የዕለቱ ኢሳት ዜናዎች . ጥቅምት 30/2010

በአቶ በረከት ስምኦን ንብረቶች ላይ የተጀመረው የሙስና ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 30/2010)በቅርቡ ስልጣን በለቀቁት በአቶ በረከት ስምኦን ንብረቶች ላይ የተጀመረው የሙስና ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነባው ደብል ትሪ ሆቴል ጋር በተያያዘ የተጀመረው ምርመራ ሙሉ በሙሉ የሆቴሉ ግንባታ የገንዘቡ ምንጭ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን አረጋግጧል።
ይህም የተፈጸመው በአቶ በረከት ስምኦን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነት ግዜ እንደሆነ መረጋገጡን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።
በአቶ በረከት ስምኦን ንብረቶች ላይ የተጀመረው የሙስና ምርመራ መቀጠሉን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
በምርመራውም በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የደብል ትሪ ሆቴል የገንዘብ ምንጭም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑና አቶ በረከት የቦርድ ስብሳቢ በነበሩበት ጊዜ የተፈጸመ መሆኑንም አረጋግጧል።
የደብል ትሪ ሆቴል ባለቤት ሆነው የተመዘገቡት አቶ ተካ አስፋውም የዳሽን ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ቢሆኑም ለዚህ ሆቴል ግንባታ በሚል ከዳሽን ባንክ ምንም አይነት ብድር እንዳልወሰዱም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር በዋናነት እንዲሰጥ የተቀመጠውን የመንግስት ፖሊሲ በመጻረር ብድሩ እንደተለቀቀም ለማወቅ ተችሏል።
በዋናነት በአምራችነትና በወጭ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ብድር እንዲሰጥ በፖሊሲ ደረጃ አቅጣጫ የተቀመጠለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሆቴሉ ግንባታ የሚውለውን ወጪ መቶ በመቶ ማበደሩንም ምርመራው አረጋግጧል።
በቅድሚያ ሁለት መቶ ሚሊየን፣በቀጣይ ደግሞ 100 ሚሊየን ብር በአጠቃላይ 300 ሚሊየን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጪ የሆነው በአቶ በረከት ስምኦን ትዕዛዝና በባንኩ ፕሬዝዳንት በአቶ በቃሉ ዘለቀ አስፈጻሚነት እንደሆነም ለኢሳት የደረሰው ማስረጃ ያሳያል።
ባንኩ ብድር ከመልቀቁ በፊት ተበዳሪው 30 በመቶ መነሻ ማቅረብ እንዳለበት ተደንግጓል።
በዚህ ሆቴል ግንባታ ግን ከተበዳሪው ወገን አንድም ሽራፊ ሳንቲም እንዳልቀረበና መቶ በመቶ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ሆቴሉ መገንባቱን ምርመራው አረጋግጧል።
የኢሳት ምንጮች የምርመራ ቡድን አሁንም ስራውን መቀጠሉን አስታውቀዋል።
መቀሌ የተጀመረው የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ስብሰባ ላይ እነ አቶ አባይ ወልዱ መልሰው የበላይነታቸውን ካላረጋገጡ በአቶ በረከት ላይ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በመገናኛ ብዙሃን ይፋ እንደሚደረግም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።
አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት በአቶ በረከት ስምኦን ላይ ከደብል ትሪ ሆቴል ጋር በተያያዘ በዚህ ወቅት ምርመራ የተጀመረው የሆቴሉ ባለንብረት ሆነው የተመዘገቡት አቶ ተካ አስፋው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ስለሚወዳደሩ የሕወሃት ሰዎች የእርሳቸውን ተቀናቃኝ የሕወሃቱን ተክለወይኒ አሰፋን ለማስመረጥ የሚደረግ ማሸማቀቅ ሊሆን ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ንብረትነቱ የአቶ በረከት ስምኦን በሚል ምርመራ የተጀመረበት፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የተገነባውና በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የሚገኘው ደብል ትሪ ሆቴል በመጪው ሰኔ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላላ ወጪው 300 ሚሊየን ብር የፈጀው ደብል ትሪ ሆቴል ባለ 11 ፎቅ ሲሆን 106 መኝታ ክፍሎች እንዳሉትም ታውቋል።

