የፖሊቲካ ጥበብ ባገራችን አብቦ ሊያፈራ? ሲያምረን ይቅር (ለውይይት መነሻ) – ከባይሳ ዋቅ -ወያ

መግቢያ፣

ከፖሊቲካ ጋር የተዋወቅኩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኜ የዩኒቬርስቲ ሪቮዎች እየመጡ ይቀሰቅሱን በነበረበት ወቅት ነበር። ያኔ፣ የፖሊቲካን ምንነት በቅጡ ያስረዳን ባይኖርም፣ ወጣ ብለን በድንጋይ የኦርቢስን ህንጻና አንበሳ አውቶብስን መደብደft የሚጠበቅብንን የፖሊቲካ ድርሻና ኃላፊነት የተወጣን ይመስለኝ ነበር። ዋናው ዓላማ ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን ማውረድና መሬትን ላራሹ ማድረግ ከሚለው ባሻገር ለምን ንጉሱ መውረድ አለባቸው፣ በማንስ ይተካሉ፣ መሬትስ ለምን ካባለመሬቶቹ ተወስዶ ለአራሹ መሰጠት አለበት የሚለውን በዚያ በጨቅላ ዕድሜያችንና ያልበሰለ ጭንቅላት፣ እንኳን ልናጣጥመው ይቅርና በደንብ ለማላመጥ አልቻልንም። ንጉሱ ወርደውና ደርግ ተክቷቸው ገና ውዥንብር ውስጥ እያለን ተማሪውን ይዘውሩ የነበሩና በዕውቀታቸውና ብስለታቸው በጣም ግዙፍ የሆኑ፣ እንኳን የኢትዮጵያን ይቅርና የአህጉራችንን ችግር ይፈታሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩ አንጋፋ ምሁራን ለሁለት ተከፍለው የቃላት ብቻ ሳይሆን የተኩስ ልውውጥ ጀመሩ። የደርግ ጡንቻም ታክሎበት ከሁለቱም ወገን ያንድ ትውልድ ምሁርና ነቃ ያለው ወጣት አለቀ።

 

የሚያሳዝነው ግን የነዚህ የመጀመርያው ለውጥ ፈላጊ ትውልድ ዓላማቸውን እንኳን በቅጡ በሕዝባችን ጭንቅላት ሳያሰርጹ በጅምላ ማለቅ ሳይሆን፣ ከዚያ መዓት በተዓምር የተረፍነው ዕድለኛ ትውልድ ዛሬ ከአምስት ምዕት ዓመት በኋላ ከነሱ ስህተት ተምረን ልዩነቶቻችንን አቻችለን በሰላም ለህዝባችን የተሻለ ነገን ዕውን ለማድረግ የሚያስችለንን የፖሊቲካን ጨዋታን ሕግ ላለመማር ወስነን፣ እንደ አንጋፋው ትውልድ እኛም ወደ ጥፋት እያመራን ነው። በተለይ በዲያስፖራ መካከል የሚካሄደውን መርዘኛ የሆነ ውይይት አይሉት ንትርክ ሳስብ፣ እንደው ውጭ አገር መሆኑ በጀ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥማ ቢሆን ኖሮ እንገዳደል ነበር ብዬ አስባለሁ። ግን ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? ሰው እንዴት ከስህተት አይማርም? ያለፈው ትውልድ የሰራውም ስህተት እንዳይደገምና፣ከተቻለ በቀና መንፈስ ተወያይተን አለመግባባቶቻችንን በጥይት ሳይሆን በሰላም ለመፍታት በሚያስችሉን ነጥቦች ላይ ለመስማማት፣ ካልሆነም ደግሞ ባለመስማማታችን ተስማምተን በሰላም ወደፊት የምንራመድበትን ጎዳን ለመቀየስ ለምን ሳይቻለን ቀረ? ለነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የለኝም፣ ግን ከችግሮቹ እንዳንላቀቅ ያደረጉንን ምክንያቶች የሚመስሉኝንና በበኩሌ የደረሰኩባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ማንሳት እፈልጋለሁ። ነጥቦቹ የራሴ ግምቶች እንጂ የሳይንሳዊ ጥናት ውጤት ስላልሆኑ ትክክል ነህ ወይም አይደለህም ሳትሉ በዚህ ሃሳብ ዙርያ “ሊሆን ይችላል” ወይም “መደረግ አለበት” የሚል ሃሳብ ካላችሁ እንድትሰነዝሩ ከወድሁ አሳስባለሁ። የያዘውን የወረወረ ፈሪ አይባልም አይደል ከነተረቱ!

