በቀጣይ ከክልል አመራሮች ወህኒ የሚወርዱ ሰዎች ሳይኖሩ እንደማይቀር ተጠቆመ

BBN

በቀጣይነት ከክልል አመራሮች ወህኒ ሊወረወሩ የሚችሉ ሰዎች ሳይኖሩ እንደማይቀር ምንጮች ጠቆሙ፡፡ በተለይ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የተባለው ቡድን፣ በቀጣይ በክልሎች ከሚነሱ ህዝባዊ ተቃውሞች ጋር በተገናኘ የክልለ አመራሮች በቁጥጥር ስር ሊያውል እንደሚችል የጠቆሙት የመረጃ ምንጮች፣ ምናልባትም በቀጣይ ከኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በቁጥጥር ስር የሚውሉ አመራሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከመረጃዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባለፈው ጊዜ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን ጠብ ተከትሎ፣ የሁለቱ ክልሎች የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ኃይለ ቃል ሲመላለሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይ የሶማሌ ክልሉ የህዝቡ ግንኑነት ኃላፊ በግጭቱ ዙሪያ ይሰጡ የነበሩት መረጃ፣ ከአንድ አመራር የማይጠበቅ እንደሆነ በወቅት ሲገለጽ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታም የፌደራል መንግስቱ መግለጫ እንዲያወጣ አስገድዶት የነበረ ሲሆን፣ በመግለጫውም የሶማሌ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊን በጽኑ ገስጿል፡፡ ፌደራል መንግስቱ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም በዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የሚመራው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቆ ነበር፡፡

አዲስ የተቋቋመው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ከዚህ በኋላ በክልሎች ለሚካሔዱ ሰላማዊ ሰልፎች እና ሰልፎቹን ተከትሎ ለሚመጡት ማንኛውም ዓይነት መዘዞች የክልል አመራሮችን ተጠያቂ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ክልሎች በየግዛታቸው የሚካሔዱ ሰልፎችን እንዴትም አድርገው ማስቆም እንዳለባቸው ያስጠነቀቀው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት፣ ይህን አድርገው በማይገኙ የክልል አመራሮች ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ ዝቷል፡፡ በኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መካከል በነበረው ግጭት ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ የክልል አመራሮች በቅርቡ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉም ራሱን የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት እያለ የሚጠራው ቡድን አስታውቋል፡፡ ይህን ቡድን በዋነኛነት የሚመሩት የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች ማለትም የህወሓት ጄኔራሎች ቢሆኑም፣ ለይስሙላ ያህል ግን የክልል የፖሊስ እና ደህንነት ኃላፊዎች ተካተውበታል፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.