አማራን ማን ነው እንዲህ አድርጎ የረገመው? – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በቀደምለት አንድ ያጥወለወለኝን መጥፎ ዜና ከሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን አደመጥኩ፡፡ ዜናው “ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ የሕፃናት የመቀንጨር ችግር በአማራ ክልል አስደንጋጭ በሆነ ደረጃ አሻቅቦ 46.5% ደረሰ!” ይላል፡፡ ከሁለት ሕፃናት አንዱ ማለት ነው፡፡ በሰቆጣ ደሞ ከዚህም የከፋ ሆኖ በ23ቱ ወረዳዎች የሕፃናት የመቀንጨር ችግር ከ60% በላይ ነው ይላል መርዶው፡፡

መቀንጨር ማለት ምን ማለት እንየሆነ የማታውቁ ካላቹህ መቀንጨር ማለት በምግብ እጥረት የተነሣ ሕፃናት ሊያሳዩት የሚገባውን አካላዊ እድገትና የሰውነት ግንባታ ለማግኘት አለመቻል፣ በዚህም ምክንያት በሽታን የመከላከል አቅም ለማጣት፣ ተገቢና ጤናማ የአእምሮ እድገትና ብቃት ለማግኘት አለመቻል ማለት ነው፡፡ በመቀንጨር ችግር የተጎዳ ሕፃን አካሉ ጥንካሬ የማጣት፣ የአእምሮ እድገቱ፣ የማሰብ ችሎታው በእጅጉ የመገደብና ደካማ በመሆን ለትምህርት ቅበላ ብቁ አለመሆንን የመሳሰሉ ቋሚ ወይም ዘላቂ ለሆኑ ችግሮች ይዳረጋል፡፡

ይህ ችግር የተገለጸው ባሕርዳር በጉዳዩ ላይ በተጠራና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተመራ ጉባኤ ላይ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በሰጡት ሰፊና ማስጠንቀቂያ የታከለበት ገለጻ ነው፡፡ ባለሞያዎቹ እነ ዶ/ር ሲሳይ ሲናሞ እንዳሉት “ችግሩ በዚህ ከቀጠለ ክልሉ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ጤናቸው በተቃወሰ፣ የማሰብ ችሎታቸው በተገደበ ወይም በተዳከመ ዜጎች ተሞልቶ ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ በመዳረግ ሕልውናው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል!” ሲሉ በአጽንኦት አስጠንቅቀዋል፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ይሄንን ሕዝብ ለዚህ አሳር ሰቆቃ የዳረገው የወያኔ ባሪያ የሆነው ድርጅቱ በሚፈጽመው ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች መሆኑን ለመሸፋፈን፣ ለመካድ ባሰበ አቀራረብ ቀርቦ በመለፍለፉ የብዙኃን መገናኛው ምን ብሎ ዘገበለት መሰላቹህ “… አቶ ገዱ የችግሩን አሳሳቢነት ደግመው በማንጸባረቅ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እንዲደረግ አጥብቀው አሳስበዋል!” ተብሏል፡፡ ጌቶቹ ገዱን ዲዛይን ሲያደርጉት (ሲተልሙት) እንዲናገር ወደ ተግባር ግን እንዳይቀይር ወይም እንዲተውን አንጅ እንዳይሠራ አድርገው ነው የተለሙት፡፡ ለዚህ ነው በተግባራዊ እንቅስቃሴ የማይደገፍ፣ በተጨባጭ እርምጃ መሬት ላይ የማይታይ ለፕሮፖጋንዳ (ለልፈፋ) ፍጆታ ብቻ የሚናገረውን ነገር ሁሉ የሚናገረው፣ የተለመደና ማለት ስላለበት ብቻ የሚለው፡፡ የወያኔ ሸፍጥ የማይገባቸው ቂላቂል ወገኖች ግን አቶ ገዱ የሚናገራቸውን ለጆሮ የሚጥሙ ነገሮች እየተመለከቱ ገዱን እንደተቆርቋሪ ይቆጥሩታል፡፡ እነኝህ የዋሀን ወገኖቻችን ገዱ የሚናገራቸውን ነገሮች ተግባር ላይ ካለማዋሉ ወይም መሬት ላይ የሚታየው ከሚናገረው በተቃራኒ መሆኑን አስተውለው እውነታው ላይ መድረስ ሲችሉ ይሄንን ሲያደርጉ ግን አይታዩም፡፡ ይሄንን ለማድረግ ንቃተ ሕሊናቸው ስለማይፈቅድላቸው ይሆናል፡፡

እንግዲህ ይታያቹህ! ከላይ በባለሙያዎች ከተጠቀሰው አኀዛዊ መረጃ የተደገፈ መርዶ እንደተረዳቹህት ግማሽ የሚሆነው የአማራ ሕዝብ ስር ለሰደደ ወይም ላጣ ለነጣ ድህነት በመዳረጉ ልጅ ወልዶ የወለዳቸውን ልጆቹን በቂ ምግብ መግቦ ማሳደግ ተስኖት ሕፃናቶቹ በመራባቸው ምክንያት በዚህ ደረጃ በስፋት የመቀንጨር የጤና ቀውስ ችግር ተዳርገዋል፡፡ ይሄ ክፉ ዜና አይዘገንንም? አያጥወለውልም? ብርድ ብርድ አያስብልም? አሁን በእውነት ትንሽ የቀረች እንጥፍጣፊ ወንድነት ብትኖረን ኖሮ ይሄንን ቅስም ሠባሪ መርዶ ሰምተን ምንም እንዳልተፈጠረ አርፈን እንቀመጥ ነበረ?

