አዲስ አበባማ የኗሪዎቿ ናት – መሐመድ አሊ መሐመድ

(አቶ መሐመድ አሊ መሐመድ የቀድሞ የቅንጅት ምክር  ቤት አባል፣ የፓርላማ አባልና ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ባለሞያነት እየሰሩ ያሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው)

ዘንድሮ ተስፋ ሰጭ ከሆኑ ክስተቶች አንዱ የነለማ መገርሳ ስለኢትዮጵያዊነት ማቀንቀንና ከአማራ ወንድሞቻቸው ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር የሄዱበት ርቀት ነው። በዚህ ሂደት አማራው ያሳየው ቅንነት; ጨዋነትና ኦሮሞ ወንድሞቹን የተቀበለበት/ያስተናገደበት ሁኔታ ልብን በፍቅር ሊሰብር የሚችል ነው። በርግጥ ኦሮሞ ወንድሞቻችን ፍቅር ሰንቀው ወደባህር ዳር በመጓዝ ባሳዩት ተነሳሽነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። አማራውም ወንድሞቹን በፍቅርና በክብር በማስተናገድ እንደወትሮው ታላቅነቱን አሳይቷል። በውጤቱም “ፍቅር ያሸንፋል” እንዲሉ ሁለቱም አሸናፊ ሆነው ታይተዋል። ይህ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከሌሎችም ጋር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታችን የፀና ነው።

ይህ ተሰፋ ሰጭና አበረታች ጅምር እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚያሳዩት የጠቅላይነት ዝንባሌ የግንኙነቱን ቀጣይነትና ውጤታማነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው። በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚነሳው የግዛት ባለቤትነት/ይገባኛል ጥያቄ ብዙ አነጋጋሪና አወዛጋቢ መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህ ውዝግብ ደግሞ ለአንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች አመች ሁኔታና ቀዳዳ ሊፈጥር እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው።

ታሪካዊ የግዛት ባለቤትነት/ይገባኛል ጥያቄውን ወደጎን ብንተወው እንኳን; አዲስ አበባ የተገነባችው በማን ዕውቀት; ጉልበትና አንጡራ ሀብት ነው? አሁን ላይስ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ማነው? በከተማዋ የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ላይስ መወሰን ያለበት ማነው? የሚሉት ጥያቄዎች ተጨባጭ ሁኔታዎችን ባገናዘበና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መመርመርና ምላሽ ማግኘት አለባቸው።

እነለማ መገርሳና ደጋፊዎቻቸው የምር በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑና ኢትዮጵያዊያንን አንድ አድርገው ለመምራት የሚያልሙ ከሆነ ለዚያ የሚመጥን አቋምና አመለካከት እንዳላቸው በተጨባጭ ማሳየት አለባቸው። በፖለቲካ ሴራና በግርግር ለመውሰድ ካልሆነ በስተቀር አዲስ አበባ የኗሪዎቿ ናት። ዕጣ ፈንታዋም መወሰን ያለበት በኗሪዎቿ ነው።

ይልቁንስ ልጆቻችንን “ኦሮሚፋ” አስተምሩልን?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.