“በኦሮሞ እና አማራ ሕዝብ ትስስር ከፍተኛ እምነትና ተሰፋ ነው ያለኝ” ጁሃር መሀመድ

በወንድወሰን ተክሉ

 የኦሮሞና አማራ ሕዝብን ለማለያየት በህወሃት መራሹ ስርዓት እየተካሄደ ያለው መሰሪ ተግባር የሁለቱን ህዝቦች ለዘመናት የቆየን ትስስር መበጠስ የማይቻለው ሲሆን ሁለቱ ህዝቦች በምንም ዓይነት ተዓምር ሶስተኛ እና አራተኛ የዓለም የዓለም ጦርነት እንካን ቢነሳ ሁለቱን ህዝቦች ማለያየት የሚቻል አይደለም ሲል ታዋቂው የኦሮሞ አክቲቪስት ጁሃር መሀመድ ገለጸ።

በኢሉባቦር ቡኖ በደሌ በተካሄደው ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑት ሰዎች በአስቸካይ ለፍርድ  መቅረብ አለባቸው ካለ በሃላ በክልሉ የደረሰው አንድን ነገድ ኢላማ ያደረገው ጥቃት በኢሉባቦር ታሪክ ውስጥ ይህን መሰል እርምጃ ተወስዶ ማየት እጅግ ያልተጠበቀ ክስተት ነው ያለው ጁሃር ሆኖም ግን ድርጊቱ ከመነሻው እስከመጨረሻው ድርስ የህወሃት መሆኑን በአጽንኦት በመግለጽ ሁለቱ ህዝቦች ከመቼውም ግዜ በላይ በመቀራረብና ህብረታቸውን በማጠበቅ እራሳቸውን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርባል።

ወጣቱ አክቲቪስት በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይና በተለይም ነገድና ዘር ተኮር በሆነው እርምጃዎች ዙሪያ ከአማራ ሬዲዮ ጋር ባደረገው ረጅም ቆይታ በዝርዝር የገለጸ ሲሆን በእኛም በኩል የአክቲቪስቱ መልእክት ፍሬያማነትን በመመልከት እንደሚከተለው ቀነጫጭበን ለማቅረብ ችለናል።

**ጁሃር መሃመድ በቡኖ በደሌ ጥቃት ላይ ከተናገረው

ኢሉባቦር ከአብሮነት ኖሮ ባህሉ ከሐረር ቀጥሎ የሚታወቅ ድንቅ ሕዝብ ነው። ሆኖም ባለፈው ሳምንት በተነሳ ብጥብጥ ወደ 15ሰዎች መገደላቸውና ከ3ሺህ በላይ አባወራዎች መፈናቀላቸው እውነት ነው።

ከሞቱት ውስጥ 8ቱ የኦሮሞ ተወላጆች ሲሆኑ 7ቱ ደግሞ የአማራ ተወላጆች ናቸው። እነዚህ የአማራ ተወላጆች በሚገርማችሁ ሁኔታ በሹመትና በስልጣን በአከባቢው ህዝብ ላይ የሰፈሩ ሳይሆን በደርግ ዘመን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከሰሜን በተለይም ከወሎና ሰሜን ሸዋ እንዲሰፍሩ የተደረጉ ጭቁን ሕዝቦች ሲሆኑ ከሀገሬው ጋር ተጋብተው፣ተዋልደውና ተቀላቅለው በመኖራቸው መለየት እስከሚያስቸግር ድረስ የተሳሰረ ህብረት የፈጠሩ ናቸው።

ሆኖም ሰለባ ሊሆኑ የተገደደቡት ዋና ምስጢር የእነሱ አማራነት ምክንያት በኦሮሞ ወገኖቻቸው የተሰነዘረባቸው ጥቌት ሳይሆን የህወሃት ሰይጣናዊ ዓላማ  ምክንያት መሆኑን ሁሉም ሰው መረዳት ያለበት ሃቅ ያለ ይመስለኛል።

