ሰማያዊ፤ የብሔራዊ እርቅና መግባባት ጉዳዮች ኃላፊ ሾመ

አዲስ አድማስ

የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አቶ ነገሠ ተፈረደኝን፣ የብሔራዊ እርቅና መግባባት ጉዳዮች ኃላፊ አድርጐ ሾመ፡፡ ባለፈው ነሐሴ 14  የተሰበሰበው የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት፤ ያለፉትን ሁለት ወራትና በጠቅላላ የዓመቱን የሥራ ክንውን ሪፖርት ያዳመጠ ሲሆን የስራ አስፈፃሚውን አሠራር በግልና በቡድን ገምግሟል፡፡
ምክር ቤቱ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ የብሔራዊ እርቅና መግባባት ቋሚ ኮሚቴን ወቅታዊነትና አስፈላጊነት በመግለፅ፣ በመተዳደሪያ ደንብ 10/7 መሠረት ሲሰራ፣ አስፈፃሚ ውስጥ እንዲካተት ማፅደቁ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ነገሠ ተፈረደኝን በኃላፊነት መድበው፣ ለብሔራዊ ምክር ቤት በማቅረብ  ያፀደቁ ሲሆን ኃላፊነትና ተግባራቸውንም በዝርዝር አቅርበው አፀድቀዋል፡፡ ምክር ቤቱ የአቶ ነገሠን ሹመት በከፍተኛ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን እርሳቸውም የተሰጣቸውን ሃላፊነት በፅናት ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡

የብሔራዊ እርቅና መግባባት ጉዳዮች ኃላፊ፣ ከሚወጣቸው የሥራ  ሃላፊነቶች  መካከል፡- የድርድር ጥያቄዎች ሲመጡ በኃላፊነት ያስተባብራል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የድርድር ሀሳቦችን በማመንጨትና ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በማፀደቅ ለመንግስት፣ ለገዥው ወይም ለሌሎች ፓርቲዎችና ድርጅቶች ያቀርባል፣ የብሔራዊ እርቅ ተሞክሮ ያላቸውን ሀገሮች፣ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በማጥናት ለውይይት ያቀርባል፣ ብሔራዊ እርቅና መግባባትን  የተመለከቱ ትምህርትና ስልጠናዎች ያዘጋጃል፣ ለብሔራዊ እርቅ የሚረዱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የልምድ ልውውጦችን ያሳልጣል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ምክር ቤቱ ያካሄደው  የዘንድሮን  የመጨረሻ 5ኛ ዓመት፣ 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ሲሆን የቀጣዩን ዓመት ዕቅድ ለማፅደቅ፣ ለነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.