የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት አጭር ምልከታ – ሰማሃኝ ጛሹ (ዶ/ር)

ላለፉት 26 አመታት  የፖለቲካ  ስልጣን በመቆጣጠር አገሪቱን የሚያስተዳድረዉ ህወሃት ከአለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ከፈተኛ የዉስጥና የዉጭ ተቃዉሞ እያጋጠመዉ ነዉ። ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረዉ መለስ ዜናዊ በመሞተበት ወቅት የህወሃት መዳከም በስፋት የተዘገበ ቢሆንም ለተወሰኑ አመታት የመለስ ራእይ በሚሉት ማወናበጃ ስር በመሸጎጥ የተወሰነ እርቀት መሄድ ችለዉ ነበር። የመለስ መሞት የአገሪቱን የጭቆና ቀንበር በመለወጥ ረገድ ምንም ለዉጥ ሳያሳይ የቀጠለ ቢሆንም በኢህአዴግ ድርጅቶች ዉስጥ ግን ከፍተኛ ዉስጣዊ መሰነጣጠቅ አምጥቷል። መለስ ዜናዊ ደካማ ሰዎችን በመሰብሰብ የተሻለ መስሎ እንዲታይ ችሎታ ያላቸዉን ሰዎች እንዲገለሉ በማድረጉ እሱን ተክቶ ጀሌዎቹን የሚጠረንፍ ሰዉ ከድርጅቱ ዉስጥ መዉጣት አልቻለም። በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲቀጥል የተቀባዉ ሃይለማርያም ደሳለኝ በራስ መተማመን የሌለዉና በብዙዎቹ የኢህአዴግ ድርጅቶች ዉስጥ ቅቡልነት የሌለዉ ነዉ። ህወሃትም አንደበተ ቆላፋ በሆኑት እንደ እነ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ባሉት መሪዎቹ አማካኝነት በፌዴራል መንግስት ደረጃ የተወከለ መሆኑና በህብረተሰቡ ዉስጥ ስርአቱ የትግሬዎች ነዉ የሚለዉ ወቀሳ እያየለ ሲመጣ ከፊት ያሉትን ዋና ዋና ቦታዎች ከሌሎች ብሄሮች ለመጡት ለይስሙላም ቢሆን በመስጠት ዋናዉን የስልጣን  መሰረታቸዉን በደህንነትና በመከላከያዉ ላይ እንዲሆን ማድረጋቸው የህወሃትን ፖለቲካዊ የበላይነት አዳከመዉ።

 

ከሁለት አመት ወዲህ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች የተነሱት ህዝባዊ አመፆች የኢህአዴግ ዉስጣዊ ጥንካሬ እንዲፈተንና የገነቡት ማእከላዊ ዴሞክራሲያዊነትና አንድ ለአምስት የፈና መወቅሮች በህዝባዊ አመፁ ምክንያት የተዳከሙ ሲሆን ብዙዎቹ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉት አመራሮች ከህዝቡ ጋር በማበር በስርአቱ ላይ አምፀዋል። ነገሮችን ለማስተካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ገድለዉና አስረዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጀዉ ጥልቅ ተሀድሶ አድርገናል ቢሉም የአስቸኳይ ጊዜዉ ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ በኦሮምያ ክልል ህዝባዊ አመፆች ተቀጣጥለዉ ቀጥለዋል። በተለይም ደግሞ አቶ ለማ መገርሳ የሚመራዉ የኦሮምያ ክልል ራሱን ከህወሃት ነፃ ለማውጣትና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሙከራ በማድረግ ላይ እያለ የተከሰተዉ የሶማሌና ኦሮምያ አወሳኝ ክልሎች ግጭት ሁኔታዉን አባብሶታል። በህወሃት የሚደገፈዉ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ልዩ ጦር በኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ ያደረሰዉ መፈናቀልና ግድያ የኦሮሞን ህዝብ ያስቆጣና በኦህዴድና በዉጭ በሚገኘዉ አክራሪው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ቡድን ጋር ተናብቦ የመንቀሳቀስ ሁኔታን ፈጠረ። ሀወሃት የሶማሌ ክልሉን ወፈፌ ፕሬዝዳንት በሚመራዉ ልዩ ጦር ላይ እርምጃ መዉሰድ አለመፈለጉ ለስርአቱ ታማኝ በሆኑ የኦህዴድ ባላስልጥናት በኩል ሳይቀር ከፈተኛ ቅሬታ ፈጠረ። በተለይም አፌ ጉባኤዉ አባ ዱላ ገመዳ በስርአቱ ዉስጥ ባልተለመደ መልኩ ስልጣኑን መልቀቁን በማሳወቅ በህወሃት ላይ ያለዉን ቅሬታ ግልፅ ያደረገ ሲሆን ይህም ሁኔታ በስርአቱ ዉስጥ ያለዉን ዉስጣዊ ክፍፍል ግልፅ አደረገዉ። አባ ዱላ የኦሮሞ ህዝብ ለህወሃት እንዲገብር ላለፉት 26 አመታት የሰራ ቢሆንም ባንድ መልኩ የመለስ ዜናዊ መሞት የፈጠረዉ ክፍተት በሌላ በኩል የኦሮሞ ህዝብ ትግል የሰጠዉ ብርታት በግልፅ ተቃዉሞዉን እንዲያዎጣዉ ገፋፍተዉታል። ሁኔታዉ የህወሃት የበላይነት በማይጠገን ደረጃ እንደተዳከመ ያበሰረ ሲሆን የአገሪቱንም የፖለቲካ ትኩሳት ከፍ አድርጎታል።

