ኦህዴድ የህወሃት ፍራንከንሽቴይን? – ባይሳ ዋቅ-ወያ

ኦህዴድ የህወሃት ፍራንከንሽቴይን? ባይሳ ዋቅወያ wakwoya2016@gmail.com

 

ሜሪ ሼሊ የምትባለዋ እንግሊዛዊት በ 1917 ዓ/ም ከአራት ጓደኞቿ ጋር ጄኔቫ አካባቢ ለዕረፍት መጥታ እያለች አንድ ቀን ማታ እንደሁ እሳት እየሞቁና እየተዝናኑ በጨዋታ መካከል እስቲ ከመካከላችን ማን በጣም አስፈሪ የሆነ ታሪክ (horror story) ባጭር ጊዜ ውስጥ ጽፎ ሊያቀርብ ይችላል ብለው ተወራረዱ። ከተወሰነ ሳምንት በኋላ የሥራችንን ውጤት እዚሁ አምጥተን እሳት እየሞቅን እንዳኝ ብለውም ወሰኑና ተለያዩ። ያኔ የ 19 ዓመት ወጣት ሜሪ መኝታ ክፍሏ ገብታ ዓይኗን ጨፍና የባጥ የቆጡን ስታወጣ ስታወርድ፣ ሊነጋ አካባቢ አስፈሪውን ታሪክ በህሊናዋ ቀረጸች። ሲነጋጋ ወጣ ብላ ባልኮኒው ላይ ተቀምጣ ከፊት ለፊቷ የተንጣለለውን የጄኔቫን ሃይቅ እየተመለከተች በዓይነ ኅሊናዋ የቀረጸችውን አስፈሪ ታሪክ በጽሁፍ ማስፈር ጀመረች። የታሪኩንም ባለቤት ዶ/ር ፍራንከንስቴይን ብላ ሰየመችው። በታሪኩ መሰረት፣ ዶ/ር ፍራንከንስቴይን የታወቀ ሳይንቲስት ኖሮ፣ ጊዜውን የሚያጠፋው ከሙታን ወንጀለኞች በድን ሬሳ ቁራጭ ሥጋ እየቀነጣጠበና አንድ ላይ እየሰፋ ነፍስ እንዲዘሩ ሙከራ ማድረግ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀንም ሁሉም ነገር እንዳሰበው ሆኖ ተሳካለት፣ ከወንጀለኞች ሬሳ ቅንጣቢ በጠፈጠፈው በድን አካል ላይ እፍ ሲልበት በድኑ ነፍስ ዘርቶ ተነስቶ ቆመ። ዶክተርም ተደሰተ፣ ዘመድ አዝማድም ተሰብስቦ፣ ከሙታን፣ ያውም ከወንጀሎች በድን አካል ቅንጣብ ነፍስ መፍጠር ይቻላል ብለው በመገረም አደነቁለት፣

