አንድ እርምጃ ወደፊት! – ከመኮንን አሻግሬ (ቨርጂኒያ አሜሪካ)

 

 

ወያኔ የአንድ ብሔር የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት ለማስፈን ሲል በዘረጋዉ ሥርዓትና ሆን ብሎ በሚያሰራጫቸዉ መርዘኛ ንግግሮችና ጽሑፎች ሳቢያ በሕዝብ መካከል አለመተማመን እንዲኖርና ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። በሒደትም እንደሀገር የመቀጠል ሁኔታ አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል። ከዚያም በላይ የእርስ በርስ ጦርነት ወይም መተላለቅን የሚያስከትል አዝማሚያ በጉልህ እየታየ ነዉ። በመሆኑም ከመቼዉም ጊዜ በላይ ሁላችንንም ሊያሳስብና የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ ግድ የሚል ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለኛል።

 

በዉጭ ሀገር የምንኖር ሰዎች እንደሁለተኛ ዜጋ በምንኖርበት ሀገር ላይ ያለን የመሥራት ነጻነት፣ የመብት ጥበቃ፣ በግዛቱ ዉስጥ በየትኛዉም ቦታ ካለሥጋት የመኖር መብታችን ሀገራችን ላይ እንደዜጋ ማግኘት ከባድ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ። እንደዉም የ____ ብሔር ተወላጆች ከ ___ ዐመታት በላይ ከኖሩበት አካባቢ ንብረታቸዉን ተነጥቀዉ እንዲወጡ ተደረጉ … በ ____ ክልል ይኖሩ የነበሩ የ ___ ብሔር ተወላጆች የአካባቢዉ ብሔረሰብ ተወላጅ አይደላችሁም በሚል በደል እየደረሰባቸዉ እንደሆነ ተገለጸ … ወዘተ የመሳሰሉትን ዜና መስማት ከመበራከቱ የተነሣ “ሀገሬ” የሚለዉ ከደማችን ጋር የተዋሃደዉ ቃል “ክልሌ” በሚል ወንዝ በማያሻግር አባባል እንዳይተካ ያሠጋል። ለነገሩ ይህም ሳያንስ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ልዩ ታጣቂ ኃይል በሚደርስባቸዉ ጥቃት ከአካባቢያቸዉ እየተፈናቀሉ አይደል!?

 

ከሥርዓቱ ጋር ካልተጠጉ ወይም “የሥርዓቱን ሰዉ” በሽርክና ካላስገቡ በስተቀር በተለይም ትላልቅ ንግድ ዉስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መሥራት የማይደፈር ወይም ዳገት ቁልቁለቱ የበዛና ለበርካታ እንግልት የሚዳርግ መሆኑን ስናስተዉል “ይህ ሀገር የኔም ነዉን?” የሚል ጥያቄ ዉስጥ ሊከተን ይችላል። በአጠቃላይ ማንም ሰዉ ካለምንም በቂ ምክንያት ከሥራ ወይም ከሚኖርበት አካባቢ ለመፈናቀል፣ ለተለያየ ዕንግልት ለመዳረግ፣ ለመታሰርና ከዚያም በላይ የከፋ ችግር ዉስጥ ለመዉደቅ በጣም የቀረበ መሆኑ አይካድም። በዚህም የተነሣ የዕለት ተዕለት ኑሮ በሥጋት የተዋጠና የመኖር ዋስትናን የነፈገ በመሆኑ ከዛሬ ነገ የከፋ ነገር እንዳይመጣ እየሆነ ያለዉን “ተመስገን” ብሎ ለመቀበል የሚዳርግ ሆኗል።

 

ሀገር የማዳን ሥራ ሁሉን ዐቀፍና ርብርብ የሚጠይቅ መሆን ይኖርበታል። በቅድሚያ ሀገራችንን ከወያኔ አገዛዝ ነጻ ማዉጣት ቢሆንም በቀጣይነት ሥርዓቱ የተከላቸዉን ቁርሾዎች፣ ጠባሳዎች፣ በአንድ ላይ አብሮ የመኖር ስሜት መኮሰስ፣ ተቻችሎ የመኖር ዘይቤ ማጣትና ለመሳሰሉት ጉዳዮችም በተጓዳኝ ምላሽ መስጠት ይጠበቃል። ታዲያ ይህ ሁሉ ኃላፊነት በፖለቲካና መሰል ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራኖች … ወዘተ ላይ ብቻ ሊጣል አይገባም። የኃይማኖት ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራትና ሌሎችም የትግሉ አካል መሆን ይኖርባቸዋል። በተለይም ከኃይማኖት ተቋማት ብዙ ይጠበቃል።

