የትምክህትና የጥበት ልብ አውልቅ ፕሮፓጋንዳ

በታደሰ ሻንቆ

በተራው ሰው ደረጃም ሆነ በኢሕአዴግ ግንባርና መንግሥት ዘንድ የሚነፍሰው የትምክህትና የጥበት አጠቃቀም፣ በአንድ ፈርጁ የህሊና ድህነትን ለአመል የመቀነስ ጥቅም እንኳ መስጠት ያልቻለ፣ ግልብ፣ ከግልብም ዲዳ ሆኗል፡፡ በሌላ ፈርጁ ደግሞ ማኅበረሰባዊ ግንኙነትን ለማቀራረብም ሆነ ችግሮችን ለመፍታት ከማገዝ ፈንታ እየጓጎጠ የሚያቆስል ጨፍራራ ነገር ሆኗል፡፡ የጽንሰ ሐሳቦች መላሸቅ ውጤት የሆነው በተራ ሰው አካባቢ የምናገኘው አጠቃቀም፣ ትምክህተኛነትን ከአማራነት ጋር አንድ እስከማድረግ የነተበ፣ በየብሔረሰብ ቋንቋና ባህል መገልገልን ሁሉ በጥበትነት እስከ መገመት ድረስ የቀለለ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ሰዎችና በፕሮፓጋንዳ አናፋሾች ዘንድ የሚታየውም የጥበት አጠቃቀም እንዲሁ የአስተሳሰብ ብልሽትን ከመብት ጥያቄና ከማኅበረሰባዊ ማንነት አጥርቶ የመለየት ችግር ያለበት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ከኢሕአዴግ ያልገጠመ አመለካከትን ወይ ጥበት ነው ወይ ትምክህት ነው ብሎ እስከመፈረጅ መፈናፈኛ ማሳጣት ተዘውትሯል፡፡ ለሕዝብ ቀለብነት በሚረጨው ፕሮፓጋንዳ ውስጥ ያለውን የይዘት ችግር ማሳየት ዞሮ ዞሮ ከመለኪያና ከቡና ስኒ ጋር የሚነፍሰውን እሳቤ ለማሳየትም ይጠቅማልና ለአዳባባይ ፍጆታ በሚረጨው ላይ እናተኩር፡፡

ስለትምክህትና ጥበት ዛሬ እየተባለ ያለው ነገር የዕውናዊነት አቅሙ የተውለቀለቀና ብልሽትን ማደናገሪያ ሆኖ እስከማገልገል እየሠራ ነው፡፡ የኢሕአዴግ የትንተና መጽሔት አዲስ ራዕይ (በ2009 የየካቲትና መጋቢት ዕትም፣ ገጽ 8) ላይ ‹‹በአሁኑ ጊዜ የትምክህት አመለካከት ከሥልጣን የተወገደው መደብ አመለካከት እንጂ ሥልጣን ላይ ያለ ገዥ አመለካከት አይደለም፡፡ የአሁኖቹ የትምክህት ኃይሎች አንድም በመሠረቱ ያለፈው ገዥ መደብ ቅሪቶች ወይም አዳዲሶቹ ጥገኞችና የእነሱ ጠበቆች ናቸው፡፡ ስለሆነም በወሳኝ መልኩ የተሸነፈ አመለካከት ነው . . . [ለዚህም] ዋነኛ ምክንያቱ . . . ማኅበራዊ መሠረቴ ነው ብሎ በሚያስበው በሰፊው የአማራ ሕዝብ ዘንድ የተጠላና የተሸነፈ ስለሆነ ነው፤›› ይላል፡፡ በዚያው ገጽ ላይ፣ የትምክህት ዋነኛ ይዘቱ የራስን ብሔር የበላይነት ማስፈን እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ዝቅ ብሎ (ገጽ 9 ላይ) ደግሞ ‹‹…የትምክህተኛው የሁልጊዜ ህልሙ… በአንድነት ስም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን መጠቅለል ነው፤›› ተብሏል፡፡ የተሸነፈ የተባለው ትምክህት ስለእውነት ዛሬ የሚብከነከነው ብሔር ብሔረሰቦችን ጠቅልሎ በአማራ የበላይነት ሥር የማስገባት ፍላጎት ነው? እንደዚህ ያለ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ባህርይ ለይቶ ለመፍታት ይረዳል? በአገራችን ውስጥ ያለው ኢትዮጵያን ከመበታተን የማትረፍ ፍላጎት ኢዴሞክራሲያዊ ሥልት እስከ መጠቀም (እስከ ደም ጠብታ የመሄድ) ጫፍ አለው፡፡ እዚህ ጫፍ ውስጥ የተገኘ ሁሉ ግን በደፈናው ትምክህተኛ ሊባል አይችልም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻውን ሊያናጭና ዘራፍ ሊያሰኝም ይችላል፡፡ ልክ እንደዚሁ ተነጣዮችን የጥበት የተስፈነጠረ ክፍል አድርጎ በመለየት ፈንታ ‹‹የጠባቦች ህልም የእኛ ነው የሚሉትን ሕዝብ ለብቻ ገንጥለው… የቡድን ፍላጎቶችን በአቋራጭ ማረጋገጥ›› አድርጎ ማጠቃለልም ትልቅ ስህተት ነው (ገጽ 9፣ ሰረዝ የተጨመረ)፡፡

ኢሕአዴግ በውስጡ ያለውን የጠባብነትንና የትምክህትን ጣጣ ለአባል ድርጅቶቹ ሲደለድል፣ ‹‹ብአዴን ትምክህተኝነትን ሲዋጋ ሕወሓት፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን ጠባብነትን ሲዋጉ …›› ይላል (ገጽ 45)፡፡ ይህንን ድልድል ቀደም ብለን ከጠቀስናቸው ‹‹የትንታኔ›› ሐረጎች ጋር እናገናዝበው፡፡ ‹‹ትምክህት የተወገደ መደብ  አመለካካት፣ ዛሬ ሥልጣን ላይ የሌለ አመለካከት፣ የቀድሞ ገዥዎች ቅሪቶች/ጠበቆች አመለካከት›› አለዚያም ‹‹የአዲሶቹ ጥገኞች አመለካከት›› የሚሉትን ሐረጎች ተመርኩዘን ትምክህት ለምን ከብአዴን ጋር እንደተያያዘ ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ የቀድሞ ገዥዎች ከአማራነት የበቀሉ፣ የዛሬው ትምክህተኛነትም የእነሱው ርዝራዥ ወይም ጠበቃ የመሆን ችግር ተደርጎ መቆጠሩን የሚያመለክት ነው፡፡ እንደዚያ ከሆነና ከገዥነት ትምክህት ከፈለቀ፣ የቀድሞው የአማራ ገዥነት ትምክህትን እንዳፈለቀ ሁሉ ስለምን የዛሬው የሕወሓት፣ የኦሕዴድም ሆነ የደኢሕዴን ገዥነት ትምክህትን አላመነጨም? ከእነዚህኞቹ አካባቢ የሚከሰት እብሪት ስለምን ከጥበት ጋር ተያይዞ ይታያል? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልስ ይቸግረናል፡፡ እኛ ቢቸግረንም የኢሕአዴግ ‹‹የትንተና›› መጽሔት መልስ አለው፡፡ ‹‹በዱሮ ጊዜ ትምክህት በሥልጣን ላይ ከነበሩ ገዥዎች የሚፈልቅ አስተሳሰብ ነበር፡፡ ጠባብነት ደግሞ ራሱን ለሥልጣን በተስፈኝነት ከሚያጨው ንዑስ ባለሀብት የሚመነጭ ነበር፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ጀምረን እነዚህ ሁለት ምንጮችን ካደረቅን በኋላ እነዚህ አመለካከቶች ከጥገኛ ኃይል የሚመነጩበት ሁኔታ እንዳለ ታይቷል›› (ሰርዝ የተጨመረ፡ ገጽ 38)፡፡

