ኦሮምኛ ከአማርኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ሊሆን ይገባል ወይ? በቋንቋ አጠቃቀም ላይ የቡድንና የግለሰብ መብት እንዴት ይጠበቃል?

“ኦሮምኛ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከአማርኛ ጋር በተጓዳኝ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት!” የሚለው ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጽንፈኛ የኦሮሞ ልኂቃን የኦሮሞ ሕዝብ “እነኝህ እነኝህ ነገሮች ካልተፈጸሙልን በስተቀር አብረን መቀጠል አንችልም! መገንጠል ነው የሚኖርብን!” ብሎ እንዲያስብ ለማድረግ “አብላጫ ቁጥር አለንና!” በማለት ከሚመዟቸው የመቆመሪያ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይሄው ዘወትር ደጋግመው እያሰሙት ያለ ጉዳይም ነው፡፡

ከነሱ በኋላም አንዳንድ የአንድነት ኃይሉ ፖለቲከኞችም (እምነተ አሥተዳደራውያን) ጥያቄውን ተቀብለውት “አዎ መሆን አለበት! ወደፊት በምንፈጥራት ዲሞክራሲያዊት (መስፍነ ሕዝባዊት) ኢትዮጵያ የምናስተናግደው ይሆናል!” እያሉ ከወዲሁ ቃል እየገቡ ይገኛሉ፡፡ እነኝህ የአንድነት ኃይል ፖለቲከኞች አላስተዋሉም ወይም ዴሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም ማለት ነው እንጅ በዴሞክራሲያዊት (በመስፍነ ሕዝባዊት) ኢትዮጵያ ኦሮምኛ ከሌሎች ቋንቋዎች ተለይቶ ከአማርኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋ የመሆን ዕድል አይኖረውም፡፡ እንዴት? የሚለውን ወደ ኋላ የምናየው ይሆናል፡፡

አስቀድመን ግን “ኦሮምኛ ከአማርኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት!” ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንይ፦

ለምሳሌ አሁን ባለው ጎሳንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የራስ ገዝ አሥተዳደር ሥርዓት “ኦሮምኛም የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት!” ብሎ ማለት ባጭሩ ምን ማለት መሰላቹህ፦ “የፌዴራሉ መንግሥት (የማዕከላዊው መንግሥት) መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች በአማርኛ እንደሚሠሩ ሁሉ በኦሮምኛም ይሥሩ፣ እኛ ኦሮሞዎች የማዕከላዊውን መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች አገልግሎት አስፈልጎን በምንቀርብ ጊዜ በኦሮምኛ ያስተናግደን፣ ሰነዶች በኦሮምኛ ይዘጋጁንል፣ የትምህርት ተቋማቱም ትምህርቶችን በኦሮምኛ ያስተምሩ!” ማለት ነው፡፡

ወያኔን እንዲህ ብሎ መጠየቅ ማለት ደግሞ ምን ማለት መሰላቹህ፦ ምድረ ትግሬ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛንም መናገር፣ መጻፍ፣ ማንበብ መቻል አለበት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ተቆጣጥረውት ያሉት ትግሮች በመሆናቸው ነው ምድረ ትግሬ ማለቴ፡፡ ምድረ ትግሬን ይሄንን አድርግ ከምትሉት ደግሞ “ዛሬውኑ ተገንጠሉ!” ብትሏቸው ይቀላቸዋል፡፡ እንኳን ኦሮምኛን በተጨማሪ ሊያውቁ ይቅርና አማርኛውን እንኳ ቢቸግር ነው እንጅ አጣርተው የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ኦሮምኛን ለማጥናት ቋጥኝ የመሸከም ያህል ከባድ ሆኖበት ነው እንጅ ወያኔ ኦሮሞን ከአማራ ጋር አቃርኖ፣ ደልሎ፣ አታሎ ከራሱ ጎን እንዲቆም ለማድረግ ካለው ሸፍጠኛ ጥረቱ የተነሣ ይሄንን ማድረግ ቢችል ደስታውን አይችለውም ነበር፡፡

