ለማ መገርሳና አዲሱ ኦህዴድ – አበጋዝ ወንድሙ

ለማ መገርሳ
ለማ መገርሳ

ላለፉት ስድስት ዓመታት ህወሓት/ኢህአዴግን እንቅልፍ ነስቶ የሚካሄደው ሕዝባዊ ትግል አንዴ ጠንከር አንዴ ላላ እያለ የወደፊት ጉዞውን አሁንም ቀጥሏል ።ከዛሬ አንድ ዓመት ከሁለት ወር በፊት፣ በኦሮሚያ የነበረውን ሕዝባዊ ዓመጽ ተከተሎ በአማራ ክልልና አንዲሁም በኮንሶ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እንቢተኝነትና ዓመጽ፣ ሀገሪቱ ወደለየለት ህዝባዊ ዓመጽ ልትሸጋገር ትችላለች፣ ስልጣኔንም ሊያሳጣኝ ይችላል የሚል ፍርሃት ያስበረገገው በህወሃት የበላይነት የሚሽከረከረው ኢህአዴግ፣ ፋታ ለማግኘትና ተቃውሞውንም ያበርድ ይሆናል በሚል መሸጋሽጎችን ለማድረግ ሞክሯል።

ከዚህ አንጻር ዘወትር እንደሚይደርገው መጠነ ሰፊ ግድያና እስር ከማድረግ በተጨማሪ፣ እንደወትሮው ታዛዥነቱን ተግባራዊ አላደረገም በሚል የአማራ ክልሉን ገዱ አንዳርጋቸውን ከስልጣኑ ለማንሳት ተንቀሳቀሶ የንበረ ቢሆንም፣ከመካከለኛና የበታች ካድሬዎች ትብብር ባለማግኘቱ ባያሳካም፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንትና የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበረውን ሙክታር ከድርንና ምክትል ጠ /ሚና የድርጅቱ ምክትል የነበረችውን አስቴር ማሞን፣ በተሾሙ በሁለት አጭር ዓመት አንስቶ በለማ መገርሳና በወርቅነህ ገበየሁ አንዲተኩ አድርጎ ነበር።

በዚህ ሳይገታም እነ ለማ በተሾሙ በወሩ፣ በመላ ሀገሪቱ፣ የሚኩራራበትን ህገ-መንግስት ወደ ጎን በማድረግ የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፣ ኮማንድ ፖስት በሚል ሀገሪቱን በወታደራዊና ደህንነት ጁንታ ስር አድርጎ ከአንድ ዓመት በላይ ቢንቀሳቀስምና ፣ነገሮች ተረጋግተዋል በሚል ቢያነሳውም፣ ሕዝባዊ ተቃውሞው ዳግም አገርሽቶ ውስጣዊ ክፍፍሉንም ገሃድ ያወጣበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ይሄም በመሆኑ የለማ መገርሳን አዲሱ ኦህዴድ በቅጡ ለመረዳት ነገሮችን በዚህ ማአቀፍ ውስጥ ማየት የግድ ነው። ለማና የሱ አስተዳደር በበርካታ ሕዝባዊ ስብሰባዎችና የምክክር መድረኮች የሚያሰሟቸው ንግግሮችና የወሰዷቸው አንዳንድ እርምጃዎች በኦሮሚያ ክልልና በሌሎችም አካባቢዎች ተሰሚነታቸው እንዲጨምር ማድረጉ ፣ አንዳንዱን ያልሆነና ያልተገባ ፈንጠዚያ ውስጥ ቢከተውም፣ ህውሃትን ደግሞ ያልተጠበቀ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶ ድርጅቱ ይሄን አዲስ ሁኔታ በምን አይነት ሊቀበለው እንደሚችል ግራ በመጋባቱ ላልተቋረጠ ስብሰባ ዳርጎታል።

ለማ መገርሳ የክልሉ ፕሬዘዳንትና የድርጅቱ ሊቀ መንበር ሆኖ ሲመረጥ ከአመራር አካላት ውጭ ብዙ ሰው ያውቀው ያልነበረ ቢሆንም፣ እውነታው ግን ለማ የድርጅቱ የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል ከመሆኑ ባሻገር ላለፉት 22 አመታትም የኦህዴድ አባል ሆኖ የዘለቀ ግለሰብ ነበር።