“ይሄ ችግር በዚህ ከፍተኛ ደረጃ እንዴት በአማራ ሕዝብ ላይ ተለይቶ ሊከሰት ቻለ?” ብለህ ማሰብ አልነበረብህም? ቢገባን ይሄ እኮ በአማራ ሕዝብ ላይ በስውር ከሚፈጸሙ የተለያዩ የዘር ማጥፋት ጥቃቶች ከፈጠራቸው ጉዳቶች ወይም አደጋዎች አንዱ እኮነው! እንዲህ በቁምህ የቀበረህን ጠላት እንዴት ነው ዓይንህን አፍጠህ ዝም ብለህ የምትመለከተው? በሰብእናህ ላይ በዚህ ደረጃ ተጫውቶ፣ አዋርዶ፣ ቅስምህን ሠብሮ፣ መጥጦ ጨረሰህ እኮ! ምን እስክትሆን ነው የምትጠብቀው? ምድረ ቅማላም ከጥጋባቸው የተነሣ የሚያደርጉትን አሳጥቷቸው፣ ወቢ ነፍቷቸው ምድሪቱ ጠባቸው እብደት ላይ ባሉበት ሁኔታ አንተ ለጋ ልጆችህን እንኳ የምታበላው አጥተህ ለእንዲህ ዓይነት ችግር መዳረጋቸውን በጸጋ ተቀብለህ ታሳልፋለህ?? ተከልሎ የተሰጠህ ሀገር እኮ የዘገምተኞች የስንኩሎች ሀገር ሆነልህ እኮ በቃ፡፡ ከእንግዲህ ዘገምተኝነት ስንኩለኝነት መገለጫህ ሆነልህ እኮ!

እንዴት ነው ታዲያ ይሄንን ሰምተህ እንዳልሰማህ የምታልፈው? ከቶ ምንድን ነው የሆንከው ወገኔ? ለዚህ ያበቃህን እንዲህ ዓይነት ጠላትህን ወያኔን አስቀምጠህ በረባ ባልረባ እርስ በእርስህ እየተፋጀህ፣ “ደም ልመልስ!” እያልክ እየተጋደልክ፣ የአጎትና የአክስት ልጅ እየተጠፋፋህ እንድታልቅ ማን ነው የረገመህ? ኧረ ምንድን ነው ጉዱ ወገን???

ይሄና ሌሎች የአሳር ዓይነቶች በዚህ መከረኛ፣ አሳረኛ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ፣ ዘግናኝ ውጤቱ በግልጽ እየታየ ምንም እንዳልተፈጠረ ዓይታቹህ የምታልፉ ይህ አሳረኛ ሕዝብ ለዚህ ደረጃ ያበቃቹህ ምሁራን፣ ነጋድያን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባጠቃላይ የአማራ ልኂቃን ሆይ! ወገናቹህ እንዲህ አሳሩን እየበላ እናንተ የራሳቹህን ኑሮ ስትኖሩ፣ ሕይዎትን ስታጣጥሙ እንዲያው ትንሽም አይተናነቃቹህም? ከወሬ ባለፈ ወገናቹህ እየደረሰበት ያለውን አደጋ የሚመጥን ወይም ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ፣ እንቅስቃሴ ነው ወይ እያደረጋቹህ ያላቹህት???

በፍጹም! እንኳንና እየደረሰበት ያለውን ግፍ ልታስተጋቡለትና ከዚህ ሁሉ አደጋ የሚታደገውን ሥራ ልትሠሩለት ወይም ልትታገሉለት ይቅርና ከነአካቴውስ እየደረሰበት ያለውን አሳር፣ ግፍ፣ ሰቆቃ ለማወቅ እንኳ መቸ ፍላጎቱ አላቹህና? ይሄው በየ የብዙኃን መገናኛው፣ በየመድረኩ እንደምናያቹህ የጠላቱ የወያኔ አርጋጅ አናጓጅ፣ አሟቂ አሸርጋጅ አይደላቹህም ወይ? ይሄ ሕዝብ መዳን ከሌላ ስፍራ ሆኖለት ቀንበሩን ጥሎ የተነሣና ነጻ የወጣ ዕለት እናንተንም የሚምራቹህ ይመስላቹሀል ወይ? እንዲያው ትንሽም እንኳ ባለዕዳነት አይሰማቹህ? እንዲያው ምን ጉዶች ናቹህ? በድህነት አቅሙ ሳይማር አስተምሮ ለዚህ ያበቃቹህ ለእንዲህ ዓይነቱ የጭንቅ ቀን እንድትደርሱለት፣ መላ እንድትሉት አልነረም ወይ?

ድል ለአሳረኛው ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.