ፍልሰተኞችን ለመርዳት የሚመደበው በጀት በሕወሃት ደህንነት መስሪያ ቤት እየተመዘበረ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 30/2010)በኢትዮጵያ ያሉና አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ፍልሰተኞችን ለመርዳት የተባበሩት መንግስታት የሚመድበው በጀት በሕወሃት ደህንነት መስሪያ ቤት እየተመዘበረ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ይህው በጀት ግን በደህንነት መስሪያ ቤቱ እየተመዘበረ በየአመቱ ያልተወራረደ በሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር እየባከነ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽን በርካታ ተሽከርካሪዎች በደህንነት መስሪያ ቤቱ ለግድያና ለአፈና እንዲሁም ለእስር ከመዋላቸው ሌላ ለባለስልጣናት የግል መገልገያነት እንደሚውሉም ለማወቅ ተችሏል።
በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ መስሪያ ቤት ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመቀናጀት 850 ሺ ፍልሰተኞችን ያስተዳደራል።
በ26 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙት ከደቡብ ሱዳን፣ከሶማሊያና ኤርትራ ለተሰደዱ ፍልሰተኞች በጀት የሚመደብለትም በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን/ዩ ኤን ኤች ሲ አር/አማካኝነት ነው።
በዚሁም የምግብ፣የጤናና የአካባቢ ጥበቃ አገልግሎቶችን መስጠት የደህንነት መስሪያ ቤቱ መጠላያዎቹን እንዲያስተዳደር ተደርጓል።
በየአመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር የሚዘንብለት ይህ የደህንነት ቤት ግን በጀቱን እየመዘበረና ከታለመለት አላማ ውጭ እየተጠቀመበት መሆኑን የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።
እንደ ምንጮቹ ገለጻ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ድርጅት በደህንነት መስሪያ ቤቱ ስር ሆኖ የተባበሩት መንግስታት በጀትን ስለሚያባክን በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች ሳይወራረዱ በእንጥልጥል ላይ ይገኛሉ።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት ይህንኑ በተመለከተ ለደህንነት መስሪያ ቤቱ ማመልከቱም ነው የሚነገረው።
ይህ ብቻ አይደለም የተባበሩት መንግስታት ለስራ ማስኬጂያ በሚል ለስደተኞች መርጃ ለደህንነት መስሪያ ቤቱ የሰጣቸው በርካታ ተሽከርካሪዎችም ለግድያ፣ለአፈናና ለእስር ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ተጠቁሟል።
በደህንነት መስሪያ ቤቱ ሹሞች የአቶ ጌታቸው አሰፋ የቀድሞ ባልደረባ አቶ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስና የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ መስሪያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘይኑ ጀማል ቤተሰቦችና ልጆች በሊሴ ገብረማርያምና በውጭ ሀገር ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈለ እንደሚማሩም ታውቋል።
አቶ ዘይኑ ጀማል በፊዚክስ ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተመረቁ በኋላ የደህንነት መስሪያ ቤቱን ተቀላቅለው በኬንያ የደህንነት አታሼ በመሆን በርካታ ስደተኞችን ያስገደሉና ያሳፈኑ መሆናቸውም ነው የሚነገረው።
በደህንነት መስሪያ ቤቱ የሚመራው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች መስሪያ ቤት ከተባበሩት መንግስታት የሚያገኘውን ገንዘብ የሚመዘብረው ለኮንስትራክሽን ከሚውሉ ግብአቶችና ከልዩ ወጭዎች የሚመደበውን ነው።
ይህው መስሪያ ቤት የሕወሃት አባላትን ከኤርትራ የተሰደዱ ናቸው በሚል በርካታ የትግራይ ተወላጆችን በዩ ኤን ኤች ሲ አር አማካኝነት ወደ ውጭ እንደሚልክም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሳውዲ አረቢያ ካላግባብ የባከነው ገንዘብ 100 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 30/2010) በሳውዲ አረቢያ እየተካሄደ ያለው ጸረ ሙስና ዘመቻ ምርመራ ካለአግባብ የባከነው ገንዘብ 100 ቢሊየን ዶላር መሆኑን አጋለጠ።
በሌብነት ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች ቁጥርም 199 መድረሱን የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታውቋል።
ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የተጀመረው ተጠርጣሪ ልኡላንን፣ሚኒስትሮችንና ነጋዴዎችን ኢላማ ያደረገው የጸረ ሙስናው ዘመቻው በ32 አመቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን የተመራ ነው።
በዘመቻው ተጠርጥረው ከተያዙት ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑት ሼህ መሀመድ አላሙዲን እንደሚገኙበት ይታወቃል።
ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ሼህ ሳውድ አል ሞጀብን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው 100 ቢሊየን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በሀገሪቱ በተደራጀ መንገድ በተፈጸመ ዝርፊያ ባለፉት ጥቂት አስርት አመታት ባክኗል ብለዋል።
ዝርፊያ ስለመፈጸሙም ጠንካራና አስተማማኝ መረጃ አለን ብለዋል።
በዝርፊያው የተጠረጠሩት የንጉሳዊ ቤተሰቦችና ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው በሀገሪቱ ያለውን የዕለት ተዕለት የንግድ እንቅስቃሴ እንዳላወከው አስታውቀዋል።
የተጠርጣሪዎቹ የግል የባንክ ተቀማጭ ሂሳብ መዘጋቱንም ተናግረዋል።
እስካሁን 1700 የባንክ ተቀማጭ የሂሳቦች መዘጋታቸውም ታውቋል።
የጸረ ሙስና ኮሚቴውም ወደ ሚቀጥለው የምርመራ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ሕጋዊ ፍቃድ እንዳለው ተናግረዋል።
አቃቢ ሕጉ አክለውም እስካሁን 208 የሚሆኑ ሰዎች ለጥያቄ መቅረባቸውንና ሰባቱ ሳይከሰሱ በነጻ መለቀቃቸውን አስታውቀዋል።
በሐገሪቱ ንጉስ ትዕዛዝ የተዋቀረው የጸረ ሙስና ኮሚቴም ስራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት በተካሄደው ምርመራም 100 ቢሊየን ዶላር በተደራጀ ዘረፋ መባከኑን የሀገሪቱ አቃቢ ህግ ጨምረው ገልጸዋል።
የተጠርጣሪዎቹን የሕግ መብት ለመጠበቅ ሲባልም በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዳቸው ፈጽመውታል ተብሎ የሚጠረጠረውን ወንጀል ግን ከመግለጽ እንቆጠባለን ሲሉ ተናግረዋል አቃቢ ሕጉ።
ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት አንዱ የሆኑት የሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ጉዳይ በኢትዮጵያ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ሲቀጥል የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዝምታን መርተዋል።
የሕወሃት ድምጽ የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ግን ጉዳዩን በተመለከተ ዘገባዎችን ሲያወጣ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ በዲፕሎማሲ መንገድ የሚመጡ መረጃዎችን እየተከታተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከዚህ ውጪ ግን ሳውዳረቢያ ሉአላዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ሌላ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

 

በምንጃር ሾንኮራ ህዝባዊ አመጽ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 29/2010)በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሾንኮራ ህዝባዊ አመጽ ተቀሰቀሰ።–በጨፌ ዶንሳ ትላንት የጀመረው ተቃውሞም ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።
የምንጃር ሸንኮራ ህዝብም የቻይና ቺፑድ ፋብሪካን በማቃጠል ማውደሙ ተገልጿል።
የአማራ ወጣቶችና የኦሮሞ ቄሮዎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ወገራ አንድ የሚሊሺያ ሃላፊ በነጻነት ሃይሎች ታፎኖ መወሰዱ ተሰምቷል።
ምንጃር ሸንኮራ ህዝባዊ አመጹ የተጀመረው ዛሬ ነው። ለ15 ቀናት መብራት ያላገኘው ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ ምሬቱን ለመግለጽ ከበቂ በላይ ምክንያት ነበረው።
ባለፉት 26 ዓመታት በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በተለየ ሁኔታ ግፍና መከራ የደረሰበት አከባቢ ነው ሰሜን ሸዋ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራና በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ሰሜን ሸዋ መድረሱ የማይቀር እንደነበር ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ቆይተዋል።
ለሁለት ሳምንት መብራት ሲያጣ የሚታገሰው አልነበረም። ፈንቅሎ ወጣ። በአቅራቢያ በሚገኘው ጨፌ ዶንሳ ከተማ የተጀመረው ተቃውሞን የምንጃር ሾንኮራ ህዝብ ዛሬ ተቀላቀለው።
ዛሬ አደባባይ የወጣው የምንጃር ሾንኮራ ህዝብ የተጠራቀመውን ብሶትና ቁጣ የገለጸው በተለይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ነው።
ምንጃርና ጨፌ ዶንሳ አንድ ላይ ተነሱ። የአማራና የኦሮሞ ልጆች ስለአንድ ዓላማ ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣታቸውን ነው ከአካባቢው ኢሳት ያነጋገራቸው የገለጹት።
በምንጃር ሾንኮራ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል።
