የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ መልዕክት ከቂሊንጦ ወኅኒ ቤት

የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች፣

አምባገነኑ የኢሕአዴግ መንግሥት ላለፉት 26 ዓመታት ሕዝባችንን በመከፋፈልና እርስበርስ በማጋጨት ለረዥም ዓመት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ባለው ፍላጎት የተነሳ ታሪክን ያለባሕሪው በማሳጠርና በማጣመም ሲመራ ቆይቷል። ሥም ማውጣት የሚያውቅበት የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊካዊ ሌላ ሌላም እያለ ነገር ግን በተግባር የሌለና አሀዳዊ ስርዓት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የይስሙላ ፌዴራሊዝም በራሱ የግጭት መነሻ ሆኖ ይገኛል። ዴሞክራሲያዊ የሚለውም ሀገርን በብቸኝነትና በብሔር የበላይነት እየመራ፣ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብቶች ተነፍገው፣ የሙያ ነጻነት ጠፍቶ አድርባይነት በነገሠበት አገር ውስጥ ስለ ዴሞክራሲ ሲያወራ እንሰማዋለን። ሕወሓት አገሪቱን በብቸኝነት በመያዝ እንደፈረስ የሚጋልባቸው ሌሎች ድርጅቶችን በማስተካከል የፖለቲካውም፣ የኢኮኖሚውም የበላይ በመሆን ንጉሥ ሆኖ መቀጠል ይፈልጋል። ይህ ፍላጎቱ እንዲሳካለት ደግሞ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ሕዝቡ እርስበራሱ እንዲፈጠር መንግሥታዊ ሽብር በመፍጠር እና ከኔ በላይ ለኢትዮጵያ በማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደግል ንብረቱ ማድረግ ይፈልጋል። በተወሰነ መልኩም በዚህ የተነሳ ጊዜ አሳልፏል። ነገር ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ያለውን የብሔር የበላይነት በደንብ ተረድቶ ጥያቄም እያቀረበ ይገኛል። በተለይም የፌዴራል ተቋማት የሚባሉት የሚባሉት በሙሉ፣ መከላከያ 4ቱም ዕዞች፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤት እና የአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የአመራርነት ቦታዎች በሕወሓት አባላት ተይዞ ይገኛል። ኢኮኖሚውም በዚህ የሕወሓት አባላት ተዘርፎ የተያዘ ነው። በአዲስ አበባ የሚገኙ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ የመንግሥት ኪራይ ቤቶች፣ አክሲዮኖች እና ሌሎችም ባልተወለደ ልጅ ሥም ሳይቀር ተይዞ ይገኛል።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣

የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት አገሪቱ በሁለት አሐዝ አድጓል የሚለው ከራሱ እና ከአባላቱ የኑሮ ደረጃ አንፃር ታይቶ እንጁ የሕዝባችንን ኑሮ የማይወክል መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ ዕድገት ሊባል የሚገባው አይመስለኝም፣ አይደለምም። ሕዝቡ የሚበላው ሲያጣ የሕወሓትን ንብረት አይደለም ሕይወታቸውንም አስጊ ነው። በአንድ ቀን ውስጥ ተቃጥሎ ወድሞ እንደሚያድር መረዳት ይኖርባቸዋል።

