ምርጫ ቦርድ የአንድነት ፓርቲን አዲስ አመራር ዕውቅና ነፈገ

አቶ ደምሰው በንቲ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ብሔራዊ ምክርቤት ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም የቀድሞ ፕሬዚደንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ያቀረቡትን የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎ በምትካቸው አቶ በላይ ፍቃዱን ፕሬዚደንት አድርጎ ማስመረጡን በመጥቀስ አዲሱ አመራር ዕውቅና እንዲያገኝ ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ ምርጫው ሕገደንቡን እና የምርጫ ህጉን ያልተከተለ ነው በማለት እንዳልተቀበለው አስታወቀ።

አቶ ደምሰው በንቲ የምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ስለጉዳዩ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዳብራሩት በአሁን ወቅት ተመርጫለሁ የሚለው አዲስ አመራር የቀድሞ የፓርቲው ፕሬዚደንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ለብሔራዊ ምክርቤቱ ባሳወቁት መሠረት አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮምቴ በማቋቋም ፕሬዚደንት እንደመረጠ አሳውቋል።
በሌላ በኩል የፓርቲው አመራር አባላት ነን ያሉ ግለሰቦች ለቦርዱ በጻፉት ደብዳቤ ብሔራዊ ምክርቤቱ የፓርቲውን ቀድሞ ፕሬዚደንት ማንሳቱ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አግባብነት እንደሌለው አቤቱታ ማቅረባቸውን አቶ ደምሰው አስታውሰዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ሁለቱም ወገኖች ያቀረቧቸውን መከራከሪያዎች ከሕጉና ከፓርቲው ሕገደንብ ጋር በማነጻጸር መመርመሩን አቶ ደምሰው አስታውሰው በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው አዲሱ አመራር ምርጫ፤ የፓርቲውን ሕገደንብና የምርጫ ሕጎችን የማያሟላ መሆኑን በማረጋገጡ ለአዲሱ አመራር ዕውቅና ከመስጠት መቆጠቡን ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም በቁጥር አ573/ፓአ/ጠ289 ለአንድነት በጻፈው ደብዳቤ ማሳወቁን ተናግረዋል። ይህም ማለት አዲሱ አመራር በቦርዱ ህጋዊነትና ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በአመራሩ ስም መንቀሳቀስ እንደማይችል አቶ ደምሰው አረጋግጠዋል።
ቦርዱ ለአንድነት ፓርቲ የጻፈውን ደብዳቤ ይዘት በተመለከተ አቶ ደምሰው በዝርዝር አስረድተዋል።
“አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት/ መስከረም 12 ቀን 2007 ዓ.ም በቁጥር አንድነት /970/2007 በተፃፈ ደብዳቤ ታኅሣሥ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም ባደረገው ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት አድርጎ የመረጣቸው ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም ለተሰበሰበው ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት በገዛ ፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን እንደለቀቁ ገልጾ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የብሔራዊ ምክር ቤት በተፈቀደለት መሠረት አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ በማቋቋም ፕሬዚዳንት እንደመረጠ አሳውቋል።
በኩል አሥር የፓርቲው አመራር አባላት ነን የሚሉ ግለሰቦች ጥቅምት 11 ቀን 2007 ዓ.ም እና ጥቅምት 14 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም ብሔራዊ ምክር ቤቱ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት ማንሳቱና በምትካቸው አዲስ ፕሬዚደንት መምረጡ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አግባብነት እንደሌለው ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል።
የቦርዱ ጽሕፈት ቤትም ፓርቲው ያቀረበውን ሰነድ ከተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም እና ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንፃር ሲመረምር፡-