 

እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረዉ ሰዉ ላይ ግፍ ሲፈጸም፣ በብሔር የተነሣ አድልዖ፣ መገለል ወይም መፈናቀል ሲደርስ፣ የጦር መሣሪያ ባልታጠቁ ተቃዋሚዎች ላይ የመንግሥት ታጣቂዎች የተኩስ እርምታ ሲከፍቱ፣ አንዱን ሕዝብ በሌላዉ ላይ በማነሣሣት ዕልቂት ሲፈጸምና የመሳሰሉት ተግባራት ሲፈጸሙ የሃይማኖት መሪዮች አይተዉ እንዳላዩ ማለፍ ያለባቸዉ አይመስለኝም። በተለይም በማዉቀዉ የክርስትና እምነት ግፍን መቃወምና ለተበደሉት ወገኖች ርኅራኄና ወገንተኝነት ማሳየት ግድ እንደሚል አምናለሁ። ይህንን ማድረግ በምንም መልኩ ዐመጽ ማካሄድ ወይም በመንግሥት አሠራር ዉስጥ ጣልቃ መግባት ተደርጎ ሊተረጎም አይችልም። በመሆኑም እያንዳንዱ ኃይማኖት እንደየእምነቱ በግለሰብ፣ በተቋምና በሕዝብ ላይ የሚፈጸመዉን በደል መቃወም ወይም ማዉገዝ ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም የዛሬ ዓመት አካባቢ ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ኃ/ማርያም ደሳለኝ የጻፉት ደብዳቤ ጥሩ ተሞክሮ እንደሆነ አምናለሁ። በኦሮሚያ ክልል፣ በጎንደር፣ በባህርዳርና በአካባቢዉ ተቀስቅሶ የነበረዉን ሕዝባዉ ዐመጽ ለመግታት መከላከያ ሠራዊቱ ተገቢዉን ዕርምጃ እንዲወስድ ጠቅላይ ሚ/ሩ ማዘዛቸዉን በመቃወም የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ ነበር። ይህ ያልተለመደ ደብዳቤ የብዙዎችን ቀልብ እንደሳበ ተረድቻለሁ። እንዲሁም ፓስተር ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና በስብከት መካከል “… እግዚአብሔር የሚያዉቀን በኢትዮጵያነት ነዉ …”  በሚል በሀገራችን ሥር የሰደደዉን ጎሣዊ አመለካከት በማዉገዝ ያስተላለፉት መልዕክት ተጠቃሽ ነዉ። ስለሆነም እንደዚህ ዓይነት መሰል ተቃዉሞዎች በተለያየ መልኩ መቀጠል ይገባቸዋል።

 

ከዚህ ጋር በተጓዳኝ በኅብረተሰቡ ዘንድ መስተዋል ያለባቸዉ ጉዳዮች እንዳሉ አምናለሁ። የምንከተለዉ አቅጣጫ በፊዚክስ ላይ እንደሚጠቀሰዉ የሴንትሪፔታል ኃይል (Centripetal Force) ያለዉ ስልት መሆን አለበት። አንዱ ሌላዉን የሚያገል ሳይሆን እንደዉም የሚስብ፣ የሚጎትት፣ እኔንም ይመለከተኛል በሚል የባለቤትነት ድርሻ የሚያጎናጽፍ መሆን እንዳለበት አምናለሁ። ይህንን በማድረግ አገዛዙን በማሣሣትና መሠረት በማሳጣት ተጠቃሚ የሚሆነዉ ሀገር በማዳን ጎራ የሚሰለፈዉ ወገን ይሆናል። ሆኖም ግን ሌላዉን ወገን በመግፋት ወይም በማግለል የሴንትሪፊዩጋል (Centrifugal) መሰል ስልት የምንከተል ከሆነ ይበልጥ የሚጠቀመዉ አገዛዙ ብቻ ነዉ። በዚህም የተነሣ የምንመኘዉ ዉጤት በቶሎና በሚፈለገዉ ደረጃ እንዳይመጣ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ እንደሚችል አምናለሁ።

