ሳውዲአረቢያ ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ ፈቀደች

(ኢሳት ዜና–መስከረም 17/2010)በአለም ላይ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ በሕግ ክልከላ ያደረገችው ብቸኛ ሀገር ሳውዲአረቢያ እገዳውን በማንሳት ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ ፈቀደች።

የሳውዲው ንጉስ ሳልማን እገዳውን በማንሳት ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀዳቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአድናቆት ተቀብለውታል።

የሴቶችን መብት ለማክበር አዎንታዊ ርምጃ ሲሉም ገልጸውታል።

ሴቶች መንጃ ፈቃድ ማውጣት እንዲችሉ የሚፈቅደው ይህ የንጉሱ ውሳኔ ከ10 ወራት በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሰኔ 24/2018 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ታውቋል።

በሳውዲ ሴቶች ዘንድ ደስታን የቀሰቀሰው ይህ ርምጃ አንዳንዶቹ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሲመኙት የነበረውን መኪና ለመግዛት መወሰናቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በሳውዲ ሴቶች ላይ የተጣለው ይህ እገዳ እንዲነሳ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲታገሉ መቆየታቸውም ይታወሳል።

ርምጃውን በመቃወም በአደባባይ መኪና ሲነዱ የተገኙ ሴቶችም ወደ ወህኒ ተግዘዋል።

እገዳውን በመቃወም በአደባባይ መኪና ስትነዳ ተይዛ 73 ቀናት በወህኒ ያሳለፈችው የሳውዲዋ አክቲቪስት ሎጄን አል ሀትወል በውሳኔው ደስታዋን የገለጸችው እግዚአብሔር ይመስገን በማለት ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ትልቅ ርምጃ ሲል የንጉሱን ውሳኔ አወድሷል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም የሳውዲው ንጉስ ሳልማን እገዳውን በማንሳት ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀዳቸውን በአድናቆት ተቀብለውታል።
ውሳኔውን የሴቶችን መብት ለማክበር አዎንታዊ ርምጃ ሲሉም ገልጸውታል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም በቲዊተር ገጻቸው በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ የሚገኝ አስፈላጊ ርምጃ ሲሉ አወድሰውታል።

አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ይህ አንድ ርምጃ ቢሆንም ሌሎች የሴቶችን መብት የገደቡ ርምጃዎች በተመሳሳይ እንዲነሱ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በሳውዲ ሴቶችና በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆትና ድጋፍ ያገኘው የንጉሱ ውሳኔ ተቃውሞም አስተናግዷል።

የሸሪያ ህግ ሴቶች መኪና እንዳይነዱ ይከለክላል።ይህ ሃይማኖታዊ ክልከላ እንዴት ተፈቀደ ሲሉም የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በአሜሪካ የሳውዲአረቢያው አምባሳደር ልኡል ካሊድ ሳልማን ንጉሱ ውሳኔውን ያሳለፉበትን ቀን ታሪካዊና ታላቅ ቀን ሲሉ በማወደስ በትክክለኛው ግዜ የወጣ ትክክለኛ ውሳኔ ነው በማለት ተቃውሞውን አጣጥለውታል።

የሳውዲአረቢያ ሴቶች ላይ አሁንም የቀጠለው እገዳ ያለባለቤታቸው ወይንም አባታቸው ወይንም ከወንድ አሳዳጊያቸው ፈቃድ ውጪ የባንክ አካውንት መክፈት ስራ መያዝ ትዳር ማፍረስ ወይንም ጉዞ ማድረግ አይችሉም።

በሆስፒታል፣ በባንክ፣ በሕክምና ቦታዎችና በመሳሰሉት አካባቢዎች ካልሆነ በቀር ወንዶች ባሉበት እንዳይገኙም የተቀመጠው እገዳ አሁንም ቀጥሏል።
ከወንድ ጋር ካልሆነ በቀር ብቻቸውን መነገድም አይችሉም።

ያለባለቤታቸው ወይንም አባታቸው ፈቃድ ፓስፖርት ማውጣትን ጨምሮ አሁንም ከሌላው የሙስሊም አለም በተለየ በሳውዲ አረቢያ ውስጥ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ የመብት ተሟጋቾች ጥሪ ቀጥሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.