በጊንጪ ዛሬ በአጋዚ ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈጸመ

 (ኢሳት ዜና–ጥቅምት 17/2010)በጊንጪ ዛሬ በአጋዚ ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈጸመ። በጥቃቱ ሁለቱ መገደላቸው ታውቋል።

የአምቦው ግድያ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አዲስ ተቃውሞ ቀስቅሷል።

በአምቦ ትላንት የተገደሉ ሰዎች የቀብር ስነስርዓትም ተፈጽሟል።

በኢሉባቡር ጎሮ የህወሀት አባል በሆኑ ሁለት ግለሰቦች መኖሪያ ቤት የጦር መሳሪያዎች መገኙቱንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ የውጭ ድጋፍ ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የህወሀት መንግስት በመጨረሻው ሰዓቱ ህዝብን ከህዝብ ከማጋጨት እንዲቆጠብ ጠይቋል።

ጊንጪ ታሪካዊ የሆነው የኦሮሞ ህዝብ እምቢተኝነት የጀመረባት ከተማ ናት። ዛሬም ከእምቢተኝነቱ አብዮት ጋር ስሟ እየተጠቀሰ ነው።

ጠዋት ላይ ነዳጅ ማደያ ፊት ለፊት በነበሩ የአጋዚ ወታደሮች ላይ በተወሰደ ርምጃ ሁለቱ መገደላቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

ከተገደሉት ሌላ ሁለት የአጋዚ ወታደሮችም ቆስለው ወደ ህክምና ቦታ መወሰዳቸው ታውቋል።

ጥቃቱ በቦምብ እንደተፈጸመ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን አካባቢው ወዲያኑ በፌደራል ፖሊስ መወረሩም ተገልጿል።

ከአምቦ በ37 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጊንጪ ትላንት መንገድ በመዝጋት የተጀመረውን ተቃውሞ ለማስቆም በገባው የአጋዚ ሃይል ላይ ጥቃቱን የፈጸመው አካል ማንነት አልታወቀም። ይህንን ተከትሎም ተጨማሪ የመንግስት ሃይል ወደ ጊንጪ መግባቱም ታውቋል።

ከአዲስ አበባ በ38 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታም ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ተሽከርካሪ ተቃጥሏል። መንገዶች በተቃጠሉ ጎማዎችና በድንጋይ ተዘግተው እንደነበሩ ታውቋል።

ከቀትር በኋላ የመከላከያ ሰራዊት ወደከተማዋ በመግባት ተቆጣጥሮታል። የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በግቢያቸው ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን የአምቦውንም ግድያ አውግዘዋል።

ዛሬ አምቦ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ጸጥታ የሰፈነባት ሆና ውላለች። ትላንት የተገደሉት ሰዎች የቀብር ስነስርዓትም ዛሬ በሶስት አብያተ ክርስቲያነት መፈጸሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የህወሃት መንግስት ዛሬ ተጨማሪ ሶስት ኦራል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሰራዊት ጭነው አምቦ የገቡ ሲሆን በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ መስፈራቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢሉባቡር የህወሀት አባል በሆኑ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት የሚደረገው ፍተሻ ቀጥሎ በጎሮ በሁለት ሰዎች መኖሪያ ቤቶች የጦር መሳሪያዎች መገኘታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በእነዚህ የህወሀት አባል በሆኑ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት የተገኙት መሳሪያዎች ቦምብን ጨምሮ የተለያዩ ለቅስቀሳ የተዘጋጁ ሰነዶች መሆናቸው ታውቋል።

ፍተሻው የቀጠለ ሲሆን አንዳንድ የህወሃት አባል የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሸሻቸውንም ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ የውጭ ድጋፍ ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደው ተቃውሞ ተጠናክሮ እንዲካሄድ ጥሪ አድርጓል።

ይህ ተቃውሞ አዲስ አይደለም የቀድሞው የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞ አካል መሆኑ መዘንጋት የለበትም ብሏል የኦፌኮ የውጭ ድጋፍ ኮሚቴ።

በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ያሰማ ህዝብ ላይ ግድያ ፈጽሞ ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም በሚል ርዕስ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ለህወሀት መንግስትም ጥሪ ያደረገ ሲሆን በመጨረሻው ሰዓት ህዝብን ከህዝብ ከማጋጨት እንዲቆጠብ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የአማራና የኦሮሞ ወገኖችህ እያደረጉት ካለው ትግል ጎን እንድትቆም ጥሪ እናቀርባለን ሲልም የኦፌኮ የውጭ ኮሜቴ በመግለጫው ጠቅሷል።

Spread the love
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  
  •  

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.