የቅኔው ዕንቡጥ ጥልቅ ሚስጢር ነው – ከሥርጉተ ሥላሴ 04.09.2017 (ዙሪክ-ሲዊዘርላንድ።)

 „እንሆ እግዚአብሄር ፍጹሙን ሰው አይጥለውም፣ የኃጢአተኞችንም እጅ አያበረታም። አፍህ እንደ ገና ሳቅ ይሞላል፣ ከንፈሮችህንም እልልታ ይሞላል። የሚጠሉህ እፈረት ይለብሳሉ፤ የኃጢአተኞችም ድንኳን አይገኝም። (መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 20- 22)

ግን ስለምን? እኮ ስለምን? የፍቅር ተፈጥሮ ህግጋት፣ ዶግማ፣ መርኽ መልዕክተኛ ስለምን ተፈሪ ይሆናል?

አንድ የህዝብ መሪ ነኝ የሚል አካል (የትግሬ ነፃ አውጪ ድርጅት) እውነት ከሆነ የፍቅርን ተፈጥሮ እንዴት እንዲህ በአደባባይ ይታገላል? እንዴት አንድ የህዝብ መሪ ነኝ የሚል አካል (የትግሬ ነፃ አውጪ ድርጅት) ስለ ስምምነት ስለምን ስጋት ይኖረዋል? እንዴት አንድ የህዝብ መሪ ነኝ የሚል (የትግሬ ነፃ አውጪ ድርጅት) አካል ስለ መግባባት ሰለምንስ እንዲህ ራድ ይይዘዋል? እንዴትስ የእርቅን መስመር እንደ ጦር ይሸሸዋል? እንዴትስ አንድ የህዝብ መሪ ነኝ የሚል አካል በልስሉስ ዬምስራች ዜና ስለምንስ እንዲህ ይርበተበታል?

… ለዛውም „የፍቅር ቀን ያወጀ፣ የመቻቻል ቀንን ያወጀ፣ የአክብሮት ቀን ያወጀᵎ“ ህም! ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ማስቀጠያ ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ ዬሰሞናት መሪ ቃል ተብለው የተለሰኑ ስንኞች አቅሙም ወርዱም አይችሉትም። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ፖሊሲና የፖሊሲው አምንጪ ማንፌስቶው ኃይለ ቃላቱን፤ እነዛን ቅዱሳን ቃላትን የመሸከም አቅማዊ ተፈጥሯቸው፤ መቅኗቸው ቅንቅን የበላው ነው። ካለ ልክ የተሰፋ ጥብቆ። ስለምን? ሥርዓቱ ሰውን ማዕከል ማድረግ ያልቻለ ስለሆነ። የጭካኔ አንበል ስለሆነ። የሐዘን ዓወጅ ነጋሪ ስለሆነ። ባጠቃላይ ወያኔዊ ሂደቶች በሙሉ ጠረናቸው ህምመተኛ ነው … መነሻ መሰረታቸው ይሁኑ ግባቸው … በቀል።

ህሊና ላለው ሰብዕዊ ፍጡር … ፍቅር እኮ ታላቅ የድህነት የምስራች ነው። ፍቅር እኮ ፍጽምናን የተጎናጸፈ መድህን ነው፣ ዬፍቅር ዕሴቱ ፈዋሽ የሆነ አዲስ የብሥራት ዜና ነው። ፍቅር እኮ የሰው ልጅ ተመራምሮ የማይደርስበት፣ ሚስጢሩ እጅግ ጥልቅ የሆነ አዲስ ቀለምም ነው። ፍቅር የወጣለት የደግነት ሐዋርያ ነው። ፍቅር መስመር የለሽ ንጹህ ውሃ ነው። ፍቅር ድንግል ነው። ያልባለቀ

ፍቅር እኮ ታላቅ የምኽረት ስምረት የመንፈስ ዓዋጅ ነው። የፍቅር ንጹህ ተፈጥሮ፣ የውስጥ አካላት የጥምረት አህትዮሽ ልዩና ልዑቅ የዕዕምሮ ለውጥ የመብቃት አብዮት ነው። ፍቅር እኮ የመጪው አዲስ ዘመን የተስፋ ማህደር ነው። ፍቅር እኮ የመኖር አንጎል ነው። ፍቅር እኮ የነፍስ እጬጌ ነው። ፍቅር እኮ ትውልድ ነው። ፍቅር እኮ ዘመን ነው። ፍቅር እኮ ንጹህ አዬር ኦክስጂን ነው።

