የኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት እስከ ሥራ ማቆም አድማ የሚደርስ ዕርምጃ ለመውሰድ ወሰነ

  • የደመወዝ ማስተካከያ ያስፈልጋል ብሏል

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጠቅላይ ምክር ቤት እንደ አዲስ ተረቅቆ የተዘጋጀውን የአሠሪና ሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ ፈፅሞ እንደማይቀበለው፣ ረቂቁ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ ሥራ ማቆም አድማ የሚደርስ ዕርምጃ ለመውሰድ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የአሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፣ ጥቅምት 15 እና 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው 40ኛው ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫ ነው፡፡

ኢሠማኮ በረቂቁ ላይ ለዓመታት በሦስትዮሽ መድረክ ጭምር ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን የሚጠቁመው የአቋም መግለጫ፣ ከዚህ ቀደም እንዲካተቱ ስምምነት ተደርሶባቸው የነበሩ አንቀጾች ተለውጠው እንደ አዲስ ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ  የሠራተኛውን መብት ፈፅሞ የሚያስከብር አለመሆኑንም አሳውቋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ የኢንዱስትሪ ሰላምን የሚያናጋ ጭምር በመሆኑ፣ ከመፅደቁ በፊት ማስተካከያ እንዲደረግበት በአቋም መግለጫው መንግሥትን ጠይቋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በተከታታይ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሠራተኛውን መብት ለማስጠበቅ የሚታገል እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

‹‹አዋጅ 337/96 ማሻሻያ ላይ ያለንን ልዩነት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለሁሉም ሚኒስትሮች ያቀረብን ቢሆንም፣ አንዳችም ምላሽ ስላልተሰጠን መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በጥሞና እንዲያይልን በአክብሮት እንጠይቃለን፤›› የሚለው የአቋም መግለጫ፣ ረቂቁ አሠሪዎችን የሚደግፍና ሠራተኞችን ያላገናዘበ በመሆኑ የጠቅላይ ምክር ቤቱ አባላት ረቁቂን ለማስለወጥ ተከታታይ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡

የረቂቅ አዋጁን አንዳንድ አንቀጾች በጥብቅ የሚቃወሙ መሆኑንና መንግሥት እንዲያስተካክል በአፅንኦት በጠየቀበት የአቋም መግለጫ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ መንግሥት አዋጁን ሕግ አድርጎ ለማውጣት እንቅስቃሴ በሚጀመርበት ወቅት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 መሠረት ዕርምጃ ለመውሰድ ወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት ዕርምጃውን የሚጀምረው በኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስተባባሪነት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ መላውን ሠራተኛ ያቀፈ የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲጠራ በማድረግ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ተሳታፊዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ሰላማዊ ሠልፍ ተደርጎ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ደግሞ፣ በማናቸውም ጊዜ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 (ለ) መሠረት በመላው አገሪቱ የሥራ ማቆም ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚል ውሳኔም አክለዋል፡፡ የኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ሠራተኞችን አንድነት እንዲያስተባብርና እንዲያስፈጽም ሙሉ ውክልና እንደሰጡት፣ የጠቅላይ ምክር ቤቱ አባላት በአቋም መግለጫቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

የኢሠማኮ የአቋም መግለጫ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን በመቃወም ለሚያስተላልፈው አገር አቀፍ ጥሪ ዘጠኙም የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖች፣ አመራሮች፣ የመሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበር መሪዎችና መላው ሠራተኞች ዝግጁ ሆኖ እንዲጠባበቅና የሚተላለፈውን መልዕክት ተግባራዊ እንዲያደርግ በሙሉ ድምፅ መፅደቁን አሳውቋል፡፡

አዲስ በቀረበው ረቂቅ የሠራተኛውን መሠረታዊ መብትና ጥቅም የሚያጓድሉ ናቸው ብሎ ያመንባቸውን አንቀጾች በሙሉ፣ እንዲሁም በነባሩ አዋጅ ውስጥ በአሠራር ሒደት ችግር ሲያስከትሉ የቆዩ አንቀጾች እንዲሻሻሉና ሌሎችም አዳዲስ አንቀጾችና ሐሳቦች ተጨምረውበት ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲላክ መደረጉንም መግለጫው አስታውሷል፡፡

