ብሄር ተኮሩ የፌደራል አገዛዝ ያስከተለው የተዛባ እድገት –ማንን ጠቀመ! ማንን ጎዳ?- – አክሎግ ቢራራ

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አክሎግ ቢራራ (ዶር)
አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ሕወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫነው ብሄር-ተኮር ፌደራሊዝም የግጭት፤ የተዛባ ወይንም ያልተመጣጠነ የክልሎች እድገትንና የተዛባ የነፍስ ወከፍ ገቢን፤ የኃብት ክምችትንና የኑሮ ልዩነቶችን አደገኛ በሆነ ደረጃ ፈጥሯል። ይህ የጠባብ ብሄርተኞች አገዛዝ ከቀጠለ ልዩነቶቹ እየጠነከሩ እንጅ እየተሻሻሉ አይሄዱም። ደጋግሜ እንዳሳሰብኩት ሁሉ፤ ይህ የጥቂቶች አገልጋይ የሆነ አገዛዝ ከቀጠለ፤ የኢትዮጵያ ቀጣይነትና ሉዐላዊነት ወደማይመለስ አደጋ ይሸጋገራል። ይህ አፋኝና ከፋፋይ አገዛዝ ከቀጠለ፤ የኢትዮጵያ 105 ሕዝብ በመተሳሰብና በመደጋገፍ አብሮ፤ ተቻችሎ፤ የተፈጥሮ ኃብቶቹን ለጋራ ጥቅም አውሎ አገሩን ከድህነትና ከጥገኝነት፤ ሕዝቡን ከእርስ በርስ ግጭትና ከውርደት ለማዳን ወደማይቻልበት ሁኔታ ይሸጋገራል። አሁን በግልጽ የሚታየው አደጋ ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን፤ ለጥቂቶች ጥቅም ሲባል፤ ቀስ በቀስ ስር እንዲሰድ የተደረገ ነው።

ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣን ከያዘበት ከዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ በኦፊሴል ደረጃ ብቻ ከ$40 ቢሊየን በላይ አግኝታለች። ስደተኛው ከዚህ ያላነሰ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሃገሩ ልኳል። በቅርቡ የውጭ ኢንቬስተሮች ብዙ ቢሊየን ዶላር ፈሰስ አድርገዋል። ገዢው ፓርቲ ልክ እዳ ነገ እንደማይከፈል በሚመስል ደረጃ ይበደራል፤ ያጠፋል። አገሪቱ እዳ በእዳ ሆናለች። የፖለቲካ ስልጣን ሲይዙ የሚበሉት ምግብ፤ የሚቀይሩት ሱሪ፤ የሚለብሱት ጫማ፤ የሚኖሩበት ዘመናዊ ቤት ወዘተርፈ ያልነበራቸው የፓርቲ፤ የክልልና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ሚሊየኔር ሆነዋል። በተለይ ህወሓቶችና ታማኞቻቸው። (Ethiopia suffers from one of the worst cases of political, economic and social capture in world history).

አበዳሪና ለጋስ ድርጅቶች የኢትዮጱያ ገዢ ፓርቲ የሚሰጠውን መረጃ ተጠቅመው “አገሪቱ በድርብ አሃዝ” እያደገች ነው። በዓለም ታዳጊ ከሆኑ አገሮች መካከል ከፍተኛውን እድገት ታሳያለች። ድህነት አጥጋቢ በሆነ ደረጃ እየተቀረፈ ነው። በዚህ መጠን እድገቷን ከቀጠለች ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር (Midddle Income Country) የመሆን እድሏ ከፍ ያለ ነው ይላሉ። እነዚህ ድርጅቶች ተራው ኢትዮጵያዊ የሚኖርበትን ሁኔታ ያውቁት ይሆን? እነዚህ ድርጅቶች በገፍ ከአገሩ የሚሰደደውን ወጣት ትውልድ ያውቁት ይሆን? እነዚህ ድርጅቶች በየቀኑ የሚሞተውን፤ የሚታሰረውን፤ እንዲሰወር የሚደረገውን፤ የሚራበውን ሕዝብ ቁጥር ያውቁት ይሆን?

የአበዳሪ ድርጅቶች ስራ ማበደር ነው። ለማበደር ተበዳሪ መኖር አለበት። ድህነት መኖት አለበት። ካላበደሩ በስተቀር ህልውናቸው የሚጠፋው ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በአብዛኛው የእድገት መረጃቸውን የሚያገኙት ከሚያበድሩት አገር ባለሥልጣናት መሆኑን በተደጋጋሚ አይቻለሁ። እንደ ዓለም ባንክ ያሉት ድርጅቶች ሙስና ነቀርሳ መሆኑን ተቀብለው ራሳቸው ያዘጋጁትን ጥናት ስራ ላይ አያውሉትም። ሆኖም፤ የአሜሪካ ጫና ከሌለባቸው ለሙሰኞች፤ ለወገንተኞች፤ ለጨቋኞች የሚሰጡትን ድጋፍ አያቆሙም። የአረቦች “የጸደይ” አብዮት ከመካሄዱ በፊት አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ የግብጽና የቱኒዢያ ኢኮኖሚዎች አጥጋቢ እድገት እንደሚያሳዩና “የኢኮኖሚዎቻቸው መዋቅሮች” እየተቀየሩ መሄዳቸውን ይናገሩ ነበር። የመዋቅር ለውጥ ማለት የገጠሩ ኢኮኖሚ ዘመናዊ እየሆነ መሄዱና የመካከለኛው መደብ አብዛኛውን ሕዝብ እየወከለ መሄዱን የሚያሳይ የእድገት ውጤት ነው። ይህ አጥጋቢ ሁኔታ ከቀረበ ከጥቂት ወራቶች በኋላ ስርነቀል የሆኑ ሕዝባዊ አመጾች ተከሰቱ። የቱኒዥያና የግብጽ አምባገነኖች ከስልጣናቸው ወረዱ። እድገትን ማጋነን ሊያጋልጥ ይችላል።