አዲሱም ፍጡር ለፈጣሪው ዶክተር ታማኝነቱን እያሳየና ያለምንም ማንገራገር የሚሰጠውን ትዕዛዝም ሆነ ምክር እየተቀበለ ጎለመሰ፣ አደገ፣ ግና ቀናት ወደ ወራት፣ወራትም ወደ ዓመታት እየተለወጡ ሲሄዱ፣ አዲሱ ፍጡር ጭራቅ ሆኖ ቁጭ አለ፥ የልብ ልብም ይሰማውና የዶክተሩን ምክርም ሆነ ትዕዛዝ እንደድሮው አለቀበልም ማለት ጀመረ፣ ዶክተሩም በመገረምና ብሎም በመናደድ “እኔ በገዛ እጄ ፈጥሬህ፣ ያውም ከሙታን ወንጀለኞች ሬሳ እንደ ድሪቶ አንድ ላይ ሰፍቼ እፍ ብዬብህ ነፍስ ያዘራሁብህ በድን፣ እንዴት አትታዘዘኝም?” ይልና ይናገረዋል፣ ጭራቁም ሲመልስ፣ “አዎ፣ በርግጥ ፈጥረኄኛል፣ ግን ደግሞ የፈጠርከኝ ለራስህ ዝና ብለህ ነው እንጂ ለኔ በጎ አስበህ ስላልሆነ አሁን አድጌ ራሴን ችያለሁና ዳግመኛ ትዕዛዝም ሆነ ምክርህን አልቀበልም” በማለቱ በሁለቱ መካከል ኃይለኛ ቅራኔ ይፈጠራል። ይባስ ብሎም ጭራቅዬው ጉልበቱን ተማምኖ ኖሮ ፈጣሪውን ራሱን ዶ/ር ፍራንከንስቴይንን ማስፈራራትና እንደሁ ያለምክንያት ባካባቢው ያገኘውን ሁሉ እየገደለ መፎለል ይጀምራል። ዶክተሩም፣ ጭራቁ የባሰ አደጋ ሳያደርስ ይዞት ለማቆምና፣ከተቻለ እንደድሮው ሊያዘው፣ አለያም እፍ ብሎ የሰጠውን እስትንፋስ መልሶ ሊወስድበትና በድን ሊያደርገው ባረጀ ጉልበቱ ማባረር ይጀምራል፣ እንኳን ደርሶበት ሊይዘው ይቅርና ተጣርቶ እንኳ ወይ ሳያሰኝ፣ ከብዙ ቀናት ጉዞና ልፋት በኋላ ልቡ ፈንድቶ በረሃ ውስጥ በሚያሳዝን ሁኔታ ሞተ፣ ጭራቁ ግን ወደ አርክቲክ ፊቱን አዙሮ መሮጡን ቀጠለ” ብላ ደመደመች ሜሪ ሼሊ። አዎ ፈጣሪው ጠፍጥፎና እፍ ብሎ ነፍስ የዘራበት ፍጡር፣ ፈጣሪውን ራሱን አስፈራርቶት ለሞት የዳረገውን አሰቃቂ ታሪክ ጽፋ ሜሪ የውርርዱ አሸናፊ ሆነች።

ይህን ከብዙ ዓመታት በፊት የተጻፈውን አስፈሪ ታሪክ ለምን እንደሆነ እንጃ ሰሞኑን አስታውሼ፣ ባገራችን በመካሄድ ላይ ከሚገኘው አገራዊ ቀውስ ጋር አንዳች የሚጋሩት ነገር ያለው መሰለኝና እዚሁ ሜሪ ሼሊ ድርሰቱን በጻፈችበት አገር ሆኜ በታሪክ አጋጣሚው እየተገረምኩ ይህንንን አጭር መልዕክት አዘል ጽሁፍ ለናንተ ለማድረስ ወሰንኩ።

ወያኔ የትግራይን ጠቅላይ ግዛት ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ራሷን የቻለች አገር ለማድረግ የትጥቅ ትግል ያካሄድ በነበረበት ዘመን (ይቅርታ፣ ዛሬም ዓላማው ያው ይመስለኛል) በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ፈልገውም ሆነ ተገደው፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስከበርና ተገንጣዩን ወያኔን ለመደምሰስ ወደ ትግራይ ይዘምታሉ፥ ታድያ በጦርነት ጊዜ መሞትና መቁሰልም ያለውን ያህል መማረክም አለና፣ በርካታ ወጣቶች በተገንጣዩ የወያኔ ወታደር ይማረካሉ።

በለስ ቀንቶት ወያኔም በጦርነቱ የበላይነትን እያገኘና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን አሸንፎ እስክ አዲስ አበባ ተጉዞ የፖሊቲካ ሥልጣን መውሰድ መቻሉን ሲያረጋግጥ፣ የትግራዩ ዶክተር ፍራንክንሽቴይን አቶ መለስ ዜናዊ፣ እነዚህን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩትን ምርኮኞች ይሰበስባቸውና “የኔው ዓይነት የፖሊቲካ ፓርቲ ፈጥሬላችሁ አብረን ወደ አዲስ አበባ ሄደን የፖሊቲካ ሥልጣኑን እንይዛለን” ብሎ በራሱ አምሳል ከምርኮኞች ሰብስቦ በፈጠረው አካል ላይ እፍ ይልበትና ኦህዴድን ይፈጠራል። አዲስ አበባም ሲደርሱና አገሪቷ በክልል ስትከፋፈል፣ የኦህዴድ አባላትም የክልሉ ባለሥልጣናት ይሆናሉ። ግን ደግሞ በወረቀት ላይ ባለሥልጣን ይባሉ እንጂ በተግባር ደረጃ ምክሩንም ሆነ ትዕዛዙን የሚቀበሉት ከፈጣሪያቸው ከመለስና ሌሎች የወያኔ ባለሥልጣናት ነበር።

