እባጭ በአስፕሪን እምቦጭስ በዝግን እንዴት ሊድን ይችላል? – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ብዙዎቻችን የማናውቀው እምቦጭ ከሲኦል እንደ መዐት እምቦጭ ብሎ የመንፈስ፣ የእምነት፣ የቅርስ፣ የታሪክና የእውቀት ምንጭ ከሆኑት ዓባይና ጣና ከተነጠፈ ስድስት ዓመታት እንዳስቆጠረ ተነግሯል፡፡ እምቦጭ በስድስት ዓመቱ ይህንን በምስል እሚታየውን ሰፊ ወረራ አኪያሂዶብናል፡፡

በባህላችን የጎበዝ ጓሮ ወይም ማሳ እንደዚህ በአረም የሚወረረው አንድም ያ ጎበዝ ሲሞት አለዚያም ያልጋ ቁራኛ ሲሆን ነው፡፡ የአገር አድባር የሆኑት ዓባይና ጣና ይህንን በመሰለ አረም መወረራቸው የሚያሳየው የአገሪቱ ጎበዞች ሞተው ማለቃቸውን አለዚያም ያልጋ ቁራኛ መሆናቸውን ነው፡፡

እምቦጭ ከኦቶማን፣ ከምስር፣ ደርቡሽና ጣልያን ወራሪዎች የማያንስ ወራሪ ነው፡፡ ምስር፣ ደርቡሽና ጣልያን ሲወሩን የኖሩት ዓባይና ጣናን እንደ እምቦጭ እየመጠጡ እኛን አስርበውና አስጠምተው ስንደክም እየገዙን ለመኖር ነበር፡፡ እኛን አስርበውና አስጠምተው ሲገዙን ለመኖር የከጀሉትን ታሪካዊ ጠላቶች የድሮ ጎበዞች ገና ድንበራችንን ሲደፍሩ እንደ አንበሳ እያገሱና እንደ ነብር እየተቆጡ ተናንቀው መልሰዋቸል፡፡ በዚህ ዘመን የወረረን እንቦጭ ግን ከድንበር አልፎ ከዋናው ከተማ ባህርዳር አካባቢ ስድስት ዓመታት ወረራውን ሲያጧጡፍ ተሸፋፍኖ ቆይቷል፡፡ ይህ የመሸፋፈን ተንኮልና እርኩስ መንፈስም ወራሪውን እምቦጭ ከኃይለ ሥላሴ ጉግሳ የከፉ ባንዳዎች መንገድ እያሳዩ እንዳመጡት ያመለክታል፡፡

መንግስት ባላቸው አገራት እንደ ጎርፍ፣ አውሎ ነፋስ፣ እሳት፣ የበሽታ፣ የተምችና የመሳሰሉት ተውሳኮች ወረረሽኝ ሲደርስ በአስቸኳይ አገራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ ችግሩ ይቀረፋል፡፡ መንግስት በሌላቸው እንደኛ ባሉ አገሮች ደግሞ እንደ እምቦጭ ያለ ወራሪ ለስድስት ዓመታት ዋና ከተማን ወሮ ውሀውን፣ ጥበቡን፣ ቅርሱን፣ እውቀቱን፣ እንሰሳቱን፣ እፀዋቱን እስኪያደርቀው ሲደባበቅ  ይኖራል፡፡ ወራሪው ውሀውን እንደ ስፖንጅ እየመጠጠ ተንሰራርቶ ራሱን መደበቅ ሲያቅተውና ሕዝብን ሲያነሳሳ ደግሞ የተነሳሳው ሕዝብ ወራሪውን እንዳይጋፈጥ ብዙ መሰናክል ይፈጠራል፡፡

ይህ መሰናክል ታልፎ ከዓባይና ጣና የተሳሰረው መንፈሳችን፣ ሃይማኖታችን፣ ታሪካችን፣ ቅርሳችን፣ ጥበባችን፣ እንሰሶቻችንና እፀዋቶቻችን ካልዳኑ ለአራት ሺ ዘመናት እነዚህን ፀጋዎች ሲጠብቁ ሰማእት የሆኑትን ቅድመ አያቶቻችንን ዳግም እንሰዋቸዋለን፤ እኛም በቁማችን እንሞታለን፤ ተከታዩን ትውልድም እንገላለን፡፡ ይህንን የተከታታይ ትውልድን ሞት ለማዳን አንዳንድ ወጣቶች በአገኟት ጨላጨሎ ሁሉ እንደ ጧት ጮራ እየሾለኩ ሲያበሩና ተስፋ ሲፈነጥቁ ይታያሉ፡፡ ወጣቶች ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከወሎና ከሸዋ እየዘመቱ አያቶቻቸው ጣሊያንን በጨበጣ እንደተናነቁት አርበኞች  እምቦጭን በጨበጣ ሲተናነቁ ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን ትንታግ ወጣቶችን ያዩ እምቦጭ አሳዳጊ ባንዶችም ለማስመሰል እየተንከባከቡ ያዘመሩትን እምቦጭ እንደ እንደ ጎመራ የፈረንጅ ካሮት ሥር እየተመለከቱ የተነሱትን ምስል አፍረጥርጠው ቢልጉት ያለቀ የጥርስ ሳሙና ያህል እውነት ጠብ በማይለው ቴሌቪዥናቸው ይለቃሉ፡፡