ኢሉባቦር በጣም ለም ናት።ሰፋፊ የመንግስት እርሻ መሬት ያለባት፣በማእድናት የበለጸገች ሀገር ናት።እነዚያ ግዙፍ የመንግስት እርሻ መሬቶች በሙሉ በስመ ኢንቨስትመንት የህወሃትና የኢፈርት ሆነዋል:እነዚያ የማእድን ስፍራዎች በሙሉ በህወሃትና ኤፈርት የተወረሱ ሆነዋል።

የቡኖ በደሌ ሕዝብ ሰላማዊ የሆነን ለሁለት ቀን ተከታታይ ሰልፍ ሲያካሄድ ጥያቄው ሁሉ የመሬት ጥያቄ ነበር። ይህ ያስጨነቃት ህወሃት የህዝቡን አትኩሮት የሚስብላትን ሌላ ኢላማ ፈለገችና ጭቁኑን ወንድሞቻችንን አማራውን እንዲጠቃ ትእዛዝ ሰጠች አስፈጸመችምም።

ዋና ዓላማዋም- በአማራና ኦሮሞ መካከል የተፈጠረውን ህብረት መግደል፣በኦህዴድና ብአዴን መካከል ያለውን መናበብ ለማቋረጥና ብሎም በአካባቢው የተነሳውን ዓመጽ ከያዘችው መሬትና ማእድን ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ ለማድረግ የወሰደችው መሰሪ ሰይጣናዊ ሴራና ተግባር ነው ሲል ይናገራል።

**ጁሃር መሃመድ-ለመሆኑ አማራና ኦሮሞ ሕብረት ሊፈጥሩ ይችላሉ? የወደፊቱስ እጣፈንታቸው ምንድነው ለሚለው ጥያቄ እንደሚከተለው መልሳል።

*ጁሃር-“የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ህብረትና አንድነት ዛሬ የሚፈጠር ወይም ዝም ብሎ ትናንት የተጀመረ ሳይሆን በትንሹ እንደ ፕ/ር መሀመድ ሀሰን በያን እንዳሰፈረው ከሺህ ዓመት በላይ የተጋዘ አንድነትና ህብረት ያላቸው ናቸው። ታሪካቸው እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽና በቀላሉም አጣልተህ የምታጋጫቸው ህዝቦች ሳይሆኑ እጅግ ስር የሰደደ ትስስር ያላቸው -በፍቅር፣በጸብ፣በህብረት፣ያለህብረት በጦርነት ያለጦርነት አንድነታዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ናቸው።

ትስስራቸው እጅግ ጥብቅ የሆነና ኮምፕሌክስ የሆነ ሲሆን በምንም ዓይነት ተዓምርም ይህንን ትስስር ማንም ሰው በቀላሉ አጣልቶና አጋጭቶ የሚያለያያቸው ህዝቦች አይደሉም፡፣

እንደ ጌታቸው ረዳ ኦሮሞና አማራ ክብሪት የሚያስፈልጋቸው ደረቅ ጭድና እሳት ናቸው ሲለን እኛ ደግሞ እየረጠብን እና ውሃ እየሆንን ያስቸገርነው ሆነናል።

የኦሮሞ እና አማራ ህብረት፣ትስስርና አንድነት እጅግ ወሳኝ የሆነና እጅግ የሚያስፈልገንም ተግባር ሲሆን በድርጊቱ [በህበረቱ] እጅግ የማምን፣ታላቅ ተስፋ ያደረግነውና ደግሞም ያለን ብቸኛ አማራጭ የመፍትሄ መንገድም በመሆኑ በጣም አምንበታለሁ።

ይህን ስል ለፖለቲካ ፍጆታ ብዪ አይደለም::ከእውነታ በመነሳት በወደፊቱ ዓላማችን ላይ የሚኖረውን ወሳኝ ሃይልና ሚናን ጠንቅቄ በመረዳት ነው።

`ይህን ደግሞ እራሳ ወያኔ ታውቀዋለች ፡እናም በተቻላት መጠን ሁሉ ይህን ወሳኝ የሆነውን የሁለቱን ህዝብ ትስስር እንዳይጠናከርና እንዳያንሰራራ የተቻላትን ሁሉ በማድረግ ሁለቱን ለማጋጨትና ለማጣላት እርምጃ እንደምትወስድ እናውቃለን ይጠበቃልም።