ወያኔ ይሄንን ጥያቄ ከተቀበለና ኦሮምኛን አጥንቶ በኦሮምኛም መጠቀም ካልቻለ ሊያደርግ የሚችለው ለእያንዳንዱ መሥሪያ ቤትና አገልግሎት ሰጭ ድርጅት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በሙሉ ኦሮምኛ አስተርጓሚዎችን ቀጥሮ ማሠራት ግድ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከወያኔ ድብቅነት ወይም ምሥጢራዊ አሠራር፣ ይሄንን ለማድረግ ከሚጠይቀው ግዙፍ ወጪ፣ ለሥራ ቅልጥፍና ካለመመቸቱና ከሌሎች ከሌሎች ነገሮች አንጻር ቢያስበው ቢያስበው፣ ቢያወጣ ቢያወርድ፣ ዙሪያውን ቢያገላብጠው ጨርሶ የማይሆን ነገር ሆኖበት ነው የተወው እንጅ ኦሮሞን ለመደለል በጣም ይጠቅመው እንደነበረ ሳይገነዘብ ቀርቶ አልነበረም ጥያቄውን ያልተቀበለው፡፡ ሌላኛው አማራጭ የፌዴራሉን መንግሥት (የማዕከላዊውን መንግሥት) የሥራ ቦታዎች በሙሉ ኦሮምኛንና አማርኛን መናገር በሚችሉ ዜጎች ማስያዝ ሊኖርበት ነው፡፡ ይሄም ደግሞ ለወያኔ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡

ይህ “ኦሮምኛ ከአማርኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋ መሆን አለበት!” የሚለው ጥያቄ ከዚህ ከጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) አሥተዳደር ውጭ በሆኑ የመንግሥት አሥተዳደር ቅርጽ ባለው የመንግሥት ሥርዓት ማለትም በአሐዳዊና ቀንቋንና ጎሳን መሠረት ባላደረገ የራስ ገዝ ሥርዓት ሲነሣ ደግሞ ምን ማለት መሰላቹህ፦ ልክ አሁን ባለው የጎሳ ራስ ገዝ የአሥተዳደር ሥርዓት ክልሎች ከየራሳቸው ቋንቋ በተጨማሪ በአማርኛም አገለግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ሁሉ ከጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) አሥተዳደር ውጭ በሆነ የመንግሥት የአሥተዳደር ቅርጽ ባለው የመንግሥት ሥርዓት “ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ ነው!” ቢባል ምን ይሆናል መሰላቹህ፦ በመላ ሀገሪቱ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች በኦሮምኛም የመሥራት ግዴታ ይኖርባቸዋል፣ በመላ ሀገሪቱ ያሉ የትምህርት ተቋማት በሙሉ ትምህርቶችን በኦሮምኛም የማስተማር ግዴታ ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ይሄ ምን ያህል ተጨማሪ ግዙፍ ወጪ የሚጠይቅ ጉዳይ እንደሆነና ለዚህች ደሀ ሀገር ደግሞ ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ጥያቄውን እያቀረቡ ያሉ ወገኖች የተገነዘቡት አልመሰለኝም፡፡

አሁን ደግሞ ከላይ “የአንድነት ኃይል ፖለቲከኞች አላስተዋሉም ወይም ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም ይሆናል እንጅ በዴሞክራሲያዊት (በመስፍነ ሕዝባዊት) ኢትዮጵያ ኦሮምኛ ከሌሎች ቋንቋዎች ተነጥሎ መጥቶ ከአማርኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋ የመሆን ዕድል አይኖረውም!” ወዳልኩት ጉዳይ ልመለስ፡፡

ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓት ማለት የሁሉም መብት እኩል የሚከበርበት ሥርዓት ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች እኩል ናቸው ማለት ነው፡፡ ቋንቋዎቻቸውም ያንዱ ከሌላው ሳይለይና ሳይበልጥ ሰማንያ ሁለቱም ቋንቋዎች እኩል ናቸው፡፡ ልብ በሉ እኩል የሚሆኑት ቋንቋዎቹ ባላቸው እሴት ጥራትና ብቃት ሳይሆን በተፈጥሯዊ ህላዌያቸው ወይም በቋንቋነታቸው ነው፡፡ አንዱ ሰው ከሌላው ሰው ድሀ ሀብታም፣ የተማረ ያልተማረ፣ ቆንጆ ፉንጋ ሳይባል ሰው በመሆኑ ብቻ እኩል ተደርጎ የመቆጠር መብት እንዳለው ሁሉ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ቋንቋ አብላጫ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ቋንቋ ስለሆነ ብቻ ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌሎች አብረው የሚታዩ ጉዳዮችም አሉ፡፡