በዚህ አባባል መሠረት የትምክህት ከገዥነት መፍለቅ፣ የጥበትም ወደ ገዥነት ከመንጠራራት መፍለቅ የዱሮ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ስለምን? ዴሞክራሲ ‹‹በመጀመሩ›› ምንጫቸው ‹‹ደርቋል››፡፡ እንግዲህ በእኛ ‹‹ዴሞክራሲ›› ገዥነትና ተገዥነት የለም መባሉ ነው፡፡ እናም ለዛሬ ጥበትና እብሪት ሌላ ምንጭ ተፈልጎ ተገኘለት ‹‹ጥገኝነት›› የሚባል፡፡ ለመሆኑ ጥገኝነት መናፍስት ነገር ካልሆነ በቀር፣ ከላይ እስከ ታች ሥልጣን ላይ ተቀምጦ በጎሰኛ በዳይነትና መጥማጭነት እየተንፈላሰሰ ሲቅለጠለጥ የታዘብነው ክፍል ገዥ ካልተባለ ምን ሊባል ነው? ደግሞስ የኢሕአዴግ አስተዳደር የብሔር ጭቆና የሌለበት ዴሞክራሲያዊ እኩልነትን ለሕዝቦች አጎናፅፎ ከሆነ በመወደስ ፈንታ፣ ስለምን እያደገ በመጣ ቅዋሜና በኢሕአዴጋዊ የበላይ ገዥነት ይነዘነዛል? ኢሕአዴግ ጎሽ የተባለው ያገኘው በልማት ረገድ እንጂ በአገዛዙ አይደለም፡፡

ሌላም መልስ የሚሻ ጥያቄ አለ፡፡ ብአዴን እንደነ ኦሕዴድ በብሔርተኝነት አዕምሮ የታሰሰ፣ ብሔርተኛ ዓላማ ያነገበ፣ በብሔር የተደራጀና የአማራ ክልልን የሚገዛ እንደ መሆኑ እንደነሱ በጥበት ችግር ስለምን አይታማም? ስለምን ከትምክህት ችግር ጋር ይዛመዳል? በዱሮው ገዥነት ርዝራዥ አስተሳሰብና ባህል የመጎተት ፈተናና ትግል ስላለበት ነው ይባል ይሆን? እንዲያ ከተባለ ደግሞ ስለአማራ የገዥነት ዘመን ሲወራ የበላይነት ሥፍራውን ስለመያዙ እንጂ፣ በገዥነቱ ውስጥማ ከሌላ ብሔረሰብ የበቀሉም ነበሩበት፡፡ በገዥነት ውስጥ ከላይና ከሥር መሆን ሊኖር፣ ከሥር የነበረ ወደ ላይ ሊወጣ፣ ከላይ የነበረ ከሥር ሊገባ ይችላል፡፡ የትግሬ መሳፍንትን የቅርብ ጊዜ የቅሬታ ምክንያት ብናስታውስ፣ በዮሐንስ አራተኛ የተዘረጋውን የትግራዊ የበላይ ገዥነት ምኒልክ ጣልቃ ገብቶ ሟቋረጡ ነበር፡፡ ይህ ታሪክ ተራ ገበሬ ድረስ የገባ የቅሬታ አሻራ ትቶ አልፏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከአማራ ሌላ የትግሬ፣ የአገው፣ የኦሮሞ መሳፍንታትም አነሰም በዛ የበላይ ገዥነት ድርሻን በተለያየ ጊዜ ተቃምሰዋል፡፡ በዱሮ ገዥነት ጀርባ መመካት አማራን ከሳበ፣ ሌላውንም የማይጎትትበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለዚህም አብነት ባለንበት የኢሕአዴግ ዘመን ውስጥ እንኳ ብሔርተኛነትን ከገዥነት ታሪክ ኩራት ጋር አጎዳኝተው የተረኩ የጽሑፍ እማኞች አንድ ሁለት ብሎ መቁጠር ይቻላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ የተጠቀምኩበት አዲስ ራዕይ መጽሔት (የካቲት መጋቢት 2009 ዕትም) ራሱ ሳያውቀው በኢሕአዴግ ውስጥ ስላለና ከድሮ ገዥነት ጋር ያልተያያዘ ትምክህትም ፍንጭ ሰጥቶናል፡፡ በኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ የተለመደውን ጥበትንና ትምክህትን አነፃፅሮ መመልከትን መጽሔቱም የሚከተል ቢሆንም፣ ገጽ 9 ላይ የጠባብነት ሌላ መገለጫ ብሎ ያሠፈረው ‹‹ራስን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቸኛ ባለቤትና ጠባቂ አድርጎ ማሰብና ሌሎችን በጥርጣሬ ዓይን የማየት አዝማሚያ›› በቅጡ ላስተዋለው የሚያንፀባርቀው ጎጇዊ ጥበትን ሳይሆን የትምክህትን ጥበት ነው (ሰረዝ የተጨመረ)፡፡