 

ከበድን ሬሳ በመለስ እስትንፋስ ነፍስ የዘሩት የኦህዴድ አባላትም፣ ፈጣሪያቸው መለስን እያወደሱ፣ ትዕዛዙንም ሆነ ምክሩን ያላንዳች ማንገራገር ሥራ ላይ እያዋሉ ቀናት ወደ ሳምንታት፣ ሳምንቶችም ወደ ወራት፣ ወራትም ወደ ዓመታት ተሸጋገሩ። ታድያ ኦህዴዶች እየጎለመሱና እየበሰሉ በሄዱ ቁጥር የፈጣሪያቸውን ምክርም ሆነ ትዕዛዝ እንደበፊቱ ያለማንገራገር ላለመቀበል ይወስናሉ። ማንገራገሩም ውሎ አድሮ ወደ እንቢተኝነት ተለወጠና ኦህዴድም ፈጣሪውን መፍራት ሳይሆን ማስፈራራትም ጀመረ። ዛሬ በተግባር እንደምናየው፣ ትናንት ፈጣሪያቸው ዶክተር ፍራንክንሽቴይን መለስ መግለጫም ሆነ መመርያ ሲሰጣቸው፣እጆቻቸውን አጣምረውና አጎንብሰው ትዕዛዙን ይቀበሉ የነበሩ አባዱላዎች ዛሬ በአደባባይ፣ ፈጣሪያቸውን ማስፈራራት ጀመረዋል። ፈጣሪውም ከበድን ሬሳ ጠፍጥፎ የሰራው ኦህዴድ የተባለው ፍጡር ዓይኑ እያየ ወደ ጭራቅነት መቀየር ብቻ ሳይሆን የራሱን የፈጣሪውን ህልውና መፈታተን መጀመሩን ይታዘባል። ፈጣሪው ወያኔም ጭራቅ እየሆነበት የመጣውን ኦህዴድን አሳድዶ ለመያዝና እፍ ያለበትን እስትንፋስ መልሶ ሊነጥቀውና ወደ ቀድሞ በድንነቱ ሊመልሰው ሙከራ እያደረገ ሲሆን፣ ጭራቁ ግን ከምንጊዜውም በላይ የልብ ልብ እየተሰማው፣ “ዋ! ትሞክረኝና” እያለው ነው። ሜሪ ሼሊም እንደደመደመችው፣ ፈጣሪው ፍጡሩን ለመያዝና ወደ በድንነት ሊመልሰው በማሳደድ ላይ ሲሆን፣ ፍጡሩ ግን፣ “አዎ፣ ለብዙ ዓመታት እንደፈለግህ ስታዘኝ፣ እኔም እንደፈጠርከኝ ስለማውቅ ስታዘዝልህ ነበር፥ ካሁን በኋላ ግን አሻፈረኝ” ብሎ ደረቱን ነፍቶ መንጎራደድ ጀምሮአል።

አዎ!ይህ ዓይነቱ ክስተተ ማለትም ሰዎች ራሳቸው ጠፍጥፈው የሰሯቸው ፍጥረታት ተመልሰው ፈጣሪዎቻቸውን አስፈራርተው ሲገድሉ ወይም ለችግር ሲዳርጉ ማየትና መስማት አልፎ አልፎም ቢሆን እየተለመደ መጥቷል። በተለይም በፖሊቲካ ህይወት ሂደት ውስጥ። ይገርማል! ራስህ ከበድን ሬሳ ጠፍጥፈህ የፈጠርከውና እፍ ብለህ ነፍስ ያዘራህበት ፍጡር ተመልሶ አንተኑ ፈጣሪውን ሲያስፈራራህና ሊገድልህ ሲሞክር!

“ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ አቃተን” አሉ አሉ ታላቁ የፊውዳሉ ዘመን የፖሊቲካ ሊቅ ፊታውራሪ ቁሴ ዲነግዴ (ኋላ ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ አባ መላ የተባሉት)። ዓፄ ኢያሱን ከሥልጣን ለማውረድና ወጣቱን ተፈሪ መኮንንን (ኋላ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ) ለማንገሥ ወሳኙን ሚና የተጫወቱት እሳቸው ነበሩ ይላል የታሪክ መጽሃፋችን። የኋላ ኋላ ግን ዓፄው እየጎለመሱና ዓልጋውንም እያመቻቹ ሲመጡ፥ የልብ ልብ ይሰማቸውና ፊታውራሪን ማግለል ሲጀምሩ ነው አሉ ታዋቂውና ጊዜ ፊቱን ያዞረባቸው አባ መላ፣ በትንሿ ጎጆአቸው ውስጥ ቁጭ ብለው እሳት እየሞቁ “ ቁጭ ብለን የሰቀልነውን………” ብለው ያንጎራጎሩት ይባላል። መንግሥቱ ኃይለማርያምም የአብዮትን ሀሁ ያስተማሩትን ምሁራንን ራሱ መልሶ በልቷቸዋል፣

ዛሬም ዶክተር ፍራንክንሽቴይን መለስ ሰሚ ያለው አይመስለኝም እንጂ፣ ከሥላሴ አካባቢ መኖርያው በተገላበጠ ቁጥርና የዛሬውን የኦህዴድ ቀረርቶ ሲሰማ፣ “ምነው ያኔ ከሙታን ሥጋ ቁርጥራጭ ጠፍጥፌ ስፈጥርህና እፍ ስልብህ አምላክ እጄን በቆረጠውና ሳንባዬንም ባጠፈው ኖሮ፣ ጠፍጥፌም ባልሰራሁህና እፍም ባላልኩብህ ነበር” እያለ የቁጭት ዕንባ ሲያነባ ይታየኛል። ግና ምን ያደርጋል፣ በጣም ዘግይቷል። ሜሪ ሼሊ ዛሬ ብትኖርና ወዳገራችን ለዕረፍት መጥታ ሳፋሪ ሎንጅ ፊትለፊት የተንጣለለውን የላንጋኖን ሓይቅ እየተመለከተች፣ ፊንፊኔ ላይ በመካሄድ ያለውን ትዕይንት ብትገመግም፣ በመጀመርያ ድርሰቷ እንደጻፈችው ሳይሆን፣ ፍጡሩ (ኦህዴድ) ፈጣሪውን (ወያኔ) ዶክተር ፍራንክንሽቴይንን ወደ ሰሜን አርክቲክ እያሳደደው ገደለው ብላ የምትጽፍ ይመስለኛል።

ግን ደግሞ ዕውነተኛው የሰው ልጆች ታሪክ የራሱ ቦይ ስላለው ማንኛቸው አባራሪ ማንኛቸው ደግሞ ተባራሪ እንደሚሆኑ በርግጠኝነት መደምደም አይቻልም። በኔ ግምት ግን ጥሩ የሚሆነው፣ ማንም ማንንም ሳያባርር፣ ሁሉም በእኩልነት ደረጃ፣ በክብ ጠረጴዛ ዙርያ ቁጭ ብሎ ማውራትና የጋራ ችግርን በጋራ መፍታት ይመስለኛል። ያገሪቷንም ችግር ለመፍታት ደግሞ መኖር ያለበት ግንኙነት፣ በፈጣሪና ፍጡር መካከል እንዳለው ሳይሆን በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ባይ ነኝ።ያ እስከሆነ ድረስ፣ ዶክተር ፍራንክንሽቴይን መለስም አርፎ ይተኛል፣ ኦህዴድም አሳዳጅ፣ ወያኔም ተሳዳጅ ከመሆን ይድናሉ።

ለመደምደም ያህል፣ ላንዳንዶቻችሁ፣ ያሟረትኩ ሊመስላችሁ ይችላል፣ ላንዳንዶቻችሁ ደግሞ ገና ምኑ ከምን ተለየና ነው ደርሰህ ትንቢት ነጋሪ የሆንከው ልትሉኝ ትችላላችሁ፣ ይሁን፣ የፈለጋችሁትን በሉ፣ እኔ ግን የፈለግሁትን የማሰብ መብት ያለኝ ታዛዥነቴም ለዓምላኬ ብቻ የሆነ፣ ሟርተኛም ለመሆን ከማንም ምድራዊ ኃይል ምክርም ሆነ ትዕዛዝ የማልቀበል የግዜር ፍጡር ስለሆንኩ፣ በኔ ሟርተኝነት ብዙም አትጨነቁ እላለሁ።

 

ተጻፈ በጄኔቫ

ኦክቶበር 20 ቀን 2017 /

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.