የዳንኤል ክብረት ፀረ ሐራጥቃ ተሐድሶ ዘመቻ ቁማር! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

መቸም ለ26 ዓመታት የዘለቀውን የወያኔንና የመናፍቃንን የተቀናጀ ፀረ ቤተክርስቲያን ዘመቻ በተለይ አሁን ላይ ነገሮች በጣም ግልጽ በሆኑበት ጊዜ ለምእመናን ለመናገር መሞከር ለቀባሪው ማርዳት እንደሆነ ሁሉም ይገነዘበዋል ብየ አምናለሁ፡፡

ወያኔ ከሀገር ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን እየተደረገ ያለው ፀረ ወያኔ እንቅስቃሴ እጅግ ካሳሰበው ሰነባብቷል፡፡ ይሄንን እንቅስቃሴ ለማዳከም፣ ለማክሸፍና ለማምከንም የተቻለውን ያህል በስውርም ሆነ በግልጽ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የዚህ ዘመቻው አካል የሆነ ጥረቱን በካድሬው (በወስዋሹ) ዳንኤል ክብረት በኩል አንድ ተልእኮ ዘርግቷል፡፡ ዳንኤል ክብረት ከሀገር ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን በተሟሟቀ መልኩ እየተደረገ ያለውን የፀረ ወያኔ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተለያየ መልኩ ሲቃወም፣ ሲያበሻቅጥ፣ ለማደናቀፍ ሲጥር የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ አትላንታ በሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የፀረ መናፍቃን ወይም ፀረ ተሐድሶ ዘመቻን ሽፋን በማድረግ የወያኔ ካድሬዎች ያመቻቹት ከዛሬ ዓርብ ጀምሮ እስከ እሑድ ለሦስት ቀናት በሚቆይ ጉባኤ ምእመናንን የዜግነት ግዴታቸውን ለሀገር፣ የክርስቲያንነት ግዴታቸውን ደግሞ ለቤተክርስቲያን እንዳይወጡ በነገሮች ሁሉ ላይ ሰው የሰውነት ድርሻ እግዚአብሔር ደግሞ የእግዚአብሔርነት ድርሻ ያለው መሆኑን በማስረሳት የሰውነት ድርሻችንን ሳንወጣ እግዚአብሔርን ብቻ ጠባቂ እንድንሆን የሚያደርግ አሳሳች ምክርና ትምህርት የተቀላቀለበት ስብከት በመስጠት ምእመናንን የማፍዘዝ የማደንዘዝ ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅተዋል፡፡ ምእመናን ሆይ! ሰው የራሱን ድርሻ ካልተወጣ በስተቀር በምንም ተአምር ምንም ነገር ቢሆን እግዚአብሔር የሚፈጽሙ የሚያሳካው አንድም ነገር አለመኖሩን ከተረዳቹህ ማንም ምንም ብሎ ሊያጭበረብራቹህ ሊያጃጅላቹህ አይችልም፡፡

የወያኔ ሸፍጠኝነት ይታያቹህ! ቤተክርስቲያን ለራሷ በሐራጥቃ ተሐድሶ ጥቃት የነፍስ ግቢ የነፍስ ውጭ ፍልሚያ ላይ ነች፡፡ ወያኔ ደግሞ ምእመናን ለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ የሰጡትን ትኩረት ለመጠቀም በማሰብ ታማኝ አገልጋዩን በፀረ ተሐድሶ አገልግሎት ሽፋን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚያደነዝዝ ከተቻለም የሚበትን መርፌ እንዲወጋለት ልኮታል፡፡

