ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለዛ ድንጋይ ነህ ተብለህ ትወረወራለህ!!! ( ወይንሸት ሞላ )

ይህን ነገር በውስጤ መመላለስ ከጀመረ የሰነበተ ቢሆንም አሁን ግን እንድናገረው በግሌ ያስገደደኝ ነገር ይህ በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ እነሱ አሁን እኔም የምስማማበት “የሁለት ህዝቦች” ታሪክ ነው::
አንደኛ ደረጃ ዜጋ እነሱ
ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ እኛ!!!

አሁን በኢትዬጵያዊ ጭዋነታችን እና የህዝቡ ባህርይ ተደምሮ ነገሮችን ሁሉ በትዝብት በመመልከት በማህበረሰባችን ውስጥም “እኛ” እና “እነሱ” የሚል ትልቅ ግንብ ተገንብቷል:: ይህ መንገድ የት እንደሚያደርሰን እንኳን አዋቂ የስድስት አመት ልጅ ቢጠየቅ የሚመጣውን አስቦ አይኑን ይጨፍናል:: በሌሎች ሀገሮች የምናየው የ”እነሱ” ና “እኛ” የሚል ሰጥአገባ እና እልቂት የምናይበት ጊዜ እሩቅ አይመስለኝም::

የእኔ እናት ኑሮ ተራራ ሆኖባት ለስኳር እና ዘይት የምትሰለፈው ከለሊቱ 11 ሰዓት ነው:: በወሬዎቿ መሀል ውሃ ከሄደች ነገ ሃሙስ ሳምንት አለፋት የሚል እሮሮ መስማት የተለመደ ነው:: መብራት አሁን ሄደ አሁን መጣ እያለች ስታወራ መስማት ጀሮዬን የሚያሰለቸኝ ወሬ ነው:: እስከዛሬ ብዙ የማያልፉ ቀኖች የማይነጉ ለሊቶች … አልፈው እዚህ ደረስን:: አሁን እዬዬም ሲደላ ነው የሚባልበት ጊዜ መጥቷል ከትግራይ ክልል ውጭ ወጣት የወለደች እናት የሚያሳስባት ይህ የኑሮ ውጣውረድ ሳይሆን “ልጄ ከአጋዚ ጥይት ተርፎ ቤቱ ገባ ይሆን?” የሚል ነው:: እጅግ በጣም አስከፊ ግዜ በኢትዬጵያ ለሁሉም እናቶች ሆኗል::

ከአለም ስምንተኛ ነው የተባለለት የአዲግራቱ መስቀል ሲገርመን ዘንድሮም በመቀሌ ሌላ ተሰርቶ “ኑ መስቀልን እናክብር” የሚል ጥሪ ለትግራይ ልጆችና ለጎብኝዎች እየተደረገ ነው:: በያዝነው ወር መቀሌ “ከሲጋራ ነፃ” እና “አረንጏዴ ከተማ” ተባለች የሚል ወሬም ሚድያውን ተቆጣጥሮ የነበረ ዜና ነው:: እዚ መንደር ማረሚያ ቤት እዛ መንደር የመኪና መገጣጠምያ ተመረቀ የሚል በአንድ ቀን በኢቢሲ ዜና ተመስገን ያነበበት ቀንም እሩቅ አይመስለኝም:: ተመሳሳይ ዜናዎችም የትየለሌ ናቸው:: በሚልዬኖች ተበጅቶለት በሚልንየም አዳራሽ የሚከበረው የአሸንዳ በአልም ያስተዛዝባል:: እጅግ ብዙ ነገር መናገር ይቻላል:: አለምም የሚያውቀው ሀቅ ነው:: ህዝባችንም ለዘብተኛ አመለካከቱ ይዞት ዝም አለ እንጂ “እኛ እና እነሱ” የሚል ግንብ ከገነባ አመታት አልፈዋል::

እኔ አሁን መናገር የምፈልገው ሞኝ ቢያስመስለኝም የትግራይ ህዝብ እራሱ ይህን በልጆቹ የሚፈፀም በደል በቃ ሊል ይገባል:: አንድም እናት ትሁን የሚመጣውን እልቂት አገናዝባ ባጠባቻቸው ጡቶቿ ልጆቻን በቃ ማለት አለባት:: የትግራይ አክቲቪስቶች የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ፖለቲከኞች በህዝባችን ላይ የተጠመደውን ቦንብ ማክሸፍ አለባችሁ:: 15 ሆናችሁም ቢሆን ልጆቻችሁን በቃ ብላችሁ ተቃውሞ ማቅረብ አለባችሁ:: የሚመጣውን እልቂት አስባችሁ ይህ በስማችን ሊደረግ አይገባም ብላችሁ መነሳት አለባችሁ!!! ምንም ማድበስበስ በማያስፈልገው ሁኔታ መጭውንም ቢሆን ፈርታችሁ ለራሳችሁ እራሳችሁ ጥብቅና መቆም አለባችሁ:: በሀገራችን ዝምታ እንደ መስማማት እንደሚቆጠር ትዘነጉታላችሁ ብየ አላስብም::

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን መጭዋ ኢትዬጵያን ማሰብ ለኔ ከብዶኛል:: ይህ በደል ያንገፈገፈው ህዝብም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ… ብሎ እየተነሳ እንዳሆነ የባለፈው አመትን ተቃውሞ እንደማሳያ መውሰድ እንችላለን:: የማያባራ እልቂት እንደሚፈጠር መገመት ቀላል ነው:: ከዚሁሉ በፊት ግን ይህ የትግራይ ህዝብ በእነዚህ አረመኔዎች አይወከልም ከምንለው ሀሳብ አንድ ደረጃ መሬት ወርዳችሁ ልጆቻችሁን በቃ በሉ:: ይህን የምለው ሞኝ ስለሆንኩ አይደለም ግን ይህን ሳልናገር ያ የምፈራው ጊዜ እንዳይመጣ በማሰብ ነው::

የትግራይ ህዝብ ልጆቹን በቃ ይበል ስለራሱ ጥብቅና ይቁም!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.