ከሳሃራ በታች የሚገኙ አገሮችን በሚመለከት አንድ ሰሞን የአይቮሪኮስት ኢኮኖሚ (The Ivoirian Economy) “ተአምራዊ እድገት” እንደሚያሳይ እነዚህ ድርጅቶችና የአፍሪካ ልማት ባንክ ይናገሩ ነበር። እድገቱና ገቢው የተዛባ በመሆኑ፤ ሙስና አገሪቱን በማድማቱ የተነሳ፤ የእርስ በርስ ግጭት ተካሂዶ የአገሪቱ ኢኮኖሚ፤ በተለይ መሰረተ ልማት እንዳልነበረ ሆነ። ብዙ ኃብት ወደመ። ብዙ ህይወት ጠፋ። አስደናቂዋ አይቮሪኮስት ልክ እንድጎረቤቶቿ ድሃና ጥገኛ ሆነች።

ይህች አገር አንድ ሰሞን ፈርሳ ነበር (Ivory Coast moved from a miracle growth to a failed state). የአፍሪካ ልማት ባንክ ቢሮውን ከአቢጃን ወደ ቱኒስ ያዘዋወረበት ዋናው ምክንያት የአገሪቱ መፈራረስ ነው።

የተፈትሮ ኃብት ባለጸጋዋ አፍሪካ አሁንም ድሃ ናት።

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተፈጥሮ ኃብት ባለጸጋ ናቸው። እንደ ቦትስዋናና ናሚቢያ ጥሩ አገዛዝ ካላቸው በስተቀር፤ የአፍሪካ አገሮች አሁንም፤ ድሃ፤ ረሃብተኛ፤ ጥገኛና ኋላ ቀር ናቸው። እንደ ኢትዮጵያ፤ ዛየር፤ ደቡብ ሱዳንና ሌሎች ወንዞችና ጅረቶች፤ ለም መሬቶችና ታታሪ ሕዝቦች የሚኖሩባቸው አገሮች ራሳቸን ለመመገብ አልቻሉም። በግጭት ተበክለዋል። ከሃያ ሰባት ዓመታት የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኋላ ከስመንት ሚሊየን በላይ የሚገመት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይራባል።

ዖሉፈሚ ታይዎ የተባለው አፍሪካዊ የማህበረሰብ ሳይንቲስት የኢትዮጵያን የእድገት እንቆቅልሽ ሁኔታ እንዲህ በሚል ጥያቄ አቅርቦታል። “How come that geography puts the source of the River Nile in Ethiopia,” but the country cannot feed itself?” የወንዞች፤ ጅረቶች፤ ዝናብ ባለፀጋዋ ኢትዮጵያ የሚጠጣ የውሃ እጥረት አለባት። ወንዞቿን አግባብ ባለው ሁኔታ አልምታ ከተሞቿን ለማስፋፋትና ሕዝቧን ለማገልገል አልቻለችም። ሌላው ዓለም ወንዞቹን ተጠቅሞ፤ ግድቦችን ሰርቶ፤ ውሃውን አቁቶ ወዘተ በምግብ ራሱን ችሎ ይኖራል። ይህች አገር አሁንም የምግብ ጥገኛ ናት። የምግብ ጥገኛዋ ኢትዮጵያ ጥቂት ስርዓት ወለድ ሚሊየኔሮችን አፍርታለች። እነዚህ አዲስ ስርዓት ወለድ ኃብታሞች ድሃውን ሕዝብ ዙረው ማየት አቁመዋል። ሁኔታው አደገኛ መሆኑን ሲገነዘቡ ኃብታቸውንም፤ ቤተሰቦቻቸውንም ያሸሻስሉ።

ዓለም ባንክና ሌሎች አበዳሪ ድርጅቶች አስደናቂ እድገት ብለው የሚጠሩት የኢትዮጵያ እድገት እንቆቅልሽ መሆኑን ደጋግሜ አሳስቤ ነበር። ምክንያቱም፤ ከብልጭልጭነቱ ባሻገር ሲመረመር፤ ይህ አስደናቂ እድገት ሚዛናዊ አይደለም። ፍትሃዊ አይደለም። በክልሎች መካከል አደገኛ የእድገት ልዩነቶችን ፈጥሯል። የገቢና የኑሮ፤ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ልዩነቶች ሊፈቱ የሚችሉ አይመስሉም። እንዲያውም ግጭቶችን እየፈጠሩ ነው።

የግፍ ግፍ

የኤሌክትሪክ ኃይል ከመሃል አገር ተስቦ፤ የመብራት ምሰሶዎቹን “የጎንደሬ ዘበኞች” እንዲጠብቁ ተደርጓል። የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመረትባቸው ቦታዎች፤ በተለይ መንደሮችና ከተማዎች ጨለማ ሆነው፤ መቀሌና ሌሎች የትግራይ ከተማዎች የኤሌክትሪክ መብራት ተጠቃሚ ሆነዋል። አንዳንድ ተመልካቾ፤ “የአማራ ክልል ጨለማ፤ የትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ባለጸጋ” መሆኑ በምን ምክንያት ነው? የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የአማራው ክልል ፓርቲ ለዚህ መልስ ሊሰጥ አልቻለም ወይንም አልፈቀደም። ምክንያቱም፤ ከጥቂት አባላት በስተቀር፤ የፓርቲው ታማኝነት ለሕወሓት ነው። ለአማራው ሕዝብ አይደለም። በየጊዜው ከሕዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች አንድም ባለሥልጣን አግባብ ያለው መልስ አልሰጣቸውም። እንዲያውም፤ ጥያቄውን የሚያቀርቡት ጎንደሬዎችና ሌሎች ግለሰቦች ክትትል ይደረግባቸዋል። ከስራቸው ይባረራሉ፤ ይታሰራሉ፤ ይገረፋሉ፤ ይሰደዳሉ፤ እንዲሰወሩ ይደረጋሉ። ህወሓት አንድም ተቆርቋሪ እንዲኖር አይፈቅድም።