በሌላ በኩል በ2008 ዓ.ም. በአማራ ክልል ውስጥ የታዩ ጣጣዎችንም የትምክሀት ውጤት አድርጎ ለመግለጽ መጣደፍ ለስህተት መጣደፍ ነው፡፡ ወደ ትግራይ ያለፈ መሬት አለኝ የሚለው በአማራ ክልል ውስጥ የተነሳው ጥያቄ በሌሎች ክልሎች መካከል ከተነሳው ጋር የባህርይ ልዩነት የለውም፡፡ ቅማንቶች ከአማራነት የተለየ ማንነት አለን ሲሉም የተነሳው ‹‹አንድ ነን፣ ለምን እንከፋፈላለን፤›› የሚለው ቅማንቶችን ጭምር ያካተተ ቅዋሜም (የነበረውን ትምክህታዊ የንቀት ታሪክ ወደ ጎን አድርገን ስንመለከተው) ከእኛ መዳፍ ውስጥ ምን ቆርጧችሁ ትወጣለችሁ በሚል ማን አህሎኝነት ፈጽሞ የማይብራራ፣ ሥልጤዎችና ወለኔዎች ከጉራጌ ማኅበረሰብ እንለያለን ባሉ ጊዜ ከተነሳባቸው ቅዋሜ ጋር በብዙ ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ቁጣ ጊዜ በትግራዊ ሰዎች ላይ የተከሰተውን መተናኮልም በጠቀስነው አዲስ ራዕይ ውስጥ እንደሠፈረው ከትምክህታዊ ጭፍን ጥላቻ የተወለደ አድርጎ ማቅረብም እውነተኛ ምክንያቱን ለይቶ መፍትሔ ለመፈለግ የማይጠቅም ነው፡፡ የመሬት ጉዳይ የታከለበት ከመሆኑ ባለፈ፣ በትግራዊነት ላይ የተዛመተው ድፍርስ ስሜት በሌሎች አካባቢዎች ውስጥ ከተዛመተው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የጋራ መነሻውም ሕወሓት መራሽ ገዥነት ውስጥ እንገኛለን ከሚል ማዕዘን ትግራዊ ሰዎችን በሥርዓቱ የበለጠ ተጠቃሚና የሥርዓቱ ጠባቂ አድርጎ መመልከት ነው፡፡ መፍትሔው የሚገኘውም ለምን ትግራዊ ላይ እንዲህ ያለ አመለካከት ወደቀ? ይህስ እንደምን ይገፈፋል? የሚሉ ጥያቄዎችን በትክክል ከመመለስ ነው፡፡ በትምክህት ማሳበቡ ረብ የለሽ መሆኑን ለማጤን ትምክህት ተሸናፊ ባልነበረበት በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ጊዜ አማራና ትግሬ በጎንደርና በሌሎቹም የአማራ አካባቢዎች ምን ያህል ተላልሶ ይኖር እንደነበር ማስታወስ ነው፡፡ እስካሁን የጠቃቀስናቸው ነጥቦች፣ ሁሉ ነገር በትምክህትና በጥበት ውስጥ ሲሰነቀር እንደማይችል ለመገንዘብ የሚያስችሉ ይመስለኛል፡፡ ትምክህትና ጥበት እንደ ዓይጥና ድመት የሚጠፋፉ ነገሮች እንዳልሆኑ ሁሉ ጥላቻና በቀልም አብረዋቸው የተፈጠሩ ነገሮች አይደሉም፡፡ ትምክህትና ጥበት ጥላቻና በቀልን የሚታጠቁት መተነኳኮልን ሲመገቡ ነው፡፡ የሥልጣን ተዛነፍ፣ ሀብት የማካበት እሽቅድምድምና ተቀደምን/ተዘረፍን ባይነት ባለበት ቅሬታዎችና መብከንከን መኖራቸው አይቀርም፡፡ ቅሬታዎች የትምክህትና የጥበት ስም ቢሰጣቸው አይገቱም፣ ለእነሱ ምንጭ የሆኑት ችግሮችም አይወገዱም፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ በድጎማ ድርሻ ላይ እከሌ ስንት ደረሰው እያሉ ማነፃፀርና ድርሻን ለማሻሻል መጣጣር የተወከሉበትን ተግባር የማካሄድ እንጂ የጥበት ተግባር አይሆንም፡፡ እዚህ/እዚያ ተዳላ የሚል ጥርጣሬን ለማስወገድና ከአጠቃላይ አገራዊ ዕይታ አኳያ መቅደምና መዘግየት ያለባቸውን ሥራዎች ከማስተዋል ጋር የፌዴራል ልማቶችን አካባቢያዊ ድርሻዎች በተመለከተ ጥሩ መግባባት እንዲዳብር ከተፈለገም ከክፍልፋይ ብሔርተኛ ሙሽት መውጣትና ለመተማመን የሚያበቃ የግልጽነትና የፍትሐዊነት ግንኙነት ማጎልበት ነው፡፡

‹‹የጠባብነት/የትምክህት ኃይሎች የመከላከያና የፀጥታ ኃይላችንን ዋና ዒላማ ያደረጉት ከሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ተነስተው… [ነው]፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከማንኛው አደጋ የሚጠብቅ… በመሆኑ ይህ ተቋም ካልፈረሰ ወይም ካልተዳከመ ዓላማቸው እንደማይሳካ በመረዳታቸው ነው፡፡ ሌላው መነሻቸው የሠራዊት የከፍተኛ ኃላፊነትን የማመጣጠኑ ሒደት በአንፃራዊነት ረዘም ያለ ጊዜን የሚጠይቅ መሆኑን የሚረዱት እንኳ ቢሆንም፣ አድልኦ እንዳለ በማስመሰል ማቅረብ ቀላልና አቋራጭ መንገድ ብለው ስለሚያስቡ… (የተጠቀሰው መጽሔት፣ ገጽ 23፣ ሰረዝ የተጨመረ)፡፡

ይህን መሳይ ማመካኛ 25 ዓመታት ካለፈው የሥልጣን ቆይታ በኋላ ይዞ መቅረብ በእጅጉ አሳፋሪ ነው!! አንደኛ ነገር ለሐሜት መነሻ የሚሆን ዝንፈት ሲኖር መደረግ ያለበት ሐሜትንና ጥርጣሬን መኮነን ሳይሆን፣ ዝንፈቱን ማስተካከል ነው፡፡ ሁለተኛ ከዝንፈት አልፎ መከላከያና ፀጥታው በአመጣጥም በአመለካከትም ወደ ኢሕአዴግ ያዘመመ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በየብሔረተኛ ወገንተኛነት የተሞላ ክልላዊ ታጣቂም ምን ያህል ደም አፋሳሽ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል እስኪሰቀጥጠን ድረስ ዓይተናል፡፡ ሦስተኛ ሕገ መንግሥቱ የሚለው የተጠቀሱት አውታራት ገለልተኛ ይሁኑ እንጂ ወደ ቡድን ወይም ወደ ፖለቲካ መስመር ያዝምሙ አይልም፡፡ አራተኛ ዛሬም ያለው ጥያቄ ገለልተኛ ሆነው ይታነፁ/ይጠናቀሩ እንጂ ብስል የአመራርና የሙያ ክህሎት ከሥራ ወጪ ሆኖ ይባክን አይደለም፡፡ አምስተኛ ገለልተኛ ይሁኑ የሚለው ጥያቄ የማይረሳ ቁልፍ ጥያቄ የሆነው፣ እመት ነፃነትና እመት ፍትሕ ማጅራታቸው ሳይያዝ፣ ለዘፈቀዳዊ የጉልበት ሥራ ሳይብረከረኩና መንግሥታዊ ግልበጣ ሳያቃዣቸው ሊኖሩ የሚችሉት በገለልተኛ መሠረት ላይ ዴሞክራሲ ሊገነባ ከቻለ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህን እውነቶች እኔ ነኝ ያለ የፕሮፓጋንዳ ሞራ ሊሸፍናቸው አይችልም፡፡ እነሱን አንድ ሁለት እያልኩ መደርደሬም ኢሕአዴግ አላወቀ ይሆናል የሚል የዋህነት ይዞኝ አይደለም፡፡ የአገራችን እውነታ ብዙ እርማትን የሚሻ መሆኑ ዓይን የማንቆር ያህል የሚታይ ነው፡፡ ማየት የፈለገም ማድረግ ያለበት ዓይኖቹን መክፈት ነው፡፡ ዓይን ከድኖ ሃራምባና ቆቦ የረገጠ መከራከሪያ ማቅረብ ትርፉ ዓይነ ደረቅነትን ማጋለጥ ብቻ ነው፡፡