የሰው ልጅ እኮ ለማንኛውም ነገር መፍትሄ ማበጀት አይችልም። የፍቅር ተፈጥሮ ግን ይችላል። የሰው ልጅ የመታገስ አቅሙ እጅግ ጠባብና ክሱ ነው። ፍቅር ግን የዳበረ፣ የፋፋ፤ አቅም ያለው ብቁ ነው። ፍቅርን የሚያሸንፍ ምንም ዓይነት የችግር አመክንዮ በምንኖርባት ፕላኔታችን ፈጽሞ የለም።

ሁልጊዜም የፍቅር ንድፍ ድል ላይ ነው። ፍቅር የወርቅ ድልድይ ነው። ምልካም አደራዳሪ ነው ፍቅር፣  ለዚህም ነው የቅኔው ዕንቡጥ ትውልዳዊ ድርሻውን የሚወጣበት ዬመርሁ መቅድም „ፍቅር ያሸንፋል“ ብሎ አህዱ ያለው። ፍቅር ጠላት የለውማና። በፍቅር ተፈጥሮ ውስጥ በቀል ሙት ነውና። ጠቢቡ ቴውድሮስ ካሳሁን ስለፍቅር ተፈጥሮ ታታሪ ነው። ትጉህ – ንብ ነው። ዓራት ዓይናማ ነው። ለፍቅር ተፈጥሮ መርሆችም እጅግም ደፋር ጀግና ነው። በቀልን፣ ቂመኝነትን በድርጊቱ የረታ … ትንታግ።

ፍቅር ሳይንስ ነው። ፍቅር ፍልስፍና ነው። ፍቅር ሙያም ነው – ለእኔ። ፍቅር  የነፍስ አናባቢ ነው። ፍቅር እኮ ትውልድ ነው። ፍቅር ነገ ነው። ፍቅር ከነገወዲያም ነው። ፍቅር ከዛም ወዲያ ነው። የፍቅርን አቅምና ችሎታ መለኪያም ደንበርም መስራት ከቶውንም አይቻልም። ይህ የቅኔ ቀንበጥ የሚታገለው ለዚህ ጥልቅ ለሆነ የመኖር፤ የራዕይ፣ የትንቢት፤ የተስፋ መንገድ ነው። ወጣቱ እኮ ከሚጠበቀው በለይ ጎልምሶ፣ ምራቁን ውጦ የተወለደ የመልካም አስተሳሰብ ፍልስፍና ፈላስማ ነው። ከፍቅር በላይ ምንስ ምድራዊ አምክንዮ አለና። ፍቅር ከሁሉም በላይ የሆነ የመልካምነት አንባ ነው።

ግጥሞችንም፤ ዜማውንም፤ የዜማውን አስተዳደር ነፋሻማ ጀረቶችን ትቼ፣ እያንዳንዱ የቃለ ምልልስ ሂደቶችን በተናጠል ቢታዩ ሰፊ የምርምር መስክ የሚሆኑ ናቸው። ዛሬ በ80 እና ከዛም ባለፈ ዕድሜ የሚገኝ የፖለቲካ ሰው አቅል አጥቶ፣ አደብ ተራቁቶበት ነው የሚታዬው። እሱ ደግሞ በወጣትነቱ ይህን የመሰለ ግርማ ሞገስ ያለው እርጋታና አርቆ አሳቢነት ከማይጠገብ ለዛ ጋር ማሳዬቱ እጅግ የሚገርም አመክንዮ ነው … ለእኔ። እራሱ የቃለ ምልልሱ የስክነት ማዕዛው፣ ጠረኑ፣ ሳቢነቱ ከቶውንም  የማይጠገብ የማስተዋል ተቋም ነው። ከልብ የማይወጣ፣ በውስጥም ጸንቶ የሚቀመጥ መልካም ጥሪት ነው። ማገር። የተወደደው እኮ በዓዋጅ ወይንም በነጋሪት፤ ወይንም ፕሮፖጋንዲስቶች በትጋት አሰማርቶ ፈጽሞ አይደለም። ንጹህ መንፈሱ እጅግ ጤናማ በመሆኑ ነው … እኔና መሰሎቼን ከውስጡ ያሰለፈን። ፈቅድን፣ ወደን፣ ደስ ብሎንም ነው መልዕክቶችን ከውስጣችን የምናዋህደው።