የተዛባ እድገት የሚከሰተው የተዛባ አስተዳደር፤ አድሏዊ ወይንም ፖለቲካዊ የፍርድ አሰጣጥ ስላለ ነው። የአሁኗ  ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የላትም፤ አይታሰብም። በቅርቡ በኬንያ ያየነው የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ አይታሰብም። In “Kenyan High Court Annuls President’s Reelection Victory, September 2, 2017,” the Washington Post remarked the unprecedented nature of such a reversal in a continent where single party governance is common.” የኬንያው ተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ የተናገሩት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ገዢዎች ትምኅርት ይሆን ነበር፤ ለመማር ፈቃደኛ የሆነ ባለሥልጣን ቢኖር። “የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ለኬንያ ሕዝብ ታሪካዊ ነው፤ ለአፍሪካ ሕዝብም ጭምር። በአፍሪካ የዲሞክራሲ ምስረታ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የኬንያው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተጭበረበረው ምርጫ ውጤት ተቀባይነት የለውም የሚል ውሳኔ ሰጠ።” ውስኔውን በማጠናከር  የ“Kenya Office of Physicians for Human Rights፣” መሪ ዶር አላይ እንዲህ ብለዋል። “ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያሰመረልን ፖሊሲ ወይንም መርህ ከሁሉም በላይ ሕገመንግሥቱ፣ የሕግ የበላይነት፤ የነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሂደትና አስተዳደር ወሳኝ መሆናቸውን ነው።” የኬንያን የወደፊት ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት  የሚወስኑት እነዚህ መርሆዎች ናቸው። የኬናያ ሕዝብ በመሪዎቹ ላይ እምነት የሚኖረው ሕገመንግሥቱና የሕግ የበላይነት በሁሉም ዜጎች ሲከበሩ ነው። ፍርድ ቤቱ አዲስ ምርጫ በሚቀጠልው ወር እንዲካሄድ ወስኗል፤ የኬንያው ፕሬዝደንት ኬንያታ የሕግ የበላይነትን በማክበር ውሳኔውን ተቀብለውታል። ይህ በኢትዮጵያ አይታሰብም።

ለማስታወስ ያክል፤ በምርጫ ዘጠና ሰባት ኢህአዴግ ተሸነፈ። ገዢው ፓርቲ ምርጫውን ቀለበሰው፤ ተቃዋሚዎቹን አስራቸው። ወገኖቻችን ጨፈጨፈ። ከዚያ ወዲህ ገዢው ፓርቲ በሚያሳፍር ደረጃ ኢህአዴግ መቶ በመቶ ያሸንፋል። ዛሬ ምክር ቤቱ አንድም ተቃዋሚ የለበትም። የምርጫ ቦርዱና ከፍተኛው ፍርድ ቤት የህወሓት/ኢህአዴግ መሳሪያ እንደሆኑ ቆይተዋል። መሳሪያ ስለሆኑ ነው የሚዘገንነው ጠባብ ብሄርተኛነትና ከዚህ ጋር የተያያዘው አድልዎ፤ ሙሰኝነትና የአስተዳደር በደል ሊቀረፉ ያልቻሉት፤ ወደፊትም የማይችሉት። ይህ ነው አገርን የሚያፈርስ።

የሕግ የበላይነት በሌለባት ኢትዮጵያ የተዛባ የክልሎች እድገትና የተዛባ ገቢ ቢከሰቱ ምንም አያስደንቅም። አገዛዙ የተመሰረተው ሁሉንም ሚዛንዊ በሆነ ደረጃ ለማገልገል አይደለም። ሆነ ተብሎ አገዛዙ በጥቂቶች! ለጥቂቶች! ማገልገል አለበት በሚል ብልሃት የተጸነሰና የሚሰራ ነው።

ማንም ሊክደው የማይችለው ሁኔታ፤ ብሄር ተኮሩ ስርዓትና አገዛዝ የተዛባ የክልሎች እድገትና የተዛባ የነፍስ ወከፍ ገቢ ፈጥሯል። የተዛባ እድገትና ኢ-ፍትሃዊ ገቢ ግጭቶችን ይፈጥሯል። ኢትዮጵያን እያፈራረሳት ነው። ለውጭ ጠላቶች እድሎችን እየፈጠረላቸው ነው።

የዚህ ትንተና ዋና መልእክት የህወሓት/ኢህአዴግ የእድገት መርሆ ጠባብ ብሄርተኛና አድሏዊ ስለሆነ፤ መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አገልጋይ ስላልሆነ፤ ግጭቶችን ሊፈታቸው አይችልም የሚል ነው። ገዢው ፓርቲ ራሱ ችግሮችን ፈጣሪ፤ ግጭቶችን ቀስቃሽ ሆኖ የፈጠራቸውን ችግሮች ሊፈታቸው አይችልም። ወንድሙን ከወንድሙ ጋር ካላጋጨ ሊገዛ አይችልም። አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች ካላደረገ ሊመዘብር አይችልም።

ይኼን ትንተና እንዳቀርብ የጎተጎተኝ ሁኔታ ዓለም ባንክ ስለ ፍትሃዊ እድገት ብዙም መናገር  የማይችል መሆኑን ስለማውቅ፤ የተዛባ እድገትና ኢ-ፍትሃዊ ገቢ ከተከሰቱ፤ እነዚህ ሁኔታዎች የሚያስከትሏቸው ህውከቶችና አደጋዎች ምን እንደሚሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማቅረብ ነው። ዓለም ባንክ በቅርቡ ስለ ኢትዮጵያ እድገት ባደረገው ሰፊ ጥናት “World Bank’s 2017–2022 Country Partnership Framework for Ethiopia” የታወቁ ባለሞያዎች ክልሎችን በማነጻጸር በመካከላቸው ጎልቶ የሚታየውን ድህነትና የሕጻናት ምግብ እጥረት (spatial or regional distribution of poverty and child malnutrition in Ethiopia) በመረጃ አቅርበውታል።