ብሔርተኛ ገዥነት ከተቋቋመ ወዲህ በአገራችን የተፈለፈሉት ጣጣዎች ብዙ ናቸው፡፡ ማናለብኝ ያሉ ዝርፊያዎች፣ አድሎዎች፣ ንቁሪያዎች፣ የኃይል ጥቃቶች፣ መብት ጭፍለቃዎች፣ ፖለቲካዊ ሾኬዎች፣ ‹‹የቤቴ መቃጠል ለትኋን በጀኝ›› የሚሉ መሳይ ብልጠቶች፣ አላታሚ አሉባልታዎች፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ መጠቃቂያዎች መርዛቸውና ሕመማቸው ቶሎ አይነቀልም፡፡ እኔ ነኝ ያለ አርቆ አሳቢ ሰውም ቢሆን፣ በብሔረሰብ ማንነቱ መገለልና መንጓለል ሲያርፍበት ወይም ለገዥ ፖለቲካ ባለማዘጥዘጡ ከተገቢ ጥቅሙና መብቱ ሲገፋ በጥቃት መመዝመዙ፣ ሚዛናዊና የእኩልነት አመለካከቱ እየተመረዘ ወደ ጅምላ ስሜቶች በመውረድና ባለመውረድ መሀል ቁም ስቅል ማየቱ አይቀርም፡፡ መጠራጠር፣ ድፍርስ ስሜቶችና ፍረጃዎች ከመቃቃር ጋር በአገራችን ፈጥነው የተባዙት ለዚህ ነው፡፡

የችግሮችን መነሻዎች በማስወገድ ረገድ ትርጉም የሚሰጥ ሥራ በማከናወን ፈንታ እንዲህ እንዲያ ያለው ድርጊት የትምክህተኞች/የጠባቦች ነው እያሉ ዛሬም ነገም ውግዘት መደርደር ህሊናን ከማታከትና ንቁሪያን ከማገልገል በቀር ትርፍ የለውም፡፡ ይህንኑ ትምህርት ለመስጠት የማያንስ ልምድም አሳልፈናል፡፡ የቅድመ ኢሕአዴጉ የሥልጣን ዘመን አማራ ገዥዎች የደመቁበትና አማርኛ ብቻውን የመንግሥታዊ ሥራ ቋንቋነቱን የተቆጣጠረበት መሆኑ በራሱ የሚረጨው መልዕክት ሳያንስ፣ ወደ ሥልጣን የመጡና የፖለቲካ ሜዳውን ያጣበቡ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ከዋናው የፖለቲካ ጥያቄ (ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጥያቄ) ይልቅ የብሔር ጉዳይን ወደፊት በማምጣትና ነጋ ጠባ ስለትምክህት/ነፍጠኛ ኃይሎች በማባዘት አወቁትም አላወቁትም ጭፍን ጥቃት በአማራነት ላይ እንዲነሳ አግዘዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዴሞክራሲ ጥያቄ ተጭበርብሮ እንዲዘነጋ የማድረግ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከዚያም ወዲህ ሌሎች በስሜት የተግለበለቡ ቅስቀሳዎች የብሔረሰብ ግጭቶችን ሲያደርሱ ታይቷል፡፡ ከእነዚህ ልምዶች በመነሳት ብሔረሰባዊ ጥላቻዎችና የበቀል ስሜቶች እንዳይራገቡና እንዳይባባሱ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ጥንቃቄያችን ግን ላይ ላዩን የሚሄድ፣ በስሜታዊነት የተሞሉ ቃላትንም ሆነ ለበቀል የሚያነሳሱ የጥቃት ዜናዎችን ባለመርጨት የግልፍታን አፍላ ሰዓት አሳልፎ፣ የድስኮራ ኮንፈረንስ ከማካሄድ በቀር ለመሸካከርና ለጥላቻ መፍለቂያ የሆኑ ዕውናዊ ችግሮችን የማስተካከል ሥራ ላይ አላተኮረምና ችግሩ ማብቂያ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በተለያዩ ክልሎች ስለተፈጸሙ ቤት ንብረት የማሳጣትና ሕይወት የመቅጠፍ ጥቃቶች አፍረጥርጠን እንተርክ ቢባል ቀላል የማይባል ጉድ አለ፡፡ የበቀል እሳት ላለማራገብ ሲባል የማለባበሳችንን ያህል ደግሞ የአማራ ትምክህተኞች ይህንን አደረጉ ለማለት አንደበታችንን አይዘንም፡፡ ከሌላ ብሔረሰብ ግድም ያገጠጠ የንቀትና የእብሪት ሥራ ሲያጋጥመን እንኳ ከትምክህት ጋር ለማገናዘብ አንደፍርም፡፡ ይህ ከምን የመጣ? ካለማወቅ? ወይስ ‹‹…የተሻረን ይመሰክሩበታል›› እንዲሉ ዓይነት ሆኖ?

ትምክህት ማን ያህለኛል ባይነት ነው፡፡ ዛሬ ካሉና ካለፉ፣ እውነተኛና ታሪካዊ ወይም አፈ ታሪካዊ ከሆኑ አኩሪ የተባሉ ክንዋኔዎችና ብልጫዎች ላይ ተጣብቆ፣ ከገዥነት ዝናዎችም ጋር የሚያዛምዱ ማኅበራዊ ክሮችን አፈላልጎ (ብጥስጣሾችንም ቢሆን ቆጣጥሮ) በመመፃደቅ የሌሎችን አስተዋጽኦዎች ማስተዋል የሚሳነው ነው ትምክህት፡፡ በዚህም ሚዛን በሳተ እሳቤውና ቁንንነቱ የሚገፋተር ንቀትን እየረጨ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ይቦረቡራል፡፡