 

ለዚህ ለተባለዉ ዓይነት አካሄድ ዕንቅፋት ይሆናሉ በሚል በራሴ የምገነዘባቸዉ ነገሮች አሉ። በርግጥ ምርምር በማድረግ የደረስኩባቸዉ ነጥቦች አይደሉም። እንዲሁ ከማየዉ፣ ከማነበዉና ከምሰማዉ በመነሣት ብቻ ነዉ። በመሆኑም የግል አስተያየት እንደመሆኑ መጠን ተሳስቼ ከሆነ ወይም ለኔ ሳይታየኝ የቀረ ነገር ካለ ለመታረም ፈቃደኛ ነኝ። ይህንን ካልኩ ዘንድ ወዳልኩት ነጥብ በዝርዝር ለማስቀመጥ እወዳለሁ።

 

  • የብሔር ፍረጃ

ሀገራችን ለምትታመስበት ችግር ዋንኛ ተጠያቂዎች ወያኔና ጭፍሮቹ ናቸዉ። ሕወሐት የአንድን ብሔር የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማምጣት በጠነሰሰዉ ሤራ ምክንያት አሁን ሀገራችን የደረሰችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። ኢ.ሕ.አ.ዲ.ግ. በሚል ጥላ ሥር የተሰባሰቡት ሌሎቹ ድርጅቶችም የሕወሐት ተፈጣሪ ቢሆኑም ለሀገሪቷ ዉድቀት ከተጠያቂነት አይድኑም።

 

ወያኔዎች (ምናልባት ምክትል የገንዘብ ሚኒስቴር ከነበሩት አቶ ወንድወሰን በስተቀር) በሙሉ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ናቸዉ። ሆኖም ግን የትግራይ ሕዝብ ይወክሉናል በሚል በስሙ እንዲታገሉለት ተስማምቶ ያቋቋመዉ ድርጅት አይደለም። ይህ መርሕ በተመሳሳይ ሌሎች የብሔር ድርጅቶችንም ይመለከታል። በመሆኑም የብሔር ድርጅቶች ለሚፈጽሙት ጥፋት እንወክለዋለን በሚል በስሙ ስለተቋቋሙ ብቻ የዚያ ብሔር ሕዝብ የሚጠየቅበት የሞራል መሠረት አይኖርም። እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ በብ.አ.ዲ.ን. ምክንያት የአማራዉ ሕዝብ፣ በኦ.ሕ.ዲ.ድ. ምክንያት የኦሮሞ ሕዝብ፣ በኦ.ነ.ግ. ምክንያት በተለይም በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአሰቦት ገዳምና በሌሎችም አካባቢዎች ለደረሰዉ ዕልቂት የኦሮሞ ሕዝብ ተጠያቂ በሆነ ነበር።

 

ከሌሎች አጋር ድርጅቶች በተለየ መልኩ የትግራይ ሕዝብ በሕወሐት አገዛዝ ተጠቃሚ ሆኗል፤ ሕዝቡም ወገንተኛነት አለዉ በሚል ሁለቱንም አንድ አድርጎ ማየቱ ተገቢ ነዉ የሚሉ ወገኖች አሉ። ለእኔ በቂ መከራከሪያ አይመስለኝም። በርግጥ ችግሩን በቅንነት ለመፍታት ከተፈለገ ሐቁን መካድ አያስፈልግም። ይኸዉም የትግራይ ሕዝብ በአገዛዙ ተጠቃሚነቱ አይካድም። ለዚህም አስረጂ ካስፈለገ “የመለስ ልቃቂት” በሚል አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ለንባብ ያበቁትን መጽሐፍ በማንበብ ብቻ ስፋቱንና ጥልቀቱን ጭምር መረዳት ይችላል።

 

