እነ ኮሎኔል ደመቀ የደመቁበት የጎንደር መስቀል (ጌታቸው ሽፈራው )

ጎንደር መስቀልን ለየት ባለ መንገድ ከሚያከብሩ አካባቢዎች ቀዳሚው ነው። ከጥቂት አመታት በፊት ኢቲቪ የጎንደርን መስቀል አከባበር በልዩ ዝግጅት ያቀርብ የነበር ሲሆን በሂደት ወደ ጎን ተብሏል። ይሁንና ኢቲቪ የጎንደርን መስቀል አከባበር በልዩ ዝግጅት ማሳየት ማቆሙ፣ በገዥዎቹ ወደ ጎን መባሉ በዓሉን አላቀዘቀዘውም። የጎንደርን መስቀል ከሚያከብረው መካከል አብዛኛው የጎንደር ህዝብ ነውና። በተለይ በዚህ ወቅት ህዝብ እየተፈፀመበት ያለውን በደል በሚገባ በመገንዘቡ ከአሁን ቀደም እንደቀላል ያየው የነበረውን ታሪክና ባህል አጥብቆ እየያዘ ነው። ይህን የህዝብ ግንዛቤ በጎንደር ብቻ ሳይሆን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በየ ክስተቱ የምንታዘበው ነው። የመስቀልን እንደምሳሌ ብንጠቅስ እንኳ በደሴ እና በባህርዳር ወጣቶች ከአገዛዙ የሚለዩበትን እሴታቸውን ሲያንፀባርቁ ታይተዋል። ሰንደቅ አላማውን ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው።

የዘንድሮው የጎንደር መስቀል ላይ ከሰንደቅ አላማው ባሻገር መፈክሮች ተደምጠዋል። አገዛዙን በበዓሉ ላይ እሱ የማይፈልጋቸው መልዕክቶች ቲሸርት ላይ እንዳይታተሙ የቻለውን ያህል ቢያደርግም የጎንደር ወጣቶች የፈራ ይመለስ፣ አንፈራም፣ ወይ ውረድ ወይ ፍረድ፣ እንከባበር……… የሚል የተፃፈባቸው ቲሸርቶችን ለብሰው ውለዋል። ከዚህም ባሻገር ይለያል ዘንድሮ፣ ሞት አንፈራም በቃን ሲሉ ተደምጠዋል። የሚወዷቸውን ጀግኖች አሞግሰዋል። ለምሳሌ ያህልም ለረዥም ጊዜ ” ጎቤ! ጎቤ!” እያሉ ጎቤ መልኬን ሲያወድሱ እንደነበር ታውቋል። እነ መለስ ዜናዊ አከርካሪውን ሰብረነዋል ስለሚሉት ህዝብ ሲዘመር ውሏል። ወጣቶቹ “አማራ! አማራ!..አትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ይመልሳል ….! ሲሉ ውለዋል። መንግስት ወደ ጎን ብሎ ይቀዘቅዛል ባለው የጎንደር መስቀል።

በጎንደር መስቀል አንድ የተለመደ ልብ አንጠልጣይ ትዕይንት አለ። ታዳሚው መስቀሉ ወደየት ይወድቃል ብሎ አይጠብቅም። ከዛ በላይ የሚጠብቀው ትይንት አለ። “የዘንድሮውን መስቀል ማን ይወስደው ይሆን? ለማንስ ይበረከታል?” ብሎ እንጅ! የደመራው ዋና መሰሶ ( መስቀሉ) ሊወድቅ ሲቃረብ የሚነደውን ደመራ ፈርጣማ ወጣቶች ይከቡታል። አንዱ ሌላኛውን እንደሚጠባበቅ በግልፅ ይታወቅባቸዋል። ልክ እንደ ራግቢ ጨዋታ በተጠንቀቅ ወደሚፋጀው እሳት ይጠጋሉ።ፖሊስ እርስ በእርስ እንዳይጎዳዱ መጠነኛ ጥረት አድርጎ ሲያቅተው ይተዋቸዋል። የእኔ ብጤ ደካማ ወደ ሁዋላ አፈግፍጎ ትይንቱን ይከታተላል። በፈርጣማዎቹ ወጣቶች የራግቢ አይነት ልፊያና ትግል መሃል እንዳይረገጥ ይጠነቀቃል። እነሱ ግን እሳቱን ከምንም ሳይቆጥሩ ይበልጥ ወደሚንቀለቀለው ደመራ ይጠጋሉ። ወገንና “ባላጋራን” አሰላለፍ እየተመለከቱ። የደመራው መሰሶ ( መስቀሉ) ገደም እስከሚል ይጠብቃሉ። በአብዛኛው አንደኛው ቡድን ሌላው ጋር ተፋልሞ መሬት ሳይነካ ይይዘዋል። እሳት ላይ ራግቢ እንደመጫወት ነው። ያውም በእሳት ኳስ።