 

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁለቱ ድርጅቶች (መኢሶንና ኢህአፓ) መካከል የነበረው ውጊያ በቃላት ደረጃ እያለ ነበር ለትምህርት ወደ ሶቪዬት ህብረት ከብዙ ጓደኞቼ ጋር ያቀናነው። ገና ሞስኮ ደርሰን ከአይሮፕላን እንደወረድን የበረዶውን የአወራረድ ስልት እንኳ አድንቀን ሳናበቃ፣ የሁለቱ ተቀናቃኝ ftድን ደጋፊዎች ተቀራምተውን በሁለት ጎራ ተከፋፍለን ኑሮ ጀመርን። ከዚያ በኋላማ በተለያየ ftድን ውስጥ ሆነን፣ “የኔ የተማሪ ማህበር ካንተ የተማሪ ማህበር የተሻለ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቆረቆራል“ የሚል መጨረሻው የማይታወቅ አዟሪት ውስጥ ገባን። ገና በአስራዎቹ ውስጥ የነበርን ለዕውነተኛ ፖሊቲካ ያልደረስን ጥሬ ልጆች ስለነበርን፣ የተማሩት አንጋፋ ፖሊቲከኞች ያደረጉትን እየኮረጅን እኛም ባቅሚቲ፣ መጣላት ብቻ ሳይሆን አብሮ አደጎቻችንና የትምህርት ቤት ጓደኞቻችንን ሳይቀር፣ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን በጅምላ መጥላት ጀመርን። አብረን አንበላም፣ አንጠጣም፣ አንነጋገርም፣ ሌላው ወገን እንደ ጠላት ስለተቆጠረ የሴት ጓደኛ እንኳ ስንመርጥ ከዚሁ ከማህበራችን ውስጥ እንጂ ወደ “ጠላት” ሰፈር መሄድ ከቶውንም አናስብም ነበር። ደግነቱ ውጭ አገር በመሆኑና የነበርንበት አገር ህግና ሥርዓት የማያላወላዳ ሆኖብን ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩት ጓደኞቻችን በየአደባባዩ ይጋደሉ እንደነበሩት ሁሉ እኛም በያለንበት እንተላለቅ ነበር። እንኳን እኛ ጨቅላዎች ይቅርና ብዙ ዓመት ውጭ አገር የኖሩና የላቀ ዕውቀት የነበራቸው የፖሊቲካ ድርጅቶች መሪዎቻችን እንኳ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ላገራቸው አንድ ላይ መቆ ም ያልቻሉትን ላገራቸው አንድ ላይ መቆም ስላልቻሉ የኛ ደርሶ መጣላት አያስገርምም።

 

ባገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር፣ያኔም ሆነ ዛሬ፣ መሰረታዊው ጥላችን የሃሳብ ልዩነት ሳይሆን፣ የሃሳብ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ፣ ”የኔ ሃሳብ ግን ካንተ የተሻለና ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕድገት ብቸኛ አማራጭ ነው” የሚለው ላይ ነው። የሚያሳዝነው ግን ዛሬም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ካለፈው ስህተታችን እንኳ መማር አቅቶን ወያኔን ከመጥላት ባሻገር በአንዲት ነጥብ እንኳ መስማማት አቅቶን በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊቲካና ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ፈጥረን “የኔ ሃሳብ ካንተ ይሻላል” “አስተሳሰቤን ካልተቀበልህ ግን ጠላቴ ነህ” “ጠላቴ እስከሆንክ ድረስ ደግሞ አብረን መኖር አንችልም” በሚል ልክፍት እንደተያዝን ቀርተናል። የታሪክ ሂደት አይታወቅምና፣ ዛሬ ወያኔ በሆነ ምክንያት ድንገት ከሥልጣን ቢወርድ፣ በሳባዎቹ ውስጥ በተለያዩ ድርጅቶች መካከል ባገራችን የተከሰተው ትርጉም የለሽ መተላለቅ ዛሬ ላለመደገሙ ዋስትና የለንም ባይ ነኝ።

 

ለምንድነው ግን የፖሊቲካ ጥበብ ዕውቀታችን እንደዚህ ቀጭጮ የቀረው?

 

ይህ ፈረንጆች የሚሉት የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ዓይነት ነው። በትምህርት ገበታ ላይ እንደማንኛውም ተማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተወዳደርንባቸው ቦታዎች ሁሉ እያሸነፍንና አንዳንዴም ከሌሎቹ ሁሉ ልቀን እየተገኘን ለምን የፖሊቲካ ጥበft ዘንድ ስንደርስ ወደ ኋላ እንደምንቀር አልገባ ካሉኝ ምድራዊ ጥያቄዎች አንዱ ነው። ሁላችንም የምንስማማበት ባይሆንም፣ በኔ ግምት ግን የሚከተሉት ዕውኔታዎች ለፖሊቲካ ጥበብ ዕውቀታችን አለመዳበር አስተዋጽዖ አድርጓል ብዬ እገምታለሁ።

 

