የሙሰኞች ወግ! – (በጌታቸው ሺፈራው)

 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት የሙስና ጉዳይ የሚታይበት ችሎት ነው። ይህ ችሎት የስንትና ስንት ሙሰኞችን ጉዳይ ይዞ በገዥዎቹ ትዕዛዝ ክሳቸውን አቋርጧል። በመቶ ሚሊዮን የዘረፉትን ሙሰኞች ክስ እያቋረጠ አሰናብቷል።

በእርግጥ ሙስና ሙስና ነው! ግን ፍርድ ቤቱ ተቆርቋሪ፣ አባሪ እና ተገን የሚሆናቸው ባለስልጣን እና ፓርቲ ያላቸውን ሙሰኞች እየለቀቀ፣ ምስኪን ሙሰኞች ላይ ብቻ ይፈርዳል።

በእርግጥ ሙሰኛ ሙሰኛ ነው። ግን መቶ ሚሊዮን ዘርፎ ክሱ የሚቋረጥለትና የማይቋረጥለት ሙሰኛ ይለያያል። በልቶ የተከሰሰ እና በልቶ በነፃ የተለቀቀ ይለያያል።

ደግሞም በመቶ ሚሊዮን የሚዘርፍ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ችግር ካላመጣ በስተቀር ክሱ አይቀጥልም። መዝረፉ እየታወቀ ክሱ ይቋረጥለታል። በገዥዎች ትዕዛዝ!

ሙሰኞች ሁሉ እኩል አይደሉም። 77 ቢሊዮን ዘርፎ ምንም አይባልም። 55 ሆነው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን የዘረፉትን ከሰስን ተብሎ ብዙ ፕሮፖጋንዳ ይነዛል። ከዛ ግን አብረዋቸው የዘረፉት ትልልቅ አሳዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ ያደርጋሉ።

የፖለቲካ ሰልጣን ካልነካ በስተቀር ቢሊዮንና ሚሊዮን ዘርፎ አይፈረድበትም። ቢሊዮንና ሚሊዮን ዝም ብሎ አይዘረፍም። ያለ ትልልቅ አሳዎቹ እውቅና እና ድጋፍ ሚሊዮንና ቢሊዮን አይዘረፍም። እናም ሚሊዮኖችን የዘረፉት ክሳቸው ይቋረጣል። ወይንም ፈፅሞ አይታሰሩም።

ክሳቸው የሚቀጥለው ምስኪን “ሙሰኞች” ናቸው በመቶ ብሮች ሙስና የሚሰሩት። ስርዓቱ አስገድዷቸው ሙስና የሚሰጡት።

ዛሬ በርካታ ሚሊዮንና ቢሊዮን ዘረፉ ተብለው ጉዳዩ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ከዋለ በኋላ ወር ባልሞላ ጊዜ ክሳቸውን የሚያቋርጠው ችሎት ጥፋተኛ ያለው ሙሰኛ እጅግ ምስኪን ነው። ያደረሰው ” ኪሳራ” መቶ ብር ነው። መቶ ሚሊዮን በልተው ክሳቸው በሚቋረጥነት ችሎት፣ 77 ቢሊዮን አውድመው ምንም በማይባሉበት ሀገር በመቶ ብር ሙስና የሚሰሩት ምስኪን ሙሰኞች ናቸው። ስርዓቱ ሙስና እንዲሰሩ የሚያስገድዳቸው!

ዛሬ ዘራፊዎችን ክሳቸውን አቋርጦ በሚሸኘው ችሎት ጥፋተኛ የተባለው ግለሰብ የባጃጅ ሾፌር ነው። ከሀገር በቀን መቶ ሀምሳ ሚሊዮን የሚዘርፉ እንዳሉ ሁሉ እሱም ከእየ ተሳፋሪው ብር ከሀምሳ ይቀበላል። ይህ ምስኪን የትራፊክ ህግን ይጥስና ትራፊክ ይይዘዋል።

የኢትዮጵያ ሾፌሮች በርካታ ጉዳይ ላይ ያማርራሉ።ለምሳሌ በሚሊዮን ሙስና በልተው የማይከሰሱት ባለስልጣናት ደስ ሲላቸው ከ30 ደቂቃ በላይ መንገድ ያዘጋሉ። ወደ ቤታቸው፣ ወደ ሆቴል………ወደ ፈለጉት ሲሄዱ መንገድ ይዘጋል። የሾፌሮች ስራ ይቆማል። ሌላም የሚያስመርራቸው ጉዳይ አለ።

ሾፌሮች ብር ከሀምሳ የሚያስገኝላቸው አንድ ተጨማሪ ሰው ጭነው ከተያዙም የመንጃ ፈቃዳቸውን ይነጠቃሉ። የመኪናው ታርጋ ይፈታል። ለጥፋታቸውስ ቅጣት ይገባ ነበር። ግን ችግሩ ወዲህ ነው!

ከትራፊክ መንጃ ፈቃዳቸውን ወይንም ታርጋውን ተቀብለው ስራ ለመጀመር አንድም ሁለት ቀንም ይፈጃል። አንድም ሁለትም ቀን ስራ ፈትተው ላለመቀመጥ ታዲያ ለትራፊኩ መቶም ሁለት መቶም ብር ሸጉጠው መንጃ ፈቃዳቸውን ቶሎ ያስመልሱና ብር ከሀምሳ፣ ሁለት ብር ከሀምሳም ከህዝብ ይለቅማሉ።

ሾፌሮቹ ሙስና የሚሰሩት የሀገር ገንዘብ ላይ ሳይሆን ኪሳቸው ላይ ጉዳት አድርሰው ነው። የባጃጁ ሾፌርም ያደረገው ይህንኑ ነው። ቶሎ ወደ ስራ ለመመለስ ለትራፊኩ መቶ ብር በመስጠቱ ተከሰሰ። መቶ ሚሊዮን፣ ቢሊዮንም ዘርፈው በሚከሰሱበት ችሎት እሱም ክስ ተመሰረተበት።

በእርግጥ ሙስና ሙስና ነው። መቶ ብርም ሙስና ነው። ግን ይህ ምስኪን በተከሰሰበት ችሎት ቢሊዮን ሰርቀው ክሳቸው ተቋርጧል። እነሱ ከህዝብ መቶ ሚሊዮንና ቢሊዮን ዘርፈው በሁለት ሳምንት ውስጥ ክሳቸው ተቋርጦ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። እሱ ግን ከኪሱ ባወጣው መቶ ብር ሁለት ወር እስር ቤት ቆይቷል። አሁንም ጥፋተኛ ተብሏል። ምን አልባት ተጨማሪም ይፈረድበታል!

ምስኪን ሙሰኛ ነዋ! ሀገር ላይ ሳይሆን ኪሱ ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ በቀን መቶ ሚሊዮን ሳይሆን ብር ከሀምሳ ሲለቅም የሚውል ምስኪን ነዋ! ተገን፣ አብሮት የሚዘርፍ ባለስልጣን የለውማ! ኢትዮጵያ ውስጥ የሙሰኛ ደረጃ ይህን ያህል የተራራቀ ነው። ሰው በዘረፈው መጠን ከለላ የሚያገኝበት ሀገር ሆናለች! ፍትህ በሌብነት፣ በሙሰኝበት ደረጃ የሚሰጥበት ሀገር ሆናለች። የሁለት የተለያዩ ዓለማት ሰዎች ሀገር! የጉድ ሀገር!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.