የጣልያኑ እምቦጭ ከዚህኛው እምቦጭ በአካልና በደመነፍስ ይለያል፡፡ የጣሊያኑ እምቦጭ አጠገቡ ያለው ሲወድቅ እንደ ባህር ቄጠማ እየተንቀጠቀጠ ይንቦቀቦቃል፤ ይኸኛው እምቦጭ ግን አጠገቡ ያለው ሲወድቅ በእልህ እንደ ነዳጅ ድፍድፍ ይንፈቀፈቅና ሥሩን እያንሰራራ የወደቀውን በእጥፍ ድርብ ይተካዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የጎጃሙ ጎበዝ አንድ ሺ የእምቦጭ እግሮች ነቅሎ ከቤቱ ሳይደርስ ፈንዳቂው እምቦጭ ሁለት ሺ እግሮች ይተካል፡፡ የጎንደሩ ጎበዝ አንድ ሺ የእምቦጪ እግሮች ነቅሎ ከደጁ ሳይደርስ ፈንዳቂው እምቦጭ ሁለት ሺ እግሮች ይተካል፡፡ የወሎው ጎበዝ አንድ ሺ የእምቦጭ እግር ነቅሎ ከጓሮው ሳይደርስ ፈንዳቂው እምቦጭ ሶስት ሺ አምስት መቶ እግሮች ይተካል፡፡ የሸዋው ጎብዝም አንድ ሺ የእምቦጭ እግሮች ነቅሎ ከሰፈሩ ሳይደርስ ፈንዳቂው እምቦጭ ሶስት ሺ አምስት መቶ እግሮች ይተካል፡፡ እርባታው በዚህ ከቀጠለ እምቦጭ ዓባይና ጣናን አጥፍቶ የዓባይን ገባሮች እየተከተለ መላ አገሪቱን ይወራል፡፡

የእምቦጭ እርባታና ወረራ እንደ ሰማይ ተንጣሎ እየታዬ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች በስተቀር ቄሱም ዝም መጣፉም ዝም ብሏል፡፡ በዚህ ወረራ የሙሴ ፅላት የተጠለለባቸው ገዳማት፣ አያሌ የብራና መጻሕፍትና ቤተክርስትያናት ለአደጋ ሲጋለጡ አቡኑና ጳጳሳት እንደ ተለመደው በልጓም እየተሳቡ የነፍሰ-ገዳዮች የልማት ካድሬ መሆኑን ቀጥለዋል፡፡ የእነዚህ ጳጳሳትና አቡን ዝምታ ጣልያንን በከበሮ የተቀበሉትን ከሀዲና ባንዳ ከበሮ ደላቂ ካህናት ያስታውሰናል፡፡ የጣና ገዳማትና ታሪካዊ ቅርሶችን እያስጎበኘ፤ የዓባይን ታላቅነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወንዝነት እየተረከና እሳት እንደተያያዘው ሰፈር የሚጨሰውን ፏፏቴ  እያሳዬ ገንዘብ እሚያግበሰብሰው የቱሪስት ኮሚሽን ቁርጡንና ክትፎውን እየዛቀ ዝም ብሏል፡፡ ልማታዊ ቦንደኛ ከበርቴዎችም ምንጩን ከላይ እየደረቀ ከታች ከተገደበው ግድብ ኮረንቲ ሸጠው ሊከብሩ የበሬን ፍሬዎች ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ የማፈያ ገዥዎቻቸውን ቁልባ ፍሬዎች ሲከተሉ ይውላሉ፡፡

