ቡና ለመጠጣት ተመራጩ ሰዓት – ዘ ቴሌግራፍ

ቡና በመጠጣት በአነቃቂው ንጥረ ነገር አማካኝነት ውሎዎን ነቃ ብለው ለማሳለፍ ከፈለጉ ተመራጩ ሰዓት ከጠዋቱ 3፡30 እስከ 5፡30 ያለው ነው ሲሉ የነርቭ ስርዓት ተመራማሪዎች የገለጹት፡፡

አንድ ሲኒ አሪፍ ቡና ከምንም ነገር በፊት በጠዋት መጠጣት ጥሩ ቢሆንም ትንሽ ረፈድ ሲል መጠጣቱ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ነው ብለዋል በዘርፉ ጥናት ያከናወኑ ሳይንትስቶች፡፡

ይህም የሆነው ኮርቲሶል የተባለውና ሰውነትን ለመቆጣጠር የሚረዳው ዋናው ሆርሞናችን ከቡናው ንጥረ-ነገር ካፌን ጋር በሚኖረው መስተጋብር ውስጣዊ ሰርዓቱንና መነቃቃትን ስለሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡

በደማችን ውስጥ የሚኖረው ኮርቲሶል ከእንቅልፍ በነቃን ቅጽበት መጠኑ ከፍተኛ ሲሆን ለአንድ ሰዓት ያህል ማለትም በአማካኝ ከጠዋቱ 2 እስከ 3 ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ሆኖ ይዘልቃል፡፡

ኮርቲሶል መመንጨት ዝቅ በሚል ሰዓት ማለትም ረፈድ ሲል ቡና መጠጣቱ አዋጭ ነው ይላሉ በቤተሳይዳ ሜሪላንድ የጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የነርቭ ስርዓት ተመራማሪው ስቴቨን ሚለር፡፡

የኮርቲስል ሆርሞን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባለበት ጊዜ ቡና መጠጣቱ ግን የቡናውን አነቃቂ ንጥረ ነገር ካፌንን እንዲላመዱት ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ማነቃቂያ እንዲፈልጉ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል ስቴቨን፡፡

ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ ከሰዓት በኋላ ቡና መጠጣት ከምሳ በኋላ የሚከሰተውን ቀልብ ያለመሰብሰብ ችግር ይፈታል ይላሉ፡፡

ስቴቨን ሚለር በደማችን የሚኖረው የኮርቲስል መጠን ምሽት 1 ሰዓት እና ከ11፡30 እስከ 12፡30 ባሉት ሰዓታትም እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ትክክለኛው የቡና መጠጫ ሰዓት ይህ ነው ለማለት እንደሰዎቹ የኮርቴስል መጠን የመጨመርና መቀነስ ሂደትና ከእንቅልፋቸው እንደሚነሱበት ሰዓት ከሰው ሰው እንደሚለያይም ነው ያስታወሱት፡፡

ያም ሆኖ በጠዋት ከእንቅልፋቸው የሚነሱ ሰዎች ከአርፋጆቹ ይልቅ ትክክለኛ የቡና መጠጫ ሰዓታቸውን ማወቅ ይችላሉ ተብሏል፡፡

አንድ ሌላ የቅርብ ጊዜ ጥናት ደግሞ ተመራማሪዎች ራሳቸው ከገበያ ጥናትና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በመከተል ከሌሎች ባለሙያዎች በይበልጥ ከፍተኛ ቡና ጠጪዎች መሆናቸውን ዘገባው ይገልጻል፡፡

አርታኢያን ወይም ኤዲተሮችና ፀሃፊዎች ደግሞ 4ኛውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ፣ ሃኪሞችና የጤና ባለሙያዎችም ይከተሏቸዋል፡፡

ጥናቱ በቀን ከአንድ እስከ 3 ወይም ከዚያ በላይ ጊዜ ከአቦል እስከ በረካው ቡና ለሚጠጡ የአገራችን ሰዎች በተለይም የቤት እመቤቶች ደረጃም አልሰጠም፣ ምንም አላለም፣ አንተዋወቅም ማለት ነው ወይስ በካምፓስ ቋንቋ ሁሉንም ‹ሰቅለዋቸው› ይሆን?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.