አዴሃን በጠገዴ ግጨው አካባቢ ለትግራይ ክልል የተሰጠው ቦታ የማያባራ የሕዝብ ግጭት ሊፈጥር እንደሚችል አስጠነቀቀ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 5/2010) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ/አዴሃን/ በጠገዴ ግጨው አካባቢ ለትግራይ ክልል በብአዴን ተላልፎ የተሰጠው ቦታ የማያባራ የሕዝብ ግጭት ሊፈጥር እንደሚችል አስጠነቀቀ።

የትግራይና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በቅርቡ ያደረጉት ስምምነት የሕዝብን ይሁንታ ያላካተተ በመሆኑ አካባቢውን ወደ ግጭትና ትርምስ ሊወስደው ይችላል ብሏል።

መላው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የአማራ ሕዝብ ወልቃይትን ለማስመለስ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ/አዴሃን/ጥሪ አቅርቧል።

በቅርቡ በግጨው ጉዳይ ላይ በጠገዴ ወረዳ የአማራና የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና አቶ አባይ ወልዱ የተፈራረሙት ስምምነት ከዚህ ቀደም ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደበትን ጉዳይ የሚቀለብስ መሆኑን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ/አዴሃን/በመግለጫው አመልክቷል።

በ1999 በሁለቱ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የትግራይ ሕወሃት ቡድን የመስፋፋት ጥያቄ ሲያቀርብና ከወልቃይት አልፎ የግጨው የእርሻ ቦታዎችን ሲወር ሕዝቡ ተቃውሞውን አቅርቦ ነበር።

በወቅቱም ጉዳዩን በውይይት መፍታት ባለመቻሉ ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ከ90 በመቶ በላይ ሕዝብ አካባቢውን የአማራ ነው በማለቱ ውጤቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መታፈኑንና ይፋ ሳይደረግ መቆየቱን የአዴሃን መግለጫ አስታውሷል።
እንደ አዴሃን መግለጫ የግጨው አካባቢ ከወልቃይት ጉዳይ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።

የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አማራነቱን አረጋግጦ ውሳኔውን ካሳወቀ ቢቆይም የብአዴን ተላላኪዎች አካባቢውን ለትግራይ አሳልፈው በመስጠት የሕወሃትን አጀንዳ ማስፈጸማቸው ታሪካዊ ስህተት መሆኑንም አዴሃን በመግለጫው ጠቅሷል።
እናም በአካባቢው በዚሁ ችግር ሳቢያ ለሚከሰተው የማያባራ ግጭት ብአዴንና አስፈጻሚዎቹ ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አዴሃን በመግለጫው አስጠንቅቋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ/አዴሃን/ የአማራ ሕዝብ ላይ በአገዛዙ እየደረሰ ያለውን በደል ለማስቀረት የትጥቅ ትግል እያካሄደ እንደሚገኝም አብራርቷል።

ስለሆነም መላው የአማራ ልጆች አዴሃን የሚያካሂደውን ትግል በመደገፍ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.