ወያኔ ለትግል “ሀ” ብሎ ሲነሣ ታሳቢ ያደረገዉ የትግራይን ሕዝብ ነዉ። አጥንቱን የከሰከሰዉ፣ ደሙን ያፈሰሰዉና ከአምሳ ሺህ ሰዉ በላይ ገብረናል የሚሉት ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለትግራይ ሕዝብ ነዉ። ይህ ደግሞ ተራ ወሬ ሳይሆን በርካታ ማስረጃ ማቅረብ የሚቻልበት ጉዳይ ነዉ። ሌላዉ ቢቀር እንኳን አቶ ገብሩ አስራት “ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ትግራይን ነጻ ካወጣን በኋላ ለምንድን ነዉ ዉጊያ የምንቀጥለዉ በሚል ከሠራዊቱ የሚኮበልሉ ተበራክተዉ እንደነበር ተጠቅሷል። በዚህም ምክንያት ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ባለዉለታ ተደርጎ ቢቆጠር አይደንቅም። እኛም ቢሆን ለትግራይ ሕዝብ በመቆሙና በመዋደቁ ሊደንቀን አይገባም። ችግሩ በማን ትከሻ? የሚለዉ ላይ ነዉ።

 

ብ.አ.ዲ.ን. ወይንም ኦ.ሕ.ዲ.ድ. አመራሮች እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ ታማኛ ሆነዉ ፍጹም ወገንተኝነት ቢያሳዩ ቅር የሚለዉ አካል ያለ አይመስለኝም። በሕዝብም ዘንድ ከበሬታና ተሰሚነት ይኖራቸዉ ነበር። ግን አልሆነም። ገና ከጅምሩ ወያኔ ዐላማዉን በተሻለ ደረጃ ለማሳካት እንዲረዳዉ ሲል የተፈጠሩ በመሆናቸዉ ታማኝነታቸዉ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ አይደለም። ለይስሙላ የክልላዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ ቢቀመጡም ከበላይ ሆኖ የሚዘዉራቸዉ ወያኔ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ። ከዚያም በላይ የትግራይ ታጣቂዎችን በክልሎች ላይ በማሰማራት እስከግድያ ድረስ የፈለገዉን ማድረግ መቻሉን አሳይቷል። እያሳያም ይገኛል። ታዲያ በዚህን ጊዜ የብ.አ.ዲን. ወይንም የኦ.ሕ.ዲ.ድ. ባለሥልጣኖች እንቅስቃሴዉን ለመግታት ቀርቶ ድርጊቱን ለማዉገዝ እንኳን ወኔ እንደሌላቸዉ ይታወቃል። በዚህም የተነሣ ሕዝቡ እንዳሉም ሊቆጥራቸዉ አልቻለም።

 

ለንጽጽር ለማቅረብ የተፈለገዉ ወያኔ በተሻለ ደረጃ እወክለዋለሁ/ታግይለታለሁ ለሚለዉ ሕዝብ ታማኛና ትርጉም ያለዉ ሥራ እንደሚሠራ ለማሳየት ነዉ። ችግሩ ያለዉ እዚህ ላይ አይደለም። በሐቅና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ቢከናወን ኖሮ በሌላዉ የኅብረተሰብ ዘንድ የተቃዉሞ ምንጭ ባልሆነ ነበር። ወያኔዎች ግን እያደረጉ ያሉት በፊዴራል መንግሥት ያላቸዉን ሥልጣን በመጠቀም የሕዝብን ሀብት ለኤፈርትና ለግለሰብ ኪስ ማደለቢያ ማድረግ፣ መሬት መቀራመት፣ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንን በአንድ ብሔር መጠቅጠቅ … ወዘተ ነዉ። እንደዚህ ዓይነት ዐይን ያወጣ ይሉኝታ ቢስ አድራጎት ማንም ሰዉ ሊቀበለዉ አይችልም። ሁሉም ዜጋ በማናቸዉም መልኩ በእኩልነት ታይቶ የሀገሪቷ ሪሶርስ ተጠቃሚ መሆንን ይፈልጋል። የሆነዉ ሆኖ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዎች በዋንኛነት ይህንን መሰል ኢፍትሐዊ ሥርዓት ጠንሳሾችና አራማጆች የሆኑት የወያኔ አባላትና እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ለሥርዓቱ ታማኝ ሆነዉ ሽፋን በመስጠት ለወያኔ ያደሩ ግለሰቦች ብቻ ናቸዉ።

 

ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ጽሑፎችንና ንግግሮችን ስሰማ ግን በጣም አዝናለሁ። የትግራይን ሕዝብ በሙሉ የወያኔ አባል አድርጎ የመፈረጅ ሁኔታ ይታያል፤ ይደመጣል። ከዚያም በላይ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ … ወዘተ በሚል የብሔር ስም እየጠሩ የመዝለፍ ነገር ያጋጥማል። በተለይም በፌስቡክ መረን የለቀቀ ነገር ይታያል። አሁን አሁንማ የትግሬዉ ባለስልጣን አቶ እከሌ፣ የትግራይ አገዛዝ … የሚሉ አጠቃቀሞች እየተለመዱ መጥተዋል። ይህ ፈጽሞ አግባብ አይመስለኝም።

 

ማንም ሰዉ መጠየቅ ያለበት በግሉና በፈቃደኝነት አባል በሆነበት ድርጅት በኩል መሆን ይገባል። በግለሰቦች ምክንያት በጅምላ ብሔር ላይ መንጠላጠል ተገቢ አይመስለኝም። ስለሆነም በብሔር ላይ ዘለፋ ማካሄድ እጅግ ከሥነ ምግባር  የወጣና ኢሞራላዊ ድርጊት ነዉ። በዚያ ላይ ይህንን ሥርዓት በማዉገዝና በመታገል ላይ ያሉትን የትግራይ ተወላጆች ጭምር የሚነካ በመሆኑ በፍጹም መታረም ያለበት አካሄድ ነዉ። በፍጥነት  ካልተገታ ግን አንዱ ለሌላዉ ግብዓት በመሆን በመጨረሻም በቀላሉ ልንወጣዉ የማንችለዉ ከፍተኛ ችግር ላይ እንዳይጥለን ያሠጋል።

 

በዚያ ላይ ልብ ልንለዉ የሚገባ ጉዳይ አለ። ይኸዉም ገዢዉ መደብ እንደዚህ ዓይነት አካሄድን እንደሚፈልገዉ መዘንጋት የለብንም። ምክንያቱም እኛ በብሔር፣ በኃይማኖት ወይም በማናቸዉ መልኩ ተከፋፍለን ስንነታረክና ስንቧቀስ እነሱ ግን ተረጋግተዉ ሥልጣናቸዉን በማደላደል ዘረፋዉን ያጧጡፉታል። በተጨማሪም በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ መሐል ሜዳ መቅረትን በመፍራት ሳያምኑበትም ቢሆን ወደ ወያኔ መጠጋትን ያስከትላል። ወያኔ ደግሞ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ራሱን ያፋፍበታል።

 

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት የተከሰቱ ሁለት ምሳሌዎችን ማንሣት ይቻላል። ጊዜዉ ምርጫ 97 የሚካሄድበት ወቅት ነበር።የመጀመሪያዉ በሚያዚያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም.  ቅንጅት በጠራዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አቶ በድሩ አደም ባደረጉት ንግግር  “ … በምርጫ ካርድ ወደመጡበት እንመልሳቸዋለን … ” የሚል አባባል ተጠቅመዉ ነበር። ምንም እንኳን አነጋገሩ አሻሚ ቢመስልም የትግራይ ባለሥልጣኖች ወይም ትግሬዎች በአዲስ አበባ ቦታ የላችሁም የሚመስል ትርጓሜ በሚሰጥ መልኩ እንዳልተናገሩ እገምታለሁ። ሁለተኛዉ የቢቢሲዉ ጋዜጠኛ ለኢንጅነር ኃይሉ ሻወልና ለሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዘናዊ ላቀረበላቸዉ ጥያቄ የተሰጠዉን ምላሽ ይመለከታል። እንደሚታወቀዉ ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል በንግግራቸዉ መካከል ትግረኛ ተናጋሪዎች በሚበዙበት አካባቢ እንኳን ሳይቀር ትግሬ ያልሆነዉን (non-Tigrian) ቅንጅት ነዉ የመረጡት ብለዉ ነበር። መቼም ኢንጂነር ኃይሉ ቅንጅት የትግሬ አይደለም በሚል መንፈስ እንዳልተናገሩት ግልጽ ነዉ። ያም ሆነ ይህ ወያኔ/ኢ.ሕ.አ.ዲ.ግ. ቀድሞዉኑ ኢንተርሀሞይ ናችሁ በሚል ቅንጅትን በአደባባይ ማዉገዝ ጀምሮ ስለነበር እነዚህን ሁለት አባባሎች በማራገብ ቅንጅትን ለመምታትና የትግራይን ሕዝብ አጋርነት/ድጋፍ ለማግኘት በእጅጉ እንደረዳዉ ይገመታል። በዚያ ላይ ከቻይና በርካታ ገጀራ ወደሀገር ዉስጥ ገብቷል እስከመባል ድረስ በስፋት ወሬ ስለተነዛ ምን ያህል የሥጋት ምንጭ ሆኖ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። እናም “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” እንዲሉ የወያኔን አካሄድና የሩዋንዳን ዕልቂት ያየ ሰዉ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል።

