አለምነው መኮንን የበላይነቱን ያሳየበት የብአዴን ነገር! – ሙሉቀን ተስፋው

እነ አለምነው መኮነንና አጋጣሚውን በመጠቀም ወደ ሥልጣን የሚሮጠው አቶ ብናልፍ አንዷለም ተስፋየ ጌታቸውንና ሰማ ጥሩነህን ሲያብጠለጥሏቸው ሰነበቱ፡፡
እነ ሰማና ጌታቸው ዋና ሲሰደቡበት የሰነበተው የመቀሌውን የእርቅ ጉባኤ አንሳተፍም የሚል ግልጽ አቋም በማሳየታቸውና ሌሎች የብአዴን ሰዎችን በንቀት ያያሉ በማለት እነ አለምነውና ብናልፍ ሞልጨዋቸዋል፡፡ አፈ ቅቤው የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ንጉሡ ጥላሁን ያለበትና የእነ የአለምነውን ቡድን የያዘ ሙሉ በሙሉ የብአዴንን የሥልጣን ኮርቻ የሚቆጣጠር ቡድን በእነ ካሣ ተ/ብርሃንና ከበደ ጫኔ እርዳታ ጎልቶ እየወጣ ነው፡፡ ንጉሡ ጥላሁን በጮኸበት ሁሉ መልስ መስጠት ላይ አተኩሯል፡፡

 

አለምነው መኮንን ሊመታቸው ካሰባቸው ሰዎች የከበደው አቶ ጌታቸው ነው ተብሏል፡፡ ከአለምነው ጋር በቀኝ ተሰልፎ ከአዲስ አበባ ባሕር ዳር እየተመላለሰ ለሕወሓት ወሬ የሚያቀብለው አቶ ያለው አባተ ነው፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደጋፊ አጥቻለሁ በሚል ተሳቆ ብዙ ጊዜ በሩን ዘግቶ ብቻውን ይውላል፡፡ አቶ ደመቀ መኮንን የታችኛውን ብአዴን አባላት ልብ ለመግዛት በጣም እየጣረ ነው፤ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የቢሮ ኃላፊዎችን ቀስ በቀስ እያስወገዳቸው እንደሆነ የሚገልሩት ምንጮች ሆን ብሎ ሲያስመስል ነው በሚል አመኔታን አጥቷል፡፡ 

 

በሙስና የተጨማለቁት የሕወሓት ወኪሎቹ ጌታቸው አምባዬ፣ ከበደ ጫኔና አህመድ አብተው የእነ አለምነውን ቡድን በማጎልበት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ ባሕር ዳር ያለው የጋሳ ሆቴል ባለቤት ለጌታቸው አምባየና ለከበደ ጫኔ ለእያንዳንዳቸው የሁለት ሚሊዮን የሁለት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ቤት ከ5 ዓመታት በፊት ገዝቶላቸዋል፡፡ 

 

አቶ አህመድ አብተው ደግሞ የገጠር መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊ በነበረበት ወቅት ለመሥሪያ ቤቱ የመጣ ቡልዶዘርና መንገድ አራሽ መኪናዎችን በስሙ ሊብሬውን አዙሮ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኦዲተሮች አጋልጠውት ነበር፤ ሆኖም የሱ ጉዳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ ይሰጠዋል ተብሎ ወዲያውኑ የሚንስቴርነት ማዕረግ አግኝቶ ወደ አዲስ አበባ ተዛወረ፡፡ አቶ አህመድ ደቡብ ወሎ ተወልዶ ያደገባትን ቀበሌ መንገድ ለማሠራት ሲል የሐይቅ እስጢፋኖስን ሐይቅ አደጋ ላይ የጣለ ሥራ አሠርቷል፡፡ በዚህ መንገድ ሥራ ቅየሳ የተነሳ ወደ ሐይቁ የሚገባው ደለል በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆነ ባለሙያዎች ብዙ ጊዜ ቢናገሩም ጉዳዩ ታፍኖ ቀርቷል፡፡ አቶ አህመድ ሐይቅ ከተማ የተገነባ ፍሳሹን ወደ ሐይቁ የሚያስገባ አንድ ሎጂ ላይ የአካባቢ ጥበቃ እርምጃ ሊወስድ ሲልም አስቁሟል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.