“ምንድናቸው?” የተባለ እንደሆነ እርግጥ ነው በአንዲት ሀገር አብላጫ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ቋንቋ የሀገሪቱ ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ የመሆን ዕድል አለው፡፡ ስለኦሮምኛ ካወራን ግን

1ኛ. ኦሮምኛ እንደሚባለው አብላጫ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ቋንቋ አይደለም፡፡ እንዴት? የሚለውን ወደ ኋላ እናየዋለን፡፡

2ኛ. ለጊዜው “ኦሮምኛ አብላጫ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ቋንቋ ነው!” ብለን እናስብና ኦሮምኛ አብላጫ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ቋንቋ ቢሆንም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነገር ወይም የሚታወቅ ቋንቋ ግን አይደለም፡፡

3ኛ. “ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ሕዝብ በአንደኛ ደረጃ የሚነገር ቋንቋ ባይሆንም በሁለተኛ ደረጃ የሚነገር ቋንቋ ነውና ግድየለም ኦሮምኛም ሌላም ሁለት ሦስት ቋንቋዎች በተጨማሪ ብሔራዊ ወይም ደግሞ የሥራ ቋንቋ ይሁኑ!” ያልን እንደሆነ የተቀሩትን ቋንቋዎች ከሚጠቀሙት ብሔረሰቦችና ጎሳዎች የእኩልነትና የመብት ጥያቄ እንዲያነሡ ማስገደድ፣ የመገፋት፣ የመገለል የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ “እኛ ከእናንተ ስለምንበልጥ እናንተ ከእኛ ስለምታንሱ ነው የእኛ ቋንቋዎች ብሔራዊ ወይም ደግሞ የሥራ ቋንቋ የሆኑት!” የሚል መልእክት ስለሚያስተላልፍና የሥርዓቱን ፍትሐዊነትና እኩልነት አጠያያቂ ስለሚያደርገው፣ ሀገሪቱንም ለከባድ ወጭ ስለሚዳርግ ካሉት 82 ቋንቋዎች ሁለት ሦስቱን ብቻ ነጥሎ ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ ማድረጉ ፍጹም ስሕተት ይሆናል፡፡

ዲሞክራሲያዊ ምኅዳር እንዲኖረን ከሆነ የምንፈልገው “እንዲህ ይሁን!” ማለቱ አግባብ አይደለም ማለት ነው፡፡ የእኩልነት የመብትና የፍትሕ ጉዳይ በሚገባ የገባንና ጠንቅቀን የተረዳን ከሆን፣ ለእኩልነት፣ ለመብትና ለፍትሕ ታማኞች ከሆንንም ይሄ ጥያቄ ከውስጣችን ሊመነጭ አይችልም፡፡ በመሆኑም “ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ ካልሆነ ሞተን እንገኛለን!” እያሉ ያሉ ወገኖች እውነት እነሱ እንደሚሉት መብትን፣ እኩልነትንና ፍትሕን ፈላጊና ለመብት፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ ታማኝ ከሆኑ ይሄንን ጥያቄ ሊያነሡ አይገባምና ለሁሉም ዜጎች መብት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ነጻነት፣ ሰላም፣ ደኅንነት ሲሉ “እኛ አብላጫ ቁጥር ያለን ነንና ቋንቋችን የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ ሊሆን ይገባል!” የሚለውን ጥያቄ መልሰው ይዋጡት፡፡

ምክንያቱም አሁንም እላለሁ “አብላጫ ቁጥር ያለን ብሔረሰብ ስለሆንን የተለየ መብት ይገባናል!” የሚለው አስተሳሰብ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ጨርሶ ቦታ የለውም፡፡ ሲጀመር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለጎሳ/ብሔር ተኮር ፖለቲካ ቦታ የለውም፡፡ ጎሳ ወይም ዘውግ ተኮር ፖለቲካንና ዲሞክራሲን ለማዋሐድ መሞከር ዘይትና ውኃን ለማዋሐድ የመልፋትን ያህል የቂል ሥራ ነው፡፡ ምክንያቱም ብሔር ተኮር ፖለቲካ አግላይ ስለሆነና የሰዎችን ወይም የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ስለሚደፈልቅ ወይም ስለሚጻረር፣ የግለሰብ መብትን የሚያከብርበት ቦታ ወይም ክፍተት ስለሌለው፣ ሰዎችን በሰውነታቸው ብቻ ወይም ዜጎችን በዜግነታቸው ብቻ ዕኩል የሚመለከትና የሚያስተናግድ የበሰለ ወይም የሠለጠነ ዕይታ፣ አስተሳሰብ፣ የብስለት ደረጃ ጨርሶ ስለሌለው ነው፡፡

