ኦሮሚያ ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሳ አለመግባባትን በህዝበ ውሳኔ ለመፍታት እየተሰራ ነው— አቶ ለማ መገርሳ

አዳማ ነሀሴ 23/2009 በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ጉዳት ሳያደርሱ  በህዝበ ውሳኔ ለመፍታት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ ። ” የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት አንድነት ጉባኤ” በሚል በቢሾፍቱ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ ፕሬዘዳንቱ ከኦሮሞ አባገዳዎች ምክር  ቤት አባላት ጋር ተወያይተዋል፤ ለተነሱ ጥያቄዎችም  ምላሽና  ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በውይይቱ ወቅት ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ በምስራቅ ሐረርጌ ፣ ባሌና በሌሎችም አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በሚከሰተው ግጭት  ህብረተሰቡ ለችግር እየተዳረገ መሆኑ ተነስቷል፡፡ በዚህም ልማቱ እየተደናቀፈ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠውም አባገዳዎቹ ለፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል። የኦሮሞ አባገዳዎች ጉባኤ ሰብሳቢና የቱለማ አባገዳ በየነ ሰንበቶ ለፕሬዝደንቱ ያቀረቡት ጉዳይ የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት ስፍራ በተገቢ  ሁኔታ ተይዞና ለምቶ የቱሪስት መዳረሻ መሆን እንዳለባት ነው።

የእምነት ነፃነት በተረጋገጠበት አገር የዋቄፈቻ እምነት ተከታዮች የቀብር ስፍራ በማጣት እየተንገላቱ ስለሆነ መፍትሔ እንዲሰጠው  ከአባገዳዎች የቀረበ ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ አባገዳዎች ምንም ዓይነት በጀት ሳይኖራቸው በግል የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው  የክልሉ መንግስት ሊያግዛቸው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

አቶ ለማ መገርሳ በሰጡት ምላሽ  ሁሉንም ችግሮች በአንድ ጀንበር መፍታት እንደማይቻል ገልጸው መንግስት ሰላምን ፣ ልማትንና  መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከምንጊዜውም በላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እንዲሁም  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን  እየተረባረበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። “ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚከሰተውን ግጭት ለማስቀረት መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠው የአንድም ሰው ሕይወት  እንዳይጠፋ መከላከል ነው ” ብለዋል፡፡

የክልሉ ፕሬዝደንት በማያያዝም በአንድ በኩል ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የህዝብ ድምፅ እንዲከበር በሌላ በኩል ደግሞ  ህዝበ ውሳኔ ባልተካሄደባቸው ከጎረቤት የክልል መስተዳድር አካላት ጋር በመወያየት የጋራ መፍትሔ የማስቀመጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የአባገዳዎች ምክር ቤትን ለማጠናከርም በቅርበት እየተመካከረ ተባብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠውላቸዋል ።

ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የእሬቻ በዓል ታዳሚዎች ቁጥር በሺህዎች የነበሩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የበዓሉ ታዳሚዎች በሚሊዮን  የሚቆጠሩ እየሆኑ መምጣታቸው መልካም መሆኑን አቶ ለማ አስታውቀዋል፡፡ ” በዓሉ የሚከበርበት ስፍራ በዓመት አንድ ጊዜ የምንሰባሰብበት ብቻ ሳይሆን  ዓመቱን ሙሉ በእንግዶች የሚጎበኝ የኢኮኖሚ ምንጭ  እንዲሆን የተጠናከረ ስራ ይከናወናል”ብለዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.