የተጋዳላይ/ተጋዳሊቶች ስታይል – መልሶ ልብ ማውለቅ (መስከረም አበራ )

ጥሩ ፖለቲካዊ ስብዕናን “የምበላው አንድ እንጀራ ነው” በሚል ሁኔታ የሚገልፅ ሰው የገዥ ፖርቲ ስራ አስፈፃሚ ሆኖ ፣ “እኔ ፖለቲከኛ እንጅ ሌላ አይደለሁም” ሲላችሁ ከአጃኢብ በቀር ምን ይባላል?

ሃገሩ ደግሞ ፖለቲካ ሁሉ የገዥ ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ የሆነበት፣የተጠያቂነት መነሻም መድረሻምበገዥ ፓርቲ ሂስ ግለሂስ መድረክ ላይ የሚያበቃበት ፣ ሃገርና ገዥፓርቲ አንለያይም ያሉበት ኢትዮጵያ መሆኑ ተስፋ ያስቆርጣል፨

ሃቁ ይህ ስለሆነ ሁለት ሰዓት ካወሩት ውስጥ አንድ ትርጉም ሰጭ ሙሉ አረፍተነገር ለመምዘዝ የሚቸግረው፣ባላቸው ከሞቱ ጀምሮ ፓርላማ ገብተው የማያውቁት ወ/ሮ አዜብ አፋቸውን ሞልተው ፓለቲከኛ ነኝ ይላሉ ፨ በዚሁ በፓለቲከኝነታቸው ሳቢያ የፓርቲ ስራ አስፈፃሚ መሆናቸውን ኮራ ብለው ይናገራሉ ፨

ተጋዳሊት መሆናቸው ከሁሉም ማዕረግ ስለሚገዝፍባቸው ተጋዳሊት እንጅ እመቤት መሆን እንደማይችሉ ፣ ቀዳማዊት እመቤት በሚለው ማዕረግ ያስጠራቸው አንድ “የተረገመ” አጋጣሚ እንደሆነ ተናግረው ፣ ጠመንጃ አንጋችነታቸው የበለጠ እንደሚገልፃቸው አውርተው ሳያበቁ ከጫካ ጀምሮ የመነገድ ልምድ ስለነበራቸው ዛሬ የኢፈርት ነጋድ ራስ ለመሆን እንደበቁ ይናገራሉ፨ ህወሃት ከጫካ ጀምሮ በራሱ አካውንት የሚንቀሳቀስ እንደነበረ ይነግሩንና አካውንት ከሰማይ ዱብ የሚል ይመስል ምንጩን ሳይናገሩ የኢፈርት ምንጩ ይሄ ነው ይላሉ (አዜብ ናቸውና እኛም ብዙ አንጠይቅም፤ ተጋዳሊቷ ዝም ብለው ልክናቸው ብለን መስማት እንቀጥላለን) ፨ወዲያው ደግሞ ህወሃት አልነገደም ፣ህገመንግስትም አልጣሰም ፣ ህወሃት በኤፈርት ላይ የመቆጣጠርም የማስተዳደርም መብት የለውም ይህ መደበላለቅ የለበትም ይላሉ ፨ (የኢፈርት ስራ አፈፃፀም ሪፖርት አስር ጊዜ ለሚያነሱት ባላቸው መለስ ቤቱ ሳይቀር እንደሚቀርብለት ኤርሚያስ ለገሰ ፅፎ አላነበብንም አሉ)፨ በሃገራችን ፍትህ ስርአት ላይ የህወሃት እጅ እንደሌለበት ሲያስረዱ ኢፈርት በሃገር ውስጥም በውጭ ሃገርም ተከሶ እንደሚያውቅ ይነግሩናል ፨ (ከላይ ህወሃት እና ኢፈርት ፀብ ወይም ዝምድና እንደሌላቸው የተነገረንን አትርሱ ። የኢፈርት መከሰስ ለህወሃት በፍትህ ስርዓት ጣልቃ አለመግባት ማስረጃ ሆኖ ሲመጣ መቼም እኛ ነፈዝ አይደለን? “እውነትም” ማለታችን አይቀር¡ )

