ከልሳነ ግፉዓንና ጠለምት የዓማራ ማንነት ጊዜያዊ ድጋፍ ኮሚቴ

ነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ/ም

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ ገዥ ቡድን አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የከፋፍለህ ግዛ ዘይቤ ለ26 ዓመት ያደረሰዉንና ዛሬም እያደረሰው ያለው ኢሰብአዊና አምባገነናዊ ተግባር ለኛ ለኢትዮጵያዊያኖች አይደለም ለመላው የዓለም ሕዝብ ገሃድ መሆኑ ግልፅ ነው። ገና ከማለዳው ይህ ዘረኛ፥ ጠባብ፥ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሆነው ቡድን በአንድና አንድ በሆነ አጀንዳ ብቻ ታውሮ ትግራይን ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጥሎ እንደ ሃገር ለማቆም ከያዘው ቅዥት የተነሳ አጎራባች ከሆኑ ክፍለ ሃገራት በግድና በሃይል ለም የሆኑ መሬቶችን ወደ ትግራይ ማስገባት ቀደም ሲል የፈፀመው ተግባር ብቻ ሳይሆን ዛሬም በስፋት እየጣረበት ይገኛል።

ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየፈፀመው ያለው አስቃቂ ድርጊት ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እያደረሰ ያለ መሆኑን ግልፅ ቢሆንም በተለይ ደግሞ በሃይል ያለ ሕዝቡ ፈቃድ ማንነታቸዉን ረግጦ ያልሆኑትን ናቸው በማለት በግዳጅ ወደ ትግራይ በአስገባቸው የወልቃይት፥ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ ለረዥም ዓመታት ስልጣን በሃይል ከመንጠቁ በፊት ጀምሮ እያደረሰ ያለው በሰው ልጆች ዘንድ ይፈፀማል ተብሎ የማይጠበቅ ግፍ በቃላት ለመግለፅ ያዳግታል።

በ ሃያ ስድስት የግፍና የመከራ ዓመታት ውስጥ ይህ ዘረኛ ቡድን የኢትዮጵያን ሕዝብ በቋንቋ ከልሎ በዘርና በጎጥ ሕዝቡ እርስ በራሱ እንዲጋጭ፥ የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነችዉን ኣገራችንን ባህር በር አልባ እንድትሆን አድርጎ ኢትዮጵያን ደካማና በማንም የውጭ ሃይል የምትደፈርና የምትጠቃ ደካማ ኣገር ለማድረግ ረዥም መንገድ ተጉዟል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በትምህርት፥በጤና እና በመሠረታዊ ልማቶች ደካማ አድርጎ ታላቋን ትግራይ ግን በሁሉም የዕድገት መለክያ ከሌሎች የተሻለችና የጠነከረች ለማድረግ ያለመታከት እየሠራ ይገኛል።

ታላቋን ትግራይ የመመሥረት ቅዠት ምክንያት ከስድስት ምዕተ ዓመታት በላይ በጎንደር ክ/ሃገር ሥር የነበሩትን ወልቃይት፥ ጠገዴና ጠለምትን ወደ ትግራይ ክ/ሃገር አስገባ። እነዚህ ወረዳዎች ከትግራይ ክ/ሃገር አዋሳኝ በመሆናቸዉና የትግርኛ ቋንቋም ለመግባቢያ ያክል በመናገራቸው ምክንያት ብቻ ባህላቸው፥ ዋናው የትውልድ ቋንቋቸው እና ከሁሉም በላይ ሳይታይና ሳይጠየቁ ያለባህላቸዉና ያለፍላጎታቸው ትግሬ ናችሁ ተባሉ። ይሁን እንጂ ጀግናው የወልቃይት፥ ጠገዴና የጠለምት ሕዝብ አንድም ጊዜ ሳያርፍ ማንነቱንና ምንነቱን ለማስከበር ያልታገለበት ጊዜ የለም።

እራሱ ወያኔ ባወጣው ሕገ መንግሥት ተጠቅመው የአማራ ማንነታቸዉንና የሚደርስባቸዉን ኢሰብዓዊ ተግባራት ለመቃወም ህጋዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው በመንቀሳቀሳቸውና ይህም የአማራ ማንነት ጥያቄ ጀግናው የጎንደር ክ/ሃገር ሕዝብና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱን የተገነዘበው ዘረኛ የወያኔ ቡድን በሁሉም ዘርፉ የሽብር ስራዉን አጠናክሮ ከመቀጠሉም በላይ የዚህ ሰላማዊ የማንነት ጥያቄ መሪዎችን በሀሰት በመወንጀል ከሶ ዛሬ በእሥር ቤት እያሰቃያቸው ይገኛል።

