ክቡር ሚንስተር – አያውቁኝም ክቡር ሚኒስትር?

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • አያውቁኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • በሰሞኑ የሙስና ግርግር ከአገር የወጣህ ነህ?
 • ኧረ ከአገር ከወጣሁ ቆይቻለሁ፡፡
 • ማን ልበል ታዲያ?
 • ከጣሊያን ነው የምደውልልዎት፡፡
 • ከዚያ ደግሞ ገንዘብ ማን ላከልኝ?
 • ኧረ ገንዘብ ተልኮልዎት አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምን ፈልገህ ነው የደወልከው?
 • ጥያቄ ልጠይቅ ነው የደወልኩት፡፡
 • የምን ጥያቄ ነው?
 • መንግሥት ምን እየሠራ ነው?
 • አንተ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ ነህ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ማን ሆነህ ነው ይኼን ጥያቄ የምትጠይቀኝ?
 • ኧረ እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ነው የምጠይቅዎት፡፡
 • መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግክ አገርህ መምጣት ትችላለህ፡፡
 • እንዳልመጣማ የጥገኝነት ወረቀቴ አላለቀልኝም፡፡
 • አገርህን ክደህ ታዲያ እንዴት ስለመንግሥት ትጠይቀኛለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር አገሬን የምክደው ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ ነው፡፡
 • ማን ነው ያስገደደህ?
 • ድህነት ነዋ፡፡
 • ስማ አገሪቷ በ11 በመቶ ዕድገት እየተምዘገዘገች መሆኗን አታውቅም እንዴ?
 • ሲባልማ ሰምቻለሁ፡፡
 • ለመሆኑ ከአገር ከወጣህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ?
 • አሥር ዓመት አልፎኛል፡፡
 • በቃ አሁን መጥተህ ብታያት ኢትዮጵያ ጣሊያንን ታስንቃለች፡፡
 • ለነገሩ መናቃችንንም ሰሞኑን በተፈጸመው ድርጊት አረጋግጫለሁ፡፡
 • ማን ነው የናቀን?
 • ጣሊያኖቹ ናቸዋ፡፡
 • ስማ ጣሊያንን ቀጥቅጠን እንዳባረርነው ረሳኸው እንዴ?
 • እሱማ የዓድዋ ድል ከእኛም አልፎ የጥቁር ሕዝብ ኩራት ነው፡፡
 • ታዲያ ይኼን እያወቅክ እንዴት ተናቅን ትላለህ?
 • ይኼ አባቶቻችን የሠሩት ታሪክ ነዋ፡፡
 • እኛም ቢሆን መድገማችን መቼ ይቀራል?
 • ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው ግን ከሚያወሩት ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡
 • ሰሞኑን ምን ተፈጸመ?
 • ይኸው የጣሊያን መንግሥት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ከፍተኛ ግፍ እየፈጸመ ነው፡፡
 • ሰው ከአገር የሚሰደደው ለምንድነው?
 • ችግር ነዋ፡፡
 • እንዴ ምንድነው የሚቸግረው?
 • ክቡር ሚኒስትር አብዛኛው ወጣት በአገሪቱ ተስፋ ቆርጦ እኮ ነው ባህር የሚሻገረው፡፡
 • ይኸው በአነስተኛና ጥቃቅን ወጣቱ እንዲደራጅ እያደረግን እይደል እንዴ?
 • እ. . .
 • ከዚያም በላይ ለወጣቶች የተለየ ፈንድ አዘጋጅተን ሥራ ፈጣሪዎች እያደረግናቸው አይደል እንዴ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር እኔ እንደሰማሁዎት ሌላ ሰው እንዳይሰማዎት?
 • አንተ ፀረ ልማት ነህ መሰለኝ?
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር በዜጎቻችን ላይ የተሠራውን ግፍ መንግሥት እንዲያወግዘው ለመናገር ነው የደወልኩት፡፡
 • የስደተኞቹን ሠልፍ የጣሊያን ፖሊስ በውኃ መበተኑ ነው ግፍ የምትለው?
 • ከእኛ አገር ጋር አነፃፅረው ነው ግፍ ያለመሰለዎት?
 • እንዲያውም ስደተኞቹ ፖሊሶቹን ማመስገን ይገባቸዋል፡፡
 • ለምን?
 • ውኃውን ስላላፈሉት!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኮንትራክተር ይደውልላቸዋል]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ እባክህ?
 • ሰላም ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሥራ እንዴት ነው?
 • ስለሥራ ጉዳይ ላወራዎት ነው የደወልኩት፡፡
 • የእኔና የአንተ ሥራ አይገናኝም እኮ፡፡
 • አውቃለሁ ግን መንግሥት ምን እየሠራ ነው ለማለት ነው፡፡
 • ምነው መንገድ መሥራት አቆመ እንዴ?
 • አዎና ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኸው በቅርቡ አይደል እንዴ የ2010 በጀት ያፀደቅነው?
 • ቢፀድቅ ምን ዋጋ አለው?
 • ምን ተፈጠረ?
 • ሥራ እኮ ቆሟል፡፡
 • በሰሞኑ ግርግር ምክንያት ነው?
 • ኧረ በፍፁም፡፡
 • ታዲያ በምን ምክንያት ነው ሥራ የቆመው?
 • ለእኔም ግራ ገብቶኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን እኔንም ግራ እያጋባኸኝ ነው፡፡
 • የሚፈርም ሰው እኮ የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አልገባኝም፡፡
 • ሥራ ሠርተን ከጨረስን በኋላ የሚፈርም ባለሥልጣን ስላጣን ገንዘባችንን መቀበል አቅቶናል፡፡
 • እ. . .
 • ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ መፈረም አቁሟል፡፡
 • ለምን?
 • በቃ በሰሞኑ የሙስና ዘመቻ ፍራቻ ሰዎች መፈረም አቁመዋል፡፡
 • እውነታቸውን ነዋ፡፡
 • እንዴ ከአቴንዳስ ውጪ ሌላ ወረቀት ላይ መፈረም ያቆሙ ነው የሚመስለው፡፡
 • ታዲያ በኋላ ማን ይገባል?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ በሀቀኝነት የምሠራ ኮንትራክተር ነኝ፡፡
 • ስማ ማንም ሰው እስኪጣራ መንገላታት አይፈልግም፡፡
 • እኔ እኮ አሁን ሥራ እንዳቆም እየተገደድኩ ነው፡፡
 • ከሰሞኑ የሥራ ማቆም አድማ ጋር በተገናኘ ነው?
 • ኧረ ለሠራተኞቼ ደመወዝ መክፈል ባለመቻሌ ነው፡፡
 • አይ እንዳዛ ከሆነ ይቻላል፡፡
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሥራ ማቆሙ ነዋ፡፡
 • ለምን?
 • ልማታዊ ሥራ ማቆም ስለሆነ!