 

  • ስሜታዊነት

የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦችን መሰንዘር፣ ሥርዓቱን መታገል፣  … ወዘተ ተገቢ ነዉ። አንዳንዶች ደግሞ ከዳር ቁጭ ብለዉ ለማናቸዉም ወገን ሳይወግኑ ገለልተኛነትን የመረጡ አሉ። ታዲያ በእነዚህ ዓይነት ግለሰቦች ላይ ለምን እኛን አልመሰላችሁም ወይንም ከእኛ ጋር ተቧድናችሁ አትታገሉም በሚመስል ሁኔታ ወቀሳ ሲነዘር ይሰማል።   “ … ሆዳም፣ አደርባይ፣ አስመሳይ፣ ኅሊናዉን የሸጠ … ” የመሳሰሉት ስድቦችም እስከመሰንዘር ይደርሳሉ። ይህም ተገቢ አይመስለኝም። ማንም ሰዉ ሌላዉን እስካልነካ ድረስ በገለልተኛነቱ ሊሰደብ ወይም ሊወገዝ አይገባም የሚል እምነት አለኝ።

 

ከዚያም በላይ የመንግሥት መዋቅር ዉስጥ የሌሉና በግል ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች “ማሽቃበጥ” የሚመስል አድራጎት ሲፈጽሙ እንኳን በትእግስት ማስተናገድ ያስፈልጋል። እንደሰዎቹ ታዋቂነት የፈጸሙትን ድርጊት በጨዋ ቋንቋ ማጋለጥ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ። ከዚያ ባሻገር ግን እጅ እጅ እስከሚል ድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተቀባበሉ መዝለፍ፣ ማንቋሸሽ፣ የተለያየ ስም መለጠፍ አእምሮአችንን፣ ጊዜአችንንና ኃይላችንን በከንቱ የማጥፋት ያህል ይሰማኛል።

 

እንደኔ እምነት የምንጽፈዉ ወይም የምንናገረዉ ንዴትን ለመወጣት ወይም ሌላዉን ወገን አንጀት ለማሳረር መሆን የለበትም። ከዚያ የዘለለ መልዕክት ሊኖረዉ ይገባል። ቢቻል መረጃ የሚሰጥ፣ የሚያስተምር ወይም ለመተራረም የሚረዳ ቢሆን ይመረጣል። የሆነዉ ሆኖ እንደዚህ መሰል አካሔድ ወያኔ/ኢ.ሕ.አ.ዲ.ግ. እንደሚፈልገዉ አያጠራጥርም። ምክንያቱም ቢያንስ በጥቃቅን ጉዳዮች የመዋጥን ነገር ስለሚፈጥር ትልቁን የሀገር ጉዳይ ቸል የተባለ ሊመስል ይችላል።

 

