ዝግጅቱን ያስተባበሩት፥ ሰበካ ጉባኤው፣ የስብከተ ወንጌል ክፍሉና የሰንበት ት/ቤቱ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ተራራ ላይ የነፈሰው ነፋስ ሜዳውን ያጠራል፤” ብለዋል መምህሩ፣ “የጸናች ከተማ” በሚል ርእስ በሰጡት ትምህርት፡፡

የሀገረ ስብከቱ የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸም በተገመገበት መድረክ፣ የስብከተ ወንጌል አፈጻጸሙ መዳከም ቢታመንም፣ በበጀት ዘመኑ፣ 198 ገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት፣ 1 ቢልዮን ብር ያህል አጠቃላይ ገቢ እንዳስመዘገቡና ከዚህም ውስጥ የሀገረ ስብከቱ የ20 በመቶ ድርሻ፣ ብር 202 ሚሊዮን መሰብሰቡ ተገልጿል፤ በቀጣዩ ዓመትም ከብር 300 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ ግብ ተጥሏል፡፡ ይህ በራሱ የሚበረታታ ቢኾንም፣ ሰበካ ጉባኤያት ተጠናክረው የገንዘቡና ልማቱ ምንጭ የኾኑት ምእመናኑ ሊገኙና በልግስና ሊሰጡ የሚችሉት፣ ዋነኛ ተልእኳችን የኾነው ስብከተ ወንጌሉ ሲጠናከርና የግብረ ኖሎት ክትትሉና ድጋፉ አስተማማኝ ሲኾን ነው፡፡

ስለዚህም፣ ከጊዜ በኋላ፣ በተጠቀሱት አድባራት ለተነቃቃውና መንጋው ለሚጠበቅበት የዕቅበተ እምነት ጉባኤ፣ ሀገረ ስብከቱ ድጋፉን ሊሰጥ ይገባል፤ ለማካሔድ ያቀዱትንም ማበረታታት ይኖርበታል፡፡ አህጉረ ስብከት፣ ሲኖዶሳዊውን የፀረ ተሐድሶ ውሳኔና የጠቅላይ ጽ/ቤቱን መመሪያ በከፍተኛ ትጋት እያስፈጸሙ በሚገኙበት፣ የመንበረ ፓትርያርኩ መቀመጫና የአህጉረ ስብከቱ ማእከል የኾነው አዲስ አበባ፣ ከዳተኝነት ተላቆና መዋቅራዊ ሻጥሩን አጽድቶ ሰልፉን መቀላቀልና ማገዝም ይጠበቅበታል፡፡ በልዩ ሀገረ ስብከት ድንጋጌው፣ በአባትነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩም ያሉት የሚከተለውን ነው፡-

“የምእመናን መቀነስ፣ ከስብከተ ወንጌል እና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ኅሊና ዕንቅፋት እየኾነ ነውና ሃይማኖታዊውን መርሕ ጠብቀን፣ አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ ሊኾን ያስፈልጋል፡፡ የምእመናንን ልብ በሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኩራት እንዲሰማቸው በሚያስችል አሠራር ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን፡፡… እኛ ካህናት ኹሌም መጨነቅ ያለብን ስለ ሀብት ድልብ ሳይኾን ስለ ምእመናን ድልብ ነው፡፡ ከአያያዝና ከትምህርት ጉድለት፣ አንድ ምእመን ከበረታችን በተወሰደ ቁጥር ሀብታችን እየቀነሰ መኾኑን በውል እንገንዘብ፡፡ ምእመናን ካሉ ሀብቱ አለና፣ በእነርሱ ተገቢ ጥበቃና አገልግሎት ካበረከትን የሚጎድልብን አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ የሰበካ ጉባኤ ዓቢይ ተልእኮም ይኸው ነው፡፡”

 

 

Spread the love
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  
 •  

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.