ለዚህ ዓይነት ተመኪነት መነሻ የሚሆኑ ስንቆች አነሰም በዛ በበርካታ ማኅበረሰባዊና አካባቢያዊ አብራኮቻችን ውስጥ ማግኘት አይገድም፡፡ ለመመኪያነት ሊውሉ የሚችሉት ነገሮች ዝርዝራቸው ብዙ ነው፡፡ ለምለምና ሰፊ መሬት፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፀጋ፣ የከበሩና የውድ ማዕድናት ፀጋ፣ የከተማ ሥልጣኔ መነሻ መሆን፣ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት መሆን፣ ከሌላው ቀድሞ ክርስትናን/እስልምናን መቀበል፣ የአንዱ ወይ የሌላው ሃይማኖት ነባር ማዕከል መሆን፣ እምነትን፣ ባህልንና ቋንቋን በጥራት ጠብቆ የማቆየት ታሪክ አለኝ ባይነት፣ የአፍሪካዊ ዴሞክራሲና የአንድ አምላክ እምነት ቀዳሚ መገኛነት፣ የፍልፍል ሥነ ሕንፃ ባለታሪክነት፣ የሰው ዘር መገኛነትና የጥንታዊ ፊደል ባለቤትነት፣ ወራሪን በቆራጥነት የመታገል ታሪክ፣ የቅኝ ኃይልን ድል አድርጎ የመመለስና ቅኝ ያለመገዛት ታሪክ፣ ወርቃማ የኪነ ጥበብና የድርሰት ሰዎች ካፈራ አካባቢ መብቀል፣ አሮጌ አገዛዝን የታገሉ ብዙ ተራማጆች ካፈራ አካባቢ መብቀል፣ የትጥቅ ትግል ባለታሪክነት፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ ለአብነት ከቀረቡት ዝርዝሮች ውስጥ ሐረሪው፣ ከፋው፣ ወላይታው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ወዘተ መኩሪያዬ የሚሏቸው ነገሮች እንደሚኖሯቸው በአክሱምነት፣ በወለጌነት፣ በጎንደሬነት፣ ወዘተም ሊመነዘሩ የሚችሉ መኩራሪያዎች እንዳሉ፣ ከዚያም በላይ ለአገር ልጅነት የኩራት ሀብት ተደርገው የሚጠቀሱ እንዳሉም መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአገራችን የተከሰቱትን ብሔረተኛ እንቅስቃሴዎችን ለአመል ገባ ብለን ካስተዋልናቸውም በሆነ ታሪካዊ ወይም ቁሳዊ ባለፀግነት ላይ የተመሠረተ ተመኪነትን ‹‹ስንበደል ኖርን›› ከሚል ግንዛቤ ጋር አዳብለው ልናገኛቸው እንችላለን፡፡

ኩራት/ተመኪነት አድሏዊነትንና ድንቁርናን ምሽጉ አድርጎ ትዕቢትን መተንፈስ (ሌሎችን ማንኳሰስ) ሲጀምር ትምክህተኛነት ይሆናል፡፡ በትምክህት ለመወጠር በገዥነት ውስጥ ማለፍ ግድ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመለየቷ በፊት በኤርትራ ልጆች አካባቢ (ፊደል ባልቆጠሩት ዘንድ ጭምር) ከቅኝ ተገዥነት የተገኘችን ‹‹ሥልጡንነት›› መመኪያ በማድረግ የጊዜውን ገዥዎቻችንን እንኳ ያልማረ ትምክህት ይንፀባረቅ ነበር፡፡ ሌላ ቀላል ምሳሌ ላክል፣ በኢትዮጵያዊ ኩራት መንፈሳቸውን ያጠገቡ የመሰላቸው ዘበናይ ወጣቶች በኤፍኤም ሬዲዮ ጭምር በሚያናፍሱት ‹‹እኛ ሐበሾች—ጠይሞች—ቆንጆዎች›› የሚል ተመፃዳቂነት ውስጥ፣ ሐበሻነት የነበረው ቅይጥ/ድብልቅ የሚል የእሳቤ ውሉ ጠፍቷል፡፡ የእኛ ቅይጥነት ከቀይነት እስከ አራራ ጥቁርነት፣ ከዞማ እስከ ቁርንጭጭነት፣ ከሰልካካነት እስከ ደፍጣጣነት የሰፋ መሆኑ፣ ዞማነት ከጥቁረትና ከደፍጣጣነት ጋር፣ ቅላት ከቁርንጭጭነት ጋር ሊገኝ መቻሉ ተስቷል፡፡ በሐሩር አየር ንብረት ውስጥ ጥቁረት ያለው ፋይዳ፣ አየር ንብረቱ ራሱ የቆዳ ቀለም መራጭነቱና አጎናፃፊነቱ አልተጤነም፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠ ጤናማ አካላዊ ቁመናን ቆንጆና ጥፉ ብሎ መፍረድም ኋላቀርነት መሆኑ ገና አልታወቀም፡፡ ከዚያም በላይ በጤናማ አመጋገብና እንቅስቃሴ ቁመናን በማቀልጠፍና ጤናን በማበልፀግ ቁንጅና የመገኘቱ ዕውቀት፣ በመውዛትና በውፍረት ሰውነትን አስተሳስሮ የበሽታ መጫወቻ ከማድረግም አስቀያሚነት የመታፈሱ ዕውቀት ገና እኛ ዘንድ የደረሰ አይመስልም፡፡ እናም በቀለም ፍካትና በመልክ ላይ የተመሠረተ አላዋቂ መመፃደቅ ብሔረሰብ ሳይለይ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከትግራይ እስከ ሶማሌ ክልል ድረስ ተደላድሎ እናገኘዋለን፡፡

ከጠቀስነው ምሳሌ መረዳት እንደሚቻለው እንዲህ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶች ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚቧጭርና ቅስምን የሚተናኮል ሚና ቢኖራቸውም፣ ፈጽሞ የፖለቲካ ሙሌት ሊሰጣቸው አይገባም፡፡ የፖለቲካ መማቻም መደረግ የለባቸውም፡፡ ተፈጥሯዊ የፆታ ልዩነትን የፆታ ማበላለጫ አድርጎ የሚመለከተው፣ አድሎኛ ማኅበራዊ ግንኙነት የተከለውን የፆታዎች ሚና ተፈጥሯዊ ድርሻ አድርጎ የሚቆጥረው፣ በሥልጠናና በትምህርት የሚገኝ የአዕምሮና የሙያ ልቀትንም ያለፆታዊ አበላላጭነት መቀበል የሚቸግረው የወንድ ትምክህተኝነት በ1960ዎች የለውጥ ሰዓት ገመናው ከመገላለጡ ሌላ በነቀፋ ብዙ ተነዝንዞ ነበር፡፡ በተለይ በደርግ ጊዜ ያ ሁሉ የቃላት ውርጅብኝ ግን የፆታ ትምክህተኝነትንም ሆነ ጭቆናውን አላመናመነውም፡፡ ጭራሽ በእልህና በብሽቀት የቤተሰብ ሰላማዊ ግንኙነትን ሲበጠብጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ፆታዊ ንቀትንና በደልን የማድከም ሥራ ከቃላት ይበልጥ ተግባራዊ የአኗኗር (የባህል) ለውጦችን እንደሚሻ ሁሉ፣ ማኅበራዊ ትምክህተኛነትና ጎጇዊ ብሔርተኛነትም የሚደክሙት በኢንዱስትሪያዊ የልማት ጎዳና ውስጥ ፍትሐዊ የመተሳሰብና የመከባበር ቤትን በማደራጀት ነው፡፡ ከቃላት ዶቅዶቄ ቅንጣት ታህሏ የተግባር ለውጥ ትበልጣለች፡፡