ሚስጢሩ ሰውን በማስተዋል ማዕከሉ በማድረጉ ነው። ሚስጢሩ በመሆን ውስጥ ፈቅዶ መኖሩ ነው። ሚስጢሩ መሆንን ከምርምር ባለፈ ስለ አነበበው፣ ስለተረጎመው፣ ስለ አመሳጠረው ነው።  ይህ ቀንበጥ የፍቅር ተፈጥሯዊ መርሆዎች የዕድማታው ብቁ ሚስጢረኛ ነው። Magnet.

እኔ የመሪነት ክህሎትም እያዬሁበት ነው። የእኔ ተመስጦ በጥበብ ሰውነቱ፤ ወይንም በጸሐፊነት የተለዬ ጸጋው ብቻ ሳይሆን የንግግሩ እርከን፤ ድንበር፤ ማዕዶተ- ትንፋሻቸው አቅሙን ገላጭ መስታውት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በተደጋጋሚም አድምጫቸዋለሁ። አይሰለቹም። አይጠገቡም። ተዘውትረው ይናፈቃሉ።

መሪነት ስጦታ ነው። መሪነት በዕውቀት ጣሪያ ብቻ ሊለካ አይችልም። ሰማያዊ መክሊትም ነው መሪነት። ቅባዕ ነው መሪነት። ለዚህ ብቻ ተለይተው የሚፈጠሩ አሉ። ሁሉም የሰው ልጅ መሪ የመሆን ፍላጎት ሊኖርው ቢችልም ወይንም የህሊና አቅም ቢኖረውም የመሪነት ግርማ – ሞገሱን፤ ማህባውን የሚያላብሰው ግን የሰማይ ምርጥነት መሆን መቻል ይመስለኛል። የሰብዕና አገነባቡ ለዚህ ብቻ የተሰጠው – እንደ ማለት።

የሆነ ሆኖ የጠቢቡ ቴውድሮስ ካሳሁን ድርጊቱ ነው የመወደዱን ፊደል ለእኔ ያስቆጠረኝ። የፊደል ገበታዬ ርቁቅ ሚስጢራዊነቱ ነው። በእሱ ያደረ ቅዱስ መንፈስ ፍጹም ልዩ ነው። እርጋተውን በተመስጦ ሳስበው መንፈሴ ሐሤት ታገኛለች። የመጪው የትውልዱ ቀጣይነት፤ የብቃት አቅም በእሱ ላይ ምስባክ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ጠቢቡ ቴወድሮስ ካሳሁን የበጎ ዕሳቤ መልዕከተኛ ነው። የመቻቻልም ልዩ ግርማ ሞገስ። እንደዚህ ለዬት ብለው የሚፈጠሩ፣ ግን ሥጋ የለበሱ የዓለም ዜጎች በተለይ ሁኔታ፣ ከዬትም ቦታ ይፈጠራሉ። እጅግ የቀደመ ንጡር ዕሳቤ ያላቸው። እርግጥ ነው በዘመናቸው ተቀባይነታቸው ሆነ ፈተናቸው ሰንሰለታማ ነው። እርግጥ በዚህ ዘርፍ የቅኔው ዕንቡጥ ዕድለኛ ነው። ሚሊዮኖች መንገዱን በጥዋቱ አክብረውለታል – ዜማዊ ስለሆነ፣ አድንቀውለታል። ቃናዊ ስለሆነ ተመስጠውለታል። አቅላቸውን ያለምንም ገድብ ሸልመውታል። መንፈሱን ውስጣችው አድርገውለታል። ሙዚቃ ጥበቡን፤ የሥነ-ጹሑፍ ይዘቱና ጣዕሙም አዲስ መንገድ ነው – ለእኔ። በሌላ በኩል የወጣለት ተናጋሪ እና ብቁ አድማጭም ነው። ውስጥን የማድመጥ አቅሙ ስዋሰው ነው። ምሩቅ። የእርቅ ድልድይ። የኔታ!