ይህን የሚያደርጉት በየ ቀበሌው የተመረጡ ጉልበታም ወጣቶች ናቸው። መስቀሉን የቀማ ቡድን የዛ አመት መስቀል ሻምፒዮን ነው። መስቀሉን ቀምቶ ይጨፍራል። ህዝብ ያወሩለታል። ያሸነፈው ቡድን ይህን የክብር መስቀል ታዲያ እጅግ ለሚያከብረው ሰው ነው የሚያበረክተው። በምላሹ ቡድኑ ድግስ ይደገስለታል። በዓሉን በደንብ የሚያከብርበት አጋጣሚ ይመቻችለታል። ለቤተ ክርስትያን የሚሰጥበት ጊዜም አለ። አንዳንዴ በከተማው የሚታወቁ ግለሰቦችም የዚህ መስቀል ተሸላሚ ይሆናሉ። የመስቀል ዋንጫ እንደማለት ነው። እምነቱን ለሚያከብሩት ወጣቶች ትልቅ ሻምፒዮና ነው። መስቀሉ ለሚሰጣቸው ደግሞ እጅግ የከበረ ስጦታ ነው።

ዘንድሮ በተደረገው የመስቀሉ ሻምፒዮና ታዲያ ቀበሌ 11 እና ቀበሌ 7 መስቀሉን ለመውሰድ ትልቅ ትግል እንዳደረጉ ታውቋል። ያሸነፉት ግን ሁለቱ ናቸው ተብሏል። ለዛም ይመስላል እዛው በዓሉ ላይ ተሳታፊ የነበሩና አብዛኛውን መረጃ የሰጡኝ ግለሰቦች ሳይቀር ተሸናፊውን እንዳላወቁ ገልፀውልኛል። በእርግጥ ከቀበሌ 11 እና ቀበሌ 7 መካከል አንደኛው መስቀሉን የቡድኑ አድርጓል። ያበረከተው ግን ሌላኛው ቢያሸንፍ ሊያበረክርለት ለሚችል አካል ነው። ግለሰብ ማለት ከብዶኝ ነው። ለኮለኔል ደመቀ ዘውዱ! ወጣቶቹ ከኮለኔል በላይ የሚያከብሩት ማን ይኖራልና?

እስካሁን በሚደረጉት ፍልሚያዎች ያሸነፈው ሰፈርን፣ ቀበሌን፣ ቡድኑንና የቡድኑን አባላት ያስጠራበታል። ዘንድሮ ግን እንዲጠራበት የተፈለገው ከሰፈርም፣ ከቀበሌም፣ በዓሉ ከሚከበርበት ከተማና አካባቢም በላይ ለሆነው ለኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ነው። በጎንደር መስቀል ውሎውን ከሚደረገው ስነ ስርዓት በተጨማሪ መስቀሉን ያሸነፉና የተበረከተላቸውም ስማቸው ይወሳል። ይደምቁበታል። የዘንድሮዎቹ ሻምፒዮኖች መስቀሉን ይዘው እየጨፈሩ ወደ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ቤተሰብ ቤት በመሄድ እንኳን አደረሳችሁ ብለው መስቀሉን በክብር እንዳስረከቡ ታውቋል። በዓሉን በተለያየ ዝግጅት፣ ከአሸነፉ በሁዋላ በሆታ ያደመቁት መጣቶች ” መንግስት” ብቻውን አንድ ጠባብ ቤት ውስጥ ላሰረው ኮለኔል ደመቀ የበዓሉን ትልቅ ክብር አበርክተውለታል። አስታውሰውታል። የጎንደር መስቀል ሰንደቅ አላማው፣ የህዝብ አላማና መፈክር ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ሲል የታሰረው ደመቀ ዘውዱ ደምቆበታል። ጎቤና ሌሎች ጀግኖች ተወስተውበታል!

(የፅሁፉን አብዛኛው ክፍል የላከልኝ ዝግጅቱ ላይ የነበር ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የማውቀው ወጣት ሲሆን እኔ ለንባብ ይመቻል ባልኩት መንገድ አቅርቤዋለሁ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.