“እኛም ስለ ሀገር አንድነት እናስባለን፤ እንጨነቃለን” አቶ ተመስገን ዘውዴ (ፖለቲከኛ)

*የምርጫ ሥርአቱ ይቀየር ሳይሆን ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ይሁን ነው ያልነው
*የፌደራል መንግስቱ፣ በክልሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም
*የህዝቡ ጥያቄ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እውቀትም በላይ ነበር ማለት ይቻላል
*አንቀፅ 39 በተግባር የማይተረጎም ከሆነ፣ በህገ መንግስቱ ውስጥ ምን ያደርጋል?
*የኦሮሞና አማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚደገፍ ነው

የቀድሞ የአንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር እንዲሁም የፓርላማ አባል የነበሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶተመስገን ዘውዴ፤በሃገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ፣ በፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣በፓርቲዎች ድርድር፣እንዲሁም የአገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

 

ለረጅም ጊዜ ከሚዲያው ጠፍተው ነው የከረሙት፡፡ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
የተለያዩ ገፅታዎች ናቸው ያሉት፡፡ እኔን በተለይ የሚያሳስበኝ እየደረሰ ያለው የዜጎች ሞትና መፈናቀል ነው፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች እየደረሰ ያለው የዜጎች መፈናቀል፣ የህይወት መውደምና የንብረት መጥፋት እጅግ አሳሳቢና አሳዛኝ ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች፣ ከገዥው ፓርቲ የሚሰጡ መልሶች በራሳቸው በጣም ያሳስበኛል፡፡ ገዥው ፓርቲ ከራሱ ውጪ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል ብሎ አያስብም፡፡ እኛ ሰላምና ዲሞክራሲን እንፈልጋለን። ሀገሪቱ የህግ የበላይነት ያለባት ሀገር እንድትሆን እንሻለን፡፡ ካድሬዎች በህዝብ መካከል የእርስ በእርስ ግጭት እየፈጠሩ ለዘመናት በአንድነትና በአብሮነት የኖረን ህዝብ በማጣላት፣ ሀገሪቱ ወዳልተረጋጋና አደገኛ የፖለቲካ ደረጃ ላይ በመድረሷ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ከእንግዲህ ዳር ቆመን ለመመልከት አንችልም፡፡ እኛም ለሀገራችን ይበጃል የምንለው ሃሳብ አለን፡፡ ይሄን ሃሳባችንን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማድረስ እየተደራጀን ቆይተናል። ህዝብ የሰላም ህይወት የሚመራበትን መንገድ ለማፈላለግ፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ጀምረናል።
በሀገሪቱ ተቃውሞዎች ወደ አደባባይ ወጥተው፣ የሰው ህይወት መጥፋት ሲጀምር፣ በርካታ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች— ለሀገር ይበጃል ያሉትን የመፍትሄ ሀሳብ ሲሰነዝሩ ነበር … በእርስዎ ግምገማ ገዥው ፓርቲ  ምን ያህሉን ሀሳብ ተቀብሎ ተግብሯል?
ገዥው ፓርቲ በጣም ጠባብና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ሲያስቀምጥ አይተናል፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑ ወጣቶችን እስር ቤት አቆይቶ ኋላም ቲ-ሸርት አልብሎ “አይደገምም!” ብሎ ጥያቄያቸውን ከመመለስ ይልቅ በጣም ዝቅተኛ በሆነ መፍትሄ መረጋጋትን አመጣለሁ ብሎ ነበር። ግን ውጤት አላመጣም፤ በእንዲህ ያለ ጠባብ አስተሳሰብ ልክ የተሰፋ ገዥ ፓርቲ፤ ከሌሎች ስለ ሀገራቸው በስፋትና በጥልቀት ከሚያስቡ አካላት የሚመጣ ሃሳብን መቀበል አይችልም፡፡ በተግባር ያየነውም ከሱ ጠባብ ሀሳብ ውጪ፣ ሌላ የተለየ ሃሳብ እንዲኖር እንደማይፈልግ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የምሁራንንም ሆነ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አካላትን ሃሳብ አላምጦ ይቀበላል፤ተቀብሎም ይተገብራል ማለት አይቻልም፡፡ እሱም እስካሁን አላደረገውም፡፡ አንድ አይነት መዝሙር ብቻ ከሚዘምሩ ካድሬዎች የሚመጣ መልስ መፍትሄ አይሆንም፡፡ እንደማይሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባየነው ተቃውሞ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ገዥው ፓርቲ የፈጠራቸው ሳይሆን ለህዝቡ ታማኝ የሆኑ ተቃዋሚዎች፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በማስተካከል ረገድሉ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ገዥው ፓርቲ ሚዲያውን በራሱ አስተሳሰብ ብቻ አንቆ ይዞ የተለዩ አመለካከቶችና መፍትሄዎች እንዳይንፀባረቁ አድርጓል፡፡ ስለዚህ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ችግር ሁነኛ፣ ለየት ያለ መፍትሄ ሲቀርብ፣ ተመልክተን አናውቅም፡፡ ይህ ህዝቡ የሚፈልገው ለየት ያለ ሀሳብ እስካልመጣ ድረስ የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግር መፍትሄ አያገኝም፡፡ መፍትሄው የአስተሳሰቦችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች መበራከት ነው፡፡ የተለየ አመለካከት ማቅረብ ነውር በሆነበት አገር ውስጥ ሆነን፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ተገኝቷል ማለት አይቻልም፡፡
መንግስት፤ በሂደት በጥልቀት እየታደሰ፣ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ ይገልፃል፡፡ ከዚህ አንፃር የህዝቡን ጥያቄ ምን ያህል ተረድቶ ምላሽ መስጠት ጀምሯል ብለው ያስባሉ?
በዋናነት ህዝብ እየጠየቀ ያለው የነፃነት ጥያቄ ነው፡፡
የነፃነት ጥያቄ ሲባል ምን ማለት ነው?\

የነፃነት ጥያቄ ስንል የራሱን ህይወት የሚመራበት፣ ባህሉን ቋንቋውን የሚያስከብርበት፣ ከገዥ ፓርቲ ረጅም እጅ የሚገላገልበትና ራሱን በራስ የማስተዳደር ሂደቱ በራሱ ውሳኔ የሚቀጥልበትን መንገድ ነው—- እየጠየቀ ያለው ማለታችን ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ  የፌደራል ስርአት ነው ያለን ቢልም ህዝብ እንደ ህዝብነቱ ራሱን እንዲያስተዳድር ሙሉ ለሙሉ ነጻነት አላገኘም፡፡ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በስውር ጣልቃ እየገቡ፣ ሲረብሹት ነው የኖሩት፡፡ አንዱን ጎሳ ከአንዱ ጎሳ በማጋጨትም ቅራኔዎችን በመፍጠርና በማባባስ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ በፌደራል ስርአት ውስጥ የፌደራል መንግስቱ አባላት የፌደራል መንግስቱ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ቆጥረው ይሰጡታል እንጂ የፌደራል መንግስቱ ለክልሎች ይሄን አድርጉ ብሎ አያዝም፡፡ ስልጣን የክልሎች ነው፡፡ እነዚህ ክልሎች ደግሞ መንግስታት ናቸው። ይሄንን ተረድቶ የፌደራል መንግስቱ በውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ አለበት፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ፈፅሞ ትክክለኛውን የፌደራል ስርአት አያንፀባርቅም፡፡ አሁን የሚታየው በክልሎች መካከል ያለው የእርስ በእርስ ግጭትም ከዚሁ ችግር የመነጨ ነው፡፡ ትልቁ ስልጣን የክልሎች መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይሄ እስካልተደረገ ድረስ እነዚህ በየጊዜው የሚፈነዱ ችግሮችን መቋቋምና ማስቆም አይቻልም፡፡ ያለፉት ሁለት ዓመታት የተቃውሞዎች መደጋገም ከዚሁ የተነሳ ነው፡፡

በአሁን ወቅት ያለው የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግር፣ “ህገ መንግስታዊ ማሻሻያና ፍተሻ የሚያስፈልገው ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

በትክክል በአሁኑ ወቅት ላሉ ፖለቲካዊ ችግሮች፣ ህገ መንግስቱን ፈትሾ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ህገ መንግስቱን አይነኬ አድርጎ መቀመጥ ችግሮችን የበለጠ ማወሳሰብ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ አንቀፅ 39 “የመገንጠል መብትን” ይፈቅዳል ግን በተግባር የማይተረጎም ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ጥያቄ ሲነሳበትና የሰው ህይወት ሲገበርበት ነው የኖረው፡፡ በተግባር የማይተረጎም ከሆነ በህገ መንግስቱ ውስጥ ምን ያደርጋል? ለምን ይሄ ውይይት አይደረግበትም። በእኔ አመለካከት፤ እንዲህ ያለው የመገንጠል መብት፤ አስቀድሞም በህገ መንግስቱ ሊካተት አይገባውም ነበር፡፡ ከሁለት መቶ እና ከመቶ አመት በላይ በስልጣኔ የገሰገሱ ሀገሮች እንኳን ይሄን ሊፈቅዱ እንደማይችሉ፣ በስፔን ከሰሞኑ ያስተዋልነው ማሳያ ነው፡፡ የእኛ ህገ መንግስት ግን “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላህ ግፋው” አይነት ሆኖ ነው፤ አስቸጋሪ ፖለቲካዊ ክርክሮችና ንትርኮችን እየፈጠረ ያለው፡፡ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል እያወቁ፣ ይሄን አንቀፅ ማካተታቸው፣ አሁን በሀገሪቱ ላለው የህዝብ ግራ መጋባት ትልቅ አስተዋኦ አለው፡፡ ስለዚህ ይሄም ሆነ ሌላው የህገ መንግስቱ አንቀፆች፣ ለህዝብ ውይይት ቀርበው፣ መፈተሸና ማሻሻያ የሚስፈልግ ከሆነም መሻሻል አለባቸው፡፡

ከሰሞኑ በክልል መንግስታት የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮች፣ ፖለቲካዊ አንድምታና ፋይዳ ምንድን ነው?

እንግዲህ አስተውለን ከተመለከትን ሁልጊዜ በአንድ ጉዳይ ላይ ተነሳሽነት የሚመጣው ከኢህአዴግ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከሌላው የሚመጣው ተቀባይነት የለውም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ተነሳሽነቶች ከህዝቡ እንዲመጡ ነው መደረግ ያለበት፡፡ ገዥው ፓርቲ የመረጣቸው ግለሰቦች አይደሉም የህዝብ ግንኙነትን ሊያመጡ የሚችሉት፡፡ ህዝቡ ራሱ የመረጣቸው ሰዎች ናቸው ይሄን ሊያደርጉ የሚገባቸው፡፡ በእርግጥ የሚደረገው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መልካም ነው፡፡ የሚደገፍ ነው፡፡ ክልል ለክልል ተገናኝተው ሃሳብ መለዋወጣቸው ጥሩ ነው። ግን ይሄ ሲሆን ሂደቶቹ የሚከናወኑት በአዛዥና ታዛዥ ሰንሰለት መሆን የለበት፡፡ መምጣት ያለበት በቀጥታ ከህዝቡ ነው እንጂ ከላይ መሆን የለበትም። ካድሬዎች የሚያመነጩት ሃሳብማ እንደማይሰራ አይተናል፡፡ ትልቁ ነገር ለህዝብ ነፃነት መስጠት ነው፡፡ ነፃነት ሳይኖረው ከላይ ከላይ በተቀባ መልኩ እንዲህ ያሉ ኩነቶችን ማድረጉ፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ አይሆንም፡፡ የሚቀባባ ነገር መቅረት አለበት፡፡ አሁን ጊዜው የሚፈቅደው አይደለም፡፡
ሌላው መንግስት፤ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግር መፍትሄ ብሎ የሚጠቅሰው፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከፓርቲዎች ጋር የሚያደርገውን ድርድር ነው፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? ድርድር ሲባል እኮ ተመጣጣኝ ኃይሎች ያስፈልጋሉ። ድርድር የሚደረገው በሁለት እኩል ወይም ተመጣጣኝ ደረጃ ላይ ባሉ ኃይሎች መካከል ነው። ታዲያ የትኛው ፓርቲ ነው፣ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚመጣጠነው? ባለቤቱና ልጆቹ እንኳ ፖለቲከኛ መሆኑን በቅጡ የማያውቁለትን አይነት ሰው በፓርቲ ስም ሰብስቦ እየተደራደርኩ ነው ማለት ቀልድ ነው። ኢህአዴግም ይሄን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እውነት ድርድሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲጠቅም ከተፈለገ በጥቂቱም ቢሆን በእግራቸው ከቆሙ ፓርቲዎች ጋር ነው መደረግ ያለበት፡፡ እንደ ሠማያዊ፣ መድረክ፣ ኢዴፓ አይነት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ካገኙና በራሳቸው ከቆሙ ፓርቲዎች ጋር ነው መደራደርም የሚገባው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፓርቲዎች ይብዛም ይነስም የሚከተላቸው ሰፊ ህዝብ አለ፡፡
በድርድሩ የምርጫ ስርአቱ ከአብላጫ ወደ ቅይጥ (አብላጫ ተመጣጣኝ) ተቀይሯል ይሄስ ፖለቲካዊ ፋይዳው ምን ያህል ነው?
እኛም ሆንን ህዝቡ ስንጠይቅ የቆየነው’ኮ የምርጫ ስርአቱ ይቀየር የሚል አይደለም፡፡ ነፃ ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ይደረግ ነው ያልነው። አሁን የተደረገው ለኢህአዴግ ገፅታ ለመገንባት የሚያስችል ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ መቶ በመቶ ምርጫ አሸንፌያለሁ ካለ በኋላ ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ተፅዕኖ እያጋጠመው ነው፡፡ ይሄን ስህተቱን ወዲያው ማረም አልቻለም፡፡ ምናልባት ተመጣጣኝ ብናደርገው፣ የተወሰኑ ተቃዋሚዎች ፓርላማ ሊገቡ ይችላሉ በሚል ግምት ነው ይሄን ያመጣው፡፡ የራሱን ገፅታ ለማሻሻል አስቦ ያመጣው ሃሣብ ነው፡፡ አስቀድሞ ለማሻሻል ያቀደውን ነው አጋር ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሰብስቦ፣ “ከእነሱ ጋር ተመካክሬ” የሚል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየሞከረ ያለው፡፡ እነዚህ አብረውት እየተደራደሩ ያሉ ፓርቲዎች፣ የተለወጠውን የምርጫ ስርአት ዘላቂ ጠቀሜታና ጉዳት በቅጡ አያውቁትም፡፡ ዝም ብለው እጨብጭበው ነው ያፀደቁለት፡፡ አንድ ኢትዮጵያ አይነት ሃገር፣ ሁለት የምርጫ ሥርአትን በአንድ ጊዜ ማስፈፀም የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ ኢህአዴግ እነማን በተመጣጣኝ ውክልና ፓርላማ እንደሚገቡ ያውቃል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት የተቃዋሚዎች ጥያቄ የነበረው የምርጫ ሥርአቱ ይቀየር ሳይሆን ኮሮጆ አትገልብጡብን፣ ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ይሁን — የሚል ነው፡፡ ተመጣጣኝ አድርጉልን የሚል አይደለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ጉዳይ የኢህአዴግን ገፅታ ለመገንባት ሆነ ተብሎ የተቀመረ ነው፡፡ የሚያሣዝነው ደግሞ ተቃዋሚዎቹ ይሄን ነገር በትክክል የተገነዘቡት አለመሆኑ ነው፡፡
እርስዎ ፓርላማ በነበሩ ወቅት ጠንካራ ክርክሮችን ያቀርቡ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በቅርቡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ባወጣው የጥናት ሪፖርት፤”ሥራ አስፈፃሚው ከፓርላማው በላይ ሆኗል፤ ፓርላማው ሥራ አስፈፃሚውን የመቆጣጠር አቅም አጥቷል” ይላል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ግምገማ ምን ይመስላል?
ፓርላማ ውስጥ እኛ በነበርንበት ጊዜ 13 ኮሚቴዎች ነበሩ፡፡ ከ13ቱ አንደኛውን ያውም የመንግስት ወጪ ቁጥጥር የሚመራው ተቃዋሚ ነበር፡፡ ነገር ግን ምን ተጨባጭ አቅም አልነበረውም። በተፅዕኖ ስር የወደቀ ነበር፡፡፡ ማንም ሃሳቡን አይቀበልም፡፡ ያም ሆኖ ፓርላማው ትንሽ ህይወት የነበረው እኛ በነበርንበት ወቅት ነው። የመንግስት አስፈፃሚ ተቋማትን የመቆጣጠር ሙሉ አቅም የነበረው ቋሚ ኮሚቴ አልነበረም፡፡ እኛ በምትሰጠን ጥቂት ደቂቃም ብትሆን ነገሮችን ለመሞገት ሞክረናል ፤ሆኖም ግን ውስጥ ገብተን በሚገባ ለመፈተሸ አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ነው ያለው። ለምሣሌ ኦዲተር ጀነራሉ፤ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በበጀት ጉድለት ሥራቸውን እንደማያከናወኑ ገልፆ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ መስሪያ ቤቶች ይሄን ችግር እንዲያስተካክሉ የተደረገ ጥረት የለም፡፡ እስካሁንም በበጁት ጉድለት ነው እየተመሩ ያሉት። አንዱ የፓርላማ ተግባር የመንግስትን አስፈፃሚ መቆጣጠር ቢሆንም በዚህ ፓርላማ ታሪክ ግን ይሄ ተግባር ተከናውኖ አያውቅም፡፡ ይሄ ቢደረግ ኖሮ ዛሬ የምናየው ችግር ሁሉ ባልተፈጠረ ነበር፡፡
በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ህዝቡ የተለያዩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበራቸው ሚና እና ድርሻ ምን ያህል ነው?
ይሄ በስፋት ልንመለከተው የሚገባ ነው፡፡ የህዝቡ ጥያቄ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕውቀትም በላይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ኢህአዴግ እነዚህን ፓርቲዎች ሰብስቦ አብሯቸው ሲደራደርም በማያወቁት ጉዳይ ነው እያነጋገራቸው ያለው። እነሱ ያልነበሩበትን ነገር ነው በህዝብ ስም እየተነጋገሩ ያሉት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝቡ ምን እያካሄደ እንደነበረ ምንም አያውቁም፡፡ ምክንያቱም በጉዳዩ አልነበሩበትም፡፡ ከመጀመሪያውም ህዝባዊ መሠረት ስለሌላቸው፣ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አልተገነዘቡም፡፡ ከጥቂቶቹ በስተቀር፡፡ ለምሣሌ ሠማያዊ፣ መድረክ… መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሠማያዊ ፓርቲ፤ የገዥው ፓርቲ ጫና ቢኖርበትም በተቻለ አቅም ቀበሌ ድረስ ወርዶ ሂደቱን ይከታተል ነበር፡፡ እነዚህ ተደራዳሪ የተባሉ ፓርቲዎች ግን በማያወቁት ጉዳይ ነው፣ እየተነጋገሩና በፊርማቸው እያፀደቁ ያሉት፡፡
ሃገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ የመውጫ መንገዶቹ ምንድን ናቸው?
እኔ እራሴ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ አስባለሁ፤ብዙ እጨነቃለሁ፡፡ የፖለቲካ ጥያቄው በእርግጥም ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የሃገራችንን ችግር ራሳችን መፍታት አለብን፡፡ የውጭዎቹ ሰዎች ዘለቄታዊ መፍትሄ አይሰጡንም፡፡ የፖለቲካው ጉዳይ እኛንም ይመለከተናል፡፡ የተወከልንባቸው ፓርቲዎች፣ ሃቀኛ መድረክ ተፈጥሮላቸው፣ በርካታ ሃሳቦችና አመለካከቶችን ማቅረብ አለባቸው፡፡ በአንድ አይነት አስተሳሰብና ሃሳብ ችግሩ አይፈታም፡፡ የተለያዩ አመለካከቶች ወደ አደባባይ መጥተው፣ ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ይሄ ካልተደረገ ግን  አሁንም ነገሮች እየተባባሱ፣ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ያመራሉ፡፡

ምን አይነት ውጤትና ለውጥ እናመጣለን ብላችሁ ታስባላችሀ?
ሰላማዊ ትግልን የመረጥነው በህዝብ ስለምናምን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ትግል ውስጥ ህዝብን ታች ድረስ ወርደን እናነጋግራለን፣ እናደራጃለን፡፡ ጭቆናው በበዛ ቁጥር የኛም ሰላማዊ ትግል እየጠነከረ ነው የሚሄደው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ እንዲኖረው ማድረግ እንፈልጋለን። ኢህአዴግን የሚገዳደር ጠንካራ አማራጭ ሆነን እንመጣለን የሚል ተስፋ አለን፡፡ እኛም ስለ ሀገር አንድነት እናስባለን፤ እንጨነቃለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.