 

ህወሃት አሁን ያለዉን የጎሳ ፌዴራሊዝም ሲያዋቅር ዋናው ታሳቢ ያደረገዉ ጉዳይ ለስልጣኔ ያሰጋኛል የሚለዉን አማራዉን ማህበረሰብ ለማዳከም በመሆኑ በጊዜዉ ህወሃት ኦህዴድ አስቦት የማያዉቀዉን ክልል ፈጥሮ ሲሰጠዉ ይህ ሁኔታ ይከሰታል ብሎ አልገመተም። ይህም የሚያሳየዉ ህወሃት በአማራዉ ላይ ያለዉ ስር የሰደደ ጥላቻ ለመግለፅ አገሪቱን ለመበትን በሚያደርስ ደረጃ  እንዲቀሳቀስ ማድረጉን ነዉ ። ብዙ ምሁራን ገና ከጅምሩ የፖለቲካዉ አካሄድ ለአገሪቱ ህልዉና አደገኛ መሆኑን ቢገልፁም ህወሃት ግን አሻፈረኝ በማለት ገፍቶበት አሁን ያለንበት መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሰናል። ላለፉት 26 አመታት የተራገበዉ የጎሳ ልዩነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ አገራዊ ማንነትና አብሮነት ተሸርሽሮ ሁሉም በየፊናው ብሄሬን ላድን በማለት እየተራወጠ ነዉ። በተለይም በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምነዉ የፖለቲካ ሃይል በዉሃ ቀጠነ ምክንያት የተከፋፈለና በህወሃት ተንኮል የተዳከመ በመሆኑ ተደራጅቶ ፅንፈኛ ብሄርተኞች የደቀኑትን የመበታተን አደጋ ለመመከት አልቻለም።

 

ይህ የፖለቲካ ሃይል በተዳከመበት ሁኔታ እየተካሄደ ያለዉ የኢህአዴግ ዉስጣዊ መከፋፈል በአገሪቱ ህልዉና ላይ የሚፈጥረዉ  ሁኔታ ከባድ ነዉ። የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን ስለኢትዮጵያ ህልዉናና ስለህዝቡ አንድነት ያላቸዉን እምነት መግለፃቸዉ አዎንታዊ ቢሆንም ይህ ብቻ የምንፈራዉን ቀዉስ ሊከላከላከልልን አይችልም። ምንም እንኳን  ለዘብተኛዉ የኦሮሞ የፖለቲካ  ቡድን የተሻለ መረጋጋት ለመፍጠር ጥረት ማድረጉ ባይቀርም በተለይ ዉስጣዊ ሽኩቻዉ ተባብሶ በጦሩና በደህንነቱ ዉስጥ መከፋፈል ከተፈጠርና ወደ አለመረጋጋት ከገባን ፅንፈኛ የኦሮሞ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የበላይነት ሊይዙ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ ነዉ። ይህም ሁኔታ ከህወሃት የመደናበር እርምጃና በሶማሌ ክልል አካባቢ ሊኖር የሚችለዉ ሁኔታ ጋር ተደማምሮ  ቀዉሱን ሊያባብሰዉ ይችላል።

 

አብዛኛዉ ህዝብ ሁኔትዉን በስጋት እየተከታተለ ሲሆን ምን መደረግ እንዳለበት ለብዙዎች ግልፅ አይደለም። በብዙ አገሮች እንዳየነዉ የብሄርና ሀይማኖት ልዩነቶች ባሉባቸዉ አገሮች የተካሄዱ የፖለቲካ ለዉጦች ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ተቀይረዉ ከዘቅጡበት መዉጣት አልቻሉም። ከዚህ ወጥመድ ለማምለጥ ያለን አማራጭ የብሄርና ሀይማኖት ልዩነቶቻችን ሳይበግሩን በአንድነት መቆምና  ይህንን አንድነት የሚያጠናክሩ የፖለቲካና ሲቪክ ማህበራትን አንድ ላይ በማምጣት ማደራጀት ነዉ።  አሁን ያለዉ በብሄር ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ አካሄድ መቋቋም የሚችልና ማህበረሰቦችን የሚያቀራርብ የፖለቲካ አካሄድ መፍጠር ሳንችል የፖለቲክ ቀዉሱ እየሰፋ ከመጣ ማንም አሸናፊ የማይሆንበትና የማንወጣበት ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ነዉ።

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.