ጥቂቶች እንደ የቅኔው ዕንቡጥ የተሰጣቸው ጥልቀት ያለውን የበጉነትን መንገድን ሳንኮችን ሳይሸሹ … ደፍረውም ይጀምሩታል …. ጋሬጣውን ሁሉ ተፋልመው፣ የተዘጋውን በር በተሟላ ብቃታቸው፣ በተሰጣቸው ሰማያዊ ረቂቅ የመንፈስ ጸጋ ታግለው ለማስከፍት  – ይተጋሉ። ተፈጥሯቸው ከብረት ቁርጥራጭ የተሠራ ጠንካራ ነው። በጥቂት ስንኝ የዕልፍ ዕላፋትን መንፈስ በፈቃደኝነት ውርሰ ዕርስታችው ያደርጋሉ። የታደሉ። መልካም ቀኖች። ውብ የአድዮ – ቃናዎች።

እጅግ የምናፍቃችሁ የሐገሬ የኢትዮጵያ ውዶች … ሽልማቶች፣

የፍቅር መርህ፣ የፍቅር ህግጋት፤ የፍቅር አስተምህሮ፤ ክህሎቱ በስልጠና ያልተደገፈ በመሆኑ ነው ዛሬ የዐለም የጋራ ልብስ (Uniform) ተዥጎርጉሮ የሚታዬው። ታዲያ ይህን ሊታደግ ከቀደምት ሀገር፤ ከፍጥረት መጀመሪያ ከእመቤት ኢትዮጵያ ብቅ ማለቱ የሚያሸልም መሆን ሲገባ እንዲህ መገፋት፤ እንዲህ መሳደድ፤ እንዲህ ዓይንህ ላፈር ማለት የቅዱሳንን የተጋድሎ ታሪክ በምልሰት እንዲቃኝ ሂደቱ ያስገድዳል። ቀደምት ቅዱሳን አባቶቻችን በዕመነታቸው ጽናት ተወግረው ያለፉት ሰማዕታት በዛ ዘመን፤ ሰው ከሥልጣኔ ጋር እምብዛም በአግባቡ በልተያያዘበት ነበር። ዛሬ በ21ኛው ምዕተ ዓመት ይህ ዓይነት አካልንና መንፈስን በድብቅ አስሮ እንደምስጥ የሚፈታተን ሂደት፤ ለዛውም የህዝብ መሪ ነኝ ከሚል ስውር ቡድን … ከጥቁሩ ዲያቢሎስ ተግባርና ምግባር ሊለይ ፈጽሞ አይችልም። መሃከነ፣ ማረን፣ ተሳህለነ፣ ከዚህም አድነን ብለን አምላካችን በጽኑ ልንማጸነው ይገባል። ቅን መሆን ብቻ ነው ለመንፈስ ጤናማነት – ሃኪሙ።

እባክህን አንተ አማኑኤል አባታችን በጥበብህ ሁንላት ለእናት ኢትዮጵያ። ለክፉ ነገር፣ ለመልካምነት ጸርነት ተደራጅቶ፣ ተቧድኖ መገኘት …. ከሳጥናኤላዊነት ለይቶ ማዬት የሚቻል አይመስለኝም። በዬጊዜው የሚያገረሽ፤ የማይሽር የበቀል ሞገድ … ቅጣት – በቅንጣት – በቅንጦት። እም

እንዴት አንድ ቀንጣ ሰውስ ከተቧደነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ መራሂ ድርጅት የፍቅር ጠላት ኃይላት ውስጥ ተነጥሎ ወይንም ተለይቶ መውጣት ይሳነዋል? እንዴት አንድ ቀንጣ ትንፋሽ የመልካም ዕሳቤ ፍርፋሪ ወይንም እንጥፍጣፊ ያለው ነፍስ ይጠፋል? እንዴትስ አንድ ቀንጣ ስለነገ የሚጨነቅ፣ የሚጠበብ ስለምን ይታጣል? እንዴትስ የጥላቻን አሸናፊ ደልዳላውን ፍቅርን አንድ የህዝብ መሪ ነኝ የሚል አካል እንዲህ በተከታታይ ይፋለማል? ትግሉ ከሀገር፤ ትግሉ ከህዝብ ሳቅ፤ ትግሉ ከህዝብ ደስታ፤ ትግሉ ከሰው ልጆች የተፈጥሮ ነፃ ሆኖ የመፈጠር ዶግማ ጋር መሆኑ ማሳዘን ብቻ ሳይሆን፣ ትውልድን – በእምታ አጋፋሪነት ያመክናል። እርግማን ነው።