አንደኛ፣ የሰው ልጅ ዕውቀትን የሚቀስመው ካካባቢው ነው፣ እኛ ግን ስለራሳችን ስለህዝባችን አኗኗራችንና ታሪካችን ከሌሎች ህዝቦች ሁሉ የተለየን ወይም የተሻልን ዘር ነን ብለን ስለምናስብ ካካባቢያችን ወይም ከሌሎች ህዝቦች የመማር ፍላጎታችን በጣም ውስን ነው። ይህም ማለት ለበጎም ሆነ ለክፉ ከሌላ አገር የባህልና የአኗኗር ዘይቤ ጋር በቅርብ ለማየትና ብሎም ለመደባለቅ ፍላጎቱ የለንም። ኢትዮጵያውያን በየሄድንበት ሁሉ ከእንጀራና ወጥ የተሻለ ምግብ ዚህ ምድር ያለ ስለማይመስለን ቋንጣና ድርቆሽ ይዘን እንዞራለን። የትም ይሁን የት በተቻለ መጠን የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ፈልገን አምሮታችንን እንወጣለን እንጂ ያለንበትንን አገር የባህል ምግብ በምንም ተዓምር አንሞክራትም። አትሌቶቻችን እንኳ ሳይቀር ለውድድር ወደ ውጭ አገር ሲሄዱ የሚችሉትን ያህል ቆሎ፣ ጩኮና በሶ ይዘው እንደሚሄዱ አንድ አሠልጣኝ የነገረኝ ትዝ አለኝ። በውጭ አገር በምንኖርበትና በምንማርበት አገር በዕረፍት ጊዜያችን ከዩኒቬርሲቲያችን ቅጥር ግቢ ውጭ የሃበሻ ሬስቶራንቶችን ማሳደድ እንጂ በከተማው ያሉትን የታሪክ ሙዚዬሞች ሄዶ ግብኝቶ ያካባቢውን ታሪክን ማወቅ ለብዙዎቻችን የጠፈር ያህል ይርቅብናል። ግን ከከተማ ከተማ መቶ ኪሎ ሜትር እየነዳን የአዛኝቷን ማህበር ወይም የልጆች ክርስትና ድግስ ላይ ለመገኘት

ጊዜም ገንዘብም አያጥረንም። በፈረንጆቹ ቋንቋ we are full of ourselves የሚሉት መሆኑ ነው!

 

ባካባቢያችን የምናየውንና የምንሰማውን ከጊዜው ጋር አዛምዶ የዕድገት ተጠቃሚ ከመሆን፣ ካስፈለገም እስከ ብዙ ሺ ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን፣ ከሁሉ በፊት የሰለጠንና ቀሪውን የዓለምን ሕዝብ ጆሮውን ይዘን ሥልጣኔን ያስተማርን መሆናችንን ዓለም ህዝብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፥ የሶስት ሺህ ዓመት ሥልጣኔ ነበረን፣ የራሳችን ፊደል ያለን የአክሱምና ላሊበላ እንዲሁም የፋሲል ግንቦች ባለቤት ነን የሚለውና በቅኝ ገዥዎች ያልተገዛን፣ አውሮፓውያንን በጦር ሜዳ ያሸነፍን ወዘተ የሚለው “ታሪካችን” የሌሎችን አስተሳሰብና የዕድገት ደረጃ እናዳናይና ከነሱም እንዳንማር አርጎናል። ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ በደንብ አጣርተን እንዳናይ ዓይናችንን ጨፍነን፣ ያለፈውን እንጂ የወደፊቱን የማንኖር ህዝቦች ነን። ታሪክ የሌለው ወይንም ፈሪ ነኝ የሚል ሕዝብ ያለ ይመስል፣ በጀግንነታችን በምድሪቷ ላይ ብቸኛ እንደሆንንና ራሳችንን ከሁሉ በላይ አድርገን እናያለን። በኔ ግምት ግን፣ ያለፈው የሶስት ሺህ ዓመት ታሪካችን እንድሁ ለኅሊና መሸንገያ ይጠቅም እንደሆን እንጂ፣ ለዛሬው ችግራችን ምንም ዓይነት መፍትሄ አይሰጥም። ከሁለት መቶ ዓመት ያነሰ ዕድሜ ያላትንና በምንም መንገድ “በጥንታዊነት” የማትታማዋ አሜሪካ፣ ዛሬ በዓለማችን የበላይ ገዢ ሆና፣ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላቸውንና የሥልጣኔ ባለቤት ነበርን ብለው የሚኩራሩትን እነ ግሪክና ኢትዮጵያን የመሳሰሉትን አገራት ሳይቀር፣ ሲራft የምትመግባቸው፣ ሌሎችም የተጣሉ አገራትን የምታስታርቅ፣ ተስማምተው የሚኖሩትን ደግሞ ለማጣላት ጉልበቱና ጥበft ያላት፣ ተረጋግቶ የሚኖረውን አገር ደግሞ ለመበታተንና የማይጥማትን ያገር መሪ ቀፍድዶ ለማሰር ወይም ከሥልጣን ለማውረድ የምትችል ኃያል አገር ሆና ስናያት የሶስት ሺህ ዓመት ታሪካችን የዛሬውን ችግራችንን ለመፍታት ብዙም እንዳልጠቀመን መገንዘብ ነበረብን ።

 