ወያኔ የወልቃይት፥ ጠገዴና ጠለምት ለም ወረዳዎችን ወደት ግራይ ማስገባት ብቻ ሳይሆን ሴት እህቶቻችንን አስገድዶ በመድፈርና ዘርን ለማጥፋት የሚፈፅመው ተግባር፤የተቃወሙትን ሁሉ በእሥር በማሰቃየት ቀሪዎቹም ተወልደው ያደጉበትን ቀዬአቸዉን ጥለው እንዲስደዱ ምክንያት ሲሆን በርካታዎቹም ፊት ለፊት ይህንን አስከፊ ዘረኛ ሥርዓት በመጋፈጥ ለ37 ዓመታት ያህል እየታገሉ ይገኛሉ።

እኛም በመላው ዓለም ዙርያ የምንገኝ የዚህ አከባቢ ተወላጆች ምንም እንኳ ወያኔ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን እየፈፀመ ያለውን ሃገርን የመበታተን፥ ሕዝብን የመከፋፈል፥ ሃይማኖትን የማጥፋት፥ ታሪካዊ ቦታዎችን እንዳልነበሩ በማድረግ፥ የታሪክ መዛግብትን ማዛባትና ማበላሸት፥ የሃገር ቅርስን ለባዕድ አሳልፎ መስጠትንና ባህልን ማንቋሸሽ የመሳሰሉትን እኩይ ተግባራትን ማየትን እንደማነኛዉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያንገበግበን ጉዳይ በመሆኑ ለፍትህ፥ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ ከሚታገሉ እንደ ጎንደር ሕብረት፥ የአንድነት ሃይሎችና በኢትዮጵያዊነታቸው ከሚያምኑ የብሔር ድርጅቶችና ከመላው ሕዝባችን ጋር አብረን የምንታገልው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እንወዳለን።

ከላይ የጠቀስናቸው አከባቢዎች ማንነታቸዉን ያጡበት፥ ህልውናቸዉን ለአደጋ የተጋለጡበት፥አማራ ምንነታቸዉን ውድቅ ተደርጎ ትግራያዊ እንዲሆኑና፥ የታላቋ ትግራይ አካል እንጂ ኢትዮጵያዊ የጎንደር አማራ አለመሆናቸዉን በግዴታ እንዲጋቱ ቢደረጉም እምቢኝ አሻፈረኝ ማንነቴ የጎንደር አማራ ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለት ወያኔን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት እየተፋለሙ ይገኛሉ።

እኛም በመላው ዓለም የምንገኝ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች ሕዝባችን ከዘረኛው ወያኔ ጋር እያደረገው ያለው የማንነትና የህልውና ትግል በተናጥል ስናደርገው የነበረውን እንቅስቃሴ ሃይላችንን የሚከፋፍል፥ የትግል ጊዜዉን የሚያራዝም መሆኑን በመገንዘብ አንድነታችንን በማጠናከር ሕዝባዝችን እያደረገው ያለዉን ሁለገብ ትግል ማንነታችንና ህልውናችንን እስኪረጋገጥ ድረስ አቅማችን በፈቀደውና በተቻለው ሁሉ ለመርዳት ይቻል ዘንድ ይኽውና የወልቃይት ጠገዴ(ልሳነ ግፉአን) እና ጠለምት የዓማራ ምንነት ጥያቄ ጥምረት ፈጥረን በጋራ ለመታገል የድጋፍ ኮሚቴ በማቋቋምና ጊዜአዊ አመራር በመምረጥ ያልተቆጠበ ድጋፋችንን ለመስጠትና የትግሉ አጋር ለመሆን ቆርጠን ተነስተናል። ባጭር ጊዜ ዉስጥም ውህደት ለመፍጠር በሂደት ላይ መሆናችን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

 

በትግላችን ማንነታችንንና ህልውናችንን እናስከብራለን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ብክብር ትኑር!!

የወልቃይት ጠገዴ ልሳነ ጉፍዓንና የጠለምት የአማራ ማንነት ጥምረት ጊዜአዊ ኮሚቴ

 

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.