እግዜር አይበለውና ዓባይና ጣና ታሪክ ሆነው ስናለቅስ “በፊት ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጪት ጥዶ ማልቀስ” እያለ ተመልካች ሳይተርትብን እስተንፋስ ያለን ሁሉ በእምቦጭ ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ መተንፈስ ይኖርብናል፡፡ የእምቦጭ ወረራ አስቸኳይ እቅድና አዋጅ ይጠይቃል፡፡ “ጎንደርና ባህርዳር ዩንቨርሲቲ መሳሪያ እየሰሩ ነው፣ እምቦጭ አጥፊ አንበጣ እየተፈለፈለ ነው” የመሳሰሉት ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ወሬዎች አዘናጊና ጎጂ ናቸው፡፡ የእምቦጭ ወረራ ዛሬ እሚጠይቀው በፍጥነት መተኮስ እሚችል የጎረሰ መሳርያ ነው፡፡ ምን ዓይነት የጎረሰ መሳርያ እምቦጭን እንደሚያንቦጨቡጨው ለመረዳት የእምቦጭን ባህሪ በብርሃን ፍጥነት መረዳት ያሻል፡፡ ባህሪውን ለመረዳትም በእንቦጭና ተመሳሳይ አረሞች ጥናት ያኪያሄዱ ሊቃውንት የእንቦጭን ባህሪ በሚችሉት መንገድ እንዲያስተምሩ ይህ ወረራ ታሪካዊ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል፡፡

የእምቦጭን ባህሪ ማወቁ ማጥፊያውን መንገድ ለመዘየድ ይረዳል፡፡ እንቦጭን የማጥፊያው ዘዴ ከባህሪው ይቀዳል፡፡ ከእምቦጭ ባህሪ የተቀዳው ዘዴ ሲገኝ ይህንን እምቦጭ ማጥፊያ ዘዴ እንዲገዙ በዜጎች በተለይም በእጃቸውም በእግራቸውም ሄደው በከበሩ ቱጃሮች ጫና ማድረግ ያሻል፡፡ ዘፋኞች፣ እስክስታ አውራጆች፣ ትያትረኞች፣ ወራቢዎች፣ ጠሐፊዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ፌስቡከኞችና ትዊተኞች ሳይታክቱ የችግሩን ግዝፈትና መፍትሔውን የማሳወቁን ሥራ እንደ ሰደድ እሳት ማጧጧፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጠላት እንደ ተምች ሲወር እንኳን የራስ የባዕድ አገር ወዳጅ ሕዝብም እንደ ንብ ገንፍሎ እየወጣ ይረዳል፡፡ በዚህ ወረራ ወቅት ድምጡን ሳያሰማ አድፍጦ የተኛ ጣሊያንን መንገድ እያሳዩ አገር እንዳስወረሩት ባንዳዎችና ከበሮ እየደለቁ እንደተቀበሉት ከሀዲ ካህናት ለዘላለም በምድርም በሰማይም ሲረገም ይኖራል፡፡

ለአገር አጥፊዎች የፖለቲካ ፍጆታና ተላላኪነት ሳይሆን ሀላፊነት ተሰምቷችሁ ጣናን ለመታደግ ደፋ ቀና የምትሉ ወጣቶች ሆይ! ባገኛችሁት ጨላጨሎ ሁሉ እንደ ጧት ጮራ እየሾለካችሁ የእምቦጭን ወረራ ለመመከት የምታደርጉት ውጊያ ያስደስታል! ዳሩ ግን የውጊያ ስልት እንደ ወራሪው ባህሪ ይለያያል፡፡ የጣሊያንን ወራሪ ቅደመ አያቶቻችን በጨበጣ ውጊያ ድል ነስተዋል፡፡ አንዱን እግር ሲነቅሉት አስር እሚተካን የእምቦጭ ወራሪ ግን እየዘገነ ነቅሎ በሚጥል የጨበጣ ውጊያ መርታት ያዳግታል፡፡ እንዲያውም እምቦጭ በጨበጣ ዝግን ሊጠፋ ይችላል ብሎ መተማመን እባጭን አስፕሪን ያድነዋል ብሎ እንደሚተማመን አላዋቂ በሽተኛ መንዘላዘልና መጃጃልም ሊሆን ይችላል፡፡ እምቦጭን ለመታገል ከሚዘግን እጅ የተሻለ መሳሪያ ባስቸኳይ ያስፈልጋል፡፡ አለዚያማ እባጭ በአስፕሪን እምቦጭስ በዝግን እንዴት ሊድን ይችላል?

 

ተመሳሳይ ጽሑፎች፡-

ጣና ዓባይና አባ ባህሩ አንድም ሶስትም  http://amharic.abbaymedia.com/archives/31775

 

አማን ነህ ወይ ዓባይ? ጣናስ አማን ነወይ?

http://www.zehabesha.com/amharic/?p=78722#sthash.SbWMmb78.gbpl

 

ጥቅምት ሁለት ሲ አስር ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.