ሶማሌው ፣ኦሮሞው፣ ሁሉም እኩል የሆኑባቸው አስተዳደሮች ያስፈልጋሉ #ግርማ_ካሳ

በቀድሞ የኤታ ማጆር ሹም ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ስም በተከፈተ የትዊተር አክዉንት ፣ ጀነራሉ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል ፕሬዘዳንቶች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ፣ ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማሪያም ደሳለኝም ጣልቃ እንዲገቡ መጠየቃቸው ይገልጻል ። የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮም እንደዘገበው ዛሬ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከተደበቁበት ወጣ ብለው መግለጫ የሰጡ ሲሆን በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል መካከል ግጭቶች በተፈጠሩባቸው ቦታዎች የፌዴራል መንግስት ህግና ስርአት እንዲያስጠበቅ ትእዛዝ ሰጥተዋል።

ጀነራል ጻድቃን እርሳቸው ስልጣን ላይ የነበሩ ጊዜ የርሳቸው ድርጅት ህወሃት ከኦነግ ጋር በመሆን ያመጣውና የዘረጋው የዘር ፖለቲካ ያመጣው ጣጣና መዘዝ መሆኑ እየታወቀ ፣ የትዊተሩ መልእክት ህወሃትን አልፎ እነ ለማን መውቀሱ ተገቢ አይመስለኝም።

የአገሪቷ ህግ መንግስት አገሪቷን በዘር በመሸንሸን፣ የሶማሌ ክልልን ለሶማሌዎች፣የኦሮሚያ ክልልን ደግሞ ለኦሮሞዎች መስጠቱ ይታወቃል። ከዚህ የተነሳ ሶማሌዎችና ኦሮሞዎች  በብዛት አብረው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ አንዳንድ ቦታም የኦሮሞም የሶማሌም ማንነት የሚያንጸባርቁ ጎሳዎች በመኖራቸው፣ ግጭቶችና ዉዝግቦች እየተደጋገሙ ተከስቷል።  እድሜ ለፌስ ቡክና ሶሻል ሜዲያ አሁን መረጃዎች በቀላሉ ስለሚወጡ ነገሮች በይፋ ታወቁ እንጂ፣  አሁን በሕይወት የሌሉት የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳናት አቶ አለማየሁ አቶምሳ በነበሩ ጊዜ፣ በርካታ ኦሮሞዎች ላይ አሁን በስልጣን ላይ ባለው የአብዲ የሶማሌ ሚሊሺያ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ነበር። ብዙ የሞቱም ነበሩ።

ግጭቶችን ለመፍታት ከአሥር አመታት በፊት በ420 ቀበሌዎች ህዝብ ዉሳኔ የተደረገ ሲሆን፣ ወደ 80% የሚሆኑ ቀበሌዎች በኦሮሚያ ውስጥ መቀጠሉን ነበር የወሰኑት።  እንደዚያም ሆኖ ለሶማሌዎች የኦሮሞ ብቻ በሆነ ክልል፣ ለኦሮሞዎች ደግሞ የሶማሌ ብቻ በሆነ ክልል መቀጠሉ አስቸጋሪ ነው። ሕዝበ ዉሳኔ ቢያደርግም፣ ባለስልጣናት ተስማማን ቢሉም፣ ችግሮቹ ሳይፈቱ ይኸው አሳዛኝ ደም መፋሰስ እያስከተለ ነው። ችግሮች ለጊዜ ጋብ ሊሉ ይችላሉ እንጂ መቼም አይፈቱም፤ አንዱ ባለቤት ሌላው እንግዳ፣ አንዱ አድነኛ ዜጋ ሌላው ሁለተኛ ዜጋ፣ ተደርጎ በሚታይበት አሰራር።

