ያለ መግደርደር ኢትዮጵያዊ ነኝ የሳዲቅ አህመድ ንግግር (ኦክላንድ ካሊፎርኒያ)

ሳዲቅ አህመድ
ሳዲቅ አህመድ

ኢትዮጵያዊነትን ሌሎች ብቻ ሳይሆኑ የማይረዱትና የማያዉቁት በእኛም በኢትዮጵያዉያኑ ዘንድ እራስን በራስ የመረዳት ችግር አለ።ኢትዮጵያዊነት የሚለካዉ አገርን በገዙ፣አገርን በመሩ ባሉና በነበሩ ሐይላት ሳይሆን፤ ህዝቡ በሰነቀዉ ልዩ የፍቅር ስንቅ ነዉ። ህዝባችን እንደ ህዝብ በፍቅር ኖረ እንጂ ከጥላቻ ጋር አለተቆራኘም። ህዝባችን በባህሉ፣በሐይማኖቱ ተከባብሮና ተዋዶ የወል እሴቶችን ገንብቶ እስካለንበት ትዉልድ ድረስ ያለችዉን ኢትዮጵያን አቆይቷል።ስለዚህ የማንነት ቀዉስን ፈጥሮ በኢትዮጵያዊነት መግደርደሩ ‘ሆድ ሲያዉቅ ዶሮ’ ማታ ነዉ።

ኢትዮጵያዊነትና ሌሎች

ታሪካዊ ቅኝት ስደረግ ኢትዮጵያዊነትን ሌሎች የሚመኙት፣ ሌሎች ሊሆኑ የሚሹት ክብር ያለዉ ዜግነት ቢሆንም ዛሬ በአገር በቀልም ይሁን ከዉጭ በመጡ ችግሮች ይህ የማንነት ኩራት ሲሸረሸር ይስተዋላል። ልብ እንበል፦የኢትዮጵያዊነት ሚዛኑ በዘመንና በትዉልድ ዉስጥ የሚቀያየሩት ስርዓተ-ማህበሮች አይደሉም። የኢትዮጵያዊነት ሚዛኑ ዘመንና ትዉልድ የማይሽረዉ በዉስጥ ላይ የሰረጸ አገርን የመዉደድ፣ በራስ የመተማመን፣አልበገር ባይነት የሞላበት፣ ጠላትን አንበርክኮ የመኖር ብቃት፣ወራሪን የመመከትና የመመለስ ክህሎት ያለዉና በታሪክ ድርሳናት ላይ የሰፈረ ልዩ መገለጫ ነዉ…የኢትዮጵያዊነት ሚዛኑ።ይህ ልዩ ገድል መግደርደርን አይሻም።ኢትዮጵያዊነትን በዚህ መልኩ ስንገልጸው የተጋነነ ይመስላል። እዉነታዉ ግን ከዚያ ለየት ይላል። እኛ የተሰጠን ያልተሰጣቸዉ፣እኛ ያለን የሌላቸዉ አዲስ ማንነትን በልቦለድ ለመገንባት ይጥራሉ። ባንጻሩ ሌሎች እኛን ስላለማወቃቸዉ ይነገራል፣አቀንቃኞችም ያቀነቅኑታል። ቢሆንም እኛዉ እራሳችንን አለማወቃችንን ሚዛን ላይ አስቀምጠን እራሳችንን እንመዝን።

