በኢትዮጵያ የሸቀጦች ዋጋ ሰማይ እየነካ ነው ተባለ

BBN news October 19, 2017

በኢትዮጵያ ያለው የሸቀጦች ዋጋ ሰማይ እየነካ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በመርካቶ፣ በአትክልት ተራ እና በሌሎችም የመዲናዋ የገበያ ማዕከላት ያለው የዕቃዎች ዋጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ነዋሪዎች በምሬት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው የዶላር ምንዛሪ ከፍ እንዲል ከተደረገ በኋላ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ችግሩ መከሰት የጀመረው የዶላር ምንዛሪ ተመን በወጣ በማግስቱ ቢሆንም፣ አሁን ግን የለየለት ደረጃ ላይ መድረሱንም ነዋሪዎቹ አክለው ተናግረዋል፡፡
የፍርራፍሬ እና አትክልት ዋጋ፣ የዘይት፣ የስኳር እንዲሁም የሌሎች መሰረታዊ ዕቃዎች ዋጋ የማይቀመስበት ደረጃ ላይ እየደረሰ እንደሚገኝ ከነዋሪዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እንደ ስኳር ያሉ ዕለታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ደግሞ፣ ከመወደድም በላይ ጭራሹኑ ከገበያ ላይ መጥፋታቸውን የሚናገሩት የችግሩ ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎች፣ በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ዘይቤ እጅግ እየከረረ መምጣቱንም ይገልጻሉ፡፡ የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ኑሮ እያነጋ ቢሆንም፣ በእጅጉ እየተጎዳ ያለው ግን ደሃው የህብረተሰብ ክፍል ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የዶላር ምንዛሪ ዋጋ መጨርመን ተከትሎ በአዲስ አበባ ብሎም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሸቀጦች እና የሌሎች ዋጋዎች መናር መፈጠሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ችግሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰበት ስለመምጣቱም በሰፊው እየተነገረ ሲሆን፣ በአንዳንድ ነጋዴዎች አካባቢ ያለው ሁኔታም እጅግ አስነዋሪ መሆኑንም ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ዕቃ ከመደበቅ ጀምሮ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በተወሰኑ ነጋዴዎች ዘንድ እየተስተዋለ እንደሚገኝ የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀሙ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች በድርጊታቸው ማፈር እንዳለባቸው ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.