ሁለተኛ፣ ከየት እንደወረስነው ባይታወቅም፣ በፖሊቲካ ባህላችን መሰረት፣ ጠላትን ማድቀቅና ማዋረድ እንጂ ማሸነፍ ብቻ በቂ መስሎ አይታየንም። ጠላታችንን መግደል ብቻ ሳይሆን መቀበሩንም በዓይናችን ካላየን ስንባንን የምናድር ይመስለናል። ወያኔ በቅንጅት አባላት ላይ የወሰደው እርምጃ አንዱ ምሳሌ ነው። ማሸነፍ ብቻ በቂ ስላልመሰለው፣ የቅንጅት አባላትን በጅምላ የዘር ማጥፋት ወንጅሎ ካሰራቸው በኋላ፣ “ይቅርታ ጠይቁኝና እፈታችኋለሁ” ብሎ አስገድዶ በማስፈረም፣ አካላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ጉዳቶችን አድርሶባቸዋል። በቅርft እነ በቀለ ገርባንና መረራ ጉዲናን “የተለየ አስተሳሰብ” ስላላቸው ብቻ ያለምንም ወንጀል ቁጥጥር ሥር ማዋሉ ሳያንስ፣ በአደባባይ ለማዋረድና ለማሳነስ፣ ብሎም ሞራላቸውን ለመስበር፣ በብረት ሰንሰለት ጠፍንጎአቸው ለፍርድ ሲያቀርባቸው በቴሌቪዥን ለህዝብ ማሳየቱ ሌላው ተጨባጭ ምሳሌ ነው። ሲወርድ ሲዋረድ ተወራርሶ ከደረሰን የፊውዳሉ ባህልም እንደምንረዳው፣ ተሸናፊ ሆኖ የመዋረድ ጽዋን ላለመቅመስ ሲሉ ነው ዜጎች በሆነ ውድድር “ሲሸነፉ”፣ አሸናፊው እጅ ገብቶ ከመዋረድ፣ እንዳቅሙ የተገኘውን መሳርያ ይዞ፣ “ማሸነፍ እንኳ ባልችል የክብር ሞት እሞታለሁ” ብለው የሚሸፍቱት። ዛሬ በተቃዋሚ ድርጅቶችና በኢህአዴግ መሃል ወይም በራሳቸው በተቃዋሚ ድርጅቶች ራሳቸው ውስጥ የተሸናፊን ሃሳብ ማስተናገድ ስለማይቻል፣ ተሸናፊው ftድን በአካልም ሆነ በመንፈስ መሸፈት አለበት። አለበለዚያ፣ በአሸናፊው እጅ ወድቆ ውርደትን መከናነብ ነው። አሸናፊና ተሸናፊ ልዩነታቸውን አቻችለው አብረው በሰላም መኖር የማይችሉበት እጅግ ኋላ ቀር የሆነ ህብረተሰብ!

 

ከዚሁ ጋር ሊያያዝ የሚችል አንድ መለያ ባህሪያችን ሆኖ ያስተዋልኩት፣ በማንኛውም ውድድርና ፉክክር ላይ ጠላትን አሸንፎ ሁሉንም መጠቅለል እንጂ ለተሸናፊው ትንሽ እንኳ የማስቀረት ልምድ የለንም። ከተሸነፍክ ሁሉንም ማጣት አለብህ፣ የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ ለዚህ ተገቢ ምሳሌ ነው። አሸናፊው ፓርቲ 50.1% ድምጽ ቢያገኝ፣ የተቀረውንም 49.9% ድምጽ ጠቅልሎ ይወስዳል እንጂ ለተቃዋሚው ፓርቲ አያስቀርም። ስለዚህ ኢህአዴግ በፓርላማው ዉስጥ 100% መቀመጫ አገኘ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መረጠው ማለት ሳይሆን 50.1% ድምጽ አገኘ ማለት ነው። ያውም በሱ አቆጣጠር መሰረት!

 

ሶስተኛ፣ በመሰረቱ ፖሊቲካ ጥበብ ነው፣ ትልቁ መገለጫው፣ እንደ ኃይማኖት ተመሳሳይ ዕምነት ያላቸውን ምዕመናን ባንድ ጣራ ሥር ሰብስቦ መስበክ ሳይሆን፣ የማይመሳሰሉ ወይም የማይቀራረft አስተሳሰቦች ያላቸውን ዜጎች አንድ ላይ አቀራርቦ ሊግባft በሚችሉበት መለስተኛ አቋም ላይ አስማማቶ አንድን አገር በሰላም መምራት ማለት ነው። ፖሊቲካ ከመማር የሚገኝ ጥበብ ነው። የዚህ ተቃራኒ የሆነውና በተፈጥሮ ሊገኝ የሚችል ግን፣ ከፖሊቲካ ጋር እያማታን የምንጠቀመው “ነገር” የሚባለውን ነው። ባገራችን ከመቼውም ቦታ ይልቅ ሁለቱም ተማተውብናል። አንድ ያገር መሪ ለምሳሌ ጥያቄዎችን በጥያቄ ወድያውኑ ለመመለስ ከቻለና፣ ወይም ደግሞ በመልሱ፣ ጠያቂውን ጋዘጤኛ ወይም ግለሰብ ካሳፈረ ወይም ካሳቀበት፣ “እሱ እኮ አይቻልም፣ አፍ አፉን ነው ያለው፣ ልክ ልኩን ነው የነገረው“ ተብሎ እንደ ትልቅ ፖሊቲከኛ ይወራለታል። ባገራችን ተነስተው ከነበሩት ”ፖሊቲከኞች“ መካከል በኔ ግምት መለስ ዜናዊ በዚህ ተራ ይመደባል። ብዙውን ጊዜ ለሚቀርftለት ጥያቄ መልስ ሲመልስ በጣም ፈጣን ነው፥ ፈጣን መልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ በመልሱ ጠያቂዎችን አሳንሶ ወይም አስቆባቸው ለማለፍ ይሞክር ነበር። በዚህም ፍራቻ ምክንያት፣ ብዙ ጋዜጤኞች ”ከሚሳቅብን “ ብለው ዳግመኛ መለስን ጋዜጣዊ ጥያቄ ለማቅረብ አይደፍሩም። ይህ በኔ ግምት የመለስን ”ነገረኝነት“ እንጂ ፖሊቲከኝነትን አያሳይም። መለስ ፖሊቲከኛ ቢሆን ኖሮ ከላይ እንዳልኩት ባገሪቷ ያሉትን የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸውን የፖሊቲካ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን እንደ ጠላት ከማየት ይልቅ፣ እንደ ተቃዋሚ ኃይል ቆጥሮአቸው፣ የተለይ ሃሳብ በማቅረባቸው እንደ ጠላት ከማየትም አልፎ እንደወንጀለኛ ቆጥሮአቸው ፍርድ ቤት ከማቅረብ፣ ከነልዩነታቸው አቅፎአቸው ላገሪቷ ዕድገት አብሮ ይሰራ ነበር። መለስ ፖሊቲከኛ ያልሆነውን ያህል ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶችም ልክ እንደ እሱ፣ በየድርጅቶቻቸው ውስጥ በየጊዜው የሚነሳውን “የተለየ ሃሳብን” አስተናግዶ አብሮ መጓዝን የማይችሉ መሆናቸውን በተግባር እያየነው ነው። ከነዚህ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ዛሬ አንዱ ሥልጣን ላይ ቢወጣ፣ የተለየ አስተሳሰብ ካላቸው ሌሎች ድርጅቶች ጋር “ልዩነትን አቻችሎ” በህብረት ይጓዛል የሚል ቅንጣት ታህል እምነት የለኝም።