ከቡኖ በደሌ በፊት በኦሮሞ ህዝብና በሶማሌ ህዝብ መካከል ጦርነት ለመቀስቀስ ያደረገችው ወንጀል ከባድ ነው-አሁን ደግሞ በቡኖ በደሌ በአማራና ኦሮሞ መካከል ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች ነገ ተነገወዲያም ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት መሰሪ እርምጃዎቻን ከመውሰድ አትታቀብም። እኛ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ይህንን እርምጃዋን እና ፍላጎታን ለማክሸፍ ትስስራችንን አጥብቀንና ነቅተን ከእዚህ በፊት እንዳከሸፍነው ማክሸፍ ይጠበቅብናል።

የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን በጋር በራቸውን ዘግተው በሁለቱ ህዝቦች ቀጣይ ሁኔታ ላይ ግልጽ ውይይት ማድረግ ይገባቸዋል። ይህ ደግሞ ወያኔን ለመጣል ብለን ብቻ የምናደርገው አይደለም። ወያኔን ለመጣል አንድ የአማራ ዞን ወይም የኦሮሞ ዞንም በቂ ነው። ነገር ግን የእነዚህ ሁለት ብሔሮች አማራና ኦሮሞ የወደፊት እጣ በአንድነት በስምምነት የሚመራ ለማድረግ በመካከላችን ያሉትን የሚያስማሙን ላይ ይበልጣ ለማጎልበት የማያስማሙን ላይም  በጋራ መፍትሄ በመፈለግ ማስተካከል ይገባል።የአማራና ኦሮሞ ትስስርና ህብረት ለሁለቱ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ጭምር ብሎም ለአፍሪካ ቀንድ እጅግ ወሳኝ መሆኑን አምናለሁ፡፣

**ለመሆኑ የአማራና የኦሮሞ የወደፊት እጣፈንታ ምን ይሆናል-ምንስ መደረግ አለበት ትላለህ ለሚለው ጥያቄ –

*ጁሃር ሲመልስ- “የሁለታችንን የወደፊት ሁኔታ በሁለት ደረጃ ከፍዪ አየዋለሁ።

1ኛ የአጭር ግዜ ዓላማና 2ኛ የረዥም ግዜ ዓላማ የምንሰራቸው ተግባሮች አሉ። በአጭር ግዜ ዓላማ ስር ፈጥነን የእሳት አደጋ ስራ መስራት ይገባናል። ወያኔ ዛሬ ወደ ሞቷ እየሄደች እንዳለች እብድ ውሻ ያንንም ይሄንንም በመልከፍ በተለይ ብሔር ብሔረሰቦችን በማጋጨት የቀራትን እድሜ ለማራዘም እየተወራጨች ባለችበት ወቅት እዚያም እዚህም እሳት ስትለኩስ እኛ እሳቱ ላይ ቤንዚን እያረከፈከፍን ስራዋን ከመስራት ተቆጥበን እንደ እሳት አደጋ ማጥፋት ይኖርብናል።

 ጣና ሃይቅ ለትግራይ ቅርብ ነው። ሆኖም የኦሮሞ ልጆች ጣናን ኬኛ ብለው ሲዘምቱ ከህዝቡ የተደረገላቸው አቀባበል የህዝብ ለህዝብ ስራ በመሆኑ በጣም የሚያስደስትና የሚያስመሰግን ቢሆንም ህወሃት ግን በጣም ነው በንዴት የበገነችው:: ያንን ህብረትና አንድነትንም ለማፍረስ ሆን ብላ ነው በመገናኛ ብዙሃን ስም ባቋቋመችው ዜና ማሰራጪያ  በመጠቀም አማሮች በኦሮሞዎች ተጨፈጨፉ ስትል ያወጀችው።

በጣም ያስደስተኝ የሁለቱም ክልሎች -የአማራውና የኦሮሚያው መግለጫዎች አንድ ተመሳሳይ ሆኖ ለህወሃት ቀዳዳ መክፈት ያለመቻላቸው ጉዳይ ነው።

የሁለቱም ወገን አክቲቪስቶችና የመገናኛ ብዙሃን ይህን መሰሉን የእሳት አደጋ አጥፊነትን ሚና በሚገባ ይጫወታሉ። ይህንን በጋራ የምንሰራቸው የእሳት አደጋ መሳይ ብርጌድ ማቃቃም ይኖርብናል።