ሆኖም ረቂቁ የጋራ ውይይት ተደርጎበታል ይባል እንጂ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያና ማኅበራዊ ፖሊሲዎችና ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የማይጣጣም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ መቅረቡን በመገንዘብ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱንም ገልጿል፡፡

የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን ለማስቻል መንግሥት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያማከለ ሕግ እንዲወጣ ይጠበቅበታል የሚለው የኢሠማኮ የአቋም መግለጫ፣ ከዚህ መሠረተ ሐሳብ በመነሳት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅና አገሪቱ በፈረመቻቸውና ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች  የሠራተኛው የመደራጀትና የመደራደር መብት ተረጋግጧል ይላል፡፡ በዚህ ረገድ የሠራተኛው የመደራጀትና የመደራደር መብት ተረጋግጧል ቢባልም፣ በተግባር ግን ተፈጻሚ አለመሆኑንም ገልጿል፡፡

እንደምንም ተቸግረው የተደራጁ የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎችና አባላት የሥራ ዋስትና ማጣት፣ በረሃብና በችግር ውስጥ መውደቅና በየፍርድ ቤቱ መንገላታት የሠራተኛው ዕጣ ፈንታ ሆኗል ብሎ እንደሚያምንም መግለጫው አመልክቷል፡፡ የማሻሻያው ረቂቅ አዋጅ ያላገናዘባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች በማለት ከዘረዘራቸው ውስጥ፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎችን ያላገናዘቡና የአገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገቡ አንቀጾች ተካተዋል ብሏል፡፡

የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው በሥራ ላይ የነበረ ሠራተኛ በአጋጣሚ የሥራ ውሉ ቢቋረጥ ገቢ የሚያስገኝ ሌላ ሥራ ላይ እስኪሰማራ የሚያገኘው ክፍያ ስለሚኖረው፣ በልቶ ማደር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ‹‹በአገራችን የሥራ ውል የተቋረጠበት ሠራተኛ ግን እንኳንስ ይህ መብት ሊኖረው ቀርቶ፣ የተቋረጠበት ደመወዝ በአብዛኛው የዕለት ጉርሱን በሚሸፍንበት ሁኔታ ላይ እንደማይገኝ እየታወቀ ረቂቅ ሕጉን ማፅደቅ ተገቢ አይደለም፤›› ብሏል፡፡

የመንግሥት ዋነኛው ዓላማ የዜጎችን መብትና ጥቅም ማስከበርና ፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል እንዲፈጠር መሥራት ጉልህ መገለጫዎቹ ሆነው ሳለ፣ አዋጁን ለማሻሻል የገቡት አንቀጾች ግን እነዚህን ግምት ውስጥ ያላስገቡ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው በማለት ረቁቂን ተቋውሟል፡፡