ኢትዮጵያ እድገት ማሳየቷ አይካድም። ጥያቄው ይኼ እድገት መሰረታዊና መዋቅራዊ የሆኑ ለውጦትችን አምጥቶ ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ያለው የእድገት ውጤት አስከትሏል ወይንስ አላስከተለም? የሚለው ነው። UNCTAD የጻፈው ሰፊ ዘገባ “እድገቱን” ተቀብሎ ኢትዮጵያ “መዋቅራዊ ለውጥ አላሳየችም” ወደሚል ድምዳሜ ደርሷል። ለምሳሌ፤ የገጠሩ ኢኮኖሚ አሁንም ኋላ ቀር መሆኑ፤ የኢንዱስትሪ ልማት አለመስፋፋቱ። ሆኖም፤ ይህ ድርጅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተዛባ እድገት አሳይቷል ከሚል ድምዳሜ ላይ አልደረሰም። የዓለም ባንክ ባለሞያዎች ግን ወደዚህ ድምዳሜ ደርሰዋል።

የዓለም ባንክ ባለሞያዎች ትኩረት የሰጡት በመንገድ ስራ በኩል ስላለው ሰፊ እንቅስቃሴና ለታደሉት ተጠቃሚዎች ህይወትን የሚለውጥ የልማት ውጤት መኖሩን ነው። ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ፤ ማለትም፤ ከ2006 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ያለውን የፌደራል መንግሥትንና የውጭ ለጋሶችን ኢንቬስትመንት መረመሩ። ከዚያ ከ2012 እስከ 2016 ባሉት አራት ዓመታት፤ በስድስት ከተሞች የታየውን የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት አጠቃቀም (Nightlights) አመዛዘኑ።

ከኩራዝ ወደ ኤሌክትሪክ

እነዚህ ከተሞችና አካባቢዎች “ከኩራዝና ከእንጨት”  ማብሰያና መብራት ነጻ ወጥተው ወደ ኤሌክትሪክ መብራት ተሸጋግረዋል። የመንገድና የባቡር ሃዲድ አገልግሎት እየተስፋፋ በሄደባቸው አገሮች ሁሉ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፤ የንግድ፤ የግል ተቋማት ምስረታዎች መሰረት እንደሚይዙና ቀጣይነት እንደሚኖራቸው በሌሎች አገሮች የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። ከተሜነት ከመንገድና ከሌላ የመጓጓዣ አገልግሎት፤ ከኢንዱስትሪ ልማት፤ ከትምህርት ተቋማትና ከሌሎች የዘመናዊ እድገት መስፈርቶች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። የዓለም ባንክ ጥናት እንዲህ ይላል። “Changes in road density pointed to greater economic concentration towards the center of Ethiopia and the north of the country. These are also areas of greater population density. Figure 2a shows that, between 2006 and 2016, the increase in road density was concentrated in certain regions, notably Ethiopia’s capital of Addis Ababa, as well as Tigray in the north of the country and in Oromia in the center.”

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መርሆዎች ከሚታወቁባቸው መለያዎች መካከል አንዱ የማእከላዊ መንግሥት ኢንቬስትመንት አድሏዊ፤ ክልላዊ፤ ጎሳዊና ጎጣዊ መሆኑ ነው። ለምሳሌ፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴና በደርግ መንግሥታት አብዛኛው ዘመናዊ ኢንቬስትመንት “አዲስ አበባና” ጥቂት ከተሞች ላይ ነበር። በአብዛኛው የገጠሩ ኢኮኖሚ ምንም አይነት የመሰረተ ልማት፤ የኢንዱስትሪ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስርጭት፤  የውሃ፤ የመጸዳጃ፤ የመገናኛ፤ የመብራትና የሌሎች የዘመናዊነት ስርጭት ትኩረት አልተሰጠውም ነበር።

ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ግዙፍ የውጭ እርዳታና ብድር ስለተገኘ፤ ስደተኛው በየመጣበት መንደርና ከተማ ቤት በመስራት፤ ዘመድ በመርዳትና በሌላ መንገድና ዘዴ ግዙፍ ገንዘብ ፈሰስ ስላደረገ ይህ ሁኔታ መለወጡ አያከራክርም። ከአስራ አምስት እስከ ሃያ በመቶ (from 15 to 20 percent) የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኑሮው የሚመካው ስደተኛው (ዲያስፖራ ተብሎ የሚጠራው) በሚልከው ገንዘብ ነው። ስደተኛው ለራሱና ለዘመዶቹ ቤቶች ይሰራል፤ የግል ተቋሞች ይመሰርታል። ለመጣበት አካባቢ ይቸራል። ቤተ ክርስቲያን፤ ትምህርት ቤት፤ መስጊድ፤ መጽሃፍት ቤት ወዘተ ይሰራል። አገሩን ሲገበኝ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ያጠፋል፤ በገፍ ይሸምታል። በየዓመቱ ቢያንስ ከአራት እስከ አምስት ቢሊየን ዶላር ይልካል። ከውጭ ከሚገኘው እርዳታ በላይ መሆኑ ነው። አገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ሸቀጣ ሸቀጥ፤ አገልግሎትና ሌላ የውጭ ምንዛሬ በላይ መሆኑ ነው። ለበጎም ይሁን ለክፉ፤ የማይካደው ሃቅ የኢትዮጵያ እድገት ከስደተኛው አስተዋጾ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው። ገዢው ፓርቲ ስደተኛውን የሚንከባከበው ለዚህ ነው።

