ትውልድ ፈታኝ ቀውጥ !!! – ኣረጋዊ በርሄ

ኣረጋዊ በርሄ

“በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ በድረቅ የደቀቀው ህዝባችን፥ በኣሁኑ ወቅት ደግሞ በግጭቶች ሳብያ እያለቀ ነው። ሃገር ከባድ ቀውጥ ውስጥ ገብታለች። በእርስበርስ ግጭቶች ሳብያ ከድንበሩ ጀምሮ ማህሉ ድረስ ባለው ህዝባችን ላይ የሞትና የመቁሰል ኣደጋዎች እየደረሱ ናቸው። በገፍ መፈናቀልና ንብረት መውደም ኣብሮ እየተከተለ ነው። ግጭቱ ባልደረሰባቸው ኣከባቢዎች ጭንቅና ፍርሃት ኣይለዋል። ይህ እየተሰራጨ ያለው ክፉ ክስተት ማቆምያ ካልተበጀለት ሃገር-ኣልባ ሊያደርገን ይችላል። ቀውጡን የፈጠረው የህወሓት/ኢህኣዴግ ገዢ መደብ ለመሆኑ ኣጠያያቂ ኣይደለም። ይህ ሓላፊነት የማይሰማው ኣምባገነን ቡድን ገና ከጅምሩ የወጠናቸው ደንባራና ስግብግብ ፖሊሲዎች እንዲሁም ኣረመንያዊ የኣገዛዝ ዘይቤዎች ኣሁን ከምንገኝበት ኣረንቋ ውስጥ ከቶናል። ኣጠቃላይ ኣቅጣጫው መላው ህዝቡን እርስበርስ የሚያፋጅ፥ ሃገርን በጎጥ ጭምር የሚበታትን ለመሆኑ በኣራቱም መኣዝናት ከሚሰማው የድረሱልን ጩኸት መገንዘብ ኣያዳግትም።

ይህን ኣሳሳቢ ምጽኣት መቀልበስና ወደ ብሩህ ስኬት መለወጥ ኣይቻልምን? ምን ቢደረግና ማን ቢያደርገው ነው ሃገራችን ከዚህ ጥልቅ ቀውጥ ማውጣት፥ ህዝባችን ደግሞ ከወረደበት መከራ ማዳን የሚቻለው? እነዚህና ተጓዳኝ የሆኑ ጥያቄዎች ለማንም ኣርቆ-ኣሳቢ ዜጋ ሁሉ እንቅልፍ የነሱና መፍትሄ ለማግኘትም እያነጋገሩ ያሉ መሆናቸው ይታወቃል። በየኣቅጣጫው ጥረትም እየተደረገ ነው፣ ሆኖም ግን ጥረቱ ከኣደጋው ኣጥፊነትና ኣጣዳፊነት ኣንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ይዘት ስለሌለው ኣደጋው ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሄድ በብዙ ሃገር-ወዳድ ዜጎች ዘንድ ስጋት ኣለ። ይህ እጅግ ኣሳሳቢ ስጋት የዚሁ ትውልድ ፈተና መሆኑ ነው። ወቅታዊና ተግባራዊ መልስም ይሻል።

ይህ “ትውልድ ፈታኝ ቀውጥ” በሚል ርእስ የቀረበው ኣጭር ጽሁፍ የችግሩን ምንጭና ተከትሎ እየመጣ ያለው ኣደጋ በማብራራት የመፍትሄ ኣቅጣጫ ይጠቁማል፣ ከወዲሁም ሓላፊነት በሚሰማቸው ዜጎች መካከል እየተካሄደ ላለው ጥረት መለስተኛ ኣስተዋጽኦ ይሆናል ብሎ ያምናል።

