አቅም ሲያንሰኝ…. ቴዲ አፍሮን, መስደብ አማረኝ -ከተማ ዋቅጅራ

የኢትዮጵያ ህዝብ አክብሮ ከፍ አድርጉ ያነገሰውን በወፍ ዘራሽ ወሬ ማውረድ አይቻልም።

ቴዎድሮስ ካሳሁን ከመነሻ ጀምሮ ስራዎችን ስንቃኘው የሚደንቅ የጥበብ ሰው፣ ኢትዮጵያዊነት የሚቀጣጠልበት የፍቅር አዝመራ፣ ባልተሄድበት አካሄድ በልዩ እይታ የሚመለከት ገጣሚ፣ መሳጭና አነጋጋሪ ነገሮችን ተረስተዋል ተብለው የሚገመቱትን ታሪኮች አሳምሮ የሚተርክ ብልህ ሰው፣ በሰው ልቦና ያልታሰቡ አጠገባችን ያሉትን እያየን የምናልፋቸውን እሴቶቻችን አጉልቶ ያሳየን መነጽራችን፣ ስራዎቹ አገርኛ ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻግሮ አለም ያደነቀው ጥበበኛ፣ እነ ዩቱብ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ተደማጭነትን ያገኘ ብሎ የክብር ማማ ለይ ያስቀመጠው አንደኛ፣ ኢንተርናሽናል ሚዲያዎች ተቀባብለው የዘገቡት ኢትዮጵያዊው የሙዚቃው ንጉስ ቴዲ አፍሮ የሚሊዮኖችን ቀልብ የገዛው ከችሎታው ተጨማሪ ለአገሩና ለህዝቡ ባለው ጥልቅ ፍቅር ጭምር ነው። እራሱን መሆን የቻለ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲ፣ የልዩ ተስጥኦ ባለቤት፣ ባለ ደብል ድጅት የፈጠራ ሰው ድንቅ ኢትዮጵያዊ፣ ፍቅር ያሸንፋል ብሎ ጥላቻን ከውስጡ ያወጣ፣ ከወደድኩሽ ሞትኩልሽ…. ካፈቀርኩሽ አበድኩልሽ… የግጥም ጥግ በተለየ እይታ ከውስጥ ወደውጪ የጥበብን ዘር የሚዘራ፣ ለስራዎቹ መጠበብ አለምን ያስደመመ ኢትዮጵያዊ ነው።

ነብር ከዥጉርጉርነቱ ኢትዮጵያዊም ከመልኩ መለወጥ እንደማይቻል ሁሉ…. የነብርን መዥጎርጎር የኢትዮጵያዊ ከለራችን… ውበት መሆኑን ተረድቶ ማንነታችንን በፍቅር በማስተሳሰር በጽናት የቆመ የኢትዮጵያ ኩራትና ውድ ልጅ ነው። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ስራ ትልቁን ድርሻ የሚወስድ፣ ለጥቅም ብሎ ህሊናውን ያልሸጠ፣ ታዋቂ ነኝ ብሎ እራሱን ያልኮፈሰ፣ ስራዎቹ እያስተማሩ የሚያዝናኑ፣ ንግግሩ እየገሰጸ መሸጋገሪያ ድልድይ የሚሰራ፣ ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ድንቅ ልጅ ነው።

ሌላው የሚደንቀኝ ደግሞ አንድ አዝማሪ የሚላት አገላለጽ አላቸው። አዝማሪ የምትባለው የምትኮነነው በሃይማኖት መንደር ነው። እነ አባ ጋር አልያም እነ ሼህ ጋር ወይንም ደግሞ እነ ፓስተር ጋር ነው። ሲጀመር የትኛውም ሃይማኖት እማ (ማማት) የሚል የለም። መምከር ከተፈለገ ለባለቤቱ መንገር ነው እንጂ የመሳደብ ስልጣን ለእናንተ አለማዊውም ሆነ መንፈሳዊ ህጉ አይደግፋችሁምና አደብ ግዙ። ለሁሉም ነገር ቦታ አለውና። ሲቀጥል ፖለቲከኛ ነኝ ብሎ ለአንድ አዝማሪ ብለው ይናገራሉ። ፖለቲከኛ አልያም የፖለቲካው ተከታይ ነን በሚሉት ይሄንን ቃል እንደመስማት የሚያሳፍርም የሚያሳምምም ነገር የለም። ምክንያቱም የአገር ገጽታ፣ ባህል፣ አመጋገብ፣ አኗኗር፣ ታሪክ፣ ፖለቱካም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከሚገለጽበት በዋነኝነት በሙዚቃዊ ጥበብ በዘፋኞች አይደለም እንዴ? ሲመቸኝ በእንኮኮ ሳይመቸኝ በካልቾ የሚባለውን አገላለጽ አቁሙ። ቴዲን ለመተቸት እርሱ ከሰራው በልጦ መስራት አልያም ተስተካክሎ መገኘት ግድ ይለናል። በራሳችሁ ላይ ትዝብትን ከማብዛት ያለውን እውነት በመቀበል ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠትን ልመዱ። ምክንያቱም ያስከብራችኋልና አልያም ቢጎመዝዛችሁም ቢመራችሁም እውነቱ ይሄ ነው።

በጥበብ የበቀሉትን ብርቅዪ ልጆቻችንን ተንከባክቦ መጠበቅ እንጂ ተረባርቦ ለመቁረጥ መጣጣሩ የማያዋጣ አልያም ለኪሳራ የሚዳርግ የፖለቲካ አካሄድ ነውና እርምት ከስሩ የሚወሰድበት ጉዳይ ነው።
ፍቅር ታላቅ መንገድ ነው ሰውና ሰውን ብቻ ሳይሆን ሰውና ፈጣሪን የሚያገናኝ የእውነት መንገድ ነውና ሁላችንም እንከተለው።

ከተማ ዋቅጅራ
06.09.2017
Email-waqjirak@yahoo.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.