ባጭሩ ከዓመታት በፊት ጀምሬ በጽሑፎቸ ስገልጽላቹህ እንደቆየሁት ጎሳ ተኮር ወይም የዘውግ ፖለቲካ በተፈጥሮው ኢዲሞክራሲያዊና ኢሰብአዊ ፖለቲካ ነው፡፡ ይሄን መረዳት መገንዘብ የሚሳነው የተማርኩ ነኝ ወይም ምሁር ነኝ የሚለውን ተውትና ተራ ሰው እንኳን ካለ ይሄ ሰው መቸም ሊበስል፣ ሊነቃ፣ ሊለወጥ፣ ሊረዳ የማይችል ነውና ከእንዲህ ዓይነት ሰዎች ምንም ነገር አትጠብቁ!

እንደምታዩት ጎሳ ተኮር ፖለቲካ ወይም የጎሳ ፌደራሊዝም (ራስ ገዝ) ሥርዓት መላ ሕዝባችንን እርስ በእርሱ ሊያፋጀው ከጫፍ ደርሷል፡፡ ወያኔ እሳቱን ማቀጣጠል በፈለገ ጊዜ ለማቀጣጠል እንደሚችል ስለሚያውቅ በኃይል አፍኖ ስለያዘውና በጉልበት ስለተቆጣጠረው ነው እንጅ በሀገራችን በየትኛውም አቅጣጫ ብትሔዱ የትኛውም ክልል ከየትኛውም ክልል ጋር ድንበር ድንበሩን በተመለከተ ማንም ከማንም ጋር ስምምነት የለውም፡፡ ዙሪያውን ሁሉም ያም የራሴ ነው፣ ይሄም የራሴ ነው የሚለውን ድንበር ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የራሱ ለማድረግ ሁሉም ቀን ጠባቂ ሆኗል፡፡ በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ዜጎች ኢትዮጵያን ረስተው ጎጥ ጎጣቸውን ብቻ እንዲያስቡ መደረጋቸው መላ ሀገሪቱን በአራቱም አቅጣጫ ክልሌ የሚሉትን ድንበር ሰበብ ያደረገ ሰዉ ካላለቀ በስተቀር መቸም ሊታረቅ፣ ሊበርድ የማይችል ግጭትና የእርስ በእርስ መተላለቅ ሊፈነዳ በቋፍ ላይ ነው ያለው፡፡ የጎሳ ፖለቲካን ጥለን ኢትዮጵያን ማሰብ ካልቻልን በስተቀር እንዴትም አድርገን ይሄንን አደጋ ልናስቀረው አንችልም፡፡

እጅግ የሚገርመው ነገር በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት በሀገሪቱና በሕዝቧ ላይ እንዲህ ዓይነት እጅግ አሳሳቢ አደጋ አንዣቦ እያለ የጎሳ ፖለቲካን ሙጥኝ ያሉና “የመጣው ይምጣ በድንበር ምክንያት ስንተላለቅ እንኑር እንጅ የጎሳ ፌደራሊዝም መቅረት የለበትም!” የሚሉ የሰው ደም የሚጠጣ ጋኔን ያደረባቸው አጋንንቶች እንደ አሸን መፍላታቸው ነው፡፡ እነኝህ ቡድኖች አጋንንት ያደረባቸው ስለሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ የዚህች ሀገር ጠላቶች ቅጥረኛ በመሆናቸው ሀገር የማፍረስ ፍላጎትና ሰይጣናዊ ዓላማ የሸመቁ በመሆናቸውም ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ዘንዳ እነኝህን የቅጥረኛና የአእምሮ ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች ጥርቅምን ጊዜ ሳንሰጥ ተረባርበን ካለማስወገድ በስተቀር ዓላማቸውና ፍላጎታቸው ከእኛ ጋር ሊታረቅ የሚችል ባለመሆኑ ከእነሱ ዘንድ ቀና ነገር ጠብቆ እነሱን ለመቅረብ መሞከር ጊዜን ከማባከንና የበለጠ እንዲደረጁ ዕድል መስጠት ካልሆነ በስተቀር ሊገኝ የሚችል ረብ አይኖርም፡፡

