ይድረስ ለኦህዴድና ብአዴን፤ ኢትዮጵያዊነቱም፣ አንድነቱም ከመፈክር እንዲያልፍ – ከያሬድ ኃይለማርያም

 

ጥቅምት 5፣ 2017 እ.አ.አ

የመጠፋፋት ዜና በሰማንበት ማግስትና ዘረኝነት ነግሶ አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላውን በማንነቱ ብቻ ሲያገል፣ ሲገል፣ ሲያፈናቅልና ሲያዋርድ እያየን ባለንበት በዚህ ክፉ ወቅት ከወደ ባህር ዳር ከተማ የተሰማው ዜና፤ ኦሕዴድና በብአዴን ያሳዩት የአንድነት ስሜትና ኢትዮጵያዊነትን የማስቀደም መንፈስ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይሁንና እነዚህ ድርጅቶች ከዳንኪራና ከሆይ ሆታ ባለፈ አገሪቱ የተጋፈጠችውን አስፈሪና ውስብስብ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰኑ እርምጃዎችን ወደፊት መራመድ ካልቻሉ የዛሬው ንግግራቸው ከባዶ ፕሮፓጋንዳነት የዘለለ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያ የተጋረጡባት ችግሮችም እንዲህ በስብሰባና አብሮ ግብር ጥሎ በማብላት በቻ የሚፈቱ አይደሉም። እነዚህ ድርጅቶች ከሚወክሉት ህዝብ ብዛትና ክልላቸው ከሚሸፍነው የአገሪቱ ሰፊ ግዛት አንጻር በአገሩት የወደፊት እጣ ፈንታም ላይ ሆነ ከገባችበት ቅርቃር እንድትወጣ ለማድረግ ያላቸውም አቅም ከፍተኛ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን እነዚህ ድርጅቶች ከዚህ ትብብር የዘለሉ እርምጃዎችንም ሲወስዱና የፌዴራል መንግስቱን፤ ኢህአዴግን ማስገደድ ሲችሉ ብቻ ነው።

ባለፉት ሁለት አመታት እነዚህ ክልሎች በሕዝብ ተቃውሞ ሲናጡ ቆይተዋል። በተቀሰቀሱት አመጾችም በሁለቱም ክልሎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያዊያን ተገድለዋል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በግፍ ታስረው ለስቃይ ተዳርገዋል። ብዙዎችም እስከ አሁን በየማጎሪያው እየተሰቃዩ ይገኛሉ። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩም ወጣቶችም ግድያና እስር ሸሽተው ለስደት ተዳርገዋል። በዚህ ቀውስ ኢትዮጵያ እንደ አገር፤ ክልሎቹም በተናጠል ለከፍተኛ ቀውስ ተዳርገዋል። በባህርዳር ከተማ በተደጋጋሚ ጊዜ የተከሰተው የቦንብ ፍንዳታ፣ በጎንደር የተከሰቱ ግጭቶች፣ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የደረሱ የንብረት ውድመቶች፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የልማት ሥራዎች መስተጓጎል፣ የነጋዴዎች የግብር ጫና ተቃውሞ፣ የጎሳ ግጭቶችና ከቅዮ መፈናቀሎች ሁለቱን ክልሎቹ በዋነኝነት፤ በጥቅሉም አገሪቱን ብልጭ ድርግም እያለ ከሚታየው የለውጥ ማእበል ጋር ተዳምሮ ክፉኛ ጎድቷታ። የፖለቲካ መረጋጋትም እንዳይኖር አድርጓል። ይህ የለውጥ ማዕበልም እያደር ሌሎች አደጋዎችን ይዞ እንደሚመጣ ከወዲሁ ምልክቶች እየታዩ ነው። ኢህአዴግ፤ በተለይም ህውሃት ጡንቻውን አሳብጦ ብሔራዊ እርቅን ሲገፋና ሲያጣጥል፣ አገራዊ መግባባትና የተረጋጋ የፖለቲካ ሽግግር እንዳይኖር እንቅፋቶችን ሲደረደር አገሪቱን እዚህ ደረጃ አድርሷታል። በየቦታው እየፈነዱ የመጡት የእርስ በእርስ ግጭቶችም የሥርዓቱ ግትርነት ያስከተላቸው መዘዞች ናቸው። በመሆኑም ይህ ባህርዳር ላይ ያሳያችውት የአንድነት፣ የፍቅርና የኢትዮጵያዊነትስ ስሜት ሕዝቡ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባና አገሪቱንም ከጥፋት እንድትድንና ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና እንድታመራ ያደርጋት ዘንድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃላችሁን በተግባር ልታሳዩት ይገባል። ከሁሉ በፊት ግን ለአገሪቱም ሆነ ለክልላችው ዘላቂ ሰላም ስትሉ ኢህአዴግን ከዚህ በሚከተሉት አጀንዳዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ ሳይዘገይ እንዲወስድ ማስገደድ ሲትችሉ ብቻ ነው የአንድነት ጉዞዋችሁ የተቃናና ከግብ የሚደርሰው።

