የኦሮሞና የአማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ፋይዳ! (ተቃዋሚዎች ምን ይላሉ?) – አለማየሁ አንበሴ

 የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች አንድነት መድረክ፤ ባለፈው ቅዳሜ በባህር ዳር ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል እንዲህ ዓይነቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሲዘጋጅ፣ በ27 ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነትና ትስስር ላይ ያተኮሩ ጥናቶች በምሁራን የቀረቡ ሲሆን የሁለቱ ክልል ፕሬዚዳንቶች፤ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ የሚያጠነጥኑ፣የአገር ፍቅርና ወኔ ቀስቃሽ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡
ህብረተሰቡን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች፣ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በእጅጉ ያደነቁ ሲሆን የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በኦህዴድና በብአዴን አማካኝነት የተካሄደውን የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች አንድነት   መድረክ በመደገፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ፋይዳው ምንድን ነው? ፖለቲካዊ አንደምታውስ? ቀጣይነት ይኖረው ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

“ፌደራሊዝም ግንብ ሳይሆን ድልድይ መገንባት አለበት”
አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ (የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ)

እንደዚህ ያሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች የሚደገፉ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ እኛ የምንፈልጋቸው ዓይነት ብሄራዊ እርቅ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ብሄራዊ እርቅ ብዙ መገለጫዎችን ያካተተ ጉዳይ ነው፡፡ ላለፉት 26 ዓመታት ከፌደራሊዝሙ ጋር ተያይዞ ሲሰበክ የቆየው የልዩነት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ይህ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፤ እነዚህን ስብከቶች ማለዘብ የሚችልባቸው ዕድሎች ሰፊ ናቸው፡፡ በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ቅራኔ ለመፍጠር ሰፊ ቅስቀሳዎች ይደረጉ ነበር፡፡ እነዚያን በተወሰነ መልኩ ለማለዘብ እድል ይሰጣል። ግን የተሟላ አይሆንም፡፡ መንግስትም እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለፕሮፓጋንዳ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ፕሮፓጋንዳውን ወደ ጎን ትቶ፣ ከልብ ከተሰራበት ግን ውጤታማ ጅምር ነው፡፡
በአሁን ወቅት የፖለቲካውን ሁኔታ ስንመለከት፣ አብዛኛው ነገር ከፌደራል መንግስቱ ወደ ክልሎች እየሄደ ነው፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ አቅም ነበረው፡፡ አሁን ግን ወደ ክልሎች በተወሰነ መልኩ የመሄድ አዝማሚያ ታያል፡፡ በሌላ በኩል በአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ቅራኔ አለ፡፡ አሁን እነዚህ ድርጅቶች እኩልነትንና የሃይል አሰላለፉን ሚዛናዊ ለማድረግ በተወሰነ መልኩ እየሞከሩ ነው፡፡ ከብአዴንና ኦህዴድ ኋላ ሰፊ ህዝብ አለ፡፡ በዚህም በኢህአዴግ ውስጥ ድርሻችን የተመጣጠነ መሆን አለበት የሚለውን ግፊት ለማሳየትም የሠሞኑን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ሊጠቀሙበትም የፈለጉ ይመስላል፡፡ ዞሮ ዞሮ የመጋቢት 2010 ዓ.ም የኢህአዴግ ጉባኤ፣ ይሄን ነገር አንጥሮ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እርግጥ ይሄ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጠራጠርን በማስወገድ ረገድ- መልካም ውጤት ያመጣ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ላለፉት ሁለት አመታት በስፋት በህዝቡ ሲቀርቡ ለነበሩ ጥያቄዎች ግን መፍትሄ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም በዋናነት የህዝቡ ጥያቄ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የህግ የበላይነት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና የሠብአዊ መብት ጥያቄዎች ናቸው እንጂ የፌስቲቫሎች አይደለም፡፡ ሊያለዝብ ይችላል እንጂ ለጥያቄዎች መልስ አይሰጥም፡፡ ችግሮችን የመፍታት እድል የለውም፡፡ አሁንም በህዝቡ የቀረቡ ጥያቄዎች አልተመለሱም – እንዳሉ ነው ናቸው፡፡
በተለምዶ ፌዴራሊዝም በህዝቦች መካከል ግምብ ሳይሆን ድልድይ ነው መገንባት ያለበት፤ ነገር ግን በኛ ሀገር በተግባር ሆኖ የታየው ድልድይ ሳይሆን ግምብ ሲገነባ ነው፡፡ ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፌደራል ስርአት፤ ሀገርን ሳይሆን የአንድ አካባቢ ጥቅምና አስተሳሰብን እያጎመራ ነው የነበረው፡፡ እንዲህ ያለው መድረክ ተጠናክሮ ከቀጠለ ሀገራዊ ስሜትን እያዳበረ ይሄዳል፡፡ ይሄ ግን ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መሆን የለበትም፡፡ ባህር ዳር ላይ “የኦሮሚያና የአማራ ህዝብ ለህዝብ” መድረክ እየተካሄደ ባለበት ወቅት በተቃራኒው ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተመደቡ ተማሪዎች በክልላቸው እንደገና ተመድበዋል፡፡ ይሄ ሌላው ተቃርኖ ነው፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ከልብ መታሰብ አለበት ባይ ነኝ፡፡

——–

“ህዝቡ፤ ፍቅርና አንድነትን ነው የሚፈልገው”
ኢ/ር ዘለቀ ረዲ (ፖለቲከኛ)

ይሄ የህዝብ ለህዝብ መድረክ መዘጋጀቱ የፈጠረውን ቅቡልነት ስመለከት፣ ከዚህ በፊት ለበርካታ ዓመታት በከፍተኛ በጀት በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ የፈንጠዚያና የፌሽታ በአል እንጂ ለውጥ እንዳላመጣ የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡
አሁን በተለይ በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ግንኙነት ስንመለከት ደግሞ ከዚህ ቀደም ህዝቡ በካድሬዎች ተወጥሮ ተይዞ ከእርስ በእርስ ፍቅርና መተሳሰብ ተገልሎ ያለው በፍላጎቱ ሳይሆን ተገዶ እንደነበር ነው የምንረዳው። ህዝቡ ፍቅርና አንድነትን እንደሚፈልግ ነው የምንገነዘበው፡፡ ይሄ ግን በካድሬዎቹና በጥላቻ ፕሮፓጋንዳዎች ተነጥቆ ነበር ማለት ነው፡፡ አሁን የሄዱበት መንገድን ሥርአቱ የበለጠ አበልፅጎ የሚጠቀምበት ከሆነ ኢትዮጵያም የምትለወጥበት፣ የምታድግበትና ህዝቡ በግፊት ሳይሆን በየኔነት ስሜት በፍቅር የሚሰራበት አጋጣሚ ይፈጠራል። እንደ‘ኔ ሀሳብ አሁን በአጋጣሚ የህዝቡን ፍላጎት አውቀውታል፤ ይሄን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ሐገሩን የሚወድ ዜጋ የማፍራት እድሉ እየተፈጠረ ያለ ይመስላል፡፡
አሁን በሀገራችን በስፋት ህውኃትንና የትግራይን ህዝብ ቀላቅሎ፣ አንድ አድርጎ የማየት ነገር አለ። ይሄ የመጣው ደግሞ ራሱ ህውኃት፣ ”የትግራይ ህዝብ ከኔ የተለየ ነው” በሚለው ላይ ተገቢውን ሥራ ስላልሰራ ነው፡፡ ኦህዴድና ብአዴን ግን የህዝብ ሥራ ለመስራት ሲሞክሩ አይተናቸዋል። ቀድሞ ኦህዴድን ህዝብ አይደግፈውም ነበር። ነገር ግን ራሱን ለለውጥ ለማዘጋጀት በሚሞክሩ ተቃውሞ ቀሰቅሰው የሚመሩ የማህበራዊ ድረ ገፅ አክቲቪስቶች ሳይቀሩ እየደገፉት ነው፡፡ በፍጥነት ነው ወደ ህዝብ የገባው፡፡ በዚህ ሂደት ትልቅ እድል ያለው ይመስለኛል፡፡ ኦህዴድ ወይም ብአዴን ይሄን እድል የሚጠቀሙበት ከሆነ ብዙ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ ህዝቡን በዚህ መንገድ ነው መያዝ ያለባቸው፡፡ የህዝብ ስሜትን ማዳመጥ አለባቸው። ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፤”አድዋ ላይ የኦሮሞ ህዝብ ሲዋጋ ተከፍሎት ሳይሆን የሀገር ፍቅር አሸንፎት” እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ይሄ ለህዝቡ ዋጋ መስጠት ነው፤ ትልቅ አስተሳሰብ ነው፡፡ እኔ እንዳጋጣሚ በመፅሃፌ፤ እነዚህን ሂደቶች ጠቁሜ ነበር፡፡ አሁን እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡ ይሄ እንዴት አስደሳች እንደሚሆን ማንም ያውቀዋል፡፡ ሁሉም ሀገሩን ይወዳል፡፡ ይሄን የሰማ ደግሞ ይደሰታል፡፡ ስለዚህ የለውጥ ሽታ እንዳለው በመረዳት ሰው ተስፋ ያደርጋል፡፡
ፌደራሊዝም በባህሪው ያልተማከለ አስተዳደር ነው፡፡ በዚህ አስተዳደር አካባቢህን እየጠቀስክ፣ ሀገርህን ነው አስበህ የምትንቀሳቀሰው፡፡ ከዚህ አንፃር የኦህዴድ ደጋፊ አይደለሁም፤ ግን አሁን የጀመረውን ዓላማ ሁሉም ሰው ቢያግዘው ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ይህ ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያን በፍቅር፣ ከአምባገነኖች እንንጠቃት ነው የምለው፡፡ አሁን ወጣቱ መለያየት ጥቅም እንደሌለው አውቋል፡፡ መንግስትም ቢሆን ህዝቡ ቢፋቀር ነው የሚጠቅመው፡፡ ይሄን አስቦ ነው መንቀሳቀስ ያለበት፡፡ ከዚህ በኋላ የሚነሱ ግጭቶችን፣ ህዝቡ ራሱ ነው ሊከላከላቸው የሚችለው፡፡ ህዝቡ አንድነትን አጥብቆ ይፈልጋል፡፡ ይሄን አስተውለው የመንግስት አካላት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለባቸው፡፡ የትግራይ ህዝብ አንድነትን እንደሚፈልግ፣ ከሰሞኑ መቀሌ ላይ ባደረገው ሰልፍ አሳይቷል፡፡

———–

“ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ማስተማር ያስፈልጋል”
አቶ ቶሎሣ ተስፋዬ (የኦህኮ ሊቀ መንበር)

በኔ እምነት እንዲህ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብሄሮችና ህዝቦች ለረጅም ዘመናት በማይነጣጠሉበት ሁኔታ አብረው ተዋደው ተከባብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ይሄ መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው፡፡ አሁን የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ የበለጠ ይሄን የህዝቡን መተሳሰብ ያጠናክራል፡፡ ከዚህ በፊትም ቢሆን የነበረው ችግር በፌደራሊዝሙ ላይ ብዥታዎች ከመኖራቸው የመነጨ ነው፡፡ የመገፋፋት ፖለቲካ ነበር ሲካሄድ የቆየው፡፡ ይህን ሁኔታ በመጠቀምም፣ ጥቂቶች ካድሬዎች፣ ህዝቡን የመለያየት ስራ ውስጥ ተጠምደው ነው  የኖሩት፡፡
የህዝብን አንድነት ከማጠናከር ይልቅ ልዩነቱን አጉልተው እያወጡ፣ ህዝቡን እርስ በእርስ እያጋጩ፣ ብዙ ክፍተቶች ሲፈጥሩ ነው የኖሩት። ይህን ለማከም የተጀመረው መንገድ የሚቀጥል ከሆነ መልካም ውጤት ያመጣል፡፡ የኛ ችግር የሚመነጨው ከፌደራሊዝሙ አለመጠናከር ነው፡፡ አንድ የጋራ ሀገርን ማዕከል አድርጎ አልተጠናከረም። ከዚህ በኋላ መሬት ላይ ተወርዶ ከተሰራ ጅምሩ ጥሩ ውጤት ያመጣል፡፡ ነገር ግን ይሄ ሂደት የህዝቡን ፖለቲካዊ ጥያቄ ይመልሳል ማለት አይደለም፡፡ አሁንም የህዝቡን ጥያቄ በጊዜ መመለስ ያስፈልጋል። አለበለዚያ የተቀበረ ቦንብ ነው የሚሆነው፡፡ ህዝቡ እርስ በእርሱ ችግር የለበትም፡፡ ችግሩ ያለው በልዩነታችን ውስጥ አንድነትን መሬት የማስያዝ ሁኔታ ባለመሰራቱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሥራ አጥነት፣ የሀብት ክፍፍል፣ የፍትህ ጉዳይ ከዚህ ጋር አይያያዝም፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው፡፡ መንግስት መመለስ አለበት፡፡ በአንድነት አስተሳሰብ ውስጥ ተድበስብሶ የሚቀር አይደለም፡፡
እኛ እንደ ፓርቲም እንደ ግለሰብም በፌደራሊዝም ውስጥ አንድነትን እንደግፋለን፡፡ ተጠናክሮም እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ ወጣቶችን ወደ ስልጣን የማምጣት ሂደትም መልካም ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይሄን ጅምር መደገፍ አለበት፡፡ ለትውልድም መተላለፍ አለበት፡፡ በትምህርት ቤት ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን የበለጠ የማሰባሰብያ ማዕከል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

——–

“የህብረተሰቡ መነሳሳት ወደ ሃቀኛ ለውጥ ሊወስደን ይችላል”
አቶ አምዶም ገ/ሥላሴ (የአረና ሥራ አስፈፃሚ)

እንደ‘ኔ በህውኃትና በብአዴን አጋፋሪነት በመቀሌ የተካሄደው መድረክ የህዝብ ለህዝብ ነበር ለማለት እቸገራለሁ፡፡ በአብዛኛው የካድሬዎች ግንኙነት ነው የነበረው፡፡ ብአዴንና ህውኃት ለነበረባቸው ፖለቲካዊ ፍጥጫ፣ እንደ እርቅ መድረክነት ነው የተጠቀሙበት እንጂ ለህብረተሰቡ እምብዛም ፋይዳ ያለው አልነበረም፡፡ ምናልባት በካድሬዎች መካከል መተማመን ይፈጥርላቸው ይሆናል፡፡ ያ ሁሉ ሰው ሞቶና ተፈናቅሎ፣ ተጎጂዎች ካሳ ማግኘት ሲገባቸው እርቅ በሚል ጉዳያቸው ተሸፋፍኖ እንዲቀር የሚያደርግ ነው የሚል ተቃውሞ አጋጥሞታል፡፡
የብአዴንና የኦህዴድ ግንኙነትን ስንመለከት ደግሞ ሁለቱም ድርጅቶች የህውኃት የበላይነት አለ የሚለውን እያስወገድነው ነው የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ የተወጠነ እንቅስቃሴ ይመስላል፡፡ ግን በዚያው ልክ ህብረተሰቡንም ለማሳተፍ ሞክረዋል። ይህ ደግሞ ነገሮችን ሊያረጋጋ ይችላል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፡፡ እንቅስቃሴው የማረጋጋት ሚና ቢኖረውም የህዝቡን ተጨባጭ የለውጥ ፍላጎት ግን አያዳፍነውም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ ነው፡፡ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱለት ይፈልጋል፡፡ በኦሮሚያ አሁን በአክቲቪስቶች በኩል ሁኔታዎች እንዲረጋጉ የመፈለግ አዝማሚያ ይታያል፤ በአማራ ክልልም እንደዚያው ነው ነገር ግን ይሄ ዘላቂ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ የህብረተሰቡ ጥያቄ ካልተፈታና ተጨባጭ ለውጥ ካልመጣ ጥያቄው ይቀጥላል፡፡ ኢህአዴግ በባህሪው ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፡፡
አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ይሄን ፍላጎት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ብቻውን አያስቀረውም፡፡ የህብረተሰቡ መነሳሳት ወደ ሃቀኛ ለውጥ ሊወስደን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “እምነቴ፣ ፖሊሲዬ የሚለወጠው በመቃብሬ ላዬ ነው” በማለት የሚታወቀው ኢህአዴግም፤ በፌስቡክ በሚመራ እንቅስቃሴ በተፈጠረ ጫና ሳይወድ በግዱ ወደ ለውጥ እያመራ ነው፡፡

———-

“ህዝብን ለማቀራረብ ማሰባቸው የሚደገፍ ነው”
አቶ ጌታነህ ባልቻ (የሰማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)

ይሄ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መልካም ነገሮች አሉት፡፡ በተለይ በዘር፣ በጎሳ የተከፋፈለውንና የሚሰጋው የዘር ግጭትን፣ ከማለዘብ አንፃር ከፍ ያለ ዋጋ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ በተለይ በአማራና በኦሮሞ ህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከርን እኛም እንደግፈዋለን፡፡ ምንም እንኳ ኦህዴድና ብአዴን፤ ሁለቱን ህዝቦች ይወክሏቸዋል የሚል እምነት ባይኖረንም መልካም ለውጥ ነው ብለን እንቀበላለን፡፡ በጋራ ህዝብን ለማቀራረብ ማሰባቸው የሚደገፍ ነው፡፡ መልካም ጅማሮ ነው፡፡
ነገር ግን ይሄንና ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን አንድ አድርጎ መመልከት አይቻልም፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፡፡ ህዝቡ የፍትህ፣ የእኩልነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይሄ ጥያቄ በራሱ መንገድ መመለስ ነው ያለበት፡፡ ኦህዴድም ብአዴንም ራሳቸውን ችለው፣ የህዝቡን ጥያቄ ለመስማት መፈለጋቸውን ማየታችን መልካም ነው። በሁለቱ ክልሎች መካከል ይህ አይነት ግንኙነት መጀመሩ ኢትዮጵያን ያጠናክራል፤ የኢትዮጵያዊነት መንፈስን ያዳብራል፡፡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረውን የጥርጣሬ ግንብ ይንዳል፡፡ ሁልጊዜ ሃውልት በመትከል ጭምር ሁለቱን አካላት ታሪካዊ ጠላት የማስመሰሉ ነገር ውሃ እየበላው የመጣ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ከጥቂት አመታት በፊት ከጉራፈርዳ አማራዎች በተፈናቀሉ ጊዜ፣ “ደን ሊጨፈጭፉ ሲሉ ተፈናቀሉ” ብሎ የሚናገር መሪ ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ተቀይሮ ችግር የተፈጠረበት ቦታ ሄደው የሚመለከቱ ባለስልጣናትን ማየታችን በራሱ ትልቅ እምርታ ነው፡፡ ሁለቱን ክልሎች የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች ዋስትናቸው የሚመሩት ህዝብ ብቻ መሆኑን አሁንም መገንዘብ አለባቸው። ከእጅ አዙር አገዛዝ አሁንም ራሳቸውን ማላቀቅ አለባቸው፡፡ ራሳችን ህዝባችንን መምራት አለብን የሚለውን አስተሳሰብ ማጠናከር አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ ለነገሩ ያላቸው ብቸኛ ምርጫም ይኸው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከህዝቡ ወግነው ታሪክ ሰርተው ማለፍ ብቻ ነው ምርጫቸው፡፡ ከተንሸራተቱ ህዝቡም ሆነ እጅ አዙር ገዥው በቀላሉ አይለቃቸውም፡፡ ለእኔ አሁን ያሉበት ደረጃ የህዝቡን ፍላጎት የተገነዘቡበት ይመስለኛል፡፡ በተደጋጋሚ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት የሚሰጧቸውን ሃሳቦች ስሰማ፣ ለውጥ እየደፈሩ መምጣታቸውን እገነዘባለሁ፡፡ ወደ ኋላም ይመለሳሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ እርግጥ ነው ብዙ የኦሮሞ ልጆች፤የፍትህና ዲሞክራሲ ጥያቄን በማንሳታቸው በየእስር ቤቶቹ ይገኛሉ፡፡ ለዚያ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ ደግሞ ለወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር፤ ከክልሉ አልፎ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ ጀምሯል፡፡ ወደፊት ደግሞ አፍሪካዊ አስተሳሰብን ይይዛል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነ አቶ ለማ መገርሳ፤ዕድላቸው ከህዝቡ ጋር መወገን ነው፡፡ እሳቸውም ይሄን አቅጣጫ ያዩት ይመስለኛል፡፡ ይሄ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.