ኢፈርትን የፖለቲካ አመራር ነው የሚመራው የሚባለው ልክ እንዳልሆነ ይነግሩናል ተጋዳሊት አዜብ ፤ ኤርሚያስ ለገሰ ደግሞ የከዜብ ባል መለስ ልማታዊ መንግስት ለመመስረት የግድ ኢፈርት በፖለቲካ አመራሩ መመራት እንዳለበት የሚያደርግ አካሄድ አውጥቶ በየ ካምፓኒው ቢያንስ አንድ የህወሃት ባለስልጣን በባለ አክሲዎንነት ገብቶ ልማቱን እንደሚያሳልጥ በድንቅ ማስረጃ አሳይቶናል(በዚህ መሃል የተጋዳላይ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ ሚስት እንዴት “የልማቱ ተጠቃሚ” እንደሆነች እያሳቀን ነግሮናል) ! የኢፈርት አስተናባሪ የሆንኩትም ካምፓኒዎቹ ድህነትን ሲታገሉ ላግዝ ብየ ቀለብ ተቆርጦልኝ ነው (CEO ደሞዝ ለማደር ነው) ብለውናል፨

ተጋዳሊቷ ይቀጥላሉ እኔም እንጀራ አልነገድኩም ፣ ወደ ቅመማ ቅመም ሽቀጣም ዞር ብየ አላውቅም ፣ የፎቁን ቢዝነስም አላውቀውም፣ ቤትም አልሰራሁም ምስጋና ይግባውና ሙክታር ቤቱን ለቆልኝ ነው የምኖረው ፣ ከዛ በፊት (ነው በሃላ?) ደግሞ ሰው ጋ ተጠግቸም ኖሬ አውቃለሁ ይላሉ፨ ሃብት አላት ለሚለኝ መጥቶ ያሳየኝና አወርሰዋለሁ፣ ለምን ጋዜጠኛ ሁሉ አስተባብሮ እንዲወረስ አያደርግም ብለዋል (እዚህ ላይ ፈገግ ብለን ነበር¡¡¡) ውልና ማስረጃ የማያውቀው ንብረት እንዴት አለ ይባላል ሲሉ ያክላሉ፨ (የሃብት መዝገብ ማሌዥያ ባንክ ሳይሆን ውልና ማስረጃ የሚከማች የሚመስለን እኛ ቂሎች ደግሞ ያው በመስማማት እራሳችንን መወዝወዛችን ነው ¡ ) ፅድት ያልኩ መሆኔን ስለማውቅ ልጣራም ዝግጁነኝ ያሉት ተጋዳሊት አዜብ እንዴውም ትግራይ ነው የኔ ኮንስቲቲዎንሲ እዛ ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር የለም ይላሉ ሃያ ምናምን አመት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተቀመጡት ሰውየ ሚስት በመሆናቸው ቀዳማዊት አመቤት ተብለው ሲጠሩ የኖሩ ሴትዮ!!

ፅድት ማለታቸውን በዚህ መልክ “ካፋቸው ማር ጠብ” እያለ አስረድተው የጨረሱት ሴትዮ ስልጣን ላይ መቆየት መዛግን እንደሚያመጣ ሲነግሩን መቃብር ከስልጣን የለያቸው የመለስ ሚስት ሳይሆን የባለ አምስት አመቱ ፕሬዚደንት የማንዴላ ሚስት መስለው ነው(ካላፈሩ አይቀር እንዲህ ነው የምን መቅለስለስ?¡)

መለስን ከማንም ጋር ማወዳደር አልፈልግም ይቅርታ ስህተትም ይመስለኛል ሲሉ የመለስ መሞት የሴትዮዋ ቀዳማዊት እመቤትነት ማብቃት እንዳጎደላት ከንግግሯ የምታስታውቀው ሚሚ ጣልቃ ገብታ እሳቸው ፊት ኪራይ ሰብሳቢና ሙሰኛ አይቆምም ነበር ትላለች ፤ ተጋዳሊት አዜብ እሱ መረጃ የለኝም ብሎ ሙሰኛን ዝም አይልም መረጃ ቢያጣ የፖለቲካ እርምጃ ይወስዳል ስትል የጠገቡ አሽከሮቹን ገለል የሚያደርግበትን የሴራ መንገድ ከጉብዝና እንድንፅፍለት እንደ አቅሚቲ ትጥራለች ! የመለስ ጥንካሬ የራሱ ዲሲፕሊን ነው ለቤተሰቦቹ ለዝርያም ይህን አደረገ አይባልም ስትል ስለ ቱጃሩ ወንድሙ ሲጠየቅ አስራስምንት አመት ስላለፈው ራሱን ጠይቁ ስለማለቱ ያነበብኩት ትዝ አለኝ ፣ሳቄ በረታ ! መለስ ለገበሬው ምርታማነት ብቻ ሳይሆን ስለ ጤናው ፣ስለ አርብቶ አየሩ ልጆች ት/ቤት ስለ ከተሜው ኮንዶሚኒየም (ይች እውነት ናት ቤት የእግዜር ኮንዶሚኒየም የ……ን አስተርታን የለ?! )

መጥኔ ማንም ለሚፈናጠጥባት ለሃገሬ !!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.