እስካሁን ከተባለው ወደ ትምክህት ሊቀየር የሚችለው ተመኪነት ዝርዝሩ ብዙ እንደሆነ፣ የትኛውም ዓይነት ትምክህት፣ የትኛውም ጎጠኝነትም ሆነ ብሔረተኝነት ሚዛን በሳተ ግንዛቤና ስሜት ላይ የመቸከል (ማለትም የጠባብነት) ባህርይ እንዳለው፣ እንዲህ ያሉ ዝንባሌዎች የፖለቲካ መስመሮች እንዳልሆኑ፣ ማናህሎኝ ባይነት የብሔርተኝነትም ገጽታ ሆኖ ሊከሰት እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ እናም ትምክህት የተባለን ነገር ሁሉ ለአንደ ወገን መስጠት ዝቅ ሲል ድንቁርና፣ ከፍ ሲል ደግሞ ማጭበርበር እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ከዚህ አለፍ ብሎ በዛሬው የፖለቲካ ሕይወታችን ውስጥ ጉልህ ሚና ስላላቸው ጥበቶች መናገር ከተፈለገም፣ ከአደናጋሪና ራስን ከሚያታልል ፕሮፓጋንዳ ወጣ ብሎ እውነቱን ለመናገር መድፈር ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከተደፈረም፣ በአሁኑ ጊዜ ለአገራችን ፖለቲካዊ ዕርምጃ ፈተና የሆኑ ሦስት ጥበቶች ይታያሉ፡፡

በየአካባቢው ትናንሽ ገዥነት የተሰማራውና በተረኛ አድሏዊነትና አንጓላይነት የተጠመደው፣ በዚህም ማኅበረሰባዊ ተዛምዶዎችንና የተባበረ ትግልን እያቆሰለ የሚገኝ ጎጃዊ ብሔረተኝነት አንዱ ነው፡፡ በደም የተገኘ ድልንና በደም የተጻፈ ሕገ መንግሥትን ምርጫ በሚባል የጨዋታ አቋራጭ ለመጣ እበላ ባይ/‹‹የኒዮሊበራል ተላላኪ›› አናስረክብም፣ ያለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር (ያለ ኢሕአዴግ ገዥነት) የተዋደቅንለት ድሉም ኢትዮጵያም አይኖሩም ባይነት ሌላው ነው፡፡

ሦስተኛው የኢትዮጵያ አንድነት አቋም ላይ የተሰካ፣ ግን ብሔር ብሔረሰባዊ የተባለን ነገር ከሩቅ የሚሸሽ፣ ብሔረሰባዊ መብቶችን የመጎናፀፍ ጤናማ እውነታን ከከፋፋይ በቀለኛ ብሔርተኝነት ነጥሎ ማየትና ከጤናማው ጋር መስማማት የተሳነው፣ አንድነትን የሃይማኖት ያህል ይዞ ዕውር ድንበሩን ከመወራጨት በቀር አንድነትን የማዝለቂያ ብልኃቱ ያልተጨበጠ ረድፍ ነው፡፡ ይህንን ረድፍ ‹‹በአባቶቻችን ተጋድሎ የተገነባች አገር እንድትፈርስ አንፈቅድም›› በሚል አቋም አቅልሎ ማጀል ስህተት ነው፡፡ በረድፉ ውስጥ የአገሪቱ መፍረስ የመተላለቅ በር መሆኑ የታወቃቸው፣ ግን ከዚህ ማምለጫው ግራ የገባቸው ከብዙ ብሔረሰብ የበቀሉ ሰዎችም ይገኛሉ፡፡ (በነገራችን ላይ የነጥቦቹ ቅደም ተከተል የክብደት ደረጃን አያሳይም፡፡) ለአንድ አገር መዝለቅ መቆርቆርና መታገል ትምክህተኛነት አደለም፡፡ ለክልል ወይም ለማኅበረሰባዊ ወገን መብት መከበርና ለፍትሐዊ ዕድገቱ መቆርቆርም ጠባብነት አይደለም፡፡ ችግር የሚመጣው አንዱን በሌላው ማጣፋት ሲከተልና አመለካከት በአንዱ ውስጥ ተውጦ ሲገነትር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አንድነትን ከማፍቀርም ሆነ ለአካባቢ ከመቆርቆርም በኩል የሚከሰቱ ገንታራ ፍረጃዎችና ተቅነዝናዥነት ያልጠበቅነው ጥፋት ውስጥ ሊማግዱን ይችላሉ፡፡ እነዚህን አጥፊ ዝንባሌዎች አስቀድሞ ማወቅ፣ አካሄድን የማረም መጀመርያ ነው፡፡

የኢሕአዴግ መስመር ገዥነቱ ካልቀጠለ በኢትዮጵያ መተላለቅ ይመጣል በሚል መከራከሪያ ወዲህም ወዲያም እያሉ ገዥነትን ለማዝለቅ መፍጨርጨር የተፈራለትን መተላለቅ አያስቀረውም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ያለው ግትርነትና ሥልጣን አጥባቂነት በሌላ መልክ የመተላለቅ ጉዞ ፊት መሪ መሆን ነው፡፡ለኢትዮጵያ አንድነት በመታመንና በመከራከር ፅናት ማናህሎኝ በሚል ትምክህት የታወሩና የብሔር/የአካባቢ መብቴ ያለንና አንቀጽ 39 አይነካብኝ ያለን ሁሉ ለአንድነት ጠንቅ በመሆን ጥርጣሬ የሚያብጠለጥሉ፣ አወቁትም አላወቁት በአድራጎታቸው የአንድነት ሳይሆን የሚጠሉት መገነጣጠል ዕቁብተኛ ናቸው፡፡ በትንንሽ የየጎጥ ሥልጣንና በወሰን ጉዳይ በመሻኮትና ደም በመቃባት የተጠመደ ክፍልፋይ ብሔርተኛነትም አናክሶና ረግጦ ለሚገዛ ኃይል ጀርባን አመቻችቶ በመስጠት ረገድ ወደር የለውም፡፡ ከዚህ ሲከፋም እርስ በርስ የሚያፋጅ ጋኔል ጎትቶ ያመጣል፡፡

‹‹ወያኔ አማራን ለማጥፋት የቆረጠ…፣ የኢትዮጵያ ፀርና ኢትዮጵያን በቁሟ እየጋጠ ያለ….›› እያሉ የጭራቅ ወሬን የሚደረድሩ፣ በእነዚህ ትይዩ ቆመው፣ ‹‹የእኛ ብሔር በአቢሲኒያውያን ቀንበር ውስጥ ፍዳውን እየቆጠረ ነው፡፡ ከእነሱ ካልተላቀቀ ነፃ ሕይወት አያገኝም…›› የሚል ገንታራነትን የሚያጦዙ፣ እነዚህ ተቃራኒ መሳይ ሁለት ወገኖች ለኢትዮጵያ ሕዝቦችም ሆነ ለዴሞክራሲ አንዳች ጠብታ ታህል አስተዋጽኦ የማያደርጉ፣ ኢሕአዴግ ወደ ዴሞክራሲ አገዛዝ እንዳይገባ በር የመዝጋት ትንቅንቅ የያዙ፣ ‹‹እኔ በሥልጣን ካልቀጠልኩ ኢትዮጵያ ትጠፋለች›› ለሚለው ገዥነት በጥብቅና እያገለገሉ የሚገኙ፣ እንዲያውም ከአሁኑ የባሰ ቀጥቃጭ አገዛዝ እንዲመጣ የሚፀልዩ አቋሞች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከማፈራረስ የየብሔር ነፃነትን ለማዋለድ የሚሹት ደግሞ አምባገነንነትን ከማገልገልም በዘለለ፣ ስንዝር ታህሏ አስተዋይነት እንኳ የጠፋችባቸው የዕልቂት ደጋሾች ናቸው፡፡