  • ሆደ ሰፊ አለመሆን

የማኅበራዊ ሚዲያና ድኅረ ገጾች መስፋፋትን ተከትሎ የመጻፍ ልምድ እየዳበረ መጥቶአል። በዚህ አጋጣሚ በርካታ መረጃዎች ይወጣሉ። እንዲሁም ለመማማሪያ የሚሆኑና የሀገራችንን የወደፊት አቅጣጫ የሚጠቁሙ ጽሑፎችም ያጋጥማሉ። ይህ መጠናከርና መበረታታት ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል። ሆኖም ግን አንድ ሰዉ የሚያቀርበዉ ሐሳብ በሌላዉ ሰዉ ዕይታ ትክክል ላይሆን ይችላል። ታዲያ ምላሹ መሆን ያለበት ትክክል ነዉ ብሎ ያመነበትን የራስን ሐሳብ ይዞ መቅረብ ብቻ ነዉ። ይህ ዓይነት አቀራረብ የቀድሞዉን ሐሳብ አመንጪ ሳይቀር ለማስተማር ዕድል ይሰጣል። እየሆነ ያለዉ ግን እንደዚያ አይደለም። ትዕግስት ማጣትና የእኔ ብቻ ትክክል ነዉ የሚል አቋም ይንጸባረቃል። በዚህም የተነሣ የተሰነዘረዉን ሐሳብ የሚያፈርስ ሌላ ትንታኔ ሳይቀርብ ጸሐፊዉ ላይ ብቻ የዘለፋ ዉርጅብኝ ማዉረድ ተለምዷል። ፈጽሞ ተገቢ አይደለም። ለማንም የሚጠቅምም አይደለም። ከዚያም በላይ እንደነዚህ ዓይነት ጸሐፊዎችን ወይም ተናጋሪዎችን በመፍራት ብቻ ሰዎች ነጻ ሆነዉ የመሰላቸዉን ሐሳብ እንዳያቀርቡ ሊያሸማቅቅ ይችላል። ስለሆነም ማንም ሰዉ ሐሳቡን የመግለጽ መብቱ ሊከበርለት ይገባል።

 

እንደምሳሌ ለማንሣት ያህል ፕሮፌሰር መሥፍን ወ/ማርያምን መጥቀስ ይቻላል። አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ እንጂ አማራ የሚባል ጎሣ የለም በሚል በአንድ ወቅት መናገራቸዉ ይታወሳል። እኔ በበኩሌ ሐሳባቸዉን ለማስረዳት ያቀረቡት ምሁራዊ ትንተና በጣም አርክቶኛል። እንዳጋጣሚም ለሥራ ጉዳይ ወደ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች አካባቢ በሄድኩበት ወቅት በተወሰነ ደረጃ ማረጋገጥ ችያለሁ። ይኸዉም ከአካባቢዉ ወጣቶች ጋር ስንጨዋወት ወቅቱ የረመዳን ጾም ስለነበር ስለአንደኛዉ ጓደኛቸዉ ሲነግሩን “እሱ አማራ ስለሆነ አይጾምም” ብለዉን ነበር። በዚህ ግራ የተጋባዉ የሥራ ባልደረባየ “እሱም እንደናንተ ኦሮሞ አይደለም እንዴ?” በሚል ለመጠየቅ ተገዶ ነበር። ለማንኛዉም ወጣቶቹ  “አማራ” የሚለዉን ቃል የተጠቀሙበት “ክርስቲያን” ለማለት ነዉ’ንጂ ብሔርን ለመግለጽ አልነበረም።

 

የሆነዉ ሆኖ ፕሮፌሰሩ ያቀረቡት ትንታኔ ትክክል አይደለም በሚል በጨዋ መልክ የራስን ትንታኔ ይዞ መቅረብ ችግር የለዉም። ያኔ የትኛዉ ትክክል እንደሆነ አንባቢ ይፈርዳል። ያንን ሳያደርጉ ግን እንዲሁ በመዝለፍ ብቻ የሰዉን ሐሳብ ለማጣጣል መሞከር ኋላ ቀርነትና ያለመብሰል ዉጤት እንደሆነ ይሰማኛል። በነገራችን ላይ በዚህ አባባላቸዉ ፕሮፌሰሩ ላይ ዘለፋ የቀረበባቸዉ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተቋምም ደረጃ ነበር። ይህ ደግሞ በይበልጥ አሳዛኝ ነዉ።

 

ለማጠቃለል ያህል ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑ አንጻር ሳናዉቀዉ የችግሩ አካል እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እንደቀልድ የሚሰነዘር አባባል መዘዝ ሊያመጣ ወይም ያለዉን ችግር ሊያባብስ ይችላል። ስለሆነም ጽሑፍ፣ ለሕዝብ የሚተላለፍ ንግግር ወይም ዜና ከስሜታዊነት ነጻ በሆነ መልኩ ቢቀርብ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደሚረዳ አምናለሁ።

 

ቸር ይግጠመን    

የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ለማግኘት ለምትፈልጉ፡- mekonnen_ashagre@yahoo.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.