ስደተኛው በገዢው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እቀባ ቢያደርግና ሕዝባዊውን አመጽ ቢደግፍ አገዛዙን ሊያንብረክከው ይችላል። ከገዢው ፓርቲ ጋር የጥቅም ግንኙነት የሌላቸው ስደተኞች ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የመንገድ ስራ መስፋፋቱን ያወሳሉ። የመንገዱ ስራ ከምርት ኃይሎች ጋር አለመያያዙን የሚያወሱም ብዙ ናቸው። “ምንም የሚመረት ነገር በሌለበት ቦታ (ባዶ ድንጋይና ተራራ ባለበት፤ የንግድ እንቅስቃሴ በማይታይበት) ዘመናዊ መንገድ መሰራቱን በቪዲዮ ቀርጸው የሚመመጡ ብዙ ናቸው። የተዛባ የፌደራል ባጀት የተዛባ እድገት ያስከተለ መሆኑን በመረጃ የሚያቀርቡ ብዙ ናቸው። ዓለም ባንክ የጻፈውን የመዛባት ሁኔታዎችና አደጋዎች እነዚህ ኢትዮጱያዊያን ቀደም ሲል ነግረውን ነበር። እኛ “ፈረንጅ አምላኩ” ስለሆንን ነው መሰለኝ ቦታ አልሰጠናቸውም። አበዳሪዎችም  እኛ ኢትዮጵያዊያን የምንጽፈውን፤ የምንናገረውን ቁም ነገር አልሰጡትም።

የመሰረተ ልማት ወሳኝነት

የመሰረተ ልማት ትርጉም ምንድን ነው?

የኤሌክትሪክ ኃይል፤ ውሃና መጸዳጃ፤ መንገድ፤ ድልድይ፤ ሃዲድ፤ ትምህርት፤ ጤና፤ ዜና፤ መረጃ፤ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ለአንድ አገር ደህንነት፤ እድገት፤ የሕዝብ ኑሮ መሻሻል ወሳኝ የሆኑ መሰረቶች  መሆናቸውን የሚያመለክት ትኩረት ማለት ነው። የዓለም ባንክና ሌሎች ጥናቶች የመሰረተ ልማትን ወሳኝነት በመረጃ አቅርበውታል። አሜሪካ በፍጥነት ያደገችው መንገዶችን፤ ሃዲዶችን፣ ግድቦችን በማስፋፋቷና ብሄራዊ ወይንም አገር አቀፍ ኢኮኖሚ ስለመሰረተች ነው። የአሜሪካ ብሄራዊ! የኢትዮጵያ ክልላዊ! ፌደራል ይባሉ እንጅ፤ ሁለቱ በጣም የተለያዩ ናቸው፤ ውጤታቸውም ይለያያል።

ዓለም ባንክ በ2009 ያካሄደው ጥናት፤ ከሳሃራ በታች የሚገኙ አገሮች እነዚህን ወሳኝ የሆኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች ስላልሰሩና የተሰሩትንም ስላልተንከባከቡ እድገታቸው በየዓመቱ ቢያንስ በሁለት በመቶ (2 percent per annum) እንዳያድግ አድርጎታል ይላል። ሰለሆነም፤ የአፍሪካ አገሮች ይኼን ክፍተት ለመሙላት ከፈለጉ በዓመት $93 billion ፈሰስ ማድረግ አለባቸው። ይኼ ግዙፍ ካፒታል ከየት ሊመጣ ነው? የሚለውን ጥያቄ አቅርቤ አንባቢ እንዲያስብበት/እንድታስብበት እጠይቃለሁ። ቁም ነገሩ እድገት ያለመሰረተ ልማት አይቻልም።

እኔ በቻድና በካሜሩን  ለአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት የኢኮኖሚ አማካሪ ሆኘ ስሰራ እነዚህ አገሮች በብዙ ወጭ የሰሯቸው መንገዶች፤ ትምህርት ቤቶች፤ የጤና ጣቢያዎችና ሌሎች እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው ፈራርሰው አይቻለሁ። ለዓለም ባንክ በጋና፤ በቶጎ፤ በናይጀሪያ፤ በኬንያ፤ በታንዛኒያና በዩጋንዳ ስመላለስ ተመሳሳይ ውድመት አይቻለሁ። መንገድ ተሰርቶ ካልተጠገነ፤ ትምህርት ቤት ተሰርቶ አስተማሪ ከሌለው ባከነ ማለት ነው።  

የኢትዮጵያን ሁኔታ ቀረብ ብየ ስከታተለው፤ ዘመናዊ የመንገድና ሌላ የመሰረተ ልማት ስራ በሁሉም ክፍለ ሃገሮች (ክልሎች) እየተስፋፋ ቢሄድ ኖሮ፤ የዜጎች እንቅስቃሴ፤ የእርስ በርስ ግንኙነት፤ ንግድ፤ የእውቀት ልውውጥ፤ የአገር አንድነትና ደህንነት ወዘተርፈ አስተማማኝ ይሆኑ ነበር እላለሁ። መንግሥት ሁሉንም ዜጎች በእኩለነት መነጽር ቢያቸው ኖሮ የእድገቱ ውጤት ሚዛናዊና ፍትሃዊ በሆነ ደረጃ እየተስፋፋ ይሄድ ነበር። በሌላ አነጋገር፤ እድገቱና የእድገቱ ውጤት ጎጣዊ ሳይሆን ብሄራዊ ይሆን ነበር። መረጃዎች የሚያሳዩት ጉዳይ፤ የፌደራሉ መንግሥት ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም አድልዎ የሚያስተናግድ የእድገት አመራር አለመቀበሉን ነው። ጠባብ ብሄርተኛ መርህ ስለሆነ፤ ሊቀበልም አይችልም። ከጅምሩ፤ የፌደራሉን መንግሥት በበላይነት የሚቆጣጠረው ህወሓት ስለሆነ ቡድኑ የባጀት ፈሰስ የሚያደርገው በፖለቲካ ውሳኔ ነው።

የዓለም ባንኩ ጥናት በካርታ ቀርጾ እንዳቀረበው (ከትንተናው ግርጌ ቀርቧል) በውጭ መንግሥታትና በአበዳሪዎች ድጋፍ “አስደናቂ እድገት” አሳይቷል የተባለው የኢትዮጵያ እድገት በአድሏዊ፤ ጎጠኛና በጠባብ ብሄርተኛ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ስለተበከለ፤ ኢኮኖሚው፤ የተፈጥሮ ኃብቱና የኢኮኖሚው ጥቅም በጥቂቶች ስለተማረከ ኢትዮጵያ ያልተመጣጠነ እድገት ስር የሰደደባት አገር ሆናለች። ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገቢና የኑሮ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ሰርቶ የሚኖረው ሕዝብ ወደ ድህነት እያመራ ይገኛል። የመሥቀል ሆነ ሌላ በዓል ሲከበር ስንት ኢትዮጵያዊ ነው “ዶሮ” ለመግዛት የሚችለው? በልቶ በሚያድረውና ጦሙን በሚያድረው መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሄዷል።