 

አራተኛ፣ በኔ ግምት፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከሰማንያ በላይ ከሆኑት ብሄሮች መካከል በህብረተሰብ የዕድገት ሂደት ውስጥ ከጋርዮሽ አስተዳደር አልፎ ባንድ የተማከለ መንግሥታዊ አስተዳደር ሥር የነበረ አለ ብዬ መቀበል ይከብደኛል። ይህም በመሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር/ብሄረሰብ የየራሱን ጥቃቂን ማህበረሰብ ይዞ ኖረ እንጂ የተለያዩ ማህበረሰቦችን ወይም ጥቃቅን ጎሳዎችን አንድ ላይ አቅፎ ያኖረ ማዕከላዊ አስተዳደር አልነበረም። ዛሬ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የወላይታ፣ የትግራይ ወይም የሲዳማ ወዘተ እያልን የምንጠራቸው ህዝቦች፣ እንደሚወራው፣ እንኳን ባንድ ኢትዮጵያ ጥላ ሥር ይቅርና ለየራሳቸው እንኳ አንድ የተማከለ የአማራ፣ የኦሮሞ ወይም የወላይታ መንግሥት አልነበራቸውም። የአማራዎቹ መሳፍንት በየሰፈሩ ንጉሥ ወይም መስፍን ነን ብለው ይገዙ የነበሩትን ያህል የኦሮሞዎችም በየቦታው በተለያዩ አባ ገዳዎች ይተዳደሩ ነበር። በኔ ግምት የዛሬዋ

ኢትዮጵያ፣ የህብረተሰብ ዕድገትን ህግ ተከትላ “መንግሥት” – state – የሆነች አይመስለኝም። በመሆኑም እንኳን ባገር ደረጃ ባንድ የተማከለ መንግሥት መተዳደር ይቅርና በጥቃቅን ftድኖች መካከል እንኳ አንድ ድርጅት ፈጥሮ ልዩነትን አቻችሎ መኖር አልተቻለም። የተማከለና “የልዩነቶች ስብስብ” በሆነ ድርጅት ውስጥ ከመታቀፍ፣ “የግል የሆነ“ የተለየ ሃሳብን ይዞ “የግል የሆነ” የተለየ ድርጅት መፍጠር የሚቀለን በዚሁ ምክንያት ይመስለኛል።

 