ጥበብ ደንበረቢስም ናት። እሷም አልቀረላት። እንዲህ ትወቃለች። የዓለም ከያኒያን ይህንን ጉድ ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? ምንስ ይታዘቡን? ከያኒ በሰለጠነው ዓለም ከንጉሥም በላይ ነው። ዓጼ ነው። በእኛ ደግሞ የካቴና ቤተኛ። እም። ስንት ጊዜ ይማጣል …

ዕንባ ቀን ይቆጥራል። ዕንባ በራሱ ቀናተኛ ነው። ሆድ ለባሳቸው፣ ለተቸገሩ፤ ለተገፉ፤ ለተገለሉ፤ በባይታወርነት ለሚንገላቱ ዕንባ ደም መላሽ ነው። ዕንባ የወንዝ ውሃ አይደለም፤ ወይንም የሸንተረር ወይንም የቧንቧ ውሃ፤ ዕንባ የመንፈስ ጦርና ጋሻ ነው። ዕንባ የማሸነፍ ገዢ መሬት ነው። በእያንዳንዱ ዝምታ ውስጥ ዕንባ አለ። ያ ዕንባ ዕዮርን የማስከፍት ይሉ ምጡቅ ነው። ለድልም ይበቃል።

ለነገሩ አሁን እኔ በእጅጉ እያሰሰበኝ ያለው የኮንሰርቱ፤ የአልበሙ ምርቃት መስተጓጎል አይደለም፤ „የወንድ ልጅ ዕንባው በሆዱ ያለው“ የሎሬቱ ቅኝት፤ ያ የውስጥ ዕንባ በዚህ የቅኔ ቀንበጥ ህይወት፣ መንፈስ ላይ የሚያሰድረው ወይንም ሊያመጣ የሚችለው የታመቀ የቁስለት ምለሽ ነው። ያመው ይሆን ብዬ እሰጋለሁ። ባይታዋርነት ውስጥን ቦርቡሮ፤ እንዲሁም ሸርሽሮ የሚጨርስ ስውር ካንስር ነው። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የውስጥ ህማማቱ ባይተወርነቱ ነው ገዝፎ የሚታዬው በአሳሩ ትንፋሽ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ በሙሉ ስደተኛ ነው። ስደተኝነት በመንፈሱ ብቸኛ እርስተኛ ሆኗል። ለዛውም በአካል ከተሰደድነው በላይ ረመጡ ላይ ያለ። ጥዋት ማታ እዬተገላበጠ የሚነገረገብ።

በሌላ በኩልም በታቀደም እንዲህ በይፋ፤ በታቀደ ግን በተሰወረ በተቀበረ ሁኔታ በቅኔው ዕንቡጥ በህይወቱ ላይ፣ እንዲሁም በቅርብ ቤተሰቡም ዙሪያ ሊደርሱ ስለሚችሉ ነገሮች ሁሉ ሊታሰብበት የሚገባ ይመስለኛል። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ስለቀጣዩ የውጪ ሐገር ጉዞም ቢሆን ዋስትና የለም። የካቴናውም ምክክር የት ላይ ሊሰክን እንደሚችል ፈጽሞ አይታወቅም። ድንቡልቡል፣  ልሙጥ ጉድጓድ። እያንዳንዱ ያለበትን፣ የቆመበትን መሬት ቢያሰተውለው ዱላው ለሁሉም ነው። ነግ ለእኔ ማለት ጥሩ ነው። አብሶ የሥነ-ጥበብ ቤተሰቦች።

