በጣና ሃይቅ ላይ የተስፋፋውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ የተዘጋጀው የእግር ኳስ ውድድር በባህርዳር ስታዲየም እንዳይካሄድ ታገደ

ውድድሩ በጠባብ ስታዲየም እንዲካሄድ የተወሰነ ሲሆን ወሳኔውም በኳስ ሜዳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋት መሆኑም ተመልክቷል። የእምቦጭ አረም በጣና ሃይቅ ላይ ያደረሰውን ጉዳትና የደቀነውን አደጋ ለማስገንዘብና ገንዘብ ለማሰባሰብ በተዘጋጀው የእግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድን ከአዲስ አበባ ወደ ባህርዳር መጓዙም ተመልክቷል። አላማውን ለማገዝና የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድንን ለመደገፍ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም በሳምንቱ መጨረሻ ባህርዳር እንደሚገቡ በመጠበቅ ላይ ናቸው። የፊታችን እሁድ በባህርዳር ስታዲየም በቅዱስ ጊዮርጊስና በባህርዳር ከነማ መካከል ውድድሩ ሊካሄድ ቀናት ሲቀረው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወጣ ማሳሰቢያ ጨዋታው ከባህርዳር ስታዲየም ወደ ጠባቡ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንዲገፋ ተደርጓል።

በዚህም በጣና ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመታደግ በገንዘባቸው ጭምር ድጋፍ ለማድረግ ቀጠሮ የያዙ የኳስ ተመልካቾች ከአዲስ አበባ የተጓዙት ጭምር ቦታ ማግኘታቸው አጠራጣሪ ሆኗል። የእግር ኳስ ፊዴሬሽኑ ማሳሰቢያውን ያወጣበትን ምክንያት ባይገልጽም አላማው በሰፊው ስታዲየም ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ግምት እንደሆነም ተመልክቷል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ወደ ባህርዳር የተጓዘው እምቦጭ አረሙን ለማስወገድ የሚደረገውን ሒደት በመደገፍ ለወዳጅነት ጨዋታ መሆኑ ይታወቃል።

የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንን እንደ አጋር ስለሚመከተው በቡድኖቹ ጨዋታ የደጋፊዎች ቅራኔ ወይንም ግጭት እንደማይከሰትም በርካቶች ይናገራሉ። በጸጥታ መስሪያ ቤቶች ግፊት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጻፈው በተባለው ደብዳቤ ጨዋታው ወደ ጠባብ ስታዲየም የተገፋው ከቢሾፍቱው የእሬቻ በአል ጋር በመገጣጠሙ እንደሆነም ታምኖበታል። የባህርዳር ሕዝብ በስታዲየሙ የእሬቻ ሰማእታትን ለማስብ እንቅስቃሴ ያደርጋል በመንግስትም ላይ ተቃውሞ ያቀርባል የሚል ስጋት በመንግስት በኩል መኖሩ ተመልክቷል። በትልልቆቹ ሁለት ብሔረሰቦች ዘንድ የአጋርነትና የድጋፍ ስሜት መንጸባረቁ በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን የማያስደስት መሆኑም ሲገለጽ ቆይቷል። መንግስት የጣና ሃይቅ ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመታደግ የሚያሳየው ቸልተኝነት ሕዝቡን ያስቆጣ በመሆኑ ይሄ ደግሞ ሌላ ተቃውሞ ይቀሰቅሳል የሚል ስጋት አለ።

የእምቦጭ አረሙን ለመከላከል የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው የሚያደርጉትንም እንቅስቃሴ መንግስት እያወከ በፓርቲ መዋቅር ሌሎችን እያደራጀ መሆኑም ታውቋል። የፊታችን እሁድ ከባህርዳር ከነማ የእግር ኳስ ቡድን ጋር በባህርዳር ስታዲየም ሊያካሂድ የነበረው ጨዋታ ወደ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የተገፋበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በቀጣዩ ማክሰኞና ሀሙስ በተመሳሳይ ከፋሲል ከነማና ከአውስኮድ ጋር በባህርዳር ስታዲየም እምቦጭ አረሙን ለመግታት የሚያደርገውን ዘመቻ ለመደገፍ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል።

ልሣነ ዐማራ-

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.