1.    ብሔራዊ ምክር ቤቱ ያስተላለፈው ውሣኔ ፓርቲው ታኅሣሥ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም ባካሄደው ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ባሻሻለው እና በቦርዱ ዕውቅና ባላገኘው የመተዳደሪያ ደንብ መሆኑን፤ /ፓርቲው ልዩ ጠቅላላ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ ለቦርዱ የጉባዔውን ውጤት ባለማሳወቁ ምክንያት በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም አንቀጽ 21 መሠረት የጉባዔውን ውጤት ለቦርዱ እንዲያሳውቅ ከቦርዱ ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ እና በቃል ተገልጾለት ሰነዱን ከሰባት ወራት በላይ አዘግይቶ እንዳቀረበ ይታወቃል/
2.    የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ዓ.ም አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 2 /ረ/ የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡ መሆን እንዳለባቸው የሚደነግግ በመሆኑ፤
በሥራ ላይ ያለውን የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ስንመረምር፡-
3.    የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10.2 /ለ/ የጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣንና ተግባር ሥር ጠቅላላ ጉባዔው አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ በመሰየም የፓርቲውን ሊቀመንበር እንደሚመርጥና እንደሚሽር የሚገልፅ በመሆኑ፤
4.    በመተዳደሪያ ደንቡ በአንቀጽ 13.3 የፓርቲው ሊቀመንበር በነፃ ውድድር በሚደረግ ምርጫ በጠቅላላ ጉባዔ እንደሚመረጥ የሚደነግግ በመሆኑ፤
5.    በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 10.2 /ሰ/ ጠቅላላ ጉባዔው በተሰናባቹ ምክር ቤት ለሚቀጥለው ምክር ቤት ወይም በአስቸኳይ ጉባዔ ላይ ዝርዝር የውክልና ጥያቄ ካቀረበ ከሥልጣኑ ሥር የሆነውንና ተዘርዝሮ በቀረበለት ጉዳይ ላይ ከሥልጣኑ ቀንሶ ለብሔራዊ ምክር ቤት በውክልና ሊሰጥ እንደሚችል እንደሚደነግግ፤ ሆኖም ጠቅላላ ጉባዔው ከሥልጣኑ ቀንሶ ለብሔራዊ ምክር ቤት የሰጠው ዝርዝር ጉዳይ ተያይዞ ያልቀረበ መሆኑ፤
6.    በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 11.2 /ሀ/ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ በሥራ ላይ በማይኖርበት ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔውን በመወከል በውክልና ተዘርዝረው የተሰጡትን ተግባራት እንደሚያከናውን ቢደነግግም እነዚህ በጠቅላላ ጉባዔው በውክልና ተዘርዝረው ለብሔራዊ ምክር ቤቱ የተሰጡ ተግባራት ተያይዘው ያልቀረቡ በመሆኑ፤
ታኅሣሥ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም በልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ተሻሽሏል የተባለው ደንብ ለቦርዱ ቀርቦ ባልፀደቀበትና ዕውቅና ባላገኘበት ተሻሻለ የተባለውን ደንብ ተከትሎ ፕሬዚዳንቱን ከኃላፊነት ማንሣትና መተካትን ጨምሮ የሚወሰዱ ማናቸውም ተመሳሳይ እርምጃዎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው እናሳስባለን።” የሚል መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ደብዳቤ መሠረት አዲሱ አመራር ፓርቲውን ወክሎ መንቀሳቀስ እንደማይችል አስታውቀዋል።

የጉዳዩ አመጣጥ
በነሐሴ ወር 2006 ዓ.ም መጀመሪያ አምስት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባላት አድማ በሚመስል መልክ በአንድ ላይ፣ በአንድ ቀን፣በአንድ ደብዳቤ ከኃላፊነት ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ አደረጉ። እነዚህ አባላት አቶ ተክሌ በቀለ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩ፣ አቶ በላይ ፍቃዱ ም/ፕሬዚደንት የነበሩ፣ አቶ ዳዊት አስራደ የኢኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩ፣ አቶ ሰለሞን ሥዩም የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ የነበሩ፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩ ናቸው። እነዚህ አባላት ከፓርቲው ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ምክንያት ያደረጉት በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አመራር ደስተኛ አይደለንም የሚል ነበር። አንዳንድ ወገኖች ይህን የቀድሞ አንድነት አመራሮች እርምጃ ኢንጂነሩን ሥልጣን እንዲለቁ ለማስገደድና የእሳቸውን አመራር ዋጋ ለማሳጣት ታቅዶ የተደረገ አድማ ነው በሚል ይተቹታል። ያም ሆነ ይህ በአንድነት አመራር ውስጥ ያለው የሥልጣን ሽኩቻ ከሐሜት አልፎ በዚህ መልኩ አፍጥጦ ለአደባባይ በቃ።