አምስተኛ፣ ሌላው ለፖሊቲካ ጥበብ ባገራችን እንዳያብብ አስተዋጽዎ ያደረገውና በማድረግም ላይ ያለው የሁሉም የተማረው ኢትዮጵያዊ ፖሊቲከኛ መሆን ወይም ለመሆን መሞከር ነው። በተለይ በስድሳዎቹና ሳባዎቹ ውስጥ ምንም ዓይነት የፖሊቲካ ፓርቲ ባልነበረበት ዘመን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ከፊውዳሊዝም ጭቆና ለማላቀቅና ለዲሞክራሲ መሰረት ለመጣል የግንባር ቀደሙን ሚና መጫወት ከተማረው ዜጋ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ተደርጎ በመወሰዱ፣ ተማሪው በሙሉ ፖሊቲከኛ መሆን፣ ወይንም ደግሞ የሆነ መስሎ መገኘት ነበረበት። በዛሬ ጊዜም፣ ወያኔ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ኢትዮጵያዊን ስላስቀየመና ባብዛኛው ያገሪቷ ዜጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥርዓቱ ሰለባ ስለሆነ፣ ይህን ግፈኛ ሥርዓት ደግሞ ለመበቀል ወይም ለማስወገድ ለተማረው ሕዝብ ያለው ብቸኛ አማራጭ ያንዱ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅት ደጋፊ ወይም አባል ሆኖ ወያኔን መታገል ነበር። ይህም ማለት፣ ምሁሩ በተማረበት የሙያ መስክ ከማገልገል ይልቅ ተቃዋሚ ሃይሎችን ተቀላቅሎ መሰረታዊ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ሲታገል ይታያል። ባጭሩ፣ ፖሊቲካን እንደሙያ መማር በባህላችን ስላልነበረ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወላጅ፣ ልጁ አብዛኛውን ጊዜ ካለፍላጎቱ ሃኪም ወይም መሃንዲስ እንዲሆንለት ይመኛል እንጂ ፖሊቲካን ሥራዬ ብሎ እንዲማር አይፈቅድለትም። እውነትም ያለፈውን ታሪካችንና ዛሬም በመከሰት ያለውን የፖሊቲካ አየር ምንመረምር ፖሊቲካን እንደሙያ ማጥናት ለእስር ቤትና ለግርፋት ይዳርግ እንደሁ እንጂ፣ ለፍቶ ላስተማረ ወላጅ አንዳችም ትርፍ አያመጣም፥ ያልተማረው መሃይም በጠብመንጃ ድጋፍ የፖሊቲካ ሥልጣን ቁንጮ ላይ ተቀምጦ ምሁሩን ሲያተራምስ ያየ ሰው፣ ዕውነትም ፖሊቲካን እንደሙያ አድርጎ መማር ዋጋ የለውም ያሰኛል።

 

መሆን የነበረበት

 

በበኩሌ፣ ባገራችን የፖሊቲካ ጥበብ ዕውቀት አብቦ እንዳያፈራ ካደረጉትና በማድረግ ላይ ይገኛሉ በማለት ከላይ የዘረዘርኳቸውን ምክንያቶች በምን መንገድ አስወግደን፣ ሌሎች አገሮች ባህላቸው አርገውት በየዕለቱ የሚኖሩትን “ልዩነቶችን አቻችሎ በሰላም አብሮ የመኖር” የፖሊቲካ ልምድ መኖር እንጀምራለን ለሚለው ጥያቄ ተገቢ መልስ ያለኝ አይመስለኝም። እንድሁ በግምት ግን ከመፍትሄዎቹ አንዱና ዋነኛው ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበው አንድ ከልምድ ያገኘሁት ነገር ባካፍላችሁ ደስ ይለኛል።

 

የፖሊቲካ ጥበብ ባንድ አገር አብቦ ማፍራት፣ ያገሪቷ የዲሞክራሲ ዕድገት ነጸብራቅ ነው። ዲሞክራሲ ባደገበት አገር ደግሞ የዜጎች መብት ሙሉ በሙሉ ስለሚከበርና ሥልጣን ላይ ያሉት ፖሊቲከኞች ደግሞ የዚያ ዲሞክራሲ የዳበረበት ህብረተሰብ ምርት ስለሆኑ፣ ህዝብን ማገልገል እንጂ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ተቃዋሚ ftድንን ወይም ግለሰብን አያጠቁም። የአስተሳሰብ ልዩነት ደግሞ ወደ ጥላቻ ስለማያመራና ባንድ ወቅት ተሸናፊ የሆነ አካል በሌላ ጊዜ ደግሞ አሸናፊ የመሆን ዕድል ስላለው፣ ተፎካካሪነት የሃሳብ መገለጫ እንጂ፣ አሸናፊው ተሸናፊን የሚያስፈራራበት ዱላ አይሆንም። ያገራችን ዕውኔታ ግን የሚያሳየው፣ ካለንበት ፊውዳላዊ አስተሳሰብ አንጻር ሲታይ ግን መሆንም ያለበት፣ መሸነፍ እንደ ውርደት ስለሚቆጠር፣ ተሸናፊ ሆኖ ከአሸናፊው ጋር ባንድ ገበታ ቀርቦ ከመብላት፣ ሌላ የራስን ማዕድ ሰርቶ በክብር መብላትን ነው። ለዚህ ነው ለምሳሌ ባንድ ፓርቲ ውስጥ የሃሳብ ልዩነት ሲፈጠር፣ ተቃዋሚው አካል ልዩ የሆነውን ሃሳftን ይዞ ፓርቲው ውስጥ ከመቅረት፣ ወጥቶ ሌላ ፓርቲ የሚመሰርተው። አሸናፊውም አካል፣ የተቃዋሚን ሃሳብ ከማስተናገድና አብሮ ከመጓዝ ይልቅ (በሌላ አነጋገር፣ ከመጨቃጨቅ ይልቅ) ተሸናፊውን ከነአስተሳሰft አባርሮ፣ መሰሎቹን ብቻ ይዞ ይቀራል። እነስዬ በህወሃት ውስጥ የተለየ ሃሳብ በማቅረባቸው ከፓርቲው ሲያስወጧአቸው “ጃኬታቸውን አሸክመን አባረርናቸው” ብሎ መለስ የተናገረው እንደ ማለት ነው።