የችግሩን ምንጭ

በኣጠቃላይ ሲታይ የሃገር ሉዓላዊነትና የህዝቡ መብት መከበር ተነጣጥለው የሚታዩ እሴቶች እንዳይደሉ ሁሉ፥ እነዚህ እሴቶች እንዲኖሩ የሚያስችል ስርዓተ-መንግስት ኣለመኖሩ የሁሉም ችግሮቻችን ዋናው ምንጭ ነው ማለት ይቻላል። እስከ ኣሁን ድረስም በኢትዮጵያችን የሃገር ሉዓላዊነትና የህዝብዋ መብት የሚያስከብር ስርኣተ-መንግስት ተመስርቶ ኣያውቅም። ለዚህም ነው ሰላም፣ እኩልነት፣ ኣንድነትና ብልፅግና  የራቀን፣ ፖለቲካዊ ባህላችንም ድንኪየ የሆነው። የሃገራችን ነፃነትና የህዝቧ የመወሰን መብት በጋራ በሚመሰረተው ስርዓተ-መንግስት ስር ሆኖ ተግባራዊነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ለዘመናት የዘለቀውን መከራ ላያበቃና በከፋ መልኩም ሊቀጥል እንደሚችል መገንዘቡ፥ ከያዝነው ርእሰ-ጉዳይ ጋር የሚታይ ኣስፈላጊና ወቅታዊ ጉዳያችን ነው።

ስርኣተ-መንግስት (ስቴት) ሲባል መንግስት (ገቨርንመንት) ከሚባለው የኣስተዳደር ኣካል የላቀ፣ ሰፊና ዘለቄታ ያለው የኣገዛዝ ዘይቤ ነው። ይህ ማለት ሰዎች ወይም ድርጅቶች ግላዊ ፍላጎታቸውን ሆን ብለው ገድበው፥ በጋራ ለሚተዳደሩበት ኣስገዳጅ መዋቅር ተገዢ የሚሆኑበት ስርዓትን ይመለከታል። ዴሞክራሲ እስከ ሰፈነ ድረስ በኣንድ ስርኣተ-መንግስት ስር የተለያዩ እንዳውም በረካታ መንግስታት ሊፈራረቁ እንደሚችሉ የታወቀ ነው።

ስለዚህም ነው የትግላችን ስትራቴጂያዊ ዓላማ በህዝቡ ሙሉ ተሳትፎና ኣመኔታ የሚዋቀር ስርኣተ-መንግስት መመስረት ይቅደም የምንለው። ይህ ሁሉን-ኣቀፍ ስርኣተ-መንግስት የተለያዩ (የግራም ይሁን የቀኝ) ርእዮተ-ዓለም የሚያቀነቅኑ ሃይሎች በእኩልነት የሚያስተናግድ ይሆናል። በዚህ ዓይነቱ ስርኣተ-መንግስት ስር ሆኖው የተለይየ ኣቋም ያላቸው ፓርቲዎች በእኩልነት ተወዳድረው ኣብላጭ የህዝብ ድምጽ ያገኙት ወገኖች መንግስት ሊመሰርቱና ሊመሩ ይችላሉ። ይህ ሂደት ዘላቂ ሰላምና ዕድገት የኑሮኣችን ኣካል የሚያደርግ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ የጋራ ስርኣት ኣስቀድሞ ሳይመሰረት የሚመጣ የመንግስት ለውጥ ‘የጉልቻ መቀያየር’ እንዲሉ፥ ቀውስን የሚያባብስ እንጂ መፍትሄ ሊሆን ከተውንም ኣይችልም። ስለዚህ የጋራው ዓላማችን የጋራ ተሳትፎን የሚጠይቀው ሁላችንን በእኩልነት የሚያስተናግድ ፍትሃዊ ስርዓተ-መንግስት መመስረት ሆኖ፣ ለዚህ በጎ ዓላማ መሳካት እንቅፋት የሚሆኑትን ሁሉ ታግሎ ማስወገድ እንደ ቅድመ ሁኔት ማየቱ የግድ ይላል።

ለዘመናት የተከማቹት ችግሮቻችን ስር የሰደዱና የተንዛዙ ቢሆኑም ቅሉ፣ በማንኛውም ዘመነ-መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት ሙከራዎች ኣልነበሩም ማለት ኣይደለም። ሙከራዎቹ ግን በኣጭር የሚያዩ፥ በዋናነት ግላዊና ወገናዊ ስግብግብ ፍላጎቶች ያጠቋቸው ቁንፁላን ኣካሄዶች ስለነበሩ ከመፍትሄነታቸው ይልቅ ሰበባቸው እያየለ መምጣቱ ኣይካድም። የችግሮቹ ምንጭ ከኋላ-ቀር ስርዓቱ ለመሆኑ ኣከራካሪ ኣይደለም። የኣጼዎቹ ይሁን የደርጎቹ እንደዚሁም የኢህኣዴጎቹ መንግስታዊ ስርዓቶች በቅርጽ ይለያዩ እንደሆን እንጂ በይዘት ኣይራራቁም። ሁሉም የህዝቡን መብት የሚንዱ የጭቆና ስርዓቶች ናቸውና። ስለዚህም የኣስመሳይ ቡድኖች ሳይሆን የመላው ህዝብ ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ ስርዓት ተመስርቶ፥ በህዝብና በሚፈጠረው መንግስታዊ ስርኣት መካከል የሚኖረው ቁልፍ ግንኙነት በማያሻማ ሁኔታ መስተካከል ኣለበት። ይህ ግንኙነት እስካልተስተካከለ ድረስ ከጨቋኝ መንግስታትና ከሚያስከትሉት ዘርፈ-ብዙ መከራ ኣንገላገልም ማለት ነው።

ከዚሁ ኣጠቃላይ ግንዛቤ በመነሳት ለወቅቱ ችግሮቻችንን ትኩረት ሰጥተን መፍትሄ ስንቃኝ፣ የችግሮቹ መንስኤ ከሶስት ኣቅጣጫዎች በኩል የሚመነጩ እንደሆኑ ማመላከት ይቻላል። እነሱም፣ 1ኛ/ ስልጣን ላይ የሚገኘው ህወሓት/ኢህኣዴግ፣ 2ኛ/ የውጭ/ባእዳን ሃይሎች፣ 3ኛ/ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ወገን፣ እኛው ራሳችን ቢባል ያስኬዳል። እነዚህ ሶሰት ክፍሎች ባንድ በኩል ራስ-ወጥ ሆኖው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የትብብርም የፀርነትም ግኑኝነት ፈጥረው ስለሚንቀሳቀሱ ለፍትህ የሚካሄደው ትግል ረጅምና ውስብስብ እንዲሆን ከማስገደዱ በላይ ሃገራችንን ለመከፋፈል፥ ህዝባችንን ለእልቂት እየዳረገ ለመሆኑ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል።

ምናልባት እዚህ ላይ በተቃዋሚው ጎራ የሚገኝ ኣካል ለትብብራችን ችግር ፈጣሪ መሆን እንዴት ይታሰባል? የሚል እሳቤ ኣይጠፋም፣ ግን መልሱ ባጭሩ ኢህኣዴግ በቀየሰው የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ መራመድ ካለ፣ ተሸፋፍኖም ይሁን በግልጽ ይከሰታልና፥ ኣሉታዊ ትብብር ይሉታል ይኸው ነው። እንግዲህ የችግሮቹን ምንጭ ባጭሩም ቢሆን ኣንድባንድ ለማየት እንሞክር፣

1ኛ/ የመጀመርያው ችግር ህወሓት/ኢህኣዴግ ሲሆን ይህ ቡድን የመሰረተው መንግስት ሽብርተኛ-ኣምባገነን ለመሆኑ የሚያከራክር ኣይደለም – ለ26 ዓመታት ተግተነዋልና። በዚህ ሽብርተኛ-ኣምባገነን መንግስት ኣማኻኝነት ኣዲስ ገዢ-መደብ ተፈጥሯል። የዚህ ኣዲስ ገዢ-መደብ ኣስኳል የህወሓት ቡድን ቢሆንም ከሁሉም ብሄር-ብሄረሰቦች የተውጣጡ በኢህኣዴግ ስም የተሰባሰቡ የገዢ-መደብ ኣባላት ኣሉበት። እንደ ገዢ-መደብ ኣባላት ሁሉም ብዝበዛውና ሽብሩ ኣምባገነናዊ በሆነ መልኩ እያካሄዱት ይገኛሉ። ጭንቀታቸው ሲያይል ‘ጊዚያዊ ኣዋጅ’ በሚል ስም ሽብርተኛነታቸውን ያከሩታል። ጎን ለጎን ደግሞ የየብሄረሰባቸው ተቆርቋሪ በመምሰል የሌሎቹ ብሄረሰቦች ተቀናቃኝ በመሆንና ልዩነትን በማስፋት ህዝብን እርስበርሱ እያጋጩ ተዝናንተው ለመግዛት ይጥራሉ። ቀደም ሲል በኣኝዋክና በኑወር ጋምቤላዎች፣ ኣሁን ደግሞ በኦሮሞና በሶማል ዜጎቻችን መካከል የተካሄዱና እየተካሄዱ ያሉ እልቂቶች – ከብዙ በጥቂቱ – እንደ ኣብነት መጥቀስ ይቻላል። ይህ ድርብ ስለት ያለበት ኣስነዋሪ የኣገዛዝ ዘዴ በተናጠል ይሁን በጣምራዊ ይዘቱ ጠንቅቆ ኣውቆ ኣልፎ መቆየት የትግል ስልቱ ‘ሀ’ ‘ሁ’ ነው።

2ኛው ችግር ባዕዳን/የውጭ ሃይሎችን ይመለከታል። ሽብርተኛ-ኣምባገነኑ ኢህኣዴግን በገንዘብ፥ በመሳርያ፥በዲፕሎማሲ፥ በማፈኛ ዘዴዎች ወዘተ፡ የሚያስታጥቁት የለመደባቸው ባዕዳን ሆነው፣ ኣሁን በዋናነት የኣሜሪካና የእንግሊዝ መንግስታት ቀጥሎ ደግሞ የኣውሮፓና የቻይና መንግስታት በፀረ-ህዝብ ቅንብሩ ተሳታፊዎች ናቸው። ሁሉ ጊዜ የሃገርን ልዕልና፣ የህዝብን ኣመኔታ መሰረት ያደረገ መንግስት እንዲኖር ኣይፈልጉም፣ ለስትራተጂያዊ ዓላማቸው ዕንቅፋት ኣድርገው ይቆጥሩታልና። የሃገሩንና የህዝቡን መብት ቅድሚያ የሚሰጥና የሚያስከብር መንግስት የማይፈልጉ ለመሆናቸው ከታሪክም ሆነ ከወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ መገንዘብ ኣይከብድም።

ከዓለምኣቀፋዊው ግኑኝነት ተነጥሎ መኖር ኣይቻልምና፣ ታድያ እነዚህ ባዕዳን ሃይሎች መቼ እና በምን ሁኔታ ላይ ስንሆን ነው በጊዚያዊነትም ቢሆን ሊተባበሩን የሚችሉ ብሎ ከታሪክም ይሁን ከወቅታዊ ተጨባጭ እውነታ ኣንፃር በቅጡ መመርመር ያስፈልጋል። ለዚህ ኣጭር መልሱ የተበታተኑት ሓይሎችን በማሰባሰብ፥ ህዝባችንን ኣደራጀትና ከጎኑ ተሰልፈን የምር ሓይል ሆነን ስንገኝ ብቻ ነው። ያኔ ብቻ ነው የምር የሚያዳምጡን።

3ኛው ችግር በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፈው ወገን ማለት ‘እኛው’ ራሳችን ጨምሮ የሚመለከት፥ ተበታትኖ የመታገል ኣባዜ ነው። ካፍንጫችን ያልራቀው እውነታ እንድሚያሳየው፣ ተበታትነን እየታገልን ኣንድባንድ እየተመታን ይኸውና 26 ዓመታት ተሰቃይተናል። ይህ የትርምስ ጉዞ ኣሁንም ኣላበቃም። የሚያበቃበት መንገድ መፈለግ እንደ ቀዳማዊ ስራ፣ ኣልያም እንደ ቅድመ-ሁኔታ ታይቶ ርብርቦሽ ሊደረግበት የሚጠይቅ ስትራተጂክ ጉዳይ ነው። የተበታተኑት የእኩልነት፣ የኣንድነት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ሓይሎች ካልተሰባሰቡና ተደራጅተው ትግሉን ካልመሩት ኢህኣዴግ ሊወገድና የስርዓት ለውጥ ሊመጣ ከተውንም ኣይችልም። በዚህም ሳያበቃ፥ የቁልቁሉ ጉዞ ተፋጥኖ ጭራሽ መግታት የማይቻልበት ኣደጋ ሊከሰት ይችላል። በኣራቱ የሃገራችን መኣዝናት እየተካሄድ ያለ ኣሳዛኝ እልቂት የሚያመላክተው ይኸው መራራ ሓቅ ነው።

ይህ ስር የሰደደው የመከፋፈል በሽታ የትግላችን ነቀርሳ ከመሆኑ ባሻገር፣ ህወሓት/ኢህኣዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ ጀምሮ የመጣ ኣድርጎ ማየቱ ደግሞ ሌላ ስህተት ሲሆን፣ ስር-ነቀሉ መፍትሄ የስርዓት ጉዳይ መሆኑ ኮለል ብሎ እንዳይታይና እንዳይጨበጥ እንቅፋት መደቀኑም ኣልቀረም። እስካሁን የነበሩን ስርዓቶች በገቢር ተመሳሳይ እንደሆኑ ከላይ መጥቀሳችን ለዚህ ነበር። በርግጥ ህወሓት/ኢህኣዴግ ክፍፍሉ በኣዲስ መልክ ኣቀነባብሮና ሕጋዊ ልባስ ሰጥቶ መተዳደርያው ደንብ ኣድርጎታል። ይህ ድርጊት ሃገራች ወደ ባሰ የመከፋፈል ኣደጋ እንድታሽቆለቁል ኣድርጓታል። ኣደጋው ደግሞ እላይ እንደተገለጸው በጣም ኣሳሳቢ መሆኑ ወቅታዊ ጭብጦች ያስረዳሉ።

 

መዘዙ፥

የችግሮቹ ምንጭ ከሶስት ኣቅጣጫ መሆኑ ካየን ዘንድ፥ ይህን ተከትሎ እየተንከባለለ በመምጣት ላይ ያለው ኣደጋስ የት ሊያደርሰን ይችላል? ኣደጋው ከመድረሱ በፊት መግቻ ሊበጅለት ኣይቻልምን? ብሎ መጠየቁ የወቅታዊው ችግሮቻችን መፍትሄ ከመፈለግ ኣንጻር ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ኣደጋው ተመልሶ ላይመጣ ዘላቂ ስርዓትና ድንብ ለማነጽ ስለሚረዳ ጥያቄው እጅግ ኣስፈላጊ  ሆኖ እናገኘዋለን።

ያለምንም ጥርጥር፥ የተቀሰቀሱት ግጭቶች ለሁሉም ወገን ኪሳራ እንጂ ትርፍ ኣላመጡም፣ ኣያመጡምም። ኣብዛኛው ኪሳራ ደግሞ መተኪያ ኣይገኝለትም፣ መዘዙም ለቀጣይ ትውልድ ሊተርፍ ይችላል። እየተንከባለለ ብሎም እያየለ በመምጣት ላይ የሚገኘው፥ ሁሉን ኣውዳሚ ኣደጋ ስፋቱና ጥልቀቱ ለመገንዘብ ይረዳ ዘንድ እንሆ ባለፉት ኣስር ዓመታት (ከ 2001 እስከ 2011 ዓ/ም/ፈረንጅ ባለው ጊዜ ብቻ) ባለሙያዎች ከዘገብዋቸው ግጭቶችና መዘዛቸው ለናሙና ያህል ኣጠናቅረን ያዘጋጀነውን ቀጥሎ ማየት ይቻላል።

ዓ/ም/ፈ                         የየኣካባቢ ግጭት                                የሞተ ሰው ብዛት

2001                            ቦረና ከ ጌሪ                                               62

2002                            ከረዩ ከ ኣፋር                                             56

2002                            ኑወር ከ ኣኝዋክ                                          60

2003                            ኦሮሞ ከ ኦጋዴኒ                                         18

2004                            ኣኝዋክ ከ ደገኞች                                        200

2005                            ኣፋር ከ ኢሳ                                              83

2006                            ጉጂ ከ ቦረና                                              125

2007                            ኒያንጋንቶም ከ ካሪ                                      ?

2008                            ደራሻ ከ ኮንሶ                                            33

2009                            ካፊቾ ከ ኦሮሞ                                           ? (70,000 ተፈናቃይ)

2010                            ጅካኒ-ኑወር ከ ሉዎ-ኑወር                               ? (32,000 ተፈናቃይ)

2011                            ኦሮሞ ከ ጉሙዝ                                         ? (1800 ተፈናቃይ)

——————-

ምንጭ፥ የተ.መ.ድ.-ኢሪን እና የኢ.ሰ.መ.ኮ. (ጥንቅሩ የቆሰሉ፥ የወደመ ንብረትና ሁሉጋ የሞቱና የተፈናቀሉ ኣይጨምርም)

—————————————————————————————————–

ይህ ኣሁን በምስራቅና በሰሜን ክፍላተ ሃገራችን የተቀሰቀሰው ግጭት ኣዲስ ክስተት ሆኖ መታየት ኣይኖርበትም፣ እላይ ለናሙና ከተጠቀሱት ግጭቶች የቀጠለ እንጂ። ህወሓት/ኢህኣዴግ ስልጣን ላይ ወጥቶ፥ ከፋፋይ ፖሊሲውን የተግባር መመርያ ሲያደርገው ጀምሮ የነበሩ ግጭቶች ናቸው፣ ኣሁንም ሃገራችንን እየናዱና ህዝቦቻችንን እያጫረሱ ያሉት። ኣያርገው እንጂ እነዚህ የተዳፈኑ ግጭቶች ባንድ ወቅት ቦግ ብለው ቢነሱ፣ የሚተርፍ ሃገር፥ የሚድን ህዝብ ይኖረናል? “ኣያርገው” ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ ደግሞ ኣይደለም። የኣምባገነኑ  ህወሓት/ኢህኣዴግ የተግባር መመርያ ነውና ይህ መሰሪ ገዢ መደብ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ “ኣይመጣምን ትተሽ፥ ይመጣልን . . . “ ብናስብና ኣደጋው ሳይቀድመን ለመፍትሄው ብንረባረብ ለሁሉም ይበጃል።

 

የመፍትሄ ኣቅጣጫ፥

ህዝብ የለውጥ ማዕበል ሊሆን ከተፈለገ ኣሰባሳቢና ኣቅጣጫ ኣመላካች ፊታውራሪ ያስፈልገዋል። እንዲሁ ጥግ ይዞ “ህዝቡ ምን ኣለ? ለምን ኣይነሳም?” ብቻ ማለት “ውጊያ ላይ ያልዋለ፥ ስለታም” እንዲሉ ኣጉል ብልጣብልጥነት ኣልያም የዋህነት ነው። ህዝቡ እንደሆን በተናጠል እየተነሳ በተናጠል እየተመታ፥ እየቆሰለና እየደማ ነው ያለው። የተበታተነ ሓይል ደግሞ እርባና እንደሌለ ይኸውና የ26 ዓመታት ውጣውረድ ግልብጭ ኣድርጎ ኣሳይቶናል። የተገኘ ለውጥም የለም። ለውጥ ስንልም፥ እላይ እንደተጠቀሰው ከመንግስት ለውጥ በእጅጉ የላቀ፥ የስርዓት ለውጥ ለማለት እንደሆነ ከወዲሁ ሊታወቅ ይገባል።

ይህ ከባድ ሓላፊነት የስርዓት ለውጥ ፈላጊዎች በሆኑ በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቪል ማሕበራት ትከሻ ላይ የወደቀ ለመሆኑ ኣጠያያቂ ኣይደለም። ይሁንና ይህ ሰፊና የተዘበራረቀ ሓይል በተለምዶ ተቃዋሚው ጎራ የተሰኘው፥  በኣንድ የጋራ ዓላማ የተጣመረ ሳይሆን የተበታተነ ለመሆኑ ቤተ እምነቶቹ ሳይቀሩ ይመሰክራሉ። ኣንዳንዶቹም ህወሓት/ኢህኣዴግ የቀየሰውን የመከፋፈል ስንጥቆች እየተከተሉ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ችግሩን በማባባስ ላይ የሚገኙ እንዳሉ መታወቅ ኣለበት። ይህ ኣዝማምያ ለጋራ ትግሉ ክፉ ነቀርሳ ከመሆኑ ኣልፎ፥ ውሎ ኣድሮ የሚያስጠይቅ የርስበርስ ጦርነት ዘርም እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ችግርን ፈቺ መሆን የነበረበት ሓይል እራሱ ችግር ሆኖ ሲገኝ፥ ችግሩ ይፈታል ብሎ ማሰብም ከቶ ኣይቻልም። ትርጉም ያለው የለውጥ ሓይል መፍጠር ከተፈለገ በየመስኩ የሚንፀባረቁት የጥበትም ይሁኑ የማንኣህሎብኝነት ከፋፋይ ኣመለካከቶች ያለይሉኝታ ማስወገድ፣ ከፋፋይ ኣጥሮችን መስበርና የተበታተነው ህዝባዊው የወገን ሓይል በየመድረኩ ማገናኘትና መልክ ማስያዝ የግድ ይላል።

ከዚህ እይታ በመነሳት፥ ኣሁን ከፊታችን ተደቅኖ ካለው ኣደገኛ ሁኔታ ኣኳያ መወሰድ ያለባቸው ኣጣዳፊ እርምጃዎች ምንድን ናቸው? ለሚለው ኣንገብጋቢ ጥያቄ ወሳኝ ኣቅጣጫ የሚያስይዙን መልሶች የሚከተሉትን ናቸው ማለት ይቻላል።

ሀ/ የተለያየ የታሪክ፥ የፖለቲካ፥ የሃይማኖት፥ የብሄረሰብ፥ የድርጅት ታማኝነት፥ የትግል ስልት . . . ወዘተ ልዩነት ይኑረን ኣይኑረን፣ የኣንድን ሃገር ዜጎች እስከሆን ድረስ በዚች ሃገር ላይ የሚደርሰው ኣደጋ ሁላችንን የሚያቆስል በመሆኑ፥ ልዩነታችን በጋራ በምንመሰርተው ስርዓት ውስጥ በኣግባቡ ለማስትናገድ በይደር ኣቆይተን፣ ኣሁን ከፊታችን ለተደቀነው ሃገራዊ ኣደጋ ለማምከን በጋራ መቆም፣

ለ/ ሁሉን የፖለቲካና የሲቪል ድርጅቶች የሚወክልና ወቅታዊ ስልጣን የተጎናጸፈ ኣስተባባር ኣካል ማቋቋም። የዚህ ኣካል ኣምሳያ ሃገር-ቤትም ውስጥ እንዲቋቋም የሚቻለውን ሁሉ ማድረግና ሁለቱም ኣካላት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማስቻል፣

ሐ/ ይህ ተነሳሽነት ማን ይያዘው ለሚለው (በኢትዮጵያውያን ዘንድ ኣወዛጋቢ የሚሆን) ጥያቄ፣ ካጋጠመን ጊዜ የማይሰጥ ችግር ኣንጻር ሲታይ መልሱ ኣቅም ያለው ወገን ቢባል የሚያስኬድ ነው። ምክንያቱ ይህ የጋራ ሃገራዊ ጉዳይ፥ በጋራ ተሳትፎ የሚደረሱ ውሳኔውች መሰረት ኣድርጎ የሚገባደድ ወቅታዊ የቤት ስራ ነውና። በዚህ ጉዳይ ቀደም ብለው ተነሳሽነት የወሰዱ ሓይሎች ካሉ ተሰባስበው ስምሪቱን ቢያጠናክሩ ለተቀላጠፈ ውጤት ማግኘት ኣስተዋጽኦ እንዳለው መገንዘብ ኣይከብድም።

መ/ ማንኛውም ዜጋ – በድርጅት ይካተት ኣይካተት – ይህን ሃገር-ኣድን የሆነው የጋራ የመፍትሄ ኣቅጣጭ እግቡ እንዲደርስ፣ በየኣቅራቢያው በሚገኘው ድርጅት ኣመካይነት ተግባራዊ ኣስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። ትውልድን የሚፈታተን ቀውጢ ወቅት ውስጥ እንገኛለን ስንል ይህንኑ ለጋራ የመጣው ኣደጋ የጋራ መፍትሄ እንደሚሻ በመገንዘብ ነው።

ይህ ኣካሄድ በመጪው ስርዓት ተጠቃሚ የሚሆነውን ወገን ሁሉ ኣሰባስቦና ኣደራጅቶ ኣደጋውን ከቀለበሰ በኋላ፥ የመጪውን ስርዓት ይዘት በጋራ የሚወስንበት የጋራ መድረክ ይሆናል የሚል እምነትም ኣለን።

ለማጠቃለል ያህል፣ ህዝባዊ መሰረት ሳይኖረው፥ ኣንድ የለየለት ኣፋኝ ቡድን መንግስታዊ ስልጣን ይዞ በሃገርና በህዝብ ላይ ገደብ-ኣልባ በደል እየፈፀመ ለ26 ዓመታት ሊዘልቅ የቻለው ህዝብ ስላልተቃወመው ወይም ድርጅቶች ስላልታገሉት ኣይደለም። ህዝቡ ይቃወማል፥ በርካታ ድርጅቶቸም ‘ይታገላሉ’፣ ነገርግን ትግሉ ቅደም-ተከተሉን ኣሳምሮ ሳያስቀምጥና ኣስተባባሪ ማዕከል ሳይፈጥር፥ በተዘበራረቀ መልኩ በመካሄዱ እግቡ ሊደርስ ኣልቻለም። ይህ ግድፈት ኣደጋውን እያባባሰ ጫፍ ላይ በማድረሱ፣ የዚህ ግድፈት ባለቤት ማለትም ያለው ትውልድ ተጠያቂ መሆኑ ባይቀርለትም፥ ኣደጋው ጭራሽ ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆን ዜጋዊ ግዴታው ሊወጣ ይገባል።

የሆነሆኖ ኣሁን ግጭቶች በመላ ሃገሪቱ እየተዛመቱ ናቸው። ህወሓት/ ኢህኣዴግ ከየኣቅጣጫው በሚሰነዘሩት ህዝባዊ ተቃውሞዎችና፣ ከውስጡም በራሱ በቅራኔዎች የተዋከበበት ወቅት እንገኛለን። ይህ ክስተት ወዴት እንደሚያመራ እሩቅ ሳንሄድ ከጎረቤቶቻችን መገንዘብ እንችላለንና ኣደጋው ሳይቀብረን፣ ተባብረን መፍትሄው እውን የምናደርግበት ኣቅጣጫ ተሎ እንያዝ እንላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

ኣረጋዊ በርሄ

ezanareg@hotmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.