የእድገት ውጤት ሚዛናዊና ፍትሃዊ ሲሆን የማህበረሰብ ኃብት ወይንም ካፒታል አገሩን አይለቅም። ምክንያቱም፤ የመስራትና የማምረት እድሎች ዝግ አይሆኑም። የኢትዮጵያ እድገት አከራካሪ መሆኑን ለማጤን  በየዓመቱ  ከአገር የሚሰደደውን ብዙ ሽህ ወጣት ትውልድ ማጤን አግባባ አለው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቋሪ መንግሥት ስለሌለ ብዙ ቢሊየን ዶላር ኃብት ከሃገር ይሸሻል። “መንግሥት የለም” ከሚያስብሉት መካከል አንዱ ምክንያት ከህግ ውጭ የሚሸሸው ግዙፍ ኃብት ነው።

ህወሓት በበላይነት የሚያሽከረክረው የፌደራሉ መንግሥት እንዲመርጥ የተገደደው ክልል ትግራይን ነው። በሁሉም የእድገት መስፈርቶች ብናየው፤ ክልል አንድ የተለየ እንክብካቤ ይደረግለታል። ከፍተኛ ባጀትና ሌሎች ድጎማዎች ይሰጡታል። ማንም ደፍሮ ለምን ይኼ አድልዎ ይካሄዳል አይልም። ለምሳሌ፤ እጅግ በጣም ድሃና ኋላ ቀር የሆነውን የዐማራውን ክልል ቀረብ ብለን እንይ። አለጀዚራ በመረጃ እንዳቀረበልን፤ “የአማራው ክልል ከአፍሪካ የመጨረሻ ድሃ” ነው። በጤና አገልግሎት የመጨረሻ ነው። ንጹህ ውሃ፤ መጸዳጃ፤ የኤሌክትሪም መብራት አይታሰብም። የኢንዱስትሪ ልማትና ከዚህ ጋር የተያያዘ የስራ እድል ህልም ነው። ለከፍተኛ ትምህርት አገር ቤትና ውጭ አገር ለመማር ያለው እድል የትግራይን ክልል አንድ መቶኛ አይሆንም። የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት በጣም ዝቅተኛ ከሆነባቸው ክልሎች መካከል አንዱ የአማራው ክልል፤ በተለይ የጎንደር ክፍለ ሃገር ነው። የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት ብዙ እምቅ ኃብት እንዳለ ይታወቃል። ሆኖም፤ የአካባቢው ሕዝብ እንዲጠቀም ስለማይፈለግ ኢንቬስተሮቹ የሚመረጡት በብሄርና በታማኝነት ነው።

ይኼ ግልጽ የሆነ አድልዎ እንዳለ ሆኖ፤ ከበፊቱ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር፤ መንደሮች፤ ከተሞች፤ ዘመናዊ የመንገድ ስራዎች መስፋፋታቸው አይካድም። እነዚህም ውጤቶች የተገኙት ከብዙ ሕዝባዊ ግፊትና አቤቱታ፤ ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ ነው። ሆኖም፤ የአማራው ክልል በኢትዮጵያ ሁለተኛውን የሕዝብ ብዛት የያዘ ቢሆንም፤ በማንኛውም የእድገት መስፈርቶች ከትግራይ ክልል ጋር ሊነጻጸር አይችልም። በነፍስ ወከፍ ገቢ፤ በጤና አገልግሎት፤ በከፍተኛ ትምህርት እድል፤ በንጹህ ውሃ፤ በመጸዳጃ፤ በምግብ አቅርቦት፤ በባንክና በብድር አገልግሎት መስፈርቶች ሲወዳደር የአማራው ክልል የተለየ በደልና ግፍ ደርሶበታል።

ትግራይ የተመረጠ ክልል መሆኑ አያከራክርም። የተመረጠ ክልል ልዩ እንክብካቤ ይደረግለታል፤ አንበሳውን የፌደራል ባጀት ያገኛል። ይህ ግዙፍ የባጀት ፈሰስ የሚካሄደው ግልጽ በሆነ ደረጃ አይደለም። የድጎማ ዘዴዎች ብዙ ስለሆኑ አልፋቸዋለሁ። የውጭ መንግሥታት ተወካዮችን፤ አምባሳደሮችን፤ ለጋሶችን፤ ደጋፊዎችን ወዘተ፤ “ትግራይ ነጻ አገር ነው” በሚያስብል ደረጃ   የሚያስተናግድ ክልል ትግራይ ነው። እንደ ነጻ አገር ሆኖ “የራሱን ወታደሮች፤ ልዩ ኃይል፤ አጋዚ የተባለ ጦር” ወደ ጎንደር የሚልክና ሰወቻችሁን አስረክቡኝ፤ መሬታችሁን ስጡኝ ይሚል የክልል አስተዳደር ትግራይ ነው።

በእኔ እምነት የዚህ ሁሉ የበላይነት አሉታዊ ውጤት መታየት ያለበት፤ በሕዝቡ ላይ በግልጽ የሚታየው ማህበረሰባዊ ጉዳት  ነው። ያልተመረጠውና ሆነ ተብሎ ወደ ኋላ እንዲቀር የተወሰነበት ወይንም ፈጽሞ ችላ የተባለው የአማራው ክልል በድህነት ኡደት (Vicious cycle of poverty) ሲማቅቅ ይኖራል። የፌደራል አገዛዝ ስለሆነ ይኼ የጠባብ ብሄርተኝነት አድልዎ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ አግባብ አለው።