ይህ ከሆነ ከሁለት ወራት በኃላ በድንገት ኢንጂነር ግዛቸው በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው በተሰማበት ዕለት አዲስ ፕሬዚደንት በፓርቲው ብሔራዊ ምክርቤት ውሳኔ ወደሥልጣን መምጣቱ ይፋ ሆነ። ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክርቤት ከኢንጂነር ግዛቸው ካቢኔ ራሳቸውን ያገለሉትን አቶ በላይ ፍቃዱን ፕሬዚደንት አድርጎ ሲመርጥ፤ ሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት ኢንጂነሩን በማህበራዊ ድረገጾች ጭምር እንደብሔራዊ ጀግና መታየት አለባቸው የሚሉ ሙገሳዎች በርክተው ታዩ።
በዚያው ሰሞን ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም ለንባብ ለበቃው ሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ ሥልጣናቸውን የለቀቁት በተደረገባቸው ጫና መሆኑን በማስረዳት እርምጃውን ለመውሰድ የተገደዱት ፓርቲውን ከውድቀት ለመታደግ በማሰብ መሆኑን ገልጸው የልዩነቱን አድማስ አሳዩ።
ሌሎች የፓርቲው አመራር እና አባላት ነን ያሉ ግለሰቦች ደግሞ ልዩነታቸውን አደባባይ ይዘው በመውጣት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከኃላፊነት የተወገዱበት መንገድ ሕጋዊ አለመሆኑን በመጥቀስ የተቃውሞ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ በአዲስአበባ ራስ ሆቴል በሰጡዋቸው መግለጫዎች ማሰማት ጀመሩ።
አቶ በላይ ፍቃዱ በብሔራዊ ምክርቤቱ ፕሬዚደንት ተብለው ከተሾሙ በኋላ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም ካቢኔያቸውን በአዲስ መልክ አዋቅረው ሥራቸውን ቀጠሉ።
ይኸው ውዝግብ የቀረበለት ምርጫ ቦርድም ጉዳዩን መርምሮ አዲሱን አመራር ምርጫ ሕግን የተከተለ አይደለም በሚል ሳይቀበለው መቅረቱን ይፋ አድርጓል።
የአንድነት ፓርቲ አዲሱ አመራር ደንብ ይከበር በሚል የሚሞግቱትንና ራሳቸውን የፓርቲው አመራና አባላት ነን ብለው የሚጠሩ ግለሰቦችን በተመለከተ ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የግለሰቦቹን እንቅስቃሴ በማጣጣል ፓርቲው በጥሩ ቀመና ላይ መሆኑን አስታውቋል። ይኸው መግለጫ እንደሚለው «አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ በአሁኑ ሰዓት ከመቼም ጊዜ በላይ በጠንካራ አቋም ላይ ይገኛል። በፓርቲው ውስጥ ጎልቶ እየታየ የመጣው የለውጥና የማንሰራራት ፍላጎት ተገንዝበው የፓርቲው ፕሬዚደንት የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው በራሳቸው ፍቃድ መልቀቃቸው የፓርቲው የዴሞክራሲ ባህል የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱን በትክክል የታየበት፤ ፓርቲው በተሻለ ቁመና ላይ እንዲጓዝ በር የከፈተ ትልቅ እርምጃ በመሆኑ ሊደነቅ የሚገባው ጉዳይ ነው። በመሆኑም ብሄራዊ ምክር ቤቱ ጥቅምት 2/2007 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የኢንጂነር ግዛቸውን የመልቀቂያ ጥያቄ አዳምጦ ካፀደቀ በኋላ የፓርቲው መተዳዳሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ አቋቁሞ ፓርቲውን በቀጣይነት የሚመራ ሰው በዕለቱ ከቀረቡት ሶስት ዕጩዎች መካከል አቶ በላይ ፍቃዱን በከፍተኛ ድምፅ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል።
አንዳንድ ወገኖች በዚህ ፍፁም ደንባዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሂደት ያለፈና የፀደቀ ጉዳይ የደንብ ጥሰት የተፈፀመ በማስመሰል ጫጫታ ለመፍጠር የተንቀሳቀሱበት ሁኔታ ቢኖርም፤ በዚህ ዴሞክራሲያዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር ላይ ምንም ዓይነት የደንብ ጥሰት ያልተፈፀመ መሆኑ አፅንኦት ሰጥተን ለመግለፅ እንፈልጋለን። አንድነት ውስጣዊ የዴሞክራሲ ባህል ያለው፤ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት የሚችልና በዚህ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ልምድ ያለው ፓርቲ ነው…” ብሏል።
አንድነት ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት በሰጠው ውሳኔ ላይ አስተያየቱን ለማካተት በማሰብ ለፕሬዚደንቱ አቶ በላይ ፍቃዱ ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን አቶ በላይ፤ ጉዳዩን የሚከታተሉት አቶ ሥዩም መንገሻ በመሆናቸው ምላሽ እንዲሰጡበት መርተውናል። አቶ ሥዩም በበኩላቸው ስብሰባ ላይ በመሆናቸው እንደማይመቻቸው በመግለጽ አቶ ግርማ ሰይፉን እንድናናግር በገለጹልን መሠረት አቶ ግርማን በተንቀሳቃሽ ሰልካቸው ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ ድምፃቸውን ማካተት ሳንችል ቀርተናል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.