ነገር ግን ከዚህ በፊት እንደሚያግበሰብሱት አልሆንላቸው ያሉ አመራሮች ለኮንትሮባንድ መንገድ ለማስከፈት ሲባል ሕዝብ ለሕዝብ ማጋጨት ተያይዘውታል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል የተፈጠረው ግጭት ዋና አቀነባባሪው የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ነው። የሶማሌን ሕዝብ በጅምላ አልሻባብ ብሎ በመፈረጅ ሲገድል ኖሯል። በተመሳሳይም የኦሮሞን ሕዝብ ኦነግ ባመለት በጅምላ እና በተናጠል ሲገድል ቆይቷል። እየገደለም ይገኛል። የሁለቱም ብሔሮች ሕዝቦች በዚህ 26 ዓመት ውስጥ የመከራ ዘመን ሲያሳልፉ ቆይተዋል። አሁንም በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። ገሎ ገዳይ አፈላላጊው የሕወሓት መንግሥት በአንፃሩ አስረሽ ምቺው ጭፈራ ላይ ይገኛሉ። በሕዝብ ደም የሚደሰት በመግደል እና በማሰር የሚያምን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የሆነ ዘረኛ መንግሥት ሕወሓት ነው።
ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በአማራ ያደረገው ጭፍጨፋ ከላይ ለጠቀስኩት ባሕሪውን የሚገልጹ ከብዙዎቹ በጥቂቱ ናቸው።
ባለፈው ዓመት በእሬቻ በዓል ላይ የኦሮሞ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ መልሶ ተቆርቋሪ ለመምሰል ሐውልት አቁሟል። የሚገርመው መከላከያ ምን ቤት ሆኖ ነው ሐውልት የሚሠራው? ሁለተኛ ደግሞ የተጨፈጨፉ ዜጎቻችንን ባለቤት ሳይሰጠው ማለትም እንደለመደው ፀረ ሠላም ማለት ካልሆነ ደግሞ መንግሥት ራሱ ኃላፊነቱን ወስዶ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው በእብሪትና በመኮፈስ ሕዝብ ምንም አያመጣም በማለት አሸዋ እና ሲሚንቶ ቀላቅሎ ማቆም ተገቢ አይደለም። የሕዝቡን በዓል በግድ ቀምቶ ለመውሰድ ባደረገው ግብግብ የገደላቸው መሆኑን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይረዳዋል ብዬ አምናለሁ።

የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች፣
በመለያየት ሳይሆን አንድ ላይ በመሆን በእኛ ላይ እየነፈሰ ያለውን አየር መከላከልና ወደ ስርዓቱ መመለስ ይኖርብናል። ጊዜ በሰጠነው ቁጥር ነገ ሐዋሳ ላይ ወላይታና ሲዳማን፣ ድሬዳዋ ላይ ኦሮሞን ከሶማሌ እና በሌሎች የአገራችን ክፍሎች ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ሳይፈጠርና አንዱ ያንዱ ስጋት ሳይሆን መንቀል ይኖርብናል።
በአጠቃላይ ስርዓቱ ሕዝብ የሚለው በራሱ ዙሪያ ያሉትንና ለስርዓቱ ታማኝ አገልጋዮችን ብቻ ነው። ስለዚህ በተለያየ ጊዜ ከስርዓቱ በሚመዘዙ ካርዶች ሳንደናገር አገራችንን ጠብቀን የጋራ ጠላታችንን የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥትን ይበቃሃል ልንለው ይገባል። ሁሌም እንደምንለው ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ለመደበቅ ይፈልጋል። በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ኪሱ ጠብ ያለለት ነገር የለም። ስለዚህ በስርዓቱ ላይ የሚደረገው የይበቃሃል ጥያቄ ወደ የዋሁ የትግራይ ሕዝብ እንዳይደባለቅ በመጠንቀቅ እና የትግራይን ሕዝብ በጎን በማሰለፍ በሕወሓት ላይ መዝመት ያስፈልጋል።

የንግድ ተቋሞቻቸው ገብቶ ባለመገልገል በአጠቃላይ የሕወሓትን ንብረት ባለመጠቀም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር እንዲያደርግ እጠይቃለሁ።
በመጨረሻም በኦሮሚያም ይሁን በሶማሌ ሕዝብ ላይ ሰሞኑን የተደረገው ጭፍጨፋ ከልብ አሳዝኖኛል። ይህንን አስነዋሪ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ተግባር ከንፈር በመምጠጥ ሳይሆን በመታገል ሳይሆነረ ሌላ ጉዳት ሳይጨምር የሥልጣን ዘመኑን ማሳጠር ያስፈልጋል። ይህ እንደሚሆንም በኢትዮጵያ ሕዝብ እተማመናለሁ።

መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ከቂልንጦ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.