 

ብዙዎቻችን ከኢትዮጵያ ውጪ በምንኖርባቸው ዲሞክራቲክ አገሮች የምናየው ግን፣ በፖሊቲካ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ሃይላት፣ ልዩነትን አቻችሎ የመኖር ጥበባቸው ከኛ በጣም በተለየ መልኩ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው። የሃሳብ ልዩነት ልክ እንደ ሰው ልጅ መልክ ልዩነት እንጂ “ያልተለመደና መኖር የማይገባው” ክስተት ስላልሆነ በድርጅቶች ውስጥ መሰረታዊ ቀውስ አያመጣም። ለዚህ ዕድገት ምክንያቱ ሶስት ነገሮች ይታዩኛል።

 

አንደኛው፣ የሥልጣን ወንበር ላይ መቀመጥ ማለት ፖሊቲከኛው ልክ እንደ ሃኪሙና መሃንዲሱ በሙያው ዜጎችን ለማገልገል እንጂ፣ ለተለየ አላማ አይደለም። ስለዚህም፣ ሃኪሙ ተቀዳሚ የሙያ ግዴታው የዜጎችን ጤንነት መንከባከብ እንደሆነ ሁሉ፣ የፖሊቲከኛም ዋነኛ አላማ የሥልጣን ወንበሩን ተጠቅሞ የዜጎችን መብት መጠበቅና የዚህም መገለጫ የሆኑትን ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችን መቀየስ ማለትነው። ባገራችን ግን ከፖሊቲካ ሥልጣን ጋር አብሮ የሚመጣና፣ ለሌሎቹ ባለሙያዎች የማይሰጥ ልዩ ጥቅም ስላለ፣ ዜጎች በተቻለ መጠን ያለሙያቸው “አሸናፊውን ፓርቲ” ተቀላቅለው፣ ህዝብን በማገልገል ፋንታ ህዝft ራሱ እያገለገላቸው ይኖራሉ። ላንድ የኢትዮጵያ ሚኒስቴር ለምሳሌ ከኪራይ ነጻ የሆነ ቪላ ቤትና እስከ ሶስት መኪና ድረስ ሲሰጠው፣ ላንድ ዕውቅ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሃኪም ወይም በሃሮማያ ዩኒቬርሲቲ ለሚያስተምር የርሻ ምሁር አንዳችም ዓይነት ልዩ ጥቅም አይሰጣቸውም። የፖሊቲካ ጥበብ ባደገባቸው ለምሳሌ እንደ ስዊድን ባሉት አገራት ግን ላንድ የፖሊቲካ ባለሥልጣን ካንድ ስዊድናዊ ሃኪም ወይም መሃንዲስ የተለየ ምንም ዓይነት ልዩ ጥቅም አይሰጠውም።

 

ሁለተኛው፣ የፖሊቲካ ድርጅቶቹ ባንድ አገራዊ ጉዳይ ላይ በመካከላቸው አለመግባባት ቢፈጠር፣ አስቀድመው በተስማሙበት መርሃ ግብር መሰረት ችግሩን ፈትተው ልዩነታቸውን በማቻቻል ወደፊት ይራመዳሉ እንጂ፣ ባሸናፊና ተሸናፊነት ተፈርጀው አይወነጃጀሉም። ልክ ሃኪሞች ያንድን በሽተኛ ህይወት ለማትረፍ መውሰድ ስላለባቸው እርምጃ የተለያየ ሃሳብ አቅርበው ቢወያዩም፣ በውስጥ የአሰራር ህጋቸው አስቀድመው ባሰቀመጡት መመርያ መሰረት ይፈቱታል እንጂ ከመካከላቸው ሃሳft ተቀባይነትን ያላገኘው ሃኪም አኩርፎ ከftድኑ ራሱን አያገልልም። ሃሳባቸው ተቀባይነትን ያገኘላቸው ሃኪሞችም እንደ አሸናፊ ተቆጥረው ልዩ ቦታ አይሰጣቸውም። የፖሊቲካ ድርጅቶችም እንዲሁ።

 

ሶስተኛው እና ዋናው የስኬታቸው ምክንያት፣ በኔ ግምት በነዚህ ባደጉት አገሮች፣ ዋናውን ሥራ የሚሰራው ቋሚ የሆነ፣ በግል እንጂ በftድን ማንኛውንም ፖሊቲካ ፓርቲ የማይደግፍ think-tank ftድን መኖር ነው፥ የዚህ ftድን አባላት በጣም የተማሩና በየመስካቸው ጠቢባን የሆኑ ያገራቸውን የወደፊት ዕጣ ሳይንሳዊ ምርምር ላይ በተደገፈ ጥናት ለመተንበይ የሚችሉ ግለሰቦች ናቸው። ደግሞ ቋሚ ስለሆኑና አሸናፊው ፓርቲ በተቀያየረ ቁጥር ስለማይቀያየሩ ያገሪቷ የፖሊቲካ መርከብ ወደፊት ረጋ ባለ መልኩ ይጓዛል። ሥራቸው ያገሪቷን የወደፊት የፖሊቲካ፣ የኤኮኖሚ፣የጤና፣የመከላከያና የትምህርት ፖሊሲ ቀይሶ ማስቀመጥ ሲሆን፣ ገዢ ፓርቲዎች ደግሞ ይህንን የምርምር ውጤት የሆነውን የፖሊሲ ምርት ተረክቦ ሥራ ላይ ማዋል ነው። መለወጥም ካስፈለገ ጉዳዩን፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለተመረጠው የህዝብ ተወካይ (ፓርላማ) ቀርቦ አወያይቶ በህዝብ ተወካዮች ውሳኔ ይወሰድበታል እንጂ አሸናፊው ፓርቲ ብቻውን ምንም ዓይነት እርምጃ አይወስድም። ይህንን ነው እንግዲህ አብቦ ያፈራ የፖሊቲካ ጥበብ የምለው።