እነዚህን የመሳሰሉ ጅል የፖለቲካ ዝንባሌዎች ወደ ምን ዓይነት ኪሳራ እንደሚወስዱ ከታወቀ አንድ ትልቅ መሰናክል ተዘለለ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ወዲያ ፖለቲካዊ ሰላምና ነፃነት ከልማት ጋር የተገናኙበት ሕይወት ውስጥ የሚያስገባውን መንገድ የመፈለግ ተግባር ይደቀናል፡፡ ከዚህ አኳያ በቁጣ መታወርና እልህን በግዑዝ ንብረትና በዜጎች ላይ መወጣት ፖለቲካ እንዳልሆነ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊ/ሐበሻ  አደለሁም›› ባይነት ወይም ምንም ሆነ ምን መነጠል አለብን የሚል አቋም ላይ መድረቅ፣ ወይም በተቃራኒው ኢትዮጵያን አናስነካም የሚል ሽለላ ፖለቲካ እንዳልሆነ ማየት ይቀላል፡፡ ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ከአፈና መዳፍ የመፈልቀቅና ዕድሜ የመስጠትም ሆነ የመቅጨት ውጤቶች በሁለት ወገኖች ድርጊታዊ መስተጋብር የሚወሰኑ መሆናቸውን መቼውንም አለመዘንጋት ነው፡፡ መንግሥት ማነቆ አላልቶ ለአደባባይ ሠልፍ ዕድል ሲሰጥ ከቁጥጥር በወጣ ግልፍታ ታውሮ የጥፋት ድርጊት ውስጥ መግባት የገዛ መብትን ማባረር ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ኃላፊነት በተሞላበት አኳኋን መብትን መጠቀም ደግሞ፣ ያ መብት ለነገም አድሮ እንዲገኝ አርቆ ማሰብ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ መብት እንዲሰፋና ሥር እንዲይዝ የመሥራት ብልህነት ነው፡፡ ይህ የፖለቲከኝነት ትንሹ ዕውቀት ነው፡፡ (በነገራችን ላይ የትኛውም የአስተዳደር አካባቢ በሆነ ሥፍራና ጊዜ ሠልፍ እንዲካሄድ ዕውቅና ሲሰጥ፣ በውስጠ ታዋቂም የተሠላፊንም ሆነ ከሠልፉ ውጪ የሆኑ ዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ድርሻንና ኃላፊነትን ለራሱም መስጠቱ ነው፡፡)

ወደ ፖለቲካ ቅመራ ከታለፈ ደግሞ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ በመመርመር መብቶችን፣ ልማትንና ሰላምን የሚያስጨብጥ መርሐ ግብር የመንደፍ ተግባር ይመጣል፡፡ በሌላ አነጋገር ወደ መነጠልም አዘመሙ ወደ አብሮ መኖር አዘመሙ፣ ዋናው ጉዳይ የራስ አዘማመም ሳይሆን፣ እውነታን እየበረበሩ ሊያጋጩ የሚችሉ የኢኮኖሚ ጥቅም ጣጣዎችን፣ ለዴሞክራሲ ባህል ባይተዋር መሆን ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን ችግሮች፣ እንዲሁም ውለው ያደሩ ብሶቶችና ቁርሾዎች ከቀጣናዊ ንጠቶችና ጉንተላዎች ጋር ተጠላልፈው ቅጥ አምባሩ ወደ ጠፋ ቀውስ የማስገባታቸውን ዕድልና ከዚያ የማምለጫ ቀዳዳዎች ሁሉ ለእውነት ታምኖ የመመርመር፣ እጅግ የሚያዋጣውን አማራጭ የማየትና የማሳየት ፈተናን የማለፉ ተግባር ነው፡፡

በራስ ፍላጎት ሀቅን ለመዳመጥ ካልተፈለገ በቀር የአፍሪካ ቀንድና የኢትዮጵያ እውነታ በራሱ ተባብሮ ለሁሉን አቀፍ ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲ ከመታገል የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በማያሻማ ደረጃ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በዚህ ላይ መግባባት ካለ ቀሪው ተግባር ጠባብ የአዕምሮ ሙሽትን እያሰፉ፣ የተበታተኑ ቡድኖችን እየሳቡ፣ በመፈራራት ማዶ ለማዶ መተያየትንና ኩርርፍን እየሰባበሩ (የትኛውንም ኢፍትሐዊ ተዛነፍና በደል እየተቃወሙ) በሕዝብ ውስጥ መግባትና ተቀባይነትን ማስፋት ነው፡፡ እዚህ ሒደት ውስጥ ከተገባ እኔ ብቻ ለፋሁ/ተዋደቅሁ፣ እኔ ብቻ አውቃለሁ፣ እኔ ብቻ ልክ፣ እኔ ብቻ ታማኝ የሚሉ ተመፃዳቂነቶች እየተቀዳደዱ የሌሎችን አስተዋጽኦ መፈለግና ማየት፣ ማወቅና ማክበር አብሮ ይመጣል፡፡ የሚቀር ቢኖር ተበለጥን እያሉ ለመብከንከንም ሆነ በለጥን እያሉ ለመታበይ መነሻ የሚሆኑ ተዛነፎችን በሒደት የማስተካከል ሥራ ውስጥ መግባት ነው፡፡

በአወሳንለት የዴሞክራሲ ቅፅር ግቢ ውስጥ እያሰብን ከሆንን ኢሕአዴግ እንዲቆይ መፈለግ ወይም ‹‹ኢሕአዴግ በቃን ይቀየር›› ማለት አያጣላም፡፡ ምክንያቱም ለሁለቱም የዴሞክራሲ ናፋቂዎች፣ የትኞቹም ፍላጎቶች በሕዝቦች እውነተኛ ድምፅ  መወሰናቸውና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ገለልተኛ ሥርዓት መዘርጋቱ የጋራ ጥያቄ ስለሚሆን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ዴሞክራሲን ፅኑ መሠረት በማስያዝ ተግባር ውስጥ መንግሥታዊ አውታራትን (መከላከያን፣ ደኅንነት፣ ፖሊስን፣ የፍትሕ ተቋማትንና ምርጫ ማስፈጸሚያ አካላትን) ከማንኛውም ፓርቲ ወገናዊነት የፀዱ አድርጎ ማነፅ ቅብጥርጥሮሽ የማይሻና ወለም ዘለም የማይባልበት ዴሞክራሲን የሚናፍቁ የየትኛውም ቡድን ደጋፊዎች ሁሉ አንድ ላይ ሊቆሙለት የሚገባ ተልዕኮ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተልዕኮው ትልቅ ፈተና አለበት፡፡ ይህንን ተቀዳሚ ማሻሻያ የማሳካቱ ተስፋ በተቃዋሚዎች ላይ አይጣል ነገር፣ የመከፋፈል ደባዎችንና አፈናዎችን በብልኃት እያረገበና በውስጣዊ ጥንካሬው እየመከተ፣ እያጎለበተ፣ ከዚህ ጋርም የአገሪቱን ጉዳዮች ከጊዜ ጊዜ በመገምገምና ትክክለኛ መፍትሔዎችን በመጠቆም ልምድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማስተዳደር የሚበቃ የፖለቲካ አቅም እንዳለው ያስመሰከረ ተቃዋሚ ፓርቲ/ግንባር እስካሁን ፈክቶ አልወጣም፡፡ ከራሳቸው ከሚወጡ መረጃዎች እንደምንረዳው ለመከፋፈል የሚያደርሷቸው ችግሮች በሰርጎ ገብ ደባዎች ብቻ የማይመካኙ፣ በራሳቸው ውስጥ በሚገለጡ ጠባብ ሩጫዎች፣ ኢዴሞክራሲያዊ ሾኬዎችና አሉባልታዊ ፍትጊያዎችም የሚመጡ ናቸው፡፡ ከእነ ድክመታቸው ኢሕአዴግን በምርጫ ውድድር በልጠው ቢወጡ እንኳ፣ ለዚያ የተስተካከለ ሜዳ ገና መች ተሟልቶ፡፡