ለማ በወጣትነት እድሜው የተቀላቀለው ኦህዴድ፣ ህወሃት ከጦር ምርኮኞች አውጣጥቶ የፈጠረው ድርጅት በመሆኑ፣ ፣ በሕዝብ ውስጥ የነበረው ድጋፍና ተቀባይነት ውሱን አንደነበረና፣ከዚህ በተጨማሪ መንግስት በቅርቡ ያካሄደው መጠነ ሰፊ ግድያና እስር ያለ ልክ ያስመረረው ህዝብ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን፣ እሱንም ሆነ የሚመራውን ድርጅት እንዲያዳምጠው ከተፈለገ፣ የግዴታ የተወሰኑ እርምጃዎችን ወደፊት መራመድ እንደሚያስፈልገው ግንዛቤ የጨበጠ መሆኑን ለማሳየት ስልጣኑን እንደተረከበ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም።

ከዚህ ቀደም የህወሓት/ኢህአዴግ ባለስላጣኖች የሚያሳዩትን እብሪትና ድንፋታ ሳይሆን፣ በለሰለሰና አክብሮት በተመላበት አቀራረብ ከህዝብ ጋር ግንኙነት ማድረግ በመጀመሩ የህዝብን ቀልብ ለመሳብ በመቻሉም ፣ጊዜ ሰጥተውት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት እንዲመዝኑት ያደረገው ተማጽኖ በተወሰነ ደረጃ ሊሳካ ችሏል።

በዚህ አንጻር የብዙ መቶዎችን ሕይወት የቀጠፈው የ2007 እሬቻ ክብረ በዓል ግድያ ዳግም አንዳይፈጸም፣ የ 2008 ክብረ በዓል ያለፈዴራል ፖሊሶችና ወታደሮች በስፍራው መኖር፣መሳሪያ ባልታጠቁ የክልሉ ፖሊሶችና አባገዳዎች በመረጧቸው ወጣቶች አስተባባሪነት አንዲካሄድ የሚለውን የህዝብ ጥያቄ ተግባራዊ ለማስደረግ መቻል፣ ከመልካም ንግግር አልፎ አንዳንድ ነገሮችን ሊያሳካ ይችላል የሚለው በሕዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ለማድረግ ችሏል።

ለማ በኦሮሚያ ክልል ያገኘውን ተሰሚነት፣ ከክልሉ አልፎ በልዩ ልዩ መድረኮች በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በሚያደርጋቸው ንግግሮችም ሆነ ድርጅቱና አባላቱ በሚያደርጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች (ለምሳሌ የኦሮሚያ ወጣቶች ጣናን ከእምቦጭ ለመታደግ በጋራ ከወንድሞቻቸው ጋር በመሆን ያደረጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴና፣ በለማ የተመራው 250 የሚሆኑ የክልሉ ባለስልጣናት፣ሽማግሌዎችና የዘፈን ባለሙያዎች የያዘ ቡድን ወደ አማራ ክልል ያደረገው የምክክር ጉዞ) የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ ለመሳብ በቅቷል።

ከለማ በርካታ ንግግሮች መረዳት እንደሚቻለው፣ ነፍሱን ይማረውና አሰፋ ጫቦ ይል እንደነበረው ኦሮሞኖቱና ኢትዮጵያዊነቱ ተጣልተው አስታራቂነት የገባ እንዳልሆነ ነው። ከህዝብ ብዛት አንጻር የህወሃት መሪዎች በቁጥር አናሳ ከሆነ ብሄረሰብ በመውጣታቸው በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ የግዴታ ልዩነትን ማራገብና አርስ በርስ ማናከስ እንደ ስትራቴጂ መጠቀም ቢገደዱም ፣ በሕዝብ ብዛት በሀገሪቱ ትልቅ ድርሻ ካለው የኦሮሞ ብሄረስብ የተገኘው ለማ ግን የዚህ አይነት የስነ ልቦና የበታችነት የተጠናወተው ባለመሆኑ ልዩነት ላይ ሳይሆን አንድነት ላይ እንዲያተኩር ያደረገው ይመስላል ።

የለማ ቡድን የሚያደርገውን ተግባራዊ እንቅስቅሴ ስንመለከት፣ ትኩረቱና አቅጣጫው በሀገሪቱ ላይ ያለውን ህገ መንግስት አንዳንድ መብቶች ለመተግበርና፣ እናት ድርጅቱ ኦህዴድ በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ በአዲስ መልክ ለማስኬድ ጥረት አያደረገ እንደሆነ ለማየት አንችላለን።

ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው አንደኛ፣ በቅርቡ በፌደራል መንግስቱ የተረቀቀው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ በሕገ መንግስት የተሰጠ የክልሎችን ስልጣን ያላገናዘበ መሆኑ ብቻ ሳይሆን’ በሕገ መንግሥት የተቋቋመን ክልል ሥልጣን በአዋጅ የተቋቋመው ባለሥልጣን የሚጋፋ ሆኖ ‘በማግኘቱ ሊጸድቅ አንደማይገባው ለጠ/ሚር ደብዳቤ አስገብቷል።

