እውን የትግራይ ህዝብ በህውሓት ትግል ተጠቃሚ ነው ?? !! (ናትናኤል አስመላሽ )

በህውሃት ትግል ሁሉም የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚ አድርጎ የሚያይ ኢትዮጲያዊ የሌላ ቢሄር ተወላጅ ብዙ ነው። አንዳንዶቹ የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝብ ስለሚጠሉት በነሱ ቤት ሁሉም ተጠቃሚ ነው። አንዳንዱ አዲስ አበባ ያለውን የህውሓት አመራሮች ፎቅ እየቆጠረ ሁሉም ትግራዋይ ያለፈለት ይመስለዋል። አንዳንዱ በመንግስት ተማሮ ጥላቻ ካሳደረ ቦሃላ ገዢ መደብ እና ህዝብ መለየት አቅቶት ሁሉም ያው ናቸው የሚል ነው። ከወደ ትግራይ የሚሰማ ስቃይ ግን ሌላ ነው፣ ማንም ያላየው ያልሰማው ስቃይ አለ። በፎቶው ላይ የምታይዋቸው ሁለቱም የህውሓት ታጋዮች የነበሩ ናቸው። ታጋይ ሃይለኪሮስ ታፈረ እና ታጋይ መብርሂት ገ/ሂወት(ጓል ፊውዳል) ይባላሉ።

እውን የትግራይ ህዝብ በህውሓት ትግል ተጠቃሚ ነው ?? !! (ናትናኤል አስመላሽ ) 1

ታጋይ ሃይለኪሮስ ታፈረ እንደማንኛውም ለውጥ ፈላጊ; ወጣት በነበረበት ወቅት ደርግን ለመጣል መስዋእትነት ከከፈሉ ወጣቶች አንዱ ነው። ታጋይ ሃይለኪሮስ ታፈረ በጦርነቱ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ አራት ጊዜ የቀዶ ጥገና አድርገዋል። ከዚህ ሁሉ አመታት ቦሃላ አሁን ሂወቱ አደጋ ውስጥ ትገኛለች። ይህንን የጤና ችግር ታክሎበት፣ ትግራይ ውስጥ ባለው የመልካም አስተዳደር ችግር ህውሓት ስለተቃወመ እና የዓረና ፓርቲ አባል ስለሆነ ብቻ፣ የነጻ የህክምና አገልጉለቱ እንዲቋረጥ ተደርገዋል። ከዚህ አልፎ መሬቱ ተቀምቶ ለህውሓት አባል እንዲሰጥ ተደርገዋል። የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ማህበርም፣ ህውሓት መቃወም ስለጀመረ እና የዓረና ፓርቲ አባልም ስለሆነ ከማህበሩ አስወግዶታል።

ታጋይ መብርሂት ገ/ሂወት(ጓል ፊውዳል) የ 1973 ዓ/ም ታጋይ ናት። በቀይ ኮኮብ ዘመቻ ከትግራይ ወደ ኤርትራ ሄዳ በናቅፋ እና በሳሕል ተራሮች መስዋእትነት የከፈለች ታጋይ ናት። ታጋይ መብርሂት ገ/ሂወት(ጓል ፊውዳል) ባሳለፈቻቸው ጦርነቶች ሰዎስት ጊዜ ቆስላለች፣ አምስት ጊዜ የቀዶ ጥገና ህክምና አድርጋለች፣ ከጭንቅላትዋ ውስጥ እስካሁን ድረስ ጥይቱ አልወጣላትም። ባለ ቤትዋም ታጋይ ኣባዲ ሓጎስ(ወዲ ራያ) ከተሰዉ ታጋዮች አንዱ ነው። ታጋይ መብርሂት አሁን በሁለት መቶ ብር ቤት ተከራይታ ትኖራለች፣ ለአራት ወራቶች ታማ ስለነበር የቤት ኪራይ መክፈያ አልበራትም። ታጋይ መብርሂት ትግሉ ለኛ ታዛቢዎች ለሌሎቹም ሆዳሞች አድርጎናል ትላለች፣ ታጋይ መብርሂት እርጅናም ተጫጭኖባት ሂወት ለማሸነፍ ሙዝ እና ብርቱካን እየሸጠች ትኖራለች።

እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ከህውሓት ትግል ተጠቃሚ አይደለም የምንለው ለዚህ ነው። ከትግሉ ተጠቃሚ የሆኑት ጥቅቲ የህውሓት አመራሮች እና ቤተሰቦቻቸው ናቸው። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ኑሮ ይህ ይመስላል። ህዝብ እና ገዢ መደብ መለየት አቅቶዋቹ ትግራዋይ ሁሉ ተጠቃሚ ነው የምትሉን ትግራይ ወረድ ስትሉ፣ ትግራይ ታጋይ ሃይለኪሮስ ታፈረ እና ታጋይ መብሪህት ትመስላለች። ሁለቱም አሁን በከፋ ችግር ውስጥ ይገኛሉ። መርዳት የምትችሉ በባንክ ሂሳባቸው በኩል መርዳት ትችላላቹ። በህውሃት ትግል የተጠቀመ ህዝብ የለም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.