ይሄንን ጉባኤ ያዘጋጁ ሰዎች የዚህ ተልዕኮ ተባባሪ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ አንዳንድ ያልገባቸው የዋሀን ከመሀል ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋነኛ አቀናባሪዎቹ ግን የወያኔ ተልዕኮ አስፈጻሚ ለመሆናቸው አትጠራጠሩ፡፡ ከዳንኤል በላቀ የትምህርት ዝግጅት፣ የሞራልና መንፈሳዊ ብቃት ደረጃ ላይ ያሉ አገንጋዮች ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ እያሉና እነሱን መጋበዝ እየቻሉ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ሰይጣናዊ ሸፍጥ የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለውን ዳንኤልን ከፍ አድርገው ሰቅለው በማራገብ ምእመናንን በእሱ እግር ስር እንዲኮለኮሉ የሚፈልጉበት ብቸኛ ምክንያት ሌላ ምንም ሳይሆን ይሄንን ስውር የወያኔን ተልእኮ ከማስፈጸም አኳያ ነው፡፡

ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ! እባካቹህ ከዳንኤል ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ ያሉ በየአሕጉሩ ያሉ ድብቅ የወያኔ ካድሬዎችን (ወስዋሾችን) ሸፍጥና ስውር ተልእኮ በመረዳት ቤተክርስቲያን እያደረገች ያለችውን ጊዜ የማይሰጥ ፀረ ሐራጥቃ ተሐድሶ ዘመቻ ችግር ገጥሞት እንዳይከሽፍ ወይም እንዳይሰናከል ጉባኤ አዘጋቾቻቹህን በቅርብ በመከታተል እንደ ዳንኤል ዓይነቱን ካድሬ ሳይሆን ምስጉንና ታማኝ አገልጋዮችን በማስመጣት ቤተክርስቲያንንና ሀገራችንን ከሐራጥቃ ተሐድሶ እና ከሐራጥቃ ተሐድሶው ፀረ ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ቃፊር ከሆነው ወያኔ ነጻ የምናወጣበትን ትግል በማጧጧፍ ታሳኩ፣ ትጠብቁ፣ ትታደጉ ዘንድ ጥሪየን በልዑል እግዚአብሔር ስም አቀርባለሁ!!!

ሌላው መጠንቀቅ ያለባቹህ ነገር ከዳንኤል ደጋፊዎች ተጠበቁ፡፡ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ የዳንኤል ደጋፊዎች በሙሉ የወያኔ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ስትጠይቋቸው ግን የወያኔ ደጋፊም ተቃዋሚም አይደለንም ይላሉ፡፡ ወያኔን ተቃዋሚ ካልሆኑ ወያኔ ተመችቷቸዋል ማለት ነው፡፡ በወያኔ እየደረሰ ያለው የቤተክርስቲያንና የሀገር ሕመም፣ ስቃይ፣ መከራና ጉዳትም ጨርሶ አይሰማቸውም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ክርስቲያን አይደሉም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊም አይደሉም፡፡ አንድ ሰው የዳንኤል ደጋፊ ሲሆን በአስገራሚ ሁኔታ ከላይ እንዳልኳቹህ ዓይነት ሰው እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ትችላላቹህ፡፡ ምናልባት ግን የዋሀን ጭፍን የዳንኤል ደጋፊዎች ብትኖሩ እባካቹህ በጭፍን አትነዱ! ምክንያታዊ ሁኑ! ምንጊዜም ቢሆን ቤተክርስቲያንን አስቀድሙ! ጭፍን ደጋፊነትና ምክንያታዊ አለመሆን ነው እየጎዳን ያለው፡፡ እግዚአብሔርን አስቡ ፍሩም! ለሰው ጥብቅናና ድጋፍ ለመስጠት ስትሉ እግዚአብሔርን እንዳታሳዝኑና እንዳይታዘባቹህም በእጅጉ ተጠንቀቁ! ይሄንን ከሳታቹህ ግን ያን ከሀዲና ቅጥረኛ ዳንኤል ጣዖታቹህ እንዳደረጋቹህትና ከእግዚአብሔር ዘንድ እጣ ፋንታ፣ ዕድል ተርታ እንደሌላቹህ እወቁት!!!

ድል ለቤተክርስቲያን!!! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.