ሁለተኛ ድርጅቱ ምክንያቱን ግልጽ አያድርግ አንጂ፣ ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ ፓርላማውን ከመሰረተ ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጠ /ሚሩ የአመቱን ፓርላማ በንግግር ሲከፍት ከፓርላማ አባላቱ 1/3 ኛ የሚሆኑ ባብዛኛው የኦህዴድ አባላት አለመገኘት የያዘው መልክት አንደነበረ ልንገነዘብ አንችላለን።

ሶስተኛ አቶ ለማ በበርካታ ንግግሮቹ ተጠሪነቱ በቅድሚያ ለክልሉ ሕዝብ በመሆኑ ከሌላ ወገን /ድርጅት የሚመጣን ትአዛዝ አንደማይቀበል ደጋግሞ ሲያቀርብ የሚሰጠው መልአክት፣ከዚህ ቀደም በኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን ያንድ ቡድን የበላይነት እየተገዳደረ መሆኑን ማሳያ አድርገን ልንወስደው አንችላለን።

እነዚህ አቶ ለማና ቡድኑ የሚያሳዩት ተነሳሽነትና አካሄድ የመጨረሻ ስኬቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን የሚወስነው ኦህዴድ በኢህአዴግ ውስጥ ሊፈጥረው የሚችለው ተጽእኖና፣ እስካሁን ኢህአዴግን በበላይነት ሲያሽከረክረው የነበረው ህወሃት፣ ይሄን የበላይነቱን ሊሽር የሚችል አካሄድ በምን አይነት መንገድ ሊቀበለው ይችላል የሚለው ትግል የሚወስነው ይሆናል።

ባለፉት 26 አመታት ህወሃት የዘረጋው ስርዓት ሕዝቡን እርስ በርስ እንዲጠራጠር ፣ ሃገራዊ አጀንዳ ይዞ ከመንቀሳቀስ ይልቅ፣ ዝቅ ሲል በመንደር ከፍ ሲል በክልል ብቻ ተወስኖ ፣ በህወሓት የበላይነት በመላ ሀገሪቱ የተንሰራፋውን አስከፊ ስርዓት እንዳይታገል ሸብቦ ይዞት ከርሞ ነበር።

ከላይ አንደጠቀስኩት የዛሬ ስድስት ዓመት የመንግስትን በሃይማኖት ጣልቃ መግባት በመቃወም በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአዲስ አበባ ተቀስቅሶ የነበረው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ሃገራዊ መልክ ሲይዝ፣በኦሮሚያ በአማራ ክልልና በኮንሶ የተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ እየተስፋፋ መሄድ ፣ገዥው ቡድን ሳይፈልግ ተገዶ የሚያደርገው መሸጋሸግ፣ ዴሞክራሲ የሰፈነባትና የሕግ የበላይነት የሚከበርባት ኢትዮጵያን ለመመስረት ለሚደረገው ትግል ውሱንም ቢሆን ጠቃሚ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

የነለማን አዲስ ተነሳሽነትና አካሄድም እንዲሁ በአንድ ጀምበር ተነስተው የወጠኑትና ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱበት ሳይሆን፣ ወደውም ሆነ ሳይወዱ ያልተቋረጠው ህዝባዊ ትግል ያሳደረባቸው ጫና መሆኑን ለአፍታም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም።

የዚህ ያልተቋረጠ የህዝባዊ ትግል ግፊት፣ ሕዝቡን አደራጅቶ ለፍትህ ለዴሞክራሲና ለሀገራዊ ብልጽግና ሊመራ የሚችል ድርጅት የሌለበት ብቻ ሳይሆን፣ ይሄንን ለማደራጀት የሚፈልጉ ወገኖችን፣ ድርጅቶቻቸውን በህገወጥ መንገድ እያፈረሰ፣ አባላቱን እያሳደደ ወህኒ በማጎር ወይንም በመግድል የተካነ፣ ጠባብ የህውሃት ቡድን የበላይነት የያዘበትን ስርዓት ለመገርሰስ ባይችልም፣ ለቀጣይ ትግሉ ግን አጅግ ጠቃሚ የሆኑ ድሎችን ሊያገኝ አንደሚችል ጥርጥር የለውም። አነዚህ የሚገኙ ድሎችን በመንተራስ ደግሞ ሕዝቡን አደራጅቶ ለበለጠ ድል ማብቃት ሕዝባዊ ትግል እናደርጋለን የሚሉ ወገኖች ኃላፊነት ነው።

አበጋዝ ወንድሙ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.