[ክቡር ሚኒስትሩን አንድ የውጭ ባለሀብት ሆቴል ይቀጥራቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር ስለመጡ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
 • አንተ ግን ምን ሆነህ ነው?
 • ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
 • በዚህ ወቅት እንዴት እንደዚህ ዓይነት ቦታ ትቀጥረኛለህ?
 • ምነው ሆቴሉን አልወደዱትም?
 • በዚህ ወቅት ከውጭ ባለሀብት ጋር መታየት ስለማያዋጣ ነዋ፡፡
 • ምን ላድርግ አስቸኳይ ነገር ገጥሞኝ ነው፡፡
 • ታዲያ ቢያንስ ቢያንስ እኔን ዱባይ መቅጠር ያቅተሃል?
 • ለነገሩ እዚያም መገናኘት እንችል ነበር፣ ግን ያው ጉዳዩ አስቸኳይ ስለሆነ ነው፡፡
 • ለመሆኑ ምን ፈልገህ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ስለጨረታው ጉዳይ ለማውራት ነው፡፡
 • አንተ ሰውዬ ጤነኛ አይደለህም አይደል?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ እንደዚህ ዓይነት ነገር እዚህ ቦታ ማውራት ለእኔ ጥሩ አይደለም፡፡
 • አጭር ደቂቃ እኮ ነው የምንወያየው?
 • ስማ እዚያ ጋ ያፈጠጡብንን ሰዎች ታውቃቸዋለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ የውጭ አገር ዜጋ ነኝ፣ እዚህ አገር ብዙ ሰው አላውቅም፡፡
 • ቆይ ጨረታውን ተወዳድረሃል አይደል?
 • ጨረታውንማ ተሳትፌ ብዙ ርቀት ተጉዣለሁ፡፡
 • ታዲያ ምን ልርዳህ?
 • እርስዎ የሰጡኝ ሰዎችም ጨረታውን እንዳሸንፍ አድርገውኛል፡፡
 • ኧረ አንተ ሰውዬ ዝም ብለህ አፍህን አትክፈት፡፡
 •  ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር ስለጉዳዩ ለማስረዳት ብዬ ነው፡፡
 • እዚያ ጋ የተቀመጡት ሰዎች አላማሩኝም ዝም ብለው እያዩን ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለማንኛውም አሁን አንድ ነገር ነው የቀረኝ፡፡
 • ምን?
 • ጨረታውን ስለማሸነፌ እርስዎ በፊርማዎ ማረጋገጥ አለብዎት፡፡
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር ገንዘቡ እንደተከፈለኝ የእርስዎን ሙሉ ኮሚሽን አስገባለሁ፡፡
 • በሳምሶናይት የያዝከው ምንድነው?
 • እስከዚያው ለሥራ ማስኬጃ እንዲሆነዎት ያመጣሁት ገንዘብ ነው፡፡
 • ስማ እኔ በብር ከሆነ አልቀበልህም፡፡
 • ታዲያ በምንድነው የሚፈልጉት?
 • በውጭ ምንዛሪ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ እንዳለች መቼም ያውቃሉ፡፡
 • እሱ አይመለከተኝም፡፡
 • ታዲያ ምን ላድርግ?
 • ክፈታ፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ኤልሲ!