በታመቀ ሴራ ውስጥ ያለች ነፍስ ናት ዛሬ የቅኔው ዕንቡጥ ዕጣ ፈንታ። ዙሪያ ገባው እሾሕ። እኔንም ሆነ፣ አቧራ ለብሳ የተቀመጠችውን ብዕሬንም ያነሳሳን ይሄው መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ቢያንስ አቅም ያላቸው ወገኖቹ ደግመን ልናገኘው በማንችለው ብቃት ላይ፣ በትጋት የጸሎት አጥር ማደረግ የሚገባ ይመስለኛል። ሁሉም እንደ አቅሙ ለዚህ የቅኔ ዕንቡጥ እንደ ዕመኑቱ የጸሎት ሥርዐት እርዳታ ቢያደርግለት ከምንም በላይ አቅምና፤ ሃይል ይሆነዋል። ጸሎት ሃይል አለው።

በተደሞ፤ በመመሰጥ፤ ከልብ በመሆን ስለ ወል ቤታችን ቀጣይነት፤ ካለ ዕድሜው ኃላፊነቱን በራሱ ላይ ለጫነ ቀንበጥ እንጸልይለት – እባካችሁን ውዶቹ ወገኖቼ – የሐገሬ ኢትዮጵያ ልጆች። አምላክ እንዲጠብቀው፣ ድንግል ጥላ ከለላ እንድትሆነው፣ የቅዱሳን ጥበቃ እንዳይለዬው፣ ይህንን የፈተና ግማድ የሚሸከምበት ትክሻው ከወትሮው በበለጠ እንዲበረታ። የእስልምና ሃይማኖት ዕምነት ተከታይ ወገኖቻችንም እንዲሁ የእነሱ ድዋ መድህን ነው። እና ቢተጉለት ጥሩ ነው። ጥበባኛው ዬኢትዮጵያ ኃብት ነው። የአፍሪካም ኩራት። ለዓለም የጥበብ ቤተሰቦችም ተምሳሌት። ሥነ – ጥበብ ደንበር የለውምና።

ሌላማ ዘመን የሸለመንን ጥቁር ልብስ፤ በራሱ ጊዜ እስኪ ቀድልን ድረስ ዕድሜም፤ ፆታም፤ ዕምነትም፤ የዕውቀት ደረጃም፤ ሳይገድበን ሁላችንም ሐዘንተኛ ነን። ለተከታታይ ሰዓታታ፣ ቀናት፤ ሳምንታት፤ ወራት፤ ለዐመታት … በቃችሁን ከበቃህ  ጋር …. ለማዬት ፈጣሪ ብቻ የሚያውቅ ዶግማ ነው። መቼ? እንዴት? እኛ አናውቀውም። አሁን አሁን ከሁሉም ነገር ወጣ ብዬ ሳዬው … በሰው እጅ ያልተሠራ መፍትሄ ነው ልዕልት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት። የችግሮቻችን መጠኑም፣ ስፋቱም፣ ጥልቀቱም፣ ርዝማኔው፣ ዓይነቱም፣ ቀለሙም፤ ትብትቡም፤ ገመዱም፣ መጫኛውም፣ ሁለመናው ስምዬለሽ ነው። ይህ የቅጣት ዘመን የታዘዘው ከሰማይ ነው። የበቃችሁ መፍትሄውም ከሰማይ ነው። ርትህ – ፍትህ – ሚዛን …  ይርባል ከእህል እውሃ በላይ። የውስጥ ሰላም ይጠማል ከንጹህ አዬር በላይ …. በላይ ….።

 

መጥኔ ለድምጽ አልቦሾቹ ዬኢትዮጵያ እናቶች ….

ለሁሉ ነገር መፈተኛ የፊት ረድፈኞች፣

የዕንባ ተርቲመኞች – መከረኞች፤

የረመጥ ሂደት ዐቃቤት ማህበረተኞች፣

የመሰነግ ግብርተኞች ጥቁር ለባሾች፤

የህቅታ ማሟሻዎች፤ የፍላሎት መርከበኞች ….

የረመጥ ሙሽሮች፤ የበቀል መሞከሪያ ጣቢያዎች፣

… መጥኔ ለኢትዮጵያ እናቶች።

 

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

„ፍቅር ያሸንፋል።“

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ደህና ሁኑልኝ።

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.