በድረዳዋ ከተማ ተመሳሳይ ችግር እንደነበረ፣ ድረዳዋ “የኦሮሞ ትሁን፣ የሶማሌ”  በሚለው መስማማት ስላልተቻለ ድረዳዋ የፌዴራል ቻርተር ከተማ እንድትሆን መደረጉ ይታወሳል። (በነገራችን ላይ ድረዳዋ ከተማ ትንሿ ሃረር በሚል በአጼ ሚኒሊክ የተቆረቆረች ከተማ መሆኗ መረሳት የለበትም) በተመሳሳይ ሁኔታ የንግድ ማእከል በሆነችዉና ወደ ኬንያ በምታስገባዋ የሞያሌ ከተማም የይገባኛል ዉዝግብ በመነሳቱ፣ በከተማዋ በሚያልፈው ዋና መንገድ በስተ ምስራቅ የሶማሌ ክልል፣ በስተምእራብ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል እንዲሆን በማድረግ፣ በሚያስቅ ሁኔታ ከተማዋ በሁለት ክልሎች ነው የምትተዳደረው። በከተማዋ ዋና መንገድ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ፣ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ወይንም የኦሮሚያ ፖሊስ ሊይዘው ይችላል። “ወሪያ ካሌ” ወይንም “አካም ጅርታ” ተብሎ ሰላምታ እየተሰጠው።

ህዝበ ዉሳኔ ጥሩ ነገር ነው። ዴሞክራሲያዊ ነው። ሆኖም የማይኖሪቲ መብትም መከበር አለበት። የአንድን ወረዳ ወይም ቀበሌ ህዝብ፣ አብዛኛው ወደ አንድ መንገድ ቢያዘነብል፣ አሁንም ለማይኖሪቲው ዋስታና ካልተሰጠ ችግር ነው።ለምሳሌ በአንድ ቀበሌ 60% ኦሮሞዎች፣ 40% ሶማሌዎች ካሉና ኦሮሞዎች ስለሚበዙ ቀበሌው ከኦሮሚያ ጋር መሆኑን ቢመርጥ፣ ችግሮች አይፈቱም። ለምን 40% የሚሆነው ሶማሌ በድምጽ በመበለጡ   የኦሮሚያ ብቻ በሆነች ክልል  መቀጠሉ ለርሱ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተደረጎ መቆጠር ነው።

ለዚህም ነው ፍቱን መፍትሄ፣ ትልቅ ማይኖሪቲ ባሉባቸው አካባቢዎች በተቻለ መጠን ሁሉንም ያቀፈ አስተዳደር መመስረቱ ነው። የተለያዩ ብሄረሰቦች ቢያንስ ከ10 በመቶ በላይ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሕብረ ብሄራዊ ይዘት ያለው አስተዳደር መኖሩ በጣም ጠቃሚ ነው።

ለምሳሌ ከሃረር በስተምስራቅ ያለውን አካባቢ (እንደ ጭናቅሰን ጃርሶ፣ ባቢሌ…ያሉትን)፣ በድረዳዋና በሃረር መካከል ያሉ እንደ አወዳይ፣ ኮምቦልቻ፣ አሮማያ/አለማያ ያሉ ቦታዎችን፣ ድሬዳዋና ሃረር ከተማን በማጠቃለል ፣ ሶማሌኛ፣ አፋን ኦሮሞና አማርኛ የሥራ ቋንቋ የሆነባት፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌው፣ አማራው፣ አደሬው..ሁሉም በእኩልነት የሚታዩባት፣ አዲስ ክልል ቢፈጠር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የክልሉ ስም ሃረር የሚለው ታሪካዊ ስም ቢሰጠው ሁሉንም ሊያስማማ ይችላል። በቃ እዚያ አካባቢ የሚኖረው ሰው የሃረር ሰው ይባላል። ትንሽ ከስሜትና ከዘር አጥር ወጥተን ነገሮችን ካየን ለሁሉም የሚበጅ ነው የሚሆነው።  ያኔ በሃረርጌ በአስተማማኝ መልኩ የዘር ግጭቶች ሊፈቱ ይችላሉ።

እንደዚሁም በሞያሌና በአካባቢዋም ተመሳሳይ የሆነ ሶማሌዉም ኦሮሞዉን፣ ሌላውም እኩል የሆኑበት አሰራር መኖሩ ከዘለቄታዊ መፍትሄ አንጻር በጣም አስፈላጊ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.