ይህ በዘውግ ቡድኖች ላይ ያነሣሁት ክስ ግን ወያኔና አጋሮቹ ከባዕዳን ጋር በመመሳጠር በአማራ ሕዝብ ላይ ጥፋት ታውጆ በግልጽ እንዲሁም እጅግ ውስብስብ በሆነ ስውር መንገድ የዘር ማጥፋት ጥቃት በአማራ ሕዝብ ላይ የተወሰደና እየተወሰደ ያለ በመሆኑ ሁኔታው አስገድዶ የአማራን ሕዝብ ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ ወያኔ ለዓላማው የመሠረታቸውን ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ መሥርቷቸው እየታገሉ ያሉትን የአማራ ድርጅቶችን አይመለከትም፡፡ ምክንያቱም እነኝህ ድርጅቶች እየታገሉ ያሉት የአማራን ሕዝብ ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግና የህልውና ቁርኝት በመኖሩ ሀገሪቱንም ከጥፋት ለመታደግ የሚታገሉ እንጅ እንደ ሌሎቹ ጠባብ የዘውግ ድርጅቶች የሀገሪቱንና የሕዝቧን ህልውና አደጋ ላይ ለሚጥል ለጠባብ የጎሳና የጎጥ ፖለቲካዊ ጥቅም ተብሎ የሚደረግ ትግል ባለመሆኑ ነው፡፡

ወደቀደመው ነገራችን እንመለስና “ቋንቋን በተመለከተ ዲሞክራሲያዊው አስተሳሰብ እንዳልከው ከሆነ ታዲያ እንዴት ዲሞክራሲያዊ በምንላቸው ሀገራት ከአንድ በላይ የሥራ ወይም ብሔራዊ ቋንቋዎች ሊኖራቸው ቻለ?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችል ይሆናል፡፡ እውነት ነው ጥቂት የማይባሉ ዲሞክራሲያዊ ሀገራት ከአንድ በላይ ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋዎች ያላቸው ናቸው፡፡ ይሄ ማለት ግን ቋንቋቸው ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ ካልተደረገላቸው የሕዝባቸው ክፍል ምንም ቅሬታ የለም፣ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ማለትም እነሱ እንዳደረጉት ነው! ማለት አይደለም፡፡ ከእነኝህ ሀገሮችም በአብዛኞቹ ቋንቋቸው ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ ካልተደረገላቸው የሕዝባቸው ክፍል ጥያቄ ሲነሣባቸው ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አነኚህ ሀገራት “ከዚህ ሁሉ ለብሔረሰቦቹ ለየራሳቸው የየራሳቸውን ቋንቋ እንዲጠቀሙ አድርገን ለሀገር አቀፍ ግን አንደኛውን መርጠን ብንጠቀም ይሻላል!” ለማለት የተገደዱም አሉ፡፡ ብቻ የተረፋቸው ጣጣ ብቻ ነው፡፡ ይሄም የሚጠበቅ ነው፡፡

እናም በዚህ ምክንያት ነው ከላይ “የአንድነት ኃይል ፖለቲከኞች አላስተዋሉም ወይም ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም ይሆናል እንጅ በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ኦሮምኛ ከሌሎቹ ቋንቋዎች ተነጥሎ መጥቶ ከአማርኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋ የመሆን ዕድል አይኖረውም!” ስል የገለጽኩት፡፡

ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ ቢሆን ሌላው ከሌሎች ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ሊነሣ የሚችለው ቅሬታ ከረጅሙ የሀገሪቱ ታሪክ አንጻር ኦሮሞ ቅርብ በሚባል ጊዜ ማለትም በ16ኛው መቶ ክ/ዘ የግራኝ አሕመድ ወረራ በፈጠረለት ምቹ ሁኔታ ከቤናዲር ሱማሌ በመነሣት ተሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ የገባና ከዚያ በኋላ ባደረገው ደም አፋሳሽ መስፋፋት ነባር ኗሪዎችን እየዋጠ ወይም በኃይል ወደ ኦሮሞነት እየለወጠ አሁን ሰፍሮ ያለበትን የሀገሪቱን ክፍል ለመያዝ የበቃ ከመሆኑ አንጻር “የእኛ የነባሮቹ ቋንቋ እያለ እንዴት…!” የሚል ጠንካራ ቅራኔ ሊያስነሣ ይችላል፡፡ ይሄም ላለመረጋጋት መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም እነኝህ ሁሉ ችግሮች ስላሉ አግባቢውና አስማሚው ሐሳብ የሚሆነው ካሉን 82 ቋንቋዎች በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነገረውን፣ የተሟላ የቋንቋ እሴቶች ያሉትን (ፊደል፣ ቁጥር…) ፣ የበለጸገ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ የሆነውን መርጦ በሥራ/ብሔራዊ ቋንቋነት መጠቀሙ ነው፡፡ መቸም የራሳችን ቋንቋ እያለን ቅኝ እንደተገዙና ማንነታቸውን ሁሉ እንደተነጠቁት ሀገራት በባዕድ ቋንቋ እንድንግባባ የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ጥያቄ ሊነሣ እንደሚችል ይሰማኛል “አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው አሁን ደግሞ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ያለው በርካታ ሕዝብ የሚናገረው፣ በእሴቶቹና በመበልጸጉ ከሌሎቹ መብለጡ ታውቆ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተመርጦ ነው ወይ?” የሚል፡፡ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቋንቋ ምርጫ አድርጎ አማርኛን ቀደም ሲል “ብሔራዊ ቋንቋየ ይሁንልኝ!” ፣ አሁን ደግሞ “የሥራ ቋንቋየ ይሁንልኝ!” ብሎ አልመረጠ ይሆናል፡፡ ይሁንና ግን አሁን ዛሬ ላይ ይሄ ምርጫ ይደረግ ቢባል ተመራጩ አማርኛ መሆኑ ማናችንንም የሚያጠራጥር አይመስለኝም፡፡

ምክንያቱም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነገረው ቋንቋ አማርኛ ነው፡፡ አማርኛን ተናጋሪው ሕዝብ አማራው ብቻ አይደለም፡፡ አማርኛን መናገር የሚችሉትን የሌሎች ብሔረሰቦችንና ጎሳዎችን አባላትንም ይጨምራል፡፡ አማርኛ የራሱ ሆሄያት ወይም ፊደላት አሉት (ከሰባቱ ፊደላትና አጋፋሪዎቻቸው በስተቀር የተቀሩት ፊደላቱ የግእዝ ፊደላት ናቸው፡፡ ከተባለ አማርኛ የተወለደው ከግእዝ በመሆኑ የአባቱ ንብረት ንብረቱ ነውና) ፣ አማርኛ ከሌሎቹ ቋንቋዎች የላቀ ወይም የበለጸገ የሥነጽሑፍ ቋንቋ ነው፡፡

በመሆኑም አማርኛ በብሔራዊ ቋንቋነት ወይም በሥራ ቋንቋነት እንዲያገለግል የተደረገው በሕዝብ ምርጫ ባይሆንም እንደ አጋጣሚ ሆኖ (by default) አማርኛ ተመርጦ እንዲያገለግል መደረጉ ትክክልና ጥያቄም የሚያስነሣ ላይሆን ችሏል፡፡ በመሆኑም ታምኖበት እንጅ በቋንቋ ጉዳይ የቸገረና የተወሳሰበ ችግር ሲያጋጥም እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ለመዳኘት የሚያገለግለውን የእንደነበረው ይቀጥልን (the status quo) የመዳኛን ስልት በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት እንደሚገደዱት እንደ ሌሎቹ ሀገራት በስታተስኮ ለማስማማት በመገደድ አይደለም አማርኛ ብሔራዊ/የሥራ ቋንቋ የሆነው ማለት ነው፡፡

