የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎቹ ምግብ እያቀረበ አለመሆኑ ተጠቆመ

BBN news October 24, 2017

በኦሮሚያ ስር የሚገኘው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎች የሚበላ ምግብ እያቀረበ አለመሆኑን ተማሪዎች ለቢቢኤን ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው አዲሱን የትምህርት ዘመን ከጀመረ ጥቂት ጊዜው ሲሆን፣ ምክንያቱ ባልታወቀ ጉዳይ ለተማሪዎቹ ምግብ እያቀረበ አለመሆኑ ታውቋል፡፡ ሁኔታውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለቢበኤን የሰጡ ተማሪዎች፣ ዩኒቨርሲቲው ምግብ እያቀረበ ባለመሆኑ ችግር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በረሃብ ሊፈጁን ነው›› ሲሉም አክለዋ፤፡፡
ዩኒቨርሲቲው በምን ምክንያት የካፌ አገልግሎቱን እንዳቋረጠ እስካሁን በይፋ የገለጸው ነገር የለም፡፡ ተማሪዎቹ እጃቸው ላይ ባለው ገንዘብ ውጭ ወጥተው እየተመገቡ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ግን ከባድ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን ከጓደኞቻችን ጋር ያለንን ሳንቲም አጋጭተን ምግብ ገዝተን እየበላን እንገኛለን፡፡›› ሲሉ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎቹ፣ የግቢው አስተዳደር የካፌ አገልግሎቱ የተቋረጠበትን ምክንያት በግልጽ እንዲነግራቸውም ጠይቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው እንደማንኛውም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎቹ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት የማቅረብ ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ አሁን ግን ይህን አገልግሎቱን ካቋረጠ ሳምንት አልፎታል – እንደ ተማሪዎቹ ገለጻ፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ብዙኃኑን ተማሪ በመወከል ችግሩ የተፈጠረው በምን ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ለግቢው አስተዳደር ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፣ የረባ ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸውንም የችግሩ ሰለባዎች ተናግረዋል፡፡ ሁኔታው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ግን ትምህርታቸውን ለመቀጠል እንደሚቸገሩም አስገንዝበዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.