1ኛ。በተለያየ የአገሪቱ ክልሎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ታስረው በግፍ በየማጎሪያው እየተስቃዩ የሚገኙ፣ በሃሰት ክስ ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ እስክንድር ነጋንና ውብሸት ታዮን ጨምሮ ሁሉም ጋዜጠኞች፣ የድረ ገጽ አምደኞችና ጦማሪያን፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ዮናታን ተስፋዮና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ እንዲሁም በእምነታቸው የተነሳ ታስረው የሚገኙ የኃይማኖት አባቶችና ተወካዮች በአስቸኳይና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፤

2ኛ。ባለፉት ሁለት አመታት በተለይም በኦሮሚያ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ከተቀሰቀሰው አመጽ ጋር ተያይዞ የሥርዓቱ ታጣቂዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ በወሰዱት የኃይል እርምጃ በሰው ሕይወትና አካል ላይ የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ ወገን እንዳይጣራ ተደርጎ ቆይቷል። ኦህዴድም ሆነ ብአዴን በክልላቸው ውስጥ ለተፈጸሙት ጥፋቶች ባንድ ወይ በሌላ መንገድ ኃላፊዎች ስለሆኑ ለይቅርታም ሆነ የተበደሉትን ክሶ በእርቅ ላይ የተመሰረተ የአንድነት፣ የፍቅርና የሰላም ጉዞ ለመጓዝ በግጭቶቹ የደረሱት ጉዳጎች በገለልተኛና በቃት ባለው አጣሪ አካለ እንዲጣራ መደረግ አለበት። የአገር ሽማግሌዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የሕግ ባለሙያዎችን፣ ምሁራንንና ፖለቲከኞችን ያካተተ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም ሁለቱ ድርጅቶች መጠየቅ አለባቸው። ከዛም አልፈው አለም አቀፍ አጣሪ ቡድን ጉዳዩን እንዲመረምር በተደጋጋሚ ጊዜ ለቀረበው ጥያቄ ከሥርዓቱ የተሰጥው አወንታዊ ምላሽ አግባብ ስላልሆነ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት አጣሪ ቡድን ወደ ክልሎቹ ገብቶ ሁኔታውን እንዲመረምር እንዲደረግ፤

3ኛ. የሁለቱ ክልል መሪዎች በባህርዳር ላይ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ የተናገሩት አስደማሚ ንግግር በእርግጥም ከልብ የመነጨና በቅን ልቦና ላይ የተመሰረተ ከሆነ እንዲህ የሚወዷት ኢትዮጵያና የሚያከብሩት ሕዝብም ከተጋረጠባቸው አስፈሪ አደጋ የተርፉ ዘንድ ሁለቱ ድርጅቶች በህውሃት የተጠረቀመውን የእርቅና የብሔራዊ መግባባት በር እንዲከፈት የመጀመሪያውን እርምጃ ሊወስዱ ይገባል። ይህውም በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገር ውስጥ ሆን ከአገር ውጭ፣ በሰላማዊ መንገድ ይሁን በነፍጥ ሕዝብንና አገራቸውን ነጻ ለማውጣት የሚታገሉ የፖለቲካ ኃይሎችን፣ የተገለሉ የአገሪቱ ምሁራንን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ የሲቪክ ማህበራትን እና የአገራቸው ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ያሳተፈ የእርቅና የብሔራዊ መግባባት መድረክ እንዲፈጠርና የተረጋጋና ሰላማዊ ሽግግር እንዲካሄድ የፊዴራል መንግስቱ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች በይፋ መጠየቅ ስትችሉ ነው።

እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች መልስ ሲያገኙ የኦሮሚያው ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና የአማራ ክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ደጉ አንዳርጋቸው የተመኟትና ያሞካሹዋት ኢትዮጵያ እውን ልትሆን አትችልም። ከዚህ ሁሉ ፉከራ በኋላ ሁለቱ ድርጅቶች ተመልሰው በእናት ድርጅታቸው ቅዠት ውስጥ የሚዋጡ ከሆነ ሕዝባቸውን ለቀጣይ ግዞት፣ አገሪቱንም ውጥንቅጥ ወደሆነ ሁኔታ የሚጨምሯት መሆኑን ከወዲሁ ሊገነዘቡት ይገባል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.