የሌሎች አገሮች ተሞክሮ በረቂቁ ተካትቷል ቢባልም፣ ሠራተኛውን የሚደግፉ እውነታዎችን ወደ ጎን በመተው አሠሪውን የሚጠቅሙትን ብቻ በመለየት መውሰድ ፍትሐዊ እንዳልሆነም አመልክቷል፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለውን የአሠሪና ሠራተኛ  አዋጅና የሠራተኛችን የመደራጀትና የመደራደር መብት የሚፃረርም ነው ብሏል፡፡ በሥራ ቦታ በሚደርስ አደጋ ምክንያት በርካታ ሠራተኞችን ለጉዳት እየተዳረጉና ይህንንም ጉዳት መቀነስ እየተቻለ፣ በሥራ ላይ አደጋና በሽታ በርካታ ሠራተኞች እየተጎዱ ባሉበትና አስፈጻሚውም አካል ሕጉን በአግባቡ ማስፈጸም ባልቻለበት ሁኔታ ረቂቁ ሕግ ሆኖ ቢወጣ የሠራተኞችን መብት መጣስ ይሆናል ብሏል፡፡ ረቂቁ የኢንዱስትሪ ሰላምን የማያሰፍንና ምርትና ምርታማነት የማያሳድግ መሆኑን ጠቅላይ ምክር ቤቱ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ የመንግሥትን ኢኮኖሚ ፖሊሲና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ እያደረገ ያለውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን የሚገልጸው የጠቅላላ ምክር ቤቱ የአቋም መግለጫ፣ እንዲህ ያለው ሕግ መዘጋጀቱ ግን ተገቢ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢሠማኮ ከዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ ቀደም ብሎ ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር በአዋጁ ረቂቅ ላይ ከመሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበራት መሪዎች ጋር እንደመከረ አስታውቋል፡፡ ሠራተኞችም መጀመርያ በድርድር፣ ካልሆነ ግን ሕግ በሚፈቅድልን ሰላማዊ ትግል መብታችንን እናስከብራለን በማለት በየደረጃው አቋማቸውን ሲያሳውቁ እንደነበር አስታውሷል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊዎች ይህ ሕግ ተግባራዊ መሆን እንደሌለበት በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቂ ግንዛቤ ያላቸው አልመሰለንም ከሚለው አስተያየት ጀምሮ፣ መንግሥት የሠራተኛውን ጥቅም የሚነካ ረቂቅ ሲቀርብለት መቀበሉ እንዳሳዘናቸው መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡

አገሪቱ ዛሬ ባለሁለት አኃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስመዝግባለች ሲባል፣ የዚህ ዕድገት ውጤት ሠራተኛው ጭምር መሆኑን ያስገነዘቡት የጠቅላላው ጉባዔ ተሳታፊዎች ለሠራተኛው እንዲህ ያለ ሕግ አይገባውም በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡ አያይዘውም ኢሠማኮ ከዚህ በላይ አጀንዳ ስለሌለው ሕጉ እንዳይፀድቅ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለበት በማለት፣ የዚህ ሕግ መውጣት ለሠራተኛው ትልቅ አደጋ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ረቂቅ ውስጥ ኢሠማኮንና አባላቱን በእጅጉ ያስቆጡና ሊለወጡ ይገባቸዋል የተባሉ ከ20 በላይ አንቀጾች በተጨማሪ ሌሎች ሐሳቦች ያሉ ሲሆን፣ ሠራተኞችን ያለማስጠንቀቂያ ሊያሰናብቱ ይችላሉ የተባሉ ረቂቅ አንቀጾች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አዲሱን የአሠሪና ሠራተኛ ረቂቅ አዋጅ ከተቃወመበት የአቋም መግለጫው ውስጥ ሌሎች ሊተገበሩ ይገባል ያላቸውን ውሳኔዎች ኢሠማኮ አሳልፏል፡፡ በተለይ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የብር ምንዛሪ ለውጥን የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡ ይህንን በተመለከተ በመግለጫው እንዳሠፈረው፣ ‹‹ከአገራችን የኑሮ ውደነት አንፃር ሠራተኛው በሚከፈለው ደመወዝ ኑሮውን ለመቋቋም ባለመቻሉ፣ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ላይ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው፤›› ብሏል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የጀመረውን የገበያ መረጋጋት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልና የሚከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እንዲቻል፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና የግል ንግድ ተቋማት የደመወዝ ማስተካከያ እንዲያደርጉ መንግሥት አቅጣጫ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ያላቸውን አስተያየት የተጠየቁትና በረቂቅ ሕጉ ምክክር ላይ በሦስትዮሽ ተሳታፊ የነበሩት የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር፣ ‹‹ሕጉ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ቢሆንም፣ እንደ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ያቀረብናቸው ማሻሻዎች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝተዋል ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በተቻለ መጠን ሰጥቶ መቀበል የሚለውን መርህ በመከተል፣ ለሁሉም የሚጠቅም ሕግ እንዲወጣ መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.