የወረዳ ካቢኔዎች መኖሪያ ቤቶች ላይም ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን አብዛኞቹ ቤቶች መፈራረሳቸው ተገልጿል።
በከተማዋ በሚገኘውና በቻይናውያን ንብረትነት የሚታወቀውን የቺፑድ ፋብሪካ በእሳት በማያያዝ እንዲወድም የተደረገ ሲሆን የፋብሪካው ሰራተኞች ተኩስ ከፍተው ሁለት ወጣቶችን ማቁሰላቸው ታውቋል።
በጨፌ ዶንሳ ከተማ የሚገኙ ቄሮዎች ለሁለተኛ ቀን ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረጉ ነው።
ከሸንኮራ ምንጃር ወጣቶች ጋር በመደዋወልና በመነጋገር ተቃውሞውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
የኦህዴድ ጽ/ቤትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች ወድመዋል። የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ በህዝቡ ላይ ተኩስ መክፈታቸውም ታውቋል።
የቻይና አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክም ከፍተኛ ወድመት ደርሶበታል። የአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሃላፊዎች ወታደሮች እንዲላኩላቸው ጥያቄ ቢያቀርብም ከመንግስት በኩል የተሰጠ መልስ እንዳልነበረ ለማወቅ ተችሏል።
የቻይና ዜጎችን ለማስወጣት ተሽከርካሪዎች የተንቀሳቀሱ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የቻይና ዜጎች ስለመውጣታቸው የታወቀ ነገር የለም።
በጨፌ ዶንሳ የመንግስት አመራሮች በአብዛኛው ለስብሰባ መቀሌ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ህዝቡ ከተማዋን ተቆጣጥሮ እስክምሽት ድረስ ተቃውሞውን በማሰማት መቀጠሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በአማራና በኦሮሞ ወጣቶች ቅንጅት በምንጃር ሸንኮራና ጨፌ ዶንሳ እየተካሄደ ያለው ጸረ መንግስት ተቃውሞ በአስቸኳይ የህወሀት ስርዓት ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቅ እንደሆነም ተገልጿል።
በሌላ በኩል በሰሜን ጎንደር ዞን ወገራ ህዝቡን ትጥቅ ለማስፈታት ዘመቻ ተሰጥቶት የተሰማራ አንድ የሚሊሺያ አመራር በነጻነት ሃይሎች ተማርኮ ወደ በረሃ እንደተወሰደ ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የሚሊሺያ አመራሩ ከነትጥቁ ታፍኖ ወደ በረሃ ከመወሰዱ በፊት ከነጻነት ሃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ያደረገ ሲሆን ረዳቱ ሲቆስል አመራሩ ግን መማረኩ ነው የተገለጸው። የቆሰለው ረዳት ሚሊሺያ ደባርቅ ሆስፒታል መግባቱም ታውቋል።
ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ የሌሎች ታሳሪዎች የባንክ ተቀማጭ ሒሳብ ታገደ
(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 29/2010)የሳውዲ አረቢያ መንግስት ባለፈው ቅዳሜ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ የሌሎች ታሳሪዎችን የባንክ ተቀማጭ ሒሳብ አገደ።
ከእስሩ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ ለአደጋ የተጋለጠው የባለሀብቶቹ ንብረት 33 ቢሊየን ዶላር እንደሚገመትም ከብሉምበርግ ዘገባ መረዳት ተችሏል።
የሼህ መሀመድ አላሙዲን ቃል አቀባይ ከብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ርምጃው በሳውዲ አረቢያ ውስጥ የተገደበና በሌሎች ሀገራት ያላቸውን ንብረት የማይመለከት መሆኑን ገልጸዋል።
ቋሚ መኖሪያቸውን በሳውዳረቢያ ጅዳ ያደረጉት ሼህ መሀመድ አላሙዲን እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ በሳውዳረቢያ ሪያድ በተካሄደው ግሎባል ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ከተገኙ በኋላ መያዛቸውና መታሰራቸውም ተመልክቷል።
ከሳውዲ ባሻገር በሞሮኮ፣በሲውዲንና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመትን ያላቸው ሼህ መሀመድ አላሙዲን የሳውዲው እስራትና እገዳ በሌሎች ሀገራት ኢንቨስትመንታቸው ላይ ተጽእኖ አይኖረውም ሲሉ ቃል አቀባያቸው ቲም ፓንደር ተናግረዋል።
በሳውዲ የተፈጠረውም ሁኔታ የንጉሳውያን ቤተሰቦች የውስጥ ችግር ነው ሲሉ ለብሩምበርግ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የ10 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ሀብት ባለጸጋ በሆኑት በሼህ መሀመድ አላሙዲንና በሌሎች ታሳሪዎች ላይ የተጣለው እገዳ የግል ተቀማጭ ሂሳባቸውን ብቻ የሚመለከት መሆኑንም የሳውዳረቢያው ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