 

መደምደምያ

 

የበሰለ የፖሊቲካ ጥበብና አሰራርን ባገሪቷ ከዳር እስከዳር አስፍኖ፣ በሌላ አነጋገር፣ ልዩነትን አቻችሎ አብሮ ለመራመድ፣ መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ነገሮች ከላይ በመጠኑም ቢሆን ከላይ ከጠቃቀስኳቸው ምክንያቶች መገምገም ይቻላል። በኔ ግምት፣ እነዚህና ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው ጉድለቶች ካልተሟሉ በስተቀር በምንም ተዓምር ካለንበት አዘቅት አንወጣም። በበኩሌ፣ ጎደሎዎቹን ለመሙላት አንዳችም ዓይነት ሂሳባዊ ፎርሙላ የለኝም። ግን ከሙያዬ ጋር በተያያዘ ልምድ ተነስቼ፣ ባገራችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በፖሊቲካ ድርጅቶች መካከል ሲካሄድ የነበረውን አስመልክቼ የሚከተለውን ለማለት እችላለሁ፣

 

በኔ ግምት፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በዲሞክራሲ ጥበብ የጎለመሰና ልዩነቶችን አቻችሎ ባንድነት ለመጓዝ ወይም ለማስጓዝ የሚችል፣ የሁሉም ዜጋ መብት የሚከበርበትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉትን ሲሚንቶና አሸዋ ለማftካት ዝግጁ የሆነ አንድም የፖሊቲካ ድርጅት የለም ባይ ነኝ። ይህም ማለት፣ ዛሬ ባለው ሁኔታ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችም ሆኑ ወያኔ ዴሞክራሲያዊ ጠባይ ኖሮአቸው ተቃዋሚ ሃሳብን የማስተናገድ ችሎታ የላቸውም ማለቴ ነው። ለወደፊት ግን ሊሆኑ ይችላሉ። እስከዚያው ድረስ ግን፣ ይህንን “ልዩነትን አቻችሎ አብሮ ለመጓዝ” ያለመቻል ደካማ ጎናችንን መቅረፍ እንኳ ባንችል፣ ቢያንስ ቢያንስ ችግሩ መቀረፍ አለበት በሚለው መሰረታዊ ሃሳብ ላይ መስማማት አለብን እላለሁ። የችግርን ይዘት መረዳት ችግሩ በገሚሱ እንደተቀረፈ ይቆጠራልና!

 

በመጨረሻም አንድ ሁሌም የሚከነክነኝን ነገር ልጠይቃችሁና ይህን ካሰብኩት በላይ የተንዛዛብኝን ጽሁፌን ልቋጥር። ጥያቄዬም፣ እስቲ ምን ብናደርግ ነው ከዚህ ኋላ ቀር “የአሸናፊና ተሸናፊ” ግንኙንትና “አሸናፊ” ሁሉን ጠቅልሎ ከሚወስድበት አስተሳሰብ ነጻ ሆነን፣ የአስተሳሰብ ልዩነትን እንደማንኛውም ዓይነት ልዩነት ተፈጥሮአዊ መሆኑን ተቀብለን፣ “ልዩነታችንን” አቻችለን አብሮ በመራመድ፣ በጋራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ረጅሙን ጉዞ የምንጀምረው? መልሱን የምታውቁ ካላችሁ እባካችሁ ዝም አትበሉ። ዛሬ ልዩነቶቻችንን አቻችለን አብሮ ለመጓዝ ዝግጁ አለመሆን ማለት ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በየቀኑ ለሚፈሰው የወገኖቻችን ደም፣ ወይንም በየእስር ቤቱ ታጉረው በወያኔ “አሰቃዮች” ነፍሳቸው በሞትና በህይወት መካከል ተንጠልጥሎ ለሚገኙ የወያኔ ሰለባዎች ሰቆቃ፣ እኛም እንደተጠበቀው ልንደርስላቸው ስላልቻልን፣ በታሪክ ፊት ከወያኔ እኩል ተጠያቂዎች ነን እላለሁ። እስቲ አስተያየታችሁን ሰንዝሩ።

 

*******

 

ጄኔቫ፣ መስከረም 23, 2017

wakwoya2016@gmail.com

55,000 Ethnic Oromos Displaced – Oromia Regional Government

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.