በ2ኛ ደረጃ እና በረጅም ግዜ ያልኩት ቅድም እንደገለጽኩትና ከዚህ በፊትም ደጋግሜ ተናግሬ ሰሚ ጆሮ ያጣሁት የሁለቱ ህዝቦች መሪዎች፣ልሂቃን እና አክቲቪስቶችም ጥልቅ ውይይት በማድረግ በመካከላችን ያሉትን ማንኛቸውንም የሚያስማሙንን እና የማያስማሙንን እየነጠልን ተነጋግረንባቸው በስምምነት በመቃጨት መሰረት ያለውን ትስስራችንን በማጠናከር በሀገራችን ጉዳይ ላይ በጋራና  በህብረት የምንቀሳቀስበትን ሁኔታ የረዥም ግዜ ተግባሮቻችን ብያቸዋለሁ።

**ለመሆኑ ኢትዮጵያ ለአንተ መፈረስ አለባት ብለህ ታምናለብ-ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ-

*ጁሃር ሲመልስ-ኦሮሞ በባህሉ አዲስ ቤት እንካን ሲሰራ አሮጌውን አፍርሶ ሳይሆን እንዳለ በመተው ነው።

የሚፈርስ ሀገርም ሆነ ህዝብ የለም።ኢትዮጵያ የኦሮሞና አማራ ሀገር ብቻ ሳትሆን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ሀገር ሆና የምትኖር ሀገር እንጂ የምትፈርስ አይደለችም። አላምንምም።

የኦሮሞ ህዝብ ከሃይለስላሴ ግዜ ጀምሮ ይዞ የተነሳቸው ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች ነው ያሉት።

1ኛ-በአካባቢያችን እና በግዛታችን በማእከላዊ በሚሾምልን ሹመኛ ሳይሆን እራሳችን በመረጥነው የራሳችን ሰው  መተዳደርን።

2ኛ-በማንነታችን፣ባህላችን፣ቃንቃችን ተከብሮልን እንድንኖር።

3ኛ-ፈጣሪ በሰጠን ሀብት የበይ ተመልካች ሳንሆን እራሳችን እየተጠቀምን እኩል እንኑር እንጂ ኢትዮጵያን እናፍርስ የሚል አይደለም።

***ለመሆኑ የአባዱላና ኦህዴድ ከህወሃት ጋር መጣላት የእውነት ነው የውሸት ነው? ለሚለው ጥያቄ 

*ጁሃር-ሲመልስ-

በአንዳንድ ሰዎች የአባዱላና ኦህዴድ ጉዳይ የውሸት ነው ሲሉ ይሰማል። ድርጊቱ እውነት ነው፡፡ጦርነት ላይ ናቸው። ግን ይህ እራስን የማወቅ ከኦህዴድም ሆነ ከብአዴን  ከራሳቸው ከውስጥ የመጣ ሳይሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት በአማራና ኦሮሞ ህዝብ በተነሳው ሞት አይፈሬ እምቢ አልገዛም ባይነት ምክንያት ነው።

ዛሬ በወያኔ እና በኦህዴድ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ግልጽ በአደባባይ የወጣና በይፋም እየታየ ያለ ነው ሲል ጁሃር ለአማራ ራዲዮ ቃለ ምልልስ ሰጥታል።

   በቃለ ምልልሱ ወቅት ጁሃር በርካታ ነጥቦችን እያነሳ  በሚደንቅ ሁኔታ ትንታኔን ሰጥቶበታል።

ህወሃት ለስልጣኑ ሲል በገዛ ወገኖቹ ላይ በሀውዜን ካደረገው የባሰ ተግባርን በአዲስ አበባ ወይም በአማራና ኦሮሞ ላይ ያደርሳል የሚል ስጋት እንዳለውም ገልጻል።

በአማራና ኦሮሞ መካከልም ሶስተኛውና አራተኛው የዓለም ጦርነት ቢነሳ  ማንም መለያየትን ሊፈጥር አይቻለውም ሲል ደግሞ ደጋግሞ አስረድታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.