የታሳሪዎቹ ኩባንያ ተቀማጭ ሒሳብ አለመታገዱንና ሕጋዊውን የባንክ ስርአት ተከትለው ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንደሚችሉም ይፋ ሆኗል።
የብሪታኒያው ዴይሊ ሜል ይፋ ያደረገውና በታዋቂው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ወለል ላይ ፍራሽና ብርድልብስ ታድሏቸው የታሰሩት ባለስልጣናት፣ባለሃብቶችና ልኡላን በቁጥር 50 ያህል መሆናቸው ተመልክቷል።
የሳውዳረቢያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ እንደገለጹት ደግሞ ይህ እስራት የመጨረሻው ሳይሆን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን በቀጣይ የሚታሰሩ መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢኮኖሚውን እንደሚያቆመው የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 29/2010)በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢኮኖሚውን እንደሚያቆመው የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ።
ኢትዮ-ቴሌኮም በበኩሉ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ስራ መስራትም ሆነ ብድር መክፈል አልቻልኩም ሲል አስታውቋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለፓርላማው የፋይናንስና በጀት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዳስታወቁት ከወጭ ንግድ እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዝቅተኛ መሆን ሀገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል።
በዚህ መልኩ ከቀጠለና የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ካልተቻለ ኢኮኖሚው ይቆማል ሲሉ መናገራቸውን አዲስ አበባ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።
መንግስት የወጭ ንግድን ማሳደግ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው እያለ የሚገኘው ዝም ብሎ መፈክር አይደለም፣በትክክል የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑ እየታየ ነው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የብር ምንዛሪ ተመን አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ሲደረግም የወጭ ንግድ ዘርፉን ለመጨመር ነው ሲሉ የባንኩ ገዢ ተናግረዋል።
የብር ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ መደረጉ ግን ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም ሲሉም አክለዋል።
በግብርናና ማኑፋክቸሪንግ በተለይም የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንደስትሪ ከፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ እንደመጣ ጥናቶች አመላክተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በተገኙበት የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በውጭ ምንዛሪና ተያያዥ ጉዳዮች ከ15 አመት በፊት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተፈጠረው 29 በመቶ የስራ እድል ከሁለት አመት በፊት በተደረገ ዳሰሳ ወደ 11 በመቶ ዝቅ ብሏል።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ዘርፉ ያደረገው የእሴት ጭመራም ከ7 በመቶ ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች ጥቅምት 27/2010 ለፓርላማው የሳይንስ፣ኮሚኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ የሩብ አመት የእቅድ ክንዋኔያቸውን ሲያቀርቡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተቋሙ ስራውን መስራትም ሆነ ብድር መክፈል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዷለም አድማሴ በአሁን ጊዜ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት መንቀሳቀስ አልቻልንም።
በተግባር ግዥ አቁመናል።በንድፈ ሃሳብ ብቻ ነው ግዥ እያከናወንን የምንገኘው በማለት አቤቱታቸውን አሰምተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በውጭ ምንዛሪ አለማግኘት ምክንያት በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ ብድሮችን መክፈልም ሆነ የራሱን ሂሳብ ማንቀሳቀስ እንዳልቻለ በግልጽ አስቀምጠዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.