የአፄ ፋሲል 351ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ -ልጅ ዓምደጺኦን ምንሊክ

ምስጢራዊቷንና ታሪካዊቷን ‹‹ጎንደር››ን የቆረቆሯት አፄ ፋሲል ያረፉት ከዛሬ 351 ዓመታት በፊት (መስከረም 15/1659 ዓ.ም) ነበር፡፡

አፄ ፋሲል የአፄ ሱስንዮስና የደብረታቦር ቆማ ፋሲለደስ ተወላጇ ወይዘሮ ወልደሰዓላ ልጅ ናቸው፡፡ በልጅነታቸው በጣና ሐይቅ ላይ ባሉ ገዳማት መንፈሳዊና ዓለማዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በቆይታቸውም ስለመንግሥት አወቃቀር፣ ስለፍርድ አሰጣጥና ስለሕዝብ አስተዳደር እንዲሁም ስለሌሎች ጉዳዮች በሚገባ አጥንተዋል፡፡

በ1624 ዓ.ም ‹‹ዓለም ሰገድ›› በሚል ስመ መንግሥት በአባታቸው ዙፋን ሲቀመጡ ‹‹ፋሲል ይንገስ፣ ተዋህዶ ይመለስ፣ የሮም ሃይማኖት ይፍለስ›› በተባለው መሰረት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን ስላደረጉ ሕዝቡ፣ የቤተ ክህነቱና የቤተ-መንግሥቱ ሰው ሁሉ ንግሥናቸውን በደስታ ተቀበለው፡፡

የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባም አዘዙ፤ የካቶሊክ ክርስትና የመንግሥት ሀይማኖት እንዲሆን ላይ ታች ብሎ አፄ ሱስንዮስን ያሳመናቸው አልፎንሶ ሜንዴዝ የተባለ የካቶሊክ ቄስና አውሮፓውያን ደቀ መዛሙርቱ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲባረሩ ተደረገ፡፡

አፄ ፋሲል በነገሱ በሦስተኛው ዓመት መልዐከ ክርስቶስ የተባለ የላስታ ባላባት ተነሳባቸውና ጥቂት ተዋግተው ንጉሱ ለጊዜው ተሸንፈው ሲሸሹ የላስታው ባላባት ቤተ-መንግሥት ገብተው በአፄ ፋሲል ዙፋን ተቀመጡ፡፡ አፄ ፋሲልም ወዲያውኑ የስሜን፣ የዳሞትንና የበጌምድር አገረ ገዢዎችን ከጎናቸው አሰልፈው ከመልዐከ ክርስቶስ ጋር ተዋጉና አሸንፈው ወደዙፋናቸው ተመለሱ፡፡

ከዚያ በኋላም ሀገሩ ሁሉ ሰላም ሆነ፡፡ ንጉሱም ከአስተዳደር ስራቸው በተጨማሪ፣ እንደምትመሰረትና የመንግሥት መቀመጫ እንደምትሆን ለረጅም ዘመናት ትንቢት ሲነገርላት የነበረችውን የጎንደር ከተማን መስርተው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አደረጓት፡፡ የጎንደር አመሰራረት ልዩ የሆነ ኃይማታዊ ምስጢር እንዳለው በታሪክ ድርሳናት ተፅፏል፡፡

አፄ ፋሲል ከድንበራቸው አልፈው ከኢትዮጵያ በስተምዕራብ በኩል ያለውን የሱዳን ግዛት የሆነውን ስናርን ማስገበር ችለዋል፡፡ በወቅቱም አዝማሪ እንዲህ ተቀኝቶላቸው ነበር፡፡

ጎንደር ቢያጉረመርም ፋሲል ፈረስህ፣
ኑብያና ስናር ወርቁን ጫኑልህ፡፡
ሳሩን ተጠየፈ የፋሲል ፈረሱ፣
ክምር የሱዳን ወርቅ ገፈራው ነው ለሱ፡፡

አፄ ፋሲል ጎንደርን (ጉንደ-ሀገር = የሀገር ራስ፣ ትልቅ ሀገር)ን መስርተውና የመንግስታቸው መቀመጫ አድርገው ፍርድ ሲሰጡ፣ ሀገር ሲያቀኑና ግዛት ሲያስፋፉ ቆይተው፣ መስከረም 15 ቀን 1659 ዓ.ም በተወለዱ በ78 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
————-
ነፍስ ይማር!
Lij AmdeTsion Menelik Ethiopia

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.