ወደ ኢሕአዴግ አንጋጦ መጠበቅም ጅልነት ይሆናል፡፡ ድህነትን ከመታገል ጋር ብዙ ብሶቶች ያሏቸውን ሕዝቦች በተቀባይነት እቅፍ ውስጥ እንኳ ማስተዳደር ከባድ ሆኖ ሳለ፣ እስከ ዛሬ በተቀባይነት መጥለቅለቅ ያልሠመረለትና የጥርነፋና የአጠባ መግዣ ሥልቱ በአሁኑ ጊዜ የከሸፈበት ኢሕአዴግ ያለማወላወል ዴሞክራሲን መሠረት የማስያዝ ለውጥ ውስጥ ለመግባት ገና ዳተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ‹‹ጠባቦችና ትምክህተኞች መከላከያችንንና የደኅንት ኃይላችንን ለማዳከም አነጣጥረዋል››፣ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶው እየሠመረ ነው›› ባይነትና በተደጋጋሚ ግምገማ ሰዎችን የመሻርና የመሾሙ ሽርጉድ ሁሉ ገለልተኛ ተቋማትን የማነፅ ዋና ጥያቄ የሚያደናግር ወይም ዙሪያ ከመታከክ ያላለፈ ነው፡፡

ኢሕአዴግን ወደ ዋናው ጥያቄ ከመጠጋት አግደው የያዙት ነገሮች ምናልባት ሁለት ችግሮች ይሆኑ ይሆናል፡፡ የዴሞክራሲ ፀሐይንና ተጠያቂነትን የፈራ ሥልጣን ወዳድነት፣ እንዲሁም ከቁጥጥር ያፈተለከ ቀውስ ቢከተልና አጋጣሚውን የተጠቀመ የጥላቻ ጎርፍ ልሰልቅጣችሁ ቢልስ የሚል ፍርኃት፡፡ እነዚህንመሰሎቹ ፍርኃቶች የሚያሳስቡ እንጂ ተንቀው የሚታለፉ አይደሉም፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ወረደ ማለት ፍጅትና መበታተን መጣ ማለት ነው›› የሚል ፍርኃትን ማናፈስ ከዴሞክራሲ ይልቅ የአምባገነንነት (ሄዶ ሄዶም የመጠፋፋት) ሰባኪ መሆን እንደሆነ ሁሉ፣ የዴሞክራሲን ጅራት ያልጨበጠ ‹‹ወያኔ በቃኸን!›› ባይ ጩኸትና አስጯሂነትም ዓይን ጨፍኖ እግር ወዳደረሰው መሄድ ነው፡፡ የጭፍን ጉዞ አብላጫ ዕድል ደግሞ አደጋ የሥርዓት አልባነት፣ የፍጅትና የመበታተን አደጋ ነው፡፡ እናም በዚህም በዚያም የሚመጡ የእሳት መንገዶችን የመዝጋትና ዴሞክራሲን ወደፊት የማስኬድ ጉዳዮች አማካይ መንገድ ወደ መፈለግ ይወስዱናል፡፡

ለዚህ ተግባር ከብዙኃን ግፊት ፈጣሪነት የተሻለ አማራጭ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ማለትም፣

  • ኢሕአዴግንም ተቃዋሚቹንም ሙጥኝ ያላለ፣ በውስጥም በውጪም የሚያስተጋባ (ቢቻል የራሱን ድረ ገጽ የፈጠረ)፣ በዝብርቅርቅ ጥያቄዎች ያልባዘነና በማሳበቢያዎችም ሆነ በፍርፋሪ ማሻሻያዎች የማይሸነገል ነፃ  የሕዝቦች ድምፅ!
  • እያሳሳቀ ሥርዓት አልባ ቀውስ ውስጥ ሊከት ከሚችል የጋጋታና የውድመት ቅዋሜ ራሱን ያራቀ፣ ሕጋዊ ሥርዓትን በተከተለ ሰላማዊ መንገድ ድምፁን የሚያሰማ ነፃ የሕዝቦች ድምፅ!
  • የባለሙያ መፈናቀል በሌለበት አኳኋን የአገሪቱ መንበረ መንግሥት አውታራት ገለልተኛ በሆነ ቁመና አንዲታነፁ በሚጠይቅ ጥያቄ ላይ ያፈጠጠና በአገዛዙ ውስጥ መመለሻ የማይኖረው መሰነጣጠቅ ከመድረሱ በፊት ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችና የአገሪቱ ምሁራን ሕዝብን ያሳተፈ የምክክርና የትብብር መድረክ ፈጥረው የለውጥ አደራውን ወደፊት እንዲገፉ የሚወተውት ነፃ የሕዝቦች ድምፅ!
  • ለዚህ የተባበረ እንቅስቃሴ ካልሆነ በቀር በመጪው ምርጫ ለየትኛውም ድርጅት ቴአትራዊ እሽቅድምድም ድምፁን መጠቀሚያ ላለማድረግ የቆረጠ (አደራውን የሚሸከም ካጣ የድምፅ ካርዱን ይህንኑ እጦቱን መግለጫ እስከማድረግ የሚሄድ) ነፃ የሕዝቦች ድምፅ!!

ይህን መሰል ነፃ እንቅስቃሴ መፈጠሩ ሕዝብን ከተቁለጭላጭነት ያወጣል፡፡ መጪው ምርጫ በገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚነትና ነፃ የብዙኃን ታዛቢነት የበለፀገ እንዲሆን የሚጠቅም ፖለቲካዊ አየር ያጎለብታል፡፡ በተቃዋሚም በኢሕአዴግም ዘንድ ያሉ የዴሞክራሲ ወገኖች ወደፊት እንዲመጡና ለተሰባሰበ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲደፋፈሩ ይረዳል፡፡ እናም መጪው ጊዜ ብሩህ የመሆኑ ዕድል ይገዝፋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.