[ክቡር ሚኒስትሩ እየተገመገሙ ናቸው]

 • እንዴት ዓይነት ደፋር ነዎት ግን ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን አደረግኩ?
 • መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ሳይቀር ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን ዘነጉት እንዴ?
 • እሱንማ እኔም በጣም የምደግፈው አካሄድ ነው፡፡
 • ትንሽ አያፍሩም እንዴ?
 • ምን ያሳፍረኛል?
 • የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ አሉ፡፡
 • ማን ነው ሌባው?
 • እርስዎ ራስዎት፡፡
 • ብንከባበር ይሻላል፡፡
 • ማስረጃ አለን እኮ፡፡
 • የምን ማስረጃ ነው?
 • መሥሪያ ቤትዎት ያወጣውን ጨረታ ያሸነፈው ማን ነው?
 • እ. . .
 • ባለፈው ሆቴል ውስጥ ኮሚሽንዎትን በውጭ ምንዛሪ ሲቀበሉ ማስረጃ አለን፡፡
 • እኔ እኮ የመንግሥት ስትራቴጂን ተከትዬ ነው፡፡
 • የምን የመንግሥት ስትራቴጂ ነው?
 • ማለቴ መንግሥት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስተመንትን ያበረታታል፡፡
 • ታዲያ የእርስዎን ሙስና ከዚህ ጋር ምን አገናኘው?
 • ያው እኔም ለአገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት አስቤ ነው፡፡
 • ኪኪኪ. . .
 • እውነቴን ነው፡፡
 • ለዛ ነው ኮሚሽንዎን በውጭ ምንዛሪ የተቀበሉት?
 • አዎ እንደነገርኩህ ስትራቴጂዬ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡
 • ምን የሚሉት ስትራቴጂ ነው?
 • የውጭ ቀጥተኛ ሙስና!

ምንጭ – ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.