በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ያለእቅድና ጥናት የተተከለው የሸንኮራ አገዳ ኪሳራ አደረሰ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 9/2010)በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ያለእቅድና ጥናት የተተከለው የሸንኮራ አገዳ ከጥቅም ውጪ በመሆኑ የ7 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ኪሳራ ማስከተሉን የፕሮጀክቱ ሃላፊዎች አመኑ።

ኢሳት በሸንኮራ አገዳው መበላሸት ምክንያት ከ7 ቢሊየን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን የውስጥ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት የምርምርና የልማት ማዕከል ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ኪዳኔ ተስፋሚካኤል እንደገለጹት አገዳውን ከማሳው ለማስወገድና ሁለተኛውን የሸንኮራ ምርት እንዲቀጥል ለማድረግ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል።

በጣና በለስ ሶስት ስኳር ፋብሪካዎችን እሰራለሁ ያለው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አንዱንም እውን አላደረገውም።

በ2002 በለስ 1፣በለስ 2ና በለስ 3 በሚል ለመገንባት ፋብሪካዎቹ ሲታቀዱ የአዋጭነት ጥናት ሳይኖርና በባለሙያዎች ሳይታመንበት እንደነበርም ይነገራል።

ከጥናቱ በፊት በነበረው ጥድፊያም የፋብሪካው ግንባታ ሳይጀመር ከ13 ሺ ሔክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ በመተከሉ ከፈረሱ በፊት ጋሪውን የማስቀደም ስራው ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል።

ሸንኮራ አገዳው አድጎ ከ2 አመት ጊዜ በኋላ ፋብሪካ ገብቶ ለስኳር ምርት ዝግጁ ቢሆንም አንድም ፋብሪካ ባለመድረሱ ከጥቅም ውጪ ሆኗል።

በአገዳው ማርጀት ምክንያት የስኳር ይዘቱን ያጣው 12 ሺ 2 መቶ ሔክታር ምርት በገንዘብ ሲሰላም ከ7 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑ ታውቋል።

ይህም 6 ሺ ቶን መፍጨት የሚችሉ ሁለት ፋብሪካዎችን መገንባት የሚያስችል ገንዘብ መክሰሩን ባለሙያዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ምርምርና ልማት ማዕከል ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ኪዳኔ ተስፋሚካኤል በበኩላቸው አሁን ከከሰረው 7 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሌላም ተጨማሪ ኪሳራ ይጠብቀናል ብለዋል።

ያረጀውን አገዳ ለማስወገድ ብቻ ተጨማሪ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ያስፈልገናል ባይ ናቸው።

አገዳውን አቃጥሎ ከማሳ ላይ ለማንሳት ከፍተኛ የሰውና የማሽነሪ ሃይል ያስፈልጋል።

አሁንም አዲስ አገዳ ለመትከል በዝግጅት ላይ ስልመሆናቸው እንጂ የፋብሪካዎቹ ግንባታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንዲገልጹ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም።

በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከተጀመሩ የስኳር ፕሮጀክቶች የኩራዝና የተንዳሆ ፋብሪካዎችም በተባለው ጊዜ ተጠናቀው ስራ ባለመጀመራቸው ከ10 ቢሊየን ብር በላይ በሸንኮራ አገዳ ማርጀት ምክንያት ኪሳራ መድረሱን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.