ምክንያቱም፤ የፌደራሉን መንግሥት የሚቆጣጠሩት የህወሓት ባለሥልጣናት ናቸው። እነዚህ ባለሥልጣናት ሆነ ብለው የመሰረተ ልማት፤ በተለይ የውሃ ኤሌክትሪክ መሳቢያ ግድቦች፤ የመንገድና የሃዲድ ስራዎች፤ የአየር ማረፊያ፤ የከፍተኛ ትምኅርት ተቋማት ወዘተርፈ ባጀት ፈሰስ ያደረጉባቸው ክልሎች በሰሜን ትግራይ፤ በማህል አገር አዲስ አበባ፤ በደቡብ ኦሮሚያ ናቸው። ከእነዚህም አንበሳውን ክፍል የያዘው የትግራይ ክልል ነው። ይህ ሁኔታ በአይን የሚታይ፤ የሚዳሰስ ስለሆነ ልዩ ጥናት አያስፈልገውም። ዓለም ባንክ ያደረገው ጥናት ጥቅም የለውም ማለት አይደለም፤ አለው። ችግሩ ጥናቱ ሳይሆን ፖሊሲው ነው። ዓለም ባንክ ችግሩን ነገረን። መፍትሄውን መፈለግ ያለብን እኛው ነን።

በመናገሻ ከተማዋ ላይ የተደረገው ልዩ ኢንቬስትመንት ይገባኛል። አዲስ አበባ ዋና መናገሻ ከተማ ከመሆኗ በላይ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስለሚገኙባት፤ የኢንዱስትሪና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ የፌደራል መንግሥት አስተዳደር ወዘተ መአከል ስለሆነች የከተማ መሬት ዋጋ ከናረባቸው መካከል አንደኛውን ደረጃ ይዛለች። የመሰረተ ልማት ስራ የተጀመረው በአሁኑ አገዛዝ አይደለም፤ አዲስ አበባ ከተመሰረተችብት ጊዜ ጀምሮ ነው። ስለዚህ አንድ ግለሰብ ውይንም ቤተሰብ ወይንም ተቋም ኃብታም ለመሆን ከፈለገ አዲስ አበባ ቤትና ንብረት እንዲኖረው ይገደዳል። ይኼ ሁኔታ በሌሎችም አገሮች የተለመደ የእድገት ሄደት ነው።

ኦሮሞያ በለም መሬት የታወቀ ክልል ከመሆኑም በላይ የብዙ ኢንዱስትሪዎች፤ የዘመናዊ እርሻዎች፤ ለውጭ ገበያ የሚላክ የአበባ አትክልት፤ የቅጠላ ቅጠል፤ የተለያዩ እህሎች፤ የቡናና ሌላ ለገበያ የሚቀርብ የሚመረትባት፤ የወርቅና ሌላ መአድን የሚመረትባት፤ ለቱሪዝም አመች የሆኑ ቦታዎች ያሉባት፤ በአጭሩ ኃብት ሊካበትባት የምታስችል ክልል ናት። የመሬት ነጠቃና ቅርሚት በሰፊው ከሚካሄድባቸው ክልሎች መካከል አንዷ ናት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ ለማግኘት ከተፈለገ ኦሮሞያና ተመሳሳይ ለም ክልሎች ላይ ኢንቬስት ማድረግ አስፈላጊ ነው። የውጭ ኢንቪስተሮች ብዙ ቢሊየን ዶላር ኢንቬስትመንት ፈሰስ ያደረጉባቸው አካባቢዎች አዲስ አበባና ኦሮምያ ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ ፍላጎት ስላለ፤ የመሬት ዋጋ ከወርቅ ዋጋ በላይ እየናረ ይሄዳል የሚባለው የወደፊት ጥቅሙንም በማየት ነው።

ለማጠቃለል፤ የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚያሳየው ሁኔታ አሳሳቢ ነው። እድገት መኖሩ ብቻ የዜጎችን ደህንነት፤ ጤናማነትና ከዱሮው የተሻለ ኑሮ መኖር አይነግረንም። እድገት አለ ሲባል ትርጉም የሚኖረው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኑሮና ህይወት ተሻሽሏል የሚያስብል መረጃ ሲኖር ነው። መጠየቅ ያለበት፤ እድገቱ ኢ-ፍትሃዊ የሆነበት ዋና ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ነው።

በክልሎችና በሕዝቦች መካከል የተመጣጠነ የፖለቲካ ስልጣን የለም። የእድገት ተጠቃሚነት፤ የነፈስ ወከፍ ገቢ፤ የግለሰቦች የኑሮ ሁኔታ ተዛብቷል። በክልሎች መካከል የሚታየው ያልተመጣጠነ እድገት ዙሮ ዙሮ የሚለካው በዜጎች ደህነነት ወይንም ድህነት ነው። የትምህርት አገልግሎት ጥራት፤ የጤና አገልግሎት ስፋት፤ የቤተሰቦች የኑሮ ሁኔታ (የሚጠጣ ንጹህ ውሃ፤ የሚኖርበት ቤት፤ መጸዳጃ፤ የኤሌክትሪክ መብራት፤ ሬዲዮና ቴሌቪዢን ወዘተ) የተዛባ ስርጭት ያሳያሉ።

ዓለም ባንክ ሊናገረው ባይፈቅድም፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን የያዘው ክፍል፤ ማለትም ህወሓት፤ የእድገቱ አንበሳው ተጠቃሚ ነው። ህወሓት ራሱን ኃብታም አድርጎ “ለራሱም ብሄር” ተርፏል። ስልጣኑ የተገፈፈው ክፍል በድህነት ይማቅቃል። ጥናቱ እንዳስቀመጠው “Remote and economically lagging regions, and Amhara Region, see lesser increases in road density. Taking the development of roads as a proxy for the development of infrastructure, this suggests that infrastructure development has not been homogeneous across all regions. It also shows that road connectivity for some regions is poor, both within those regions and with other regions, with consequences for labor mobility, the transportation of goods and services, and for agricultural productivity as the distance and travel times to markets are longer.”

