በቁጥር 30 የሚሆኑ የወልቃይት ተወላጆች 24 ሰአታት በካቴና ታስረው በደል እንደሚፈጸምባቸው ተገለጸ

(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 25/2009) ከሁመራና አካባቢዋ ተይዘው ወደ መቀሌ ወህኒ ቤት የተጋዙ በቁጥር 30 የሚሆኑ የወልቃይት ተወላጆች 24 ሰአታት በካቴና ታስረው በደል እንደሚፈጸምባቸው ተገለጸ።

የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ እንዳስታወቁት ከመካከላቸው 6ቱ የደረሱበት አልታወቀም።
ሰዎቹ ይረሸኑ አልያም ወደሌላ እስር ቤት ይወሰዱ የታወቀ ነገር አለመኖሩን አመልክተዋል።

ከሁመራና አካባቢዋ የተያዙትና ወደ መቀሌ የተጋዙት የወልቃይት ተወላጆች ከሰኔ 17 2009 ጀምሮ 24 ሰአታት ሙሉ በካቴና ታስረው እንደሚውሉና እንደሚያድሩ በማህበራዊ ገጻቸው የገለጹት አቶ አብርሃ ደስታ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ካቴናው ከእጃቸው የሚወልቀው በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ገላቸውን ለመታጠብ ነው።

በወህኒ ቤቱ ውስጥ ከሌሎች እስረኞች ተለይተው በካቴና የታሰሩት የወልቃይት ተወላጆች ብቻ መሆናቸውንም መረዳት ተችሏል።

ከመካከላቸው ስድስቱ ተለይተው የተወሰዱ ሲሆን እነዚህም ተረሽነው የሆናል የሚል ስጋት በሌሎች ዘንድ አሳድሯል።

በሌላም በኩል ከምድር በታች ታስረው ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳለም አቶ አብርሃ ደስታ በገጻቸው አስፍረዋል።

የወልቃይት ተወላጆች ለብቻ ተነጥለው ሲታሰሩ ደግሞ በፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆኑ ሰርቀው በተራ ወንጀል የታሰሩ ወልቃይቶችም በካቴና እንዲታሰሩ መደረጋቸውም ታውቋል።

በኮለኔል ደመቀ ዘውዱ የሚመራው የወልቃይት የማንነት ኮሚቴ አባላት ወልቃይት የአማራ ነው በሚል የጀመሩት እንቅስቃሴ በጉልበት ከተገታ በኋላ ከፊል የኮሚቴ አባላት ሲታሰሩ የቀሩት ከሀገር ተሰደዋል።–የተገደሉ መኖራቸውም ተመልክቷል።

የእንቅስቃሴው መሪ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ በአዲስ አበባና በጎንደር ክስ ተመስርቶባቸው በጎንደር ወህኒ ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል።

የወልቃይት ተወላጆች ሕወሃት ስልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ በኋላ ለ40 አመታት የዘር ማጽዳት ግፍ ሲፈጸምባቸው እንደቆየ ሲናገሩ ቆይተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.