ሳይረሳ “የአብላጫ ቁጥር አለን የሚባለው አነጋገር እውነታ ላይ የተመሠረተ አባባል አይደለም!” ያልኩትን ላብራራ፡፡ ይሄንን ስላቹህ በወያኔ ዘመን የተደረጉ የሕዝብ ቆጠራዎች ኦሮሞ አብላጫ ቁጥር እንዳለው አያረጋግጡም እያልኩ አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁለት ከዚህ “የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር ነው!” ተብሎ ከሚጠቀሰው ቁጥር 10 ሚሊዮን (አእላፋት) የሚሆነው ኦነግና ወያኔ ሀገሪቱን ከተቆጣጠሩ ጊዜ ጀምሮ በአማራ ሕዝብ ላይ በፈጸሙት ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ጥቃት ለመትረፍ ሲልና ተገዶም እራሱን ወደ ኦሮሞነት የቀየረ አማራ ነው፡፡ አማራ ማንነቱን ለመደበቅና ለመቀየር የተገደደው በዚህ የሀገራችን ክፍል ብቻ አይደለም፡፡ አማራ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በመላ ሀገሪቱ በመሆኑ በየሚኖሩበት ሀገር ወዳለው ብሔረሰብና ጎሳ ማንነታቸውን የቀየሩት አማሮች ቁጥር የትየሌሌ ነው፡፡ በመሆኑም አብላጫውን ቁጥር የያዘው ኦሮሞ ነው የሚባለው አባባል ትክክል አይደለም፡፡ የአማራ ቁጥር በጣም በርቀት ይልቃል፡፡

ሌላው መግለጥ የምፈልገው ጉዳይ ምንድን ነው መሰላቹህ በዚህ በቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ የቡድን መብት እና የግለሰብ መብት እንዴት ሳይሸራረፍ ማስጠበቅ ማስከበር ይቻላል? የሚለውን ዐቢይ ጉዳይ ነው፦

በቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ የቡድን መብት ሊጠበቅ የሚችለው ማንም እንደሚያውቀው ብሔረሰቦችና ጎሳዎች በየራሳቸው ቋንቋዎች የመማር፣ የመዳኘት፣ የመገልገል መብትን በማረጋገጥ ነው፡፡ አስቸጋሪ መስሎ የሚታየው በቋንቋ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ የግለሰብን መብት እንዴት ማስከበር እንደሚቻል ነው፡፡ እሱም ቢሆን በቀላሉ መፍታት ይቻላል ብየ አምናለሁ፡፡ ከአንድ ሀገር ሕዝብ እንደሚጠበቀው ሁሉ ብሔራዊ መግባባት (National consensus) ግን የግድ አስፈላጊ ነው፡፡

ብሔራዊ መግባባት ካለን ሁሉም ዜጋ የሚያውቀውና የሚሠራበት ሀገር አቀፍ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ማለት ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ ሊኖረን እንደሚገባ እናምናለን ማለት ነው፡፡ ይሄ የወያኔ አገዛዝ በሀገር አቀፍ ደረጃ አማርኛን የሥራ ቋንቋ አድርጎ ቢደነግግም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት አለ ቢባልም ተግባር ላይ የሚታየው ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ የክልል መንግሥታት የሚባሉት ማለትም አማርኛን የክልላቸው መንግሥትም የሥራ ቋንቋ ያደረጉት ሳይሆኑ እንደ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልል የሚባሉት ክልሎች መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት አገልግሎትን በአማርኛ ለሚጠይቃቸው ተገልጋይ አገልግሎት መስጠት አይፈልጉም፣ በት/ቤቶችም የአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ላይ ተማሪዎችን ጥለው እንዲወጡ በማድረግና “አማርኛን መማር የሚፈልግ ተማሪ ስለሌለ!” የሚል ምክንያት በመስጠት በት/ቤቶች የአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ እንዲታጠፍ አድርገዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የይስሙላ ሳይሆን በትክክል የሚሠራ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረሳችን የቋንቋን አጠቃቀም በተመለከተ የግለሰብ መብትን ለማስጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ መግባባት እንበል ለምሳሌ በሀገራችን እንደ ብዙዎቹ ምዕራባውያን ሀገራት ቋንቋን ወይም ብሔረሰብን መሠረት ያላደረገ የፌዴራል (የራስ ገዝ) አሥተዳደር አደረጃጀትን ለምሳሌ የደርግ ዘመኑን የክፍላተ ሀገር አከላለልን የፌዴራል (ለራስ ገዝ) አሥተዳደር አድርጎ የሚጠቀም የፌዴራል አሥተዳደር ሥርዓት ተመሠረተ እንበል፡፡ ወይም ደግሞ ዜጎች በመረጡት የየራሳቸው ተመራጮች የሚተዳደሩበትና በየቋንቋቸው የመጠቀም መብት የተከበረበት አሐዳዊ የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት ተመሠረተ እንበል፡፡