ለም መሬት፤ ወንዞች፤ ታሪካዊ ቦታዎች ወዘተርፈ ያለው የአማራው ክልል እና ሩቅ ናቸው የሚባሉት፤ ግን እምቅ የተፈጥሮ ኃብት ያላቸው፤ ጋምቤላ፤ ቤኔ ሻንጉል ጉሙዝ፤ አፋር፤ ኦጋዴን ለምን ጎልቶ በሚታይ ደረጃ ወደኋላ እንዲቀሩ፤ በድህነትና በየእርስ በርስ ግጭቶች ኡደት እንዲሰቃዩ ተደረገ ወይንም ባይደረግም ተፈቀደ? የሚለውን ጥያቄ በመጀመሪያ ደረጃ መመለስ ያለበት ያልተመጣጠነ የክልሎች እድገትና የነፈስ ወከፍ ገቢ ፖሊሲ የሚከተለው ህወሓት/ኢህአዴግ ነው። ሆኖም፤ ይህ ቡድን ችግሩን ፈጣሪ ስለሆነ ሌሎቻችን በታሪክ ተጠያቂዎች ነን። መልስና አማራጭ መስጠት ግዴታችን ነው።

የዓለም ባንኩ ኢኮኖሚስት ማይክል ጊገር የደመደመው ትክክል ነው። ሌሎቻን በተደጋጋሚ እንዳሳሰብነው፤  ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ፤ ስላምና እርጋታ፤ አብሮና ተቻችሎ መኖር ሊኖር የሚችለው ገዢው ፓርቲ የሚከተለው የእድገት ፖሊሲ ሁሉንም የኢትዮጵያን ዜጎች፤ በዜግነታቸውና በሰብእነታቸው መስፈርት ብቻ የእድገቱ ተካፋዮችና ተጠቃሚዎች ሲያደርግ ነው።

ይህ ምኞት ሆኖ እንዳይቀር ከተፈለገ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የፖለቲካው ስልጣን ባለቤት መሆን አለበት። የፖለቲካ ስልጣን ሽግግር ያስፈልጋል የምልበት ዋና ምክንያትም ይኼው ነው።

እስካሁን ያየሁት አስጊ ሁኔታ ያስተማረኝ አበይት ጉዳይ እንዲህ የሚል ነው። ሚዛናዊነት የሌለው የህወሓት/ኢህአዴግ የእድገት መርህ ግጭቶችን ፈጥሯል። በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው የገቢና የኑሮ ልዩነት አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። አበዳሪ ድርጅቶች ከደሙ ንጹህ አይደሉም። አበዳሪ ድርጅቶችና መንግሥታት ሁኔታውን ችላ ብለው ያዩታል። እኛ ጫና ማድረግ ያለብን አበዳሪዎችና እንደ ቻይና ያሉ ራሳቸውን የሚጠቅሙ የብድር ለጋሶች የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ ከሰብአዊ መብቶች መከበር ጋር እንዲያይዙት አቤቱታ ማቅረብ ነው።

በዚህም መሰረት፤ የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ድርጅቶች፤ ግለሰቦች፤ አባቶች፤ እናቶች፤ እህቶች  በአንድ ላይ ሆነው የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊሰጥ የመደበውን ባጀት፤

  • ከሕግ የበላይነትና ከሰብአዊ መንቶች መከበር ጋር እንዲያይዛቸውና

 

  • የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ዓለም ባንክ የሚለግሰውን ድጋፍ ለመጠቀም ከፈለገ፤ በሕዝቦችና በክልሎች መካከል የሚደረገው አድልዎ እንዲቆምና ሁሉም ሕዝቦችና ክልሎች የእድገቱ ተካፋዮች እንዲሆኑ ቃል እንዲገባ፤ አለያ ድጋፉ እንደሚቆም አቋም መወሰድ ነው፤

 

  • ህወሓት/ኢህአዴግን የሚደግፉ መንግሥታትና ለጋስ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን አደጋ በቀላሉ ካዩት ኢትዮጵያ የነገዋ ሶማሊያ፤ ሶሪያ ወይንም ደቡብ ሱዳን ትሆናለች። እንዲያውም፤ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከእነዚ አገሮች የባሰ ሊሆን ይችላል።

 

  • ምክንያቱም፤ የኢትዮጱያ ሕዝብ ብዙ ነው፤ የአገሪቱ አቀማመጥ ቁልፍ ነው። ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶች ተከባለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዳጆችና ሁሉም ቅንነት የሚያሳዩ ኢትዮጵያዊያን አዲስ ስታንዳርድ የተባለው ጋዜጣ በርእሰ አንቀጹ September 27, 2017 “Ethiopia is grappling with heightened risk of state collapse” በሚል ያቀረበውን በጽሞና አይቶ የአቋም ለውጥ ማድረግ ታሪካዊ ግዴታ ነው። “It is time for orderly transition… Ethiopia is fast descending into turmoil as the result of incessant state-sanctioned violence and repression. Popular demands that precipitated a three year-long protest,which started in Oromia in 2014 and then spread to the Amhara and other regions, remain unaddressed.

 

  • The discontent in the two most populous regional states, Oromia and Amhara, home to two-thirds of thecountry’s population of over 100 million, is deep and widespread. The resulting anxiety, expressed by serious Ethiopia watchers, is confirmed by the country’s leader, Prime Minister Hailemariam Desalegn, who once warned that the continued protests could push Ethiopia into a situation similar to what has prevailed in neighboring Somalia for the last 26 years: state collapse.”

 

ከዚህ የበለጠ ብሄራዊ ጥሪ ለማድረግ አይቻልም። ይህ እድል ካመለጠን ሌላ እድል ይኖረናል የሚል ግምትም ሆነ እምነት የለኝም።

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

የመንገድ ስራ የተስፋፋባቸው የትግራይ ክልል፤ አዲስ አበባና አካባቢወቿ

የመሰረተ ልማት ስፋት፤ ጥልቀትና የማታ የኤሌክትሪክ መብራት ስርጭት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.