ባለቤት አልባ ታሪክ

አንድ የታሪክ ምሁር በአንድ አዉደ ጥናት ላይ ባህር ማዶ ተገኝተዉ ከሌላዉ አለም ምሁራን ጋር የአለምን ታሪክ ሲፈትሹ የገጠማቸዉን ያስረዳሉ። የጎረቤት አገራት የኢትዮጵያን ታሪክ ሰርቀዉ የኛ ነዉ ሲሉ ይሰማሉ። በዚህም የፈጠራ የልቦለድ ታሪክ ግራ ይጋቡና የጎረቤት አገሩን ምሁር የተዛባዉን ታሪክ እንዲያስተካክሉና የኢትዮጵያን ታሪክ ሰርቀዉ የኛ ነዉ ማለት እንደሌለባቸዉ ያስረዳሉ። የጎረቤት አገሩም ምሁር ሲመልሱ “ታሪኩ የኢትዮጵያ እንደሆነ እናዉቃለን። በታሪካቹ እናንተ አልኮራቹም።ታሪኩ ባለቤት አልባ እየሆነ ሲመጣ እኛ ይገባኛል ባይነትን አቀረብን” ብለዉ ይመልሳሉ። ይህ ነዉ ባለቤቱ ያቀለለዉን አሞሌ ባለ እዳ አይቀበለዉም ማለት። እኛ የማንነት ቀዉስ ተፈጥሮብን ስንግደረደር ለሌች አገራት ታሪካችንን ሰርቀዉ ታሪካቸዉ ሊያረጉት እይግደረደሩም።

ስለዚህ መጤ የሆነዉን የማንነት ቀዉስ አሰወግደን በታሪካችን እንኩራ። ዘመን በማመጣዉ የማንንነት መታወክ ትዉልዱ ሰለባ መሆን የለበትም። የእንጀራ እናትም ሆኑ አሳዳጊ እናቶች እናት የሚለዉ መጠሪያ ሊሰጣቸዉ ይችላል። ግን የወለደች እናትን ሊተኩ አይችሉም። እናት ደሃም ብትሆን፣ ብትከሳም፣ብትገረጣም ሁሌ እናት ናት። ኢትዮጵያችንም ምንም ደሃ ብትሆን፣ምንም የተፈጥሮ አደጋና የአየር መዛባት ቢያጠቃትም፣ ጨቋኞች ቢፈራረቁባትም ይህች ዉድ አገር ለድርድር የምትቀርብ አይደለችም ። ስለዚህ በኢትዮጵያዊነትና ስለ ኢትዮጵያዊነትነት መግደርደሩ ይብቃና ሁሉንም ሊያማክል የሚችል፣ወደፊት እንጂ ወደሗላ የማንመለስበት ፍትሃዊ ስርዓት እንገንባ።

ልዩ ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ዉብ አገር ናት። የሰዉ ልጅ የዘር ምንጭ መሰረት የሆነች ናት። 3.2 ሚሊዮን አመት እድሜ ያላት የሉሲ (ድንቅ ነሽ) ቅሬተ-አካል ኢትዮጵያ ልዩ መሆኗን ተበስሮበታል።4.4 ሚሊዮን አመት እድሜ ያላት የአርዲ ቅሬተ-አካል የኢትዮጵያን ልዩ መሆን አረጋግጧል። ከዚህም ባሻገር በሁለት ትላልቅ አብረሐማዊ ሐይማኖቶች መሰረት ናት።በሁለቱ እምነቶች ቅዱሳን መጽሃፍት ዉስጥ ታላቅ ቦታ ያላት፣ ሶስተኛዉ አብራሃማዊ ሐይማኖት የሆነዉ የአይሁዳዉያን እምነት አሻራ ያለባት አገር ናት ኢትዮጵያ። ይህችን ሌላዉ እኔ ከርሷ በሆንኩ ብሎ የሚመኛት ኢትዮጵያን ትቶ አዲስ ማንነት ለፍጠር መጣሩ የማንነት ቀዉስ ነዉና ያለመግደርደር ኢትዮጵያዊ እንሁን።

ኢትዮጵያ የያኔሐ ያልና ገናና አገር

ኢትዮጵያ ባለችበትና በነበረችበት መልከዓምድራዊ አቀማመጥ ዙርያ ከ1400 አመታት በፊት አራት ሐያላንና ገናና መንግስታት እንደነበሩ የታሪክ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ። የኢራን፣የኢራቅ፣የግብጽና የሐበሻ ሐያላን መንግስታት። እስልምና በአረብ የቁረይሽ ጎሳዎች ዘንድ ተቀባይነት አጥቶ አማኒያን ሲገደሉ፣ሲገረፉና ሲሰቃዩ ሙስሊሞችን ለማዳንና ሐይማኖቱን ለማቆየት ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ፋርሷን ኢራን አልመረጡም።አረባይቷን ኢራቅ ወይም ግብጽን አልመረጡም። የመረጡት ሰዉ የማይበደልባት፣ፍትህ የጸናባትን የያኔዋን ገናና ሐያል አገር ሐበሻን ቢሆን እንጂ።

ፍትህ ያለባትን፣ቃልን የማያጥፉ ህዝቦችን ያፈራችውንና እንግዳ ተቀባይ የሆነችዋን ኢትዮጵያን ነብዩ በመምረጣቸዉ ሳቢያ ሳቢያ 1.7 ቢሊዮን ተከታዮች ያሉት ሀይማኖት ዛሬ በአለም ላይ መስፋፋት ችሏል። ይህ ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚያኮራ እንጂ አንገት የሚያስደፋ አይደልም። ኢትዮጵያን በአለም ላይ ከነበሩት ሐያላን መንግስታ ተርታ ያኔ ያሰለፋት በምድሯ ላይ ፍትህ የሰፈነ ስለነበረ ነዉ። በአገሪቷ ላይ ማንም የማይበደልበትን ፍትሃዊ ስርዓት ካነገስን ገናናነታችን ተመልሶ ይመጣል። ስለዚህ አገራችን ደሃ በመሆኗ ሳቢያ በመለዮዋ፣በሰንደቅ አላማዋና በኢትዮጵያዊ ማንነት መግደርደሩ አብቅቶ ያለመግደርደር ኢትዮጵያዊ እንሁን።

የእህቴ ስም ኢትዮጵያ ነዉ

አባቴና (ነፍሱን ይማረዉና-አላህ ይርኸመዉና) የርሱ ትዉልዶች ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመገኘት አያሌ መስዋእትነትን ከፍለዋል። ጭቆናን ተጋፍጠዉ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ ትዋቀር ዘንድ ታግለዋል። ፍትህን እየጠየቁ ኢትዮጵያዊነትን ጠበቅ አርገዉ ይዘዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድረገዉ እያዉለበለቡ “ቢላዲ ቢላዲ ፊዳኪ ደሚ (አገሬ አገሬ ደሜ ላንቺ መስዋእት ይሁን)” ሲሉ የአገር ፍቅር ስሜትን ከአንደበታቸዉ ወደ ልቦናቸዉ ልከዋል።”ኢትዮጵያ አገራችን፣ክርስቲያን ወንድማችን፣ይመስክር ደማችን አንድ ነዉ እጣችን”…የሚል የወል መፈክርን አሰምተዋል። ቢጨቆኑም ኢትዮጵያዊ ማንነትን ትተው በማንነት ቀዉስ የሌላ አገር ማንነትን አልፍለጉም። ኩሩ ጥቁር ህዝቦች እንጂ አረብ ነን አላሉም!…ለዉጥ ፈላጊ የነበሩ የወላጅ አባቴ ትዉልዶች።ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗ ሲበሰር፣ ወላጅ አባቴ የታናሽ እህቴን ስም ኢትዮጵያ ብሎ ሰየመው። ለኔ ኢትዮጵያዊነት የትግል ዉጤት ነዉ። ለኔ ሰንደቅ አላማዋን ማዉለብለቡ ከአባቴ ትዉልድና በርሱ ዘመን ከነበሩት ድንቅ ታጋዮች በአደራ የተሰጠኝ ታሪካዊ ቅርስ ነዉ። ሰንደቅ አላማን በማዉለብለቤ የአባቴን አደራ መተግበር በመሆኑ አዉለበልበዋለሁ-ለብሰዋለሁም።ኢትዮጵያዊነት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።ኢትዮጵያዊነት የምንግደረደርበት አይደልምና በኢትዮጵያዊነት መግደርደሩ ይብቃ።

ታሪክን በምልስት

ኢትዮጵያን ከአረቡ አለም ጋር የሚገናኟት ታሪካዊ እዉነታዎች ሲቃኙ ንግድና የባሪያ ፍንገላ ሆነዉ በጉልህ ይወሳሉ። ኢትዮጵያ ገናና ሐያል በነበረችበት ወቅት በዘር ዉስጥ ጀግና ተዋጊን፣ጎበዝ ገጣሚን፣ነገር አዋቂ (ዲፕሎማሲም ሊሆን ይችላል)፣ፖለቲከኞችን ለማፍራት አረቦች የሐበሻ ሴቶችን በማግባትና ልጅ በመዉለድ የሐበሻን ደም የማደባለቅ ባህላዊ እምነት ነበራቸዉ። በዚህም ሳቢያ በኢስላም ታሪክ ዉስጥ ቁልፍ ቦታን የያዙ ኢትዮጵያዉያን ነበሩ። ያኔ ኢትዮጵያዊነትን በደም ዉስጥ ለማደባለቅ የሌላ አገር ሰዎች ከጣሩ እንደምን ኢትዮጵያ ዛሬ ደሃ በመሆኗ ብቻ በኢትዮጵያዊነት መግደርደር ይኖራል? ኢትዮጵያ ዛሬ የቁስ ሀብት ደሃ ብትሆንም በታሪኳ፣በወደፊት ጸጋና ተስፋ ደሃ አይደለችምና በኢትዮጵያዊነት መግደርደሩ ይብቃ።

ኢትዮጵያዉያን ኢስላም ያለበት ደረጃ ይደርስ ዘንድ ከፍተኛ አስተዋጾ አደርገዋል።የነብዩ መሐመድ (ሰአወ) መረገዝን ቀድሞ በማወቅ ኢትዮጵያዉያንን የቀደመ አልነበረም።ስለምን? የአሚና (የነብዩ እናት) ረዳትና አጽናኝ ኢትዮጵያዊቷ በረካ ነበረችና ነዉ።ነበዩ ተወልደዉ አይናቸዉን ሲገልጹና ማየት ሰጀምሩ ከናታቸው ቀጥሎ ቀድመዉ ያዩያት ኢትዮጵያዊቷ በረካን ነበር። የነብዩ እናት በጉዞ ላይ ታመው ሲሞቱ እርሳቸዉን በርሃ ላይ በመቅበር፣ህጻኑን መሐመድ ለቤተሰቦች መልሶ በማምጣትና እንደ እናት ሆኖ በማሳደግ የኢትዮጵያዊቷ በረካ ታሪክ የገዘፈ ነዉ።በነብዩ አንደበት «ከእናቴ በሗላ እናቴ ናት!» የሚለዉን ማእረግ የተቀዳጀችዉ ኢትዮጵያዊቷ በረካ ብቻ ናት። ይህች ኢትዮጵያዊት ነብዩ ልጄ ብለዉ ያሳደጉትን (አዳፕት ያደረጉትን) ልጅ አግብታ ሁሳማ ቢን ዛይድ የሚባል ልጅን ወልዳለች። ነብዩ ለትዮጵያዉን በደምም ባይሆን በዘመኑ ህጋዊ የጉዲፈቻ አጠራር አያት ነበሩ ለማለት ይቻላል።
ይህ በናቱ ኢትትዮጵያዊ የሆነዉ ኡሳማ ቢን ዛይድ የነብዩ መሐመድ የጦር ጀነራል በመሆን አገልግሏል። የመዲና ግዛት የገንዘብ ሚኒስቴር የነበረዉ፣የመጀመሪያዉን አዛንን የስግደት ጥሪ ያሰማዉ፣ የነብዩ ቃል አቀባይ የነበረው፣ነብዩ ‘የእግርህን ኮቴ ገነት ዉስጥ ሰማሁት’ ያሉት ብቸኝዉ ሰዉ፣ በቃልኪዳኑ ጸንቶ የሞተዉና በጥቁር ህዝቦች ዘንድ ለነጻነት በሚደረግ ትግል ዉስጥ እንደ ፈርጥ የሚታየዉ ቢላል ኢትዮጵያዊ ነዉ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት የሚያኮራ፣የሚያስመካ ቢሆን እንጂ የምንግደረደርበት አይደለም።

ከነብዩ መሐመድ ሞት በሗላ ኸሊፋ ሁለተኛ (2ኛ ተከታይ መሪ) የነበሩት፣ሰፊ ግዛታቸዉን በፍትህ ይመሩ የመሩት፣በ አለም ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መካከል የመቻቻልን ፈር የቀደዱት፣ በአመራር ብስለታቸዉና ፈጣሪን በመፍራት የሚታወቁት ኡመር ኢብኑል ኸጣብ (ረአ) በአያታቸዉ ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ የታሪክ ምሁራን ያስተምራሉ። ይህ የመሪነት ብቃታችንን የሚያሳይ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚያግደረድር አይደለም።

ከአረብ ኢአማኒያን ጋር እራስን ለመከላከል በተደረጉ ጦርንርቶች ዉስጥ ጀግና ኢትዮጵያዉያን ባህር ተሽግረዉ መጥተዉ ተሳትፈዋል። የነብዩን ተከታዮች ሲገለሉ፣አድማ ሲደረግባቸዉ፣ንብረታቸዉ ተዘርፎ ችግር ሲፈጠር ኢትዮጵያዉያን ስንቅ ጭነዉ ባህርን አቋርጠው መጥተዉ አብልተዋቸዋል። ከኢትዮጵያ የሆኑ እንግዶች ነብዩ ዘንድ ሲመጡ ነበዩ እንደ ቤተሰብ አቅፈዉ ስመዉ በጃቸዉ አጉርሰዋቸዉ ተንከባክበዋል።ይህች አገር የተባረከች ትሆን ዘንድ ነብዩ ጸልየዋል።ነብዩ «ሐበሾች ካልኳቹ አትንኳቸዉ!» ሲሉ አዋጅን አዉጀዋል። ይህቺን አገር የነካ፣ፍቅሯን ያወከ፣ በምድር ላይ ሲታወክ ታይቷል። እናም የዚህ ዉብ ታሪክ ባለቤቶች በመሆናችን ኢትዮጵያዊነትን በኩራት እንጂ በመግደርደር አንግለጸዉ። እንኩራ በኢትዮጵያዊነታችን!!

እረኛ የነበረዉ የንጉስ ቤተሰብ
ኢትዮጵያዊነት ጽናት ነዉ! ኢትዮጵያዊነት ቃልኪዳን ነዉ!ኢትዮጵያዊነት ለጥቅም አለመደለል ነው!

በቤተሰብ ግጭት በህጻንነቱ ወደ አረቢያ የተሸጠዉ ኢትዮጵያዊ የንጉስ ቤተሰብ በድር በሚባል ቦታ ፍየልና ግመል ይጠብቅ እንደነበር የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ። የንግስናዉን ቦታ የሚሸፍን ሁነኛ ሰዉ ሲታጣ እረኛ የነበረው የንጉስ ቤተሰብ ተፈልጎ ከተሸጠበት አረቢያ ይመጣና ይነግሳል። ይህ ንጉስ ስሙ አስሃማ (ነጃሺ) ይባላል።የመካ ሙስሊሞች ሲሰደዱ ይኸው ንጉስ ተቀብሎ ያስተናግዳል። መካ ዉስጥ ቁርዐንን ማንበብ፣ ኢስላምን መተግበር የሚያስደበድብ ከዚያም በላይ እስክ አመገድል የሚያደርስ በነበረበት ዘመን፥ ያ ክርስቲያን ንጉስ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቁርዓን እዳይነበብ ኢስላም እንዳይተገበር አልከለከለም።

ኢስላም ከመካ ቀጥሎ ቅዲስትቲቱ መዲና ሳይደርስ ኢትዮጵያ ገብቶ ነበር። በአለም ታሪክ ዉስጥ በእምነት ሳቢያ ለሚደረግ ስደት ጥገኝነት በመስጠት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ አገር በመሆን ስትታወስ መኖሯ የታሪክ ሐቅ ነው። በዚያች ከዉጪ ድረስ ካህናት መጥተዉ ክርስትናን በሚማሩባት አገር ሙስሊሞች ያለችግር እምነትን ተገበሩ። በሰላም በደስታ መኖራቸዉን ቀጠሉ። የመካ ሙስሊሞች በኢትይጵያ ሳቢያ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እርድታን በማግኘታቸዉ ዛሬ ኢስላም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ችሏል።

ጥገኞቹ እንደወንጀለኛ ተይዘዉ እንዲመለሱ አረብ ኢአማኒያን ላቅ ያለ የወርቅ ስጦታ ለእጅ ለመንሻነት ለኢትዮጵያዊዉ ንጉስ ይዘዉ መምጣታቸው በታሪክ የሰፈረ እዉነታ ነው። አረቦቹ ስደተኛ ሙስሊሞችን ለማስመለስ ነገር አዋቂን ዲፕሎማትን ልኡክ አደረጉ። ፍትህን ባገሩ ላይ ያስፈነዉ ንጉስ በዙፋኑ ላይ ተሰይሞ፣ጉዳዩን በችሎት አጣርቶ ሲያበቃ «ጋራን የሚያክል ወርቅ ብትሰጡኝ ጥገኞቹን አሳልፌ አልሰጥም!» ሲል በጥቅም የማይደለል መሆኑን አሳየ።ለጥገኞቹም «መሬቴ መሬታቹ ነዉ ኑሩበት!» ሲል ትእዛዙን ይፋ አደረገ። ያ ፍትሃዊዉ ኢትዮጵያዊ ንጉስ የመጀመሪያዎቹን ሙስሊሞች በመጠበቅና በመንከባከብ ዛሬ 1.7 ቢሊየን አማኒያን ያሉት ሐይማኖት እንዲኖር አርጓል።

በፖለቲካና በዲፕሎማሲዉ ዘርፍ ነብዩ መሐመድን አጋዥ ባልነበረበት ወቅት ፍትህ የሰፈነባትን ሐያልና ገናና አገር ኢትዮጵያን ማግኘታቸዉን አንዳንድ የስነ ሀይማኖት ተመራማሪ የሆኑ ምሁራን ሲተነትኑት ኢትዮጵያ ምድራዊ ምርጫ ሳትሆን ሰማያዊና መለኮታዊ ምርጫ ነበረች ይላሉ። የኢትዮጵያ ንጉስ ፍትሃዊ መሆኑን ነብዩ ቀደም ሲል ለተከታዮቻቸዉ ማስረዳታቸዉ እዉነት መሆኑን የኢትዮጵያ ንጉስ በቃልኪዳኑ ያስመሰከረ ነዉ ሲሉ ምሁራን ይገልጻሉ።ንጉሱም በጉቦና በሙስና ሳይታለል የኢትዮጵያን ታሪክ ከፍ አርጎ ያኖረ ነዉ። ይህም ንጉስ (ቀድም ሲል እንደጠቀስኩት) በቤሰብ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ተሽጦ ፍየልና ግመል ሲጠብቅበት በነበረዉ የበድር ሜዳ ላይ ሙስሊሞች ታላቅ ድልን በጠላቶቻቸው ላይ ተጎናጽፈዋል። ድሉንም የታሪካቸዉ አሻራ አርገዉት እስከዛሬ ይኖራሉ።

ይህ ታሪክ የሁላችንም ነዉ። ይህ ታሪክ የጋራ ነዉ። ይህንን የመሰለ አኩሪ ታሪክ ያለን ሰዎች የምእራብ የቅኝ ግዛት ተስፋፊዎች በበከሉት የማንነት ቀዉስ ልንጠቃ አይገባም። ቀኑ ሳያልፍ ያለ መግደርደር ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገን ይዘን አገራችንን አገር በቀልከሆኑ ባንዳዎች፣ጸረ ኢትዮጵያዉያን አምባገነናዉያን እንረከብ።

ዉድ ወገኖቼ ሆይ፦ እኔ ይህንን ታሪክ ሳነሳ እናንተን ለመስበክ አይደለም። ታሪኬ ታሪካቹ ስለሆነ እንጂ። ብዙ የሚያኮራ ታሪክ አለን። ግን እያለን እንደሌለን ሆነን የታሪክና የማንንነት ደሃ ልንሆን አይገባም። ትላንት የኢትዮጵያዊ የዘር ፍሬ ለጀግንነት፣ለምጥቀት፣ለዲፕሎማሲያዊ ብቃት፣የተዋጣለት ጸሃፊ ለመሆን ከተፈለገ ዛሬ ለምን ኢትዮጵያዊነት የማንነት ቀዉስ ይገጥመዋል? ኢትዮጵያን በመጽሃፍ ቁዱስና በቁርዓን ቦታ ያላቸዉ ምርጥ ህዝቦች ናቸዉ። ምርጥ መሆን ጸጋ ቢሆንም መመረጥን አለማወቅ ግን ከከሳሪዎች ጎራ ያሰልፋልና መመረጣችንን እንወቅ።

ልክ እንደ መጽሃፍ ቅዱስ ሁሉ፤ ኢትዮጵያዉን በተለያየ መልኩ በኢስላማዊ መዛግብት ዉስጥ ተገልጸዋል። ጀግና ሆነዉ ተዋግተዋል። ታማኝ ሆነዉ የህይወት መስዋእትነትን ከፍለዋል። ከመካከለኛዉ ምስራቅ እስከ ደቡብ ኤስያ የጀግንነት ታሪካዊ አሻራቸዉን አሳርፈዋል። ዛሬ ያነሳሗቸዉ ነጥቦች በጣሙን ጥቂቶች ናቸዉ። የሗላዉን ከቃኘን የፊትን መመልከት እንችላለን። የሗላ የሌላቸዉ ትዉልዶች ልቦለድን በታሪካዊ መዘክርነት ሲጠቀሙ እኛ ኢትዮጵያዊነትን በአንድ ስርዓተ-ማህበር ጠፍረን፣ የኢትዮጵያዊነት ጸጋና ዋጋን ከአንድ ንጉስ ጋር ወይም አገረ ገዢ ጋር አቆራኝተን የትላንት እስረኞች ልንሆን አይገባም።

ጨቋኞች በትላንትዉ ፈተና፣በትላንትናዉ ችግርና ዉጣዉረድ አስረዉን ዛሬንና ነገን ሊነጥቁን የሚያደቡ በመሆናቸዉ እንጠንቀቃቸዉ። ዛሬ ካመለጠ አይመለስም። ዛሬ ሲያመልጥ ነገም ይሰወራል። ስለዚህ የኛ የሆነችዋን ነገ በአገር ፍቅር ስሜት እንረከብ። ቅር ከመባባል ይልቅ ይቅርታ መባባልን እናስቀድም። ወደሗላ ማለቱን ትተን ወደፊት እንራመድ። ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት እንድሆን የምንሻ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ እንደቀድሞ ሐያልና ገናና እንድ ሆን የምንሻ ከሆነ ማንም የማይበደልባት የፍትህ አገር እናድርጋት። ፍቅር ጥላቻን ድባቅ ይመታዋልና ወደ ድሉ ደጃፍ አብረን እንጓዝ። በዚያች ኢትዮጵያ በምትባለዋ ታሪካዊት አገር መወለድ ምነኛ አማረ!…ኢትዮጵያዊነት ያኮራል!…ኢትዮጵያዊነት ያስከብራል…በኢትዮጵያዊነት አንግደርደር። ጥራትና ልእልእና የተገባዉ አላህ ኢትዮጵያን ይጠብቃት። አላህዬ አንተ እኮ ኢትዮጵያችንን መርጠሃታል…ህዝቦቿን አንተ ጠብቅ። ከጨቋኞች ነጻ አርጋቸዉ።
አባቴ እንዲህ ይል ነበር «ማንንም ለመበደል አልመኝም።ማንም እንዲያጠቃኝ አልሻም።ፈጣሪዬን የምለምነዉ በደለኛዎቼን ለመከላከል የምወስደዉ እርምጃ እንደ ሐጢዓት እንዳይቆጥርብኝ ነዉ።» ህወሃት የሚባለዉ ጨቋኝ ስርዓት በ አገራችንንና በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለዉን ጥቃት ፈጣሪያችን ያዉቃል። ይህንኑ ጨቋኝ ህወሃት ለመከላከል፣ወገናችንና አገራችንን ለመታደግ የምንወስደዉን እርምጃ እንደ ሐጢዓት እንዳይቆጥርብን። አሚን! በኢትዮጵያዊነት ሁሌም እንኩራ በኢትዮጵያዊነት አንግደርደር።ልብ ያለዉ ልብ ይበል! አመሰግናለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.