ብሔራዊ መግባባቱ በእነዚህ ሁለት የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓቶች መቀሌ ላይ ወይም ጅጅጋ ላይ ያሉ ትግሬ ወይም ሱማሌ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ቋንቋን በተመለከተ የግለሰብ መብታቸው ማለትም ወደ እነዚህ ክፍላተ ሀገር ለሥራ ጉዳይ ወይም ለኑሮ በሚሔዱበት ጊዜ የሀገር አቀፍ የሥራ ወይም ብሔራዊ ቋንቋ ያልሆነውን የአካባቢውን ቋንቋ ለእነሱ ደግሞ ሦስተኛ ቋንቋ የሚሆነውን የክልሉን አገልግሎት ለማግኘት ሲባል ያለ ፍላጎታቸው ለማወቅና በዚያም ለመጠቀም ለመስተናገድ ያለመገደድና በቡድን መብት አሠራር ያለመቸገር የግለሰብ መብታቸው እንዴት ይጠበቃል? የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ያስችላል፡፡

እንዴት ይጠበቃል? ለሚለው ጥያቄ መልሱም እነኝህ የአካባቢውን ቋንቋ የማያውቁ ግለሰቦች እዚያው መንግሥታዊ አገልግሎት የማግኘት የዜግነት መብት ስላላቸው የአካባቢውን ቋንቋ ባለማወቃቸው ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት አጥተው ወይም ተነፍገው በቡድን መብት ምክንያት የግለሰብ መብታቸው እንዳይጣስ የአካባቢውን መንግሥታዊ አገልግሎት በሀገር አቀፉ ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋ የማግኘት መብታቸውን በማስከበር የቋንቋ አገልግሎትን በተመለከተ የግለሰብ መብታቸው በዚህ መልኩ ይጠበቃል፡፡

እነኝህ ግለሰቦች በሥራ ጉዳይ ወይም በሌላ ምክንያት ለመኖር በሔዱባቸው የሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በአፍመፍቻ ቋንቋ ትምህርቱ በሚሰጥባቸው ት/ቤቶች ልጆቻቸው የአካባቢውን ቋንቋ ካለማወቃቸው የተነሣ ትምህርት በአካባቢው ቋንቋ መማር የማይፈልጉ ቢሆኑ ለመማር የሚገደዱ አይሆኑም፡፡ ይሁንና የቡድን መብትን ለመጠበቅ ለማክበር በየአካባቢው የሚሰጠው ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ስለሚሆን የትምህርት አገልግሎትን ለማግኘት ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን እነኝህ ውሑዳን ዜጎች ወይም ግለሰቦች ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ሲሉ በግል ተነሣሽነት የጋራ በሆነው በሀገር አቀፉ የሥራ/ብሔራዊ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጥ የግል ወይም የኮሚዩኒቲ (የሕዝብ) ት/ቤትን ለመክፈትና ልጆቻቸውን ለማስተማር ቢፈልጉ ይሄ መብታቸው የሚከበርላቸው ይሆናል፡፡

በዚህ መልኩ ነው ወደፊት በምትኖረውና ከጠንቀኛውና ዜጎችን “ክልላቹህ ስላልሆነ!” በሚል ምክንያት ሰብአዊና የዜግነት መብታቸውን አሳጥቶ በአንድ ሀገር ውስጥ ሦስት አራት ዓይነት የዜግነት ደረጃ በሚያወጣውና በተፈጥሮው ፀረ ዲሞክራሲያዊና ፀረ ሰብአዊ መብቶች ከሆነው የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) ሥርዓት በተላቀቀችው ዲሞክራሲያዊት (መስፍነ ሕዝባዊት) ኢትዮጵያ የቡድን መብትንና የግለሰብ መብትን ሳይሸራረፍ ማክበርና ማስከበር የምንችለው፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.