በአማራ ክልል ለትግራይ ተወላጆች የተለየ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ተሰጠ

(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 30/2009)በአማራ ክልል ለትግራይ ተወላጆች የተለየ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ተሰጠ።

ትላንት በባህርዳር በተደረገ ሚስጥራዊ ስብሰባ በህወሀት የበላይነት ከተያዘው ብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት በመጡ ሰዎች አማካኝነት የቀድሞው ውሳኔ ተቀልብሶ ከዛሬ ነሀሴ 30 2009 ጀምሮ በአማራ ክልል ነዋሪ ለሆኑ የትግራይ ተወላጆች የ24ሰዓት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ መተላለፉ ታውቋል።

ባህር ዳር ከተማ
ባህር ዳር ከተማ

ከሶስት ሳምንት በፊት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ገዱ አንዳርጋቸው በመሩት ስብሰባ ሀሳቡ ቀርቦ ከአማራ ደህንነትና ፖሊስ በቀረበ ተቃውሞ ውድቅ ተደርጎ እንደነበር የኢሳት ምንጮች አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል ወደባህርዳርና ጎንደር የሚያስገቡ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የፍተሻ ኬላዎች ሊቋቋሙ መሆኑ ተገልጿል።

በአማራ ክልል የተከሰቱትን ህዝባዊ ንቅናቄዎች ተከትሎ በስልጣን ላይ ያለው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት በክልሉ ለሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጥበቃ እንዲደርግላቸው ትዕዛዝ ማስተላለፉ ለብዙዎች ግራ የሚያጋባ ሆኗል።

የነሀሴ አንድ የሰማዕታት መታሰቢያ ማግስት በጎንደር በተካሄደ ስብሰባ ለትግራይ ተወላጆች የተለየ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ሀሳብ ቀርቦ በወቅቱ ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው።

በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተመራው የጎንደሩ ስብሰባ ላይ የህወሀት ተወካዮች የአማራ ክልል መንግስት ለትግራይ ተወላጆች ጥበቃ እንዲያደርግ መጠየቃቸው ከአማራ ደህንነትና ፖሊስ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ይህን የምናደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርም በሚል በመቃወማቸው ሀሳቡ ውድቅ ተደርጎ ቆይቷል።

ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ትላንት በባህር ዳር ሚስጢራዊ ስብሰባ ተደርጓል።

በአማራ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ከመከላከያ፣ ከጸረ ሽምቅና ከአድማ ብተና የተወጣጡ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ስብሰባውን የጠራው በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የስብሰባው አጀንዳ የነበረውም በአማራ ክልል በተለይም በባህርዳርና ጎንደር ነዋሪ ለሆኑ በዋናነትም ንብረትና ሀብት ላላቸውንና ቁልፍ በሆነ የመንግስት ሃላፊነቶች ላይ ለሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች የተለየ ጥበቃ እንዲደረግ ውሳኔ ማስተላለፍ ነው።

በውሳኔው መሰረት ከዛሬ ነሀሴ 30 2009 ጀምሮ የትግራይ ተወላጆች ንብረቶቻቸውን፣ ድርጅቶቻቸውን፣ መኖሪያ ቤቶቻቸውን ጨምሮ ግለሰቦቹ የ24 ሰዓት ጥበቃ ይደረግላቸዋል።

በባለፈው የጎንደሩ ስብሰባ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሀሳቡን እንደማይቀበለው ካስታወቀ በኋላ የትግራይ ተወላጆች ጉዳዩን ወደ ፌደራል መንግስቱ በመውሰድ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ማቅረባቸውን ለመረዳት ተችሏል።

ይህን ተከትሎም ነው ጉዳዩ በስቸኳይ እንዲታይ ከበላይ መመሪያ ተላልፎ የህወሀት ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊዎች ወደ ባህርዳር በማቅናት የትላንቱን ስብሰባ የጠሩት።

በዚህኛውም ስብሰባ የአማራ ክልል ፖሊስ ተወካዮች ተቃውሞ አቅርበዋል። ከህዝቡ እንድንነጠል እያደረጋችሁን ነው።
ከዚህ በፊት ለአንዳንድ ሆቴሎችና የንግድ ቦታዎች የተለየ ጥበቃ በማድረጋችን ሰፊ ቅሬታ ተፈጥሯል፣ ህዝቡ እኛን ዝቅ አድረጎ እንዲመለከተን እየተደረግን ነው የሚል ተቃውሞ ቢያቀርቡም የህወሀት ተወካዮች የበላይ ትዕዛዝ በመሆኑ ተግባራዊ እንድታድርጉ በሚል ስብሰባውን ማጠናቀቃቸውን ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ወደ ጎንደርና ባህርዳር የሚያስገቡ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የፍተሻ ኬላዎች ሊቋቋሙ እንደሆነ የደረሰን መረጃ አመለከቷል።

ወደ ባህርዳር የሚያስገቡ 3 በሮች እንዲሁም ወደ ጎንደር የሚወስዱ 2 መንገዶች ላይ አድማ በታኝ አባላት የተጠናከረ ጥበቃና ፍተሻ የሚደረግላቸው ኬላዎች እንደሚቋቋሙ ተገልጿል።

በዋና ዋና መንገዶች ማለትም ከወረታ ደብረታቦር መገንጠያ፣ ከበለሳ ወደ ጎንደር መታጠፊያ፣ አዲስ ዘመንና ሌሎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በተደጋገሙባቸው አካባቢዎች ባሉ ዋና ዋና መስመሮች ላይ ተመሳሳይ ፍተሻና ጥበቃ እንዲደረግ መወሰኑም ታውቋል።

ከመቼ